Print this page
Sunday, 19 December 2021 00:00

የግፍ ጥጉ?

Written by  ከኢሳይያስ ልሳኑ በዛብ
Rate this item
(2 votes)

   (የመግደል-- የማፈራረስ-- የማውደም-- ልኩ ምን ይሆን??)
            የግፍ ጩኸትና ሰቆቃ - ሲቃና ጩኸቱ ከምድሪቱ ሽቅብ፣ ከሰማያት ሰማይ ወጥቶ ይሰማል፡፡ በከንቱ የፈሰሰው የ’አቤል” ደምም እኛም ዘንድ ይጮሃል፡፡ ከአምላክም ደጃፍ ይፈሳል...
ይሄ ከሲኦል ቅጥር ፈልሶ የመጣ ርኩሰት.... እኩይ የሰይጣን ቡድን ....  ወያኔ ይሉት አረመኔ -  እውን ከሰው ፍጥረት ነውን?  አይሁዳውያን በናዚ የአሽዊትዝ የማጎሪያ ካምፕ አሳር ፍዳ ከቆጠሩበት - የስቃይ መርግ ከወረደበት፣ ከሞት ፍልሚያ በተአምር ከተረፉት መካከል አይሁዳዊ ፐሪሞ ሌቪ ይጠቀሳል፡፡ ከማለፉ በፊት "ይህ ሰው ከሆነ" (If this is a man) የሚል መጽሐፍ አሳትሟል፡፡ ሰብዓዊነት ጫጭቶ ከሞተበትና ሊጠፋ ጥራዥ ብራዥ ከሚባልበት ቀጭን መስመር ላይ ሳለ እያውጠነጠነ የጻፈውን መጽሐፍ ርዕስ ተዋስኩት፡፡
ዛሬ በእኛ አምባ - በእኛ ምድር - በእኛ ሰፈር - በሰይጣናዊው ቡድን የደረሰውን ክፋት - የተቆጠረውን ፍዳ - የወረደውን ስቃይ እያሰብኩ .... እያየሁ... ፈጻሚ ፊታውራሪዎቹ - ገዳይ ግፍ ፈጻሚዎቹ - እውን ሰዎች ከሆኑ... አልኩና አዎን ርዕሱን ወሰድኩት...፡፡ ከቶ ይህን ሁሉ ጥፋትና ውድመት የፈጸመው “ሰው” ነውን? ....ያሰኛል፡፡  
ቀድሞ ---
ውሾች በውድቅት ለሊት አላዝነዋል... የክፉ ጣር ምልክት የሆነችው የለሊት ወፍ ክንፏን ነስንሳ .... እንደ ጉጉት ጮሃለች....!
እና ሳጥናኤል የሚጋልባቸው ቀንዳም ፈረሶቹ ተጭነው ... የእልቂት ደወል የደወሉት .. አሌፍ አድርገው የተነሱት ከሰሜን እዝ መከላከያ ... ከቀበሮው ጉድጓድ ውስጥ ውሎ ከሚያድረው፣ ቁር የለ ሀሩር - ለሊት የለ ቀን - ተኮራምቶ ከሚኖረው የኢትዮጵያ ወታደር  ነበር፡፡....ሀገርና ድንበር ብሎ ፊቱን አዙሮ ከሚጠብቅበት .... ወገኖቼ  አሉ ብሎ ተስፋ ከጣለበት  .... ከጀርባው በጩቤያቸው ወጉት፣ በጥይት እሩምታ ፈጁት... ራቁቱን ነዱት.... አስከሬኑን ከምድሪቱ ዘርግተው ጨፈሩበት ....፡፡
አልበቃቸውም ... ያኔ ግፋቸውን አስፍተው ጀመሩት እንጂ... በማይካድራ የዘር ማጥፋት የሴራቸው ትብትብ መፈታት ጀመረ.፡፡ .. ምስኪኖች ለጉልበት ስራ - ድሆች ተሯሩጦ ዲናር ለማግኘት - ቁራሽ እንጀራ ቀለብ ለመስፈር ከባዕቷ የተገኙ ወገኖች ... በጅምላ... ተረፈረፉ፣.... አስከሬን በአስከሬን ላይ እየተደረበ በየጥሻው ... በየጉረኖው ...  በየመንገዱ ..... በየስርጡ ... በየጓሮው ተጣለ።... ጭልፊት አስካካ.... ጅብም አሽካካ...   
ከዚያ.... ከዚያማ ....
ጭና - ጭፍራ - መዘዞ - ሀዲላላ - አፋር - ጉሊሶ - የካራ ምሸግ - አንጾኪያና ገምዛ - ጋሸና - ኮምቦልቻ - ሐይቅ - ቡርቃ - ሸዋ ሮቢት ደብረ ሲና .... ወዘተ.... እያለ ቀጠለ፡፡
የጅምላ መቃብር .... እዚያና  እዚህ.... ኮቴያቸው በረገጠበት - እግራቸው በገባበት ስፍራ ሁሉ.....ክፉ ወግ - እርኩስ ዱካቸው ሆነ፡፡    
እዚያ...
አዛውንቱ አለቀሱ... እርር ትክን ብለው አነቡ - ከፊታቸው የተገደሉትን ሚስታቸውን .... ይጦሩኛል ያሉዋቸው ልጆቻቸው - ፍሬዎቻቸው ... ተቀጠፉ.... ደማቸው ፊታቸው ተረጨ..... ‘ቤቴንስ ሰው ሰርቶ ይመልሰዋል.... የፈረሰውስ ይገነባል.... የጎደለው የተዘረፈው ጓዳና ማሳዬስ መልሶ ይሞላል.... ወገኖቼ እናት ዓለሜን - የትዳር ጓዴን .... ምንጭቁላ ልጆቼንስን ... ማን ይተካልኝ? ... ስጣራ ማን አቤት ይበለኝ..... ‘እያሉ አለቀሱት፡፡ ወደ ሰማይ የረጩት እምባ.... ቁልቁል ምድሪቱን ያረሰረሱበት እምባ .... ፈሰሰ... አንደበታቸው እስኪዘጋ አለቀሱት....
እዚህ ደግሞ...
አረጋዊቷ እናት ሸዋ ሮቢት ላይ ... ዕድሜ ብቻ ሳይሆን ኑሮ እንደ ቂሪላ ያለፋቸው .... ቆዳቸው ሽብሽብ ብሎ.... የምጣዱ ጢስ ከፊል አጥቁሯቸው... ሰይጣን ወያኔዎቹ ሳይደርሱ ልጆቻቸውን አሽሽተው.... መጡባቸው.... እኒያ ከሲኦል ደጃፍ - ከሰይጣን የኮረጁ  ታጣቂዎች፣ እንጀራቸውን በልተው - ውሃቸውን ጠጥተው ... በጥጋብ ሲያገሱ - እንደ ምራቃቸው ጢቅታ ንቀው እኒያን ጎልማሲት በግዴታ ወሲብ አዋረዷቸው... ምነው የንጋት ቅንድቦች ቢዘጉ ... ምነው ጀንበር ወድቃ ሰማይ አፉን ከፍቶ ምድር ተሰንጥቃ - ምጽዓት በሆነ ... በውስጥ በልቡናቸው - በአካል በዓይናቸው አነቡት አለቀሱት ... ሰይጣናዊ ወንበዴዎቹ በተባረሩ በተደመሰሱ ማግስት ታዲያ እኒያ ጎልማሲት፣ ‹ልጄ ሲመጣ እንዲያየኝ አልፈልግም’ ብለው ከራሳቸው ጋር ተነጋግረው - እፍረትና እድፍ ተሰምቷቸው፣ በስጋ እረክሻለሁ ብለው፣ ራሳቸውን አናግረው - ራሳቸውን አጠፉ.... አዎን ራሳቸውን አሳረፉ፡፡
በዚህ በኩል
ነገ ተስፋ ብለው በንጹህ ልቡና ከአፈሯ እሚጫወቱ ህጻናትን ነጥሎ ... አባትን መግደል.. እናትን መድፈር ... እህት ሴቶችን ማንገላታት...
ወዲያ ደግሞ
ባልየውን የፊጥኝ አስረው... በመሳሪያ አስፈራርተው ...ባለቤቱን ... እህቱን ... የቤቱን ባለቤት ሴት ልብስ አስወልቀው እርቃናቸውን - ራቁታቸውን አቁመው ... ለግዴታ ወሲብ እየተጋበዙ... ተጎማለሉ ... አሉ፡፡
ምን ያልተፈጸመ ግፍ አለ...?
አስራ ስድስት ቤተሰቦችን በአንድ ቤት ሰብስቦ እሳት ለኩሶ ማቃጠል....... አረጋውያንና ህጻናት - እናቶችና ሴቶች የተጠለሉበትን መጠለያ ጣቢያን ...በመድፍ መደብደብ ... በላውንቸር ባዙቃ ማረስ... እና ከተሞች እንዳልነበሩ ወደሙ ... ተሽከርካሪዎች እንደ ጧፍ ነደዱ...ተሸክመው ለመዝረፍ ያልቻሉትን ተሳቢ... ከባድ መኪና እሳት ለኩሰው ሩጫ...
መሰረተ ልማቶችም - የአውሮፕላን ማረፊያ ቴሌኮምኒኬሽን - መብራት ሀይል - ውሃና ፍሳሽ... ሆስፒታሎች .... ክሊኒኮች ... ሆቴሎች ... በእሳት ጋዩ.. እንዲፈራርሱ ተደረገ.... 
አብያተ ክርስቲያናት ... መስጊዶች እስከነ መምህራኑ እስከነ አገልጋዮቹ... በጥይት ኢላማ ሆኑ ..... የመደርመስ የመፍረስ ክፉ እድል ደረሳቸው ...
የወደመው ንብረት - የፈሰሰው የሰው ደም - የጠፋው የሀገር ሀብት መች ተቆጥሮ... መች ተዘርዝሮ.... እንዲያው በድፍኑ የትየለሌ ነው በሉ፡፡
እንስሳቱም አልቀሩ.... የጋማ ከብቶቹ..... አልተረፉም .... ለወሬ ነጋሪ ... እንዳይተርፍ ..ከቆሙባት መሬት በቀር ሟች የሆነ ሞት... ጠፊ የሆነ ጥፋት ተለቀቀበት... ክፉ ሰይጣናዊ በቀል ነውና ... አንዳች የሳጥናኤል መናፍስት ጋልቧቸዋልና .... የደም መጋኛ ሰፍሮባቸዋልና ... የሞት ነጋሪቱን - የእልቂት ደወሉን - የእኩይ እምቢልታውን አንባረቁት.... በወገን ሞት በደስታ ለጊዜው አስካኩ ... በህዝብ ስቃይ ለአፍታ ተፍነከነኩ...  
ታዲያ ... እነዚህ የጠመንጃ ፍቅረኞች - የደም ማፍሰስ ዛር የተጠናወታቸው ርኩሳን ከቶ ከየቱ ማህጸን ወጡ ማለት ይቻላል??.....  
የእኩይነትና የሰናይ አውደ ግንባሩ የሰው ልቡና ይባል ነበር፡፡ በሰው ልቡና ውስጥ የእኩያ  ተኩላውን አሳድጎ አውሬ መሆን ይቻላልም ተብሏል፡፡ እንዲህ በአካል አውሬ በይዘትም አውሬ ... ሰው እንዲህ በሰውነት ሳጥናኤል ብሎ ግን ማንም አልጠበቀም... ምንኛስ ከአስፈሪ የህወሓት አውሬዎች ጋር እንደነበርን ... እየዘገነነን አሁን እናስበዋለን...።
የቃኤል ዱካ - በወንድም ደም ማፍሰስ የመኩራራት ... በእህት ሞት መዘባነን የሚቀላቸውም እንደሆኑ አወቅን...፡፡
እኛ በዚህ ዘመን በዓይናችን አይተን የመሰከርነው ግፍና በደል ከሰይጣን ብብት ስር ያደገ መሆኑን አሰመርን፡፡ የእኩይነት ትርጓሜው መልኩና ይዘቱ ሩቅም ሳንሄድ አጠገባችን ተከስቶ ለመጽሄተ ቃላችን ፍቺ - ለመዝገበ ቃላችን አስረጂ ምስሉ ጨምረን ለታሪክ እንድናወሳው ከአፍንጫቸን ስር ኹነቱን አየን፡፡
ይህን መሰል ክፋት ግን ይህን ያህል እርኩሰት እንዲህም ያለ እኩይነት ነበረ ተብሎም ቢነገር - ባናየው በኢትዮጵያና በኢትዮጵያውያን ላይም ሲደርስ ባንመሰክር ኖሮ ተጋነነም ባልን ነበር፡፡ አረ ከቶ ከእነዚህ የሳጥናኤል ሽፍቶች ጋርስ እንዴት ነበር አብረን የኖርነው?
እውነት እኮ ነው - “ይህ - ሰው ከሆነ” ማለቴ ነው፡፡
ግን - ተማርን፡፡ አወቅን፡፡ ሰው እንዲህ አራዊት እንደሚሆን - የሳጥናኤል ፈረስ እንደሚጋልብ.... ይብላን ታሪክ ለሚይዘው ቀለም... ይብላን ለዚህ ዘመን ክፉ አዚመኞች.... በታሪክም በእግዚአብሔርም ፊት ለሚቆሙት የሳጥናኤል ሽፍቶች....
እንጂ ለኢትዮጵያማ መጪው ብርሃን የመላው ... እንደ ገጣሚው አሰኛኘት፤
“አንቺ የፍቅር እናት በይ ሌማቱን ስፊ፣
አንቺ የፍቅር ሀገር ባንድ ሰፌድ ንፊ፣
ከእንግዲህ ነውና በረከትሽ ሰፊ”!
(ይሁና - ይበል! ይበል!)
የተኛበትን አፈር ገለባ ያድርግለትና፣ ሎሬት ጋሽ ጸጋዬ ገብረ መድህን፣ ‘ረሀብ ስሙ ወያኔ ነው!’ ሲል ግጥም ጽፏል፡፡ ይሄ ግጥሙ ስለ ፖለቲካ እኩያን ሳስብ ዘወትር ከእዝኔ ይሰማኛል፡፡
ከዚያ ውስጥ ጥቂት ስንኞችን ልውረድ፡-
“አስራ ሁለት ሚሊዮን ሕዝብ - እንደቅጠል የሚረግፈው
እንደሪቅ በሆዱ እሚሳብ - እንደተምች አርባ እግር ያለው፣
ኮቴው ያረፈበት ደጅ ሣር ቅጠሉን የሚያደርቅ
የእኩይ ተምሳል ባለኤሰው - ተውሳክ ማለት ወያኔ ነው”፡፡

Read 11118 times