Saturday, 18 December 2021 14:33

የየራሳችን ቀያይ መስመሮች...

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(2 votes)

"በዚህም ሆነ በዛ “ኑ...” ብለን ጠርተናቸው የሚመጡበት ካጡ...አለ አይደል... ሥጋ አቅርቦ ቢላዋ መንሳት አይነት እንዳይሆን የሚመለከታቸው እንደ ልዩ ሁኔታ ወስደው (ደግሞም ልዩ ነው!) በተቻለ መጠን ቢያንስ “ኑ...” ያልናቸው አንድ ሚሊዮኑ ኢትዮጵያውያን መምጣት የሚችሉበትን መንገድ ማመቻቸት ተገቢ ነው፡፡ እነሱም የሚመጡበትን መንገድ የሚፈልጉ፣ ወይ እየፈለጉ ያሉ ይመስለናል፡፡"
               
            እንዴት ሰነበታችሁሳ!
“አይመጣምን ትተሽ ይመጣልን ያዥ፤” የሚሏት ነገር አለች፡፡ እናማ... ምን መሰላችሁ...ያው በኢኮኖሚ ምናምን ነገር በመአት ምክንያቶች መጪዎቹ ጊዜያት ቀላል አይሆኑም፡፡ ታዲያ...አለ አይደል...ስለ ኑሮ ውድነት፣ ስለ ብሪቱ ጡንቻ መቀነስ አይነት ነገሮች ተንታኞች ምናምን የሚባሉት ሳያስፈልጉን የሁሉንም በር እያንኳኳ ስለሆነ አሳምረን እናውቀዋለን፡፡ እናማ ቀደም ሲልም ኑሮ  ከባብዶ ከርሞ ስለነበር፣ አሁን ሀገራችን ያለችበት ሁኔታ ደግሞ ነገሮችን እያባባሳቸው ስለሆነ፣ ጫናው ቢከብድ አይገርምም፡፡ ለነገሩ ምን መሰላችሁ... የጤፉ ጆንያ ተራግፎበት ግራ የገባውና የሚያማርር መአት እንዳለ ሁሉ የፈረንሳይ ሽቶ ዋጋ ጣራ ነካ ብለው ‘የኑሮ መወደድን’ የሚያማርሩ እንዳሉ ልብ በሉልኛማ! ኮሚክ እኮ ነው...አንዳንዴ ስታስቡት በቃ “እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል፣” የሚሉት ነገር ከነዘር ማንዘሩ እኛ ላይ የሰፈረ ነው የሚመስለው፡፡
ስሙኝማ....እንግዲህ ጨዋታም አይደል፣ ከእነ አንድ ሺህ ምናምን ችግራችን የእኛ ህብረተሰብ እኮ የምር የሚረዳዳ ህብረተሰብ ነበር፡፡ አንድ ጣሳ ሹሮ እንኳን ተርፎት ከዛው ላይ ለጎረቤቱ የሚያካፍል ህብረተሰብ ነበር እኮ! “እከሊት ጤፍ አልቆብኝ መሶቤ ባዶ ነው፡፡ እስቲ ሁለት ወይ ሦስት አንጀራ ላኪልኝ፣” ተብሎ አራትና አምስት እንጀራ የሚልክ ህብረተሰብ ነበር እኮ! የት ቦታ ላይ ይሄ ክር እንደተበጠሰ አንድዬ ብቻ ነው የሚያውቀው፡፡
እኔ የምለው...ምድረ ፈረንጅ ምን አድርጉ ነው የሚለን! አሀ...እነሱ ሰዎች መቼ ነው ከትከሻችን ላይ የሚወርዱት! በቃ ስለ እኛ የሆነ ሰበብ ፈጥረው ካልተሰበሰቡ የሚያቃዣቸው ነገር አለ እንዴ! ነገርዬውማ...አለ አይደል፣ የሌላው ሌላው ምክንያት እንዳለ ሆኖ፣ አሁንም እንደ ጥንቱ “እኛ ያልነውን ‘በእናንተ መጀን’ ብለው የማይቀበሉን እንዴት ቢደፍሩን ነው!” ብለው ነው እየተጠራሩ ሊያስርቡንም፣ ምናምን ሊያደርጉንም እየዶለቱ ያሉት። ምን መሰላችሁ...በተለይም ከዚች ከድሀ ክፍለ አህጉራችን እንደኛ አይነት “ብንከባበር ይሻላል” የሚል ቃና ያላቸው ምላሾች ገጥሟቸው አያውቅማ!
ነገር ግን የሚወስዷቸው እርምጃዎች አይጎዱንም ማለት አይደለም፡፡ እንክት አድርገው ይጎዱናል፡፡ እነሱም የሚፈልጉት ይህንኑ ነው፤ ጉዳቱ ሲጸናብን በግንባራችን ተደፍተን “ማሩን፣ አይለምደንም!” እንድንል! እና ለዚህ ነው በተለይ የኑሮ ክብደቱ ላይ እየተረዳዳን ለመወጣት መሞከር ያለብን፡፡ አለበለዛ እጅግ ከባድ ነው የሚሆነው፡፡ በዚህ ላይ ደግሞ ወቅት እየጠበቁ በህዝብ ስቃይና መከራ ሊያተርፉ የሚፈልጉ ክፍሎች አሉ። ይህንንም የነዳጅ ዋጋ በጨመረ በማግስቱ ጀምሮ እያየነው ነው፡፡
እናማ... እንደ ሁልጊዜው ይቺን አስቸጋሪና ፈታኝ ወቅት ጠብቆ “ቢቀር ምናባቱ!” ለማለት ትንሽ በሚያስቸግሩ አስፈላጊ ሸቀጦች ዋጋ ላይ በአናት አናቱ እየቆለለ ‘ጂ ፕላስ ቱ’ው ላይ ሌላ ሁለት ፎቅ ስለመጨመር ብቻ የሚያስብ አለ፡፡ የሚያስብ ብቻ ሳይሆን እቅድ የሚያወጣ፡፡ ኮሚኩ ነገር ምን መሰላችሁ...እንደ ሁልጊዜውም ዋጋው የሚጨምረው አዲስ በገቡ ምርቶች ላይ ሳይሆን ለወራት በመጋዘን ተቆልፈው አቧራ ሲጠጡ በከረሙት ላይ ሁሉ መሆኑ! (የአንዳንድ የሀገራችን ነጋዴዎች ጭካኔ ግርም የሚል ነው፡፡) ደግሞላችሁ... ይቺን አስቸጋሪና ፈታኝ ወቅት በመጠቀም  በህግ ከሚደነገገው ታሪፍ ውጪ በትራንስፖርትና መሰል አገልግሎቶች ላይ ‘ሂሳብ’ እየቆለለ የሳምንት የምናምን ሺህ ብር የዕቁብ መዋጮ እንዳይጎድል መከራችንን የሚያበላን ሾፌርና የታክሲ ባለቤት መአት ነው (‘እንዲሁም ረዳት’ የሚለው ይጨመርልንማ!)
“ሂሳብ...”
አስር ብራችሁን ላጥ አድርጋችሁ ለረዳቱ ትሰጡታለችሁ፡፡ አንድ ብር ይመልስላችኋል፡፡
“አስር ብር ነው እኮ የሰጠሁህ!”
“አውቃለሁ...”
“አንድ ብር ብቻ ነው የመለስክልኝ፡፡ ሂሳቡ ሰባት ብር አይደለም እንዴ!”
“ዘጠኝ ብር ሆኗል፡፡”
ከዚህ በኋላ ወላ “ታሪፉ እንደዚህ አይደለም!” “እናንተ ሰዎች እንደፈለጋችሁ ነው እንዴ ዋጋ የምትቆልሉት!” ምናምን አይነት እሰጥ አገባ ውስጥ ብትገቡ፣ ያው እንግዲሀ ራሳችሁ መውጫችሁን አዘጋጅታችሁ ቢሆን ይሻላል፡፡ አሀ...ለሁለት ብር ብላችሁ ሀያ ዓመት የማይለቅ ዘለፋ ይገጥማችኋላ! ደግሞ ይቺ ባዶ፣ አንድ አትበቃ ይመስል ለቁርስ የተበላች ሦስት እርጥብ ከሞላቸው ሆድ ምናምን የምትመጣ እብሪት፣ ለባለሙያዎች ትንታኔ እንኳን  አትመችም፡፡
እናላችሁ.... የኑሮ መክበዱ እንዳለ ሆኖ በዚህ አጋጣሚ ሊከብሩና ወደሚፈልጓት ሌክሰስ፣ ወይም ቪ ኤይት ሦስተኛ መኪናቸው ጠጋ ማለት የሚፈልጉ የሚያደርሱብን ጫና ቀላል አይደለም ለማለት ያህል ነው፡፡ እናላችሁ...ግዴላችሁም ያለችንን ሹሮም ሆነ በርበሬ የምንበዳደርበት ባህል ለዚህ ጊዜ ነው የሚረዳው፡፡
ስሙኝማ...እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ.... ለገና ስለሚመጡት ወገኖቻችን ...አለ አይደል... የእውነተኛ እንግዳ ተቀባይነታችንን ማሳያ አሁን ነው፡፡ በእርግጥ የሚመጡት ወደ አንዲቷ ሀገራቸው ቢሆንም ለበርካታ ዓመታት ተለያይተን የቆየን እንግዶቻችን ናቸው። በየፈረንጁ ከተማ በከፍተኛ ቁጥርና በከፍተኛ ወኔ አደባባይ ወጥተው ሲጮሁላት የነበረችው ሀገራቸው፣ በየመገናኛ ዘዴዎች እውነቷን ጮክ አድርገው ሲያሰሙላት የነበረችው ሀገራቸው፣  ጠላቶቿ ሊቀብሩት የሚፈልጉትን ታሪኳን አደባባይ እያወጡ ለሌሎች አፍሪካውያን ጭምር ኩራት እንድትሆን ያደረጓት ሀገራቸው ምንም እንኳን ከባድ ችግር ላይ ያለች ብትሆንም፣ እነኚህ “አይዞሽ ችግርሽን በጋራ እንወጣዋለን” ሊሏት የሚመጡ ልጆቿን፣ “የቁርጥ ቀን ልጆቼ እንኳን በደህና መጣችሁልኝ!” ብላ ልትቀበላቸው ይገባል፡፡ ግን ደግሞ ሁሉም የልባቸው እንዳይደርስ በተለይ አሜሪካ ያሉ ወገኖቻችን የመጓጓዣ አውሮፕላን የማግኘትና የትኬት ችግር እየገጠማቸው እንደሆነ እየነገሩን ነው፡፡
“ስማ መቼ ነው የምትገባው?”
“የት የምገባው?”
“አዲስ አበባ ነዋ! ምንድነው በጠዋቱ ስንት ጠርሙስ በድዋይዘር ብትጠጣ ነው!”
“እባክህ የምመጣ አይመስለኝም፡፡”
“ደግሞ ሀሳብህን ለወጥክ?”
“ምን ሀሳቤን እለውጣለሁ፣ ትኬት የለ፣ አውሮፕላን የለ!”
“ይኸው ሌሎቹ እየገቡ ነው እኮ፡፡”
“እነሱ ከወራት በፊት ትኬት ስለገዙ ነው የተሳካላቸው፡፡”
በዚህም ሆነ በዛ “ኑ...” ብለን ጠርተናቸው የሚመጡበት ካጡ...አለ አይደል... ሥጋ አቅርቦ ቢላዋ መንሳት አይነት እንዳይሆን የሚመለከታቸው እንደ ልዩ ሁኔታ ወስደው (ደግሞም ልዩ ነው!) በተቻለ መጠን ቢያንስ “ኑ...” ያልናቸው አንድ ሚሊዮኑ ኢትዮጵያውያን መምጣት የሚችሉበትን መንገድ ማመቻቸት ተገቢ ነው፡፡  እነሱም የሚመጡበትን  መንገድ የሚፈልጉ፣ ወይ እየፈለጉ ያሉ ይመስለናል፡፡
  ደግሞላችሁ... አሁን ቀደም ብለው እየገቡ ያሉትም በስጨትጨት እያሉ ያሉበት ነገር አለ...የጉምሩክ ሂደቱ እጅግ በርካታ ሰዓታት መውሰዱ፡፡ እንደውም ብዙዎች በገበቡት እለት ሂደቱ ስለማያልቅላቸው በሁለተኛውና በሦስተኛው ቀን እየተመላለሱ እንደሆነ እየሰማን ነው፡፡ በእርግጥ የጉምሩክ መሥሪያ ቤት የራሱ አሠራሮች አሉት፡፡ በተለይም አሁን ባለንበት አስቸጋሪ ጊዜና ጠላቶቻችን አንድ ሺህ አንድ ተንኮሎች እያሰቡና እየሞከሩ ባሉበት ወቅት ቁጥጥሮች መጥበቃቸው የግድ ነው፡፡ በዚህ ላይ የበዓል ሰሞን የመንገደኛው ፍሰት በጣም ስለሚጨምር ይህ ተጨማሪ ጫና መፍጠሩ የማይቀር ነው፡፡ እንደዚህም ሆኖ የጉምሩክ ሰዎች እንግዶቻችን እንዳይጉላሉ መውሰድ የሚገቧቸውን እርምጃዎች ሁሉ እንደሚወስዱ አርግጠኞች ነን፡፡ መሆን ያለበትም እንዲሁ ነውና!  
ስሙኝማ...ግዴላችሁም፣ በዚህ በበዓል ሰሞን እንደው ሸመታው ላይ እጃችንን ቆጠብ ብናደርገው ክፋት የለውም፡፡ አንድዬ እድሜና ጤናውን፣ ከምንም በላይ ደግሞ ሰላሙን ይስጠን እንጂ በዓላት ነገም፣ ከነገ ወዲያም ይመጣሉ፡፡ እናማ...እንዲህ ኑሮ በተወደደበት በ“ከማን አንሼ!” አይነት ቀሺም አስተሳሰቦች የያራሳችንን ቀያይ መስመሮች ባናልፍ አሪፍ ይሆናል ለማለት ያህል ነው፡፡
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 1718 times