Saturday, 18 December 2021 14:42

ሱዝቤይ በ277 አመታት ከፍተኛውን የ7.3 ቢ ዶላር ሽያጭ አስመዝግቧል

Written by 
Rate this item
(0 votes)

  ላለፉት 277 አመታት በአለማቀፍ የስነጥበብና ቅርሳ ቅርሶች አጫራችነት ሲሰራ የቆየው ታዋቂው ኩባንያ ሱዝቤይ፣ በተገባደደው የፈረንጆች አመት 2021 በታሪኩ ከፍተኛው የሆነውን የ7.3 ቢሊዮን ዶላር አመታዊ ሽያጭ ማስመዝገቡን አስታውቋል፡፡
ኩባንያው የታዋቂ ሰዓሊያንን ዝነኛ ስራዎች፣ የስነጥበብ ውጤቶች፣ ታሪካዊ ቁሳቁሶችና ውድ ቅርሶችን ጨምሮ በአመቱ ለጨረታ ካቀረባቸው ቁሳቁሶች በድምሩ 7.3 ቢሊዮን ዶላር ማግኘቱን ባለፈው ረቡዕ እንደገለጸ ነው ዘ ጋርዲያን የዘገበው፡፡
እ.ኤ.አ በ1744 በለንደን የተመሰረተውና ዋና መስሪያቤቱን በኒውዮርክ ያደረገው ዝነኛው አለማቀፍ አጫራች ኩባንያ ሱዝቤይ፣ ዘንድሮ በታሪኩ ከፍተኛውን ሽያጭ እንዲያስመዘግብ ከረዱት ጉዳዮች መካከል የቅንጦት ቁሳቁስ በከፍተኛ ዋጋ የሚገዙ ቅርስ ሰብሳቢዎች መበራከታቸው እንደሚገኙበት የጠቆመው ዘገባው፣ በቀሩት ሳምንታት 20 ሽያጮችን ስለሚያከናውን አጠቃላይ ገቢው ከዚህም ከፍ ሊል እንደሚችል መነገሩን አመልክቷል፡፡
ኩባንያው በአመቱ 57 እቃዎችን እያንዳንዳቸውን ከ15 ሚሊዮን ዶላር በላይ መሸጡን ያስታወሰው ዘገባው፣ በአመቱ በከፍተኛ ዋጋ የተሸጠው ደግሞ 92.2 ሚሊዮን ዶላር ያወጣው ቦቲሲሊ የተባለ የታዋቂ ሰዓሊ የስዕል ስራ መሆኑንም አክሎ ገልጧል፡፡ በአመቱ ከፍተኛ ሽያጭ ከተመዘገበባቸው መካከል ዘመናዊ ስዕሎች ቀዳሚነቱን እንደሚይዙ የተነገረ ሲሆን፣ ኩባንያው ከስዕሎች ሽያጭ 4.3 ቢሊዮን ዶላር ማግኘቱንም ለማወቅ ተችሏል፡፡
ፈረንሳዊው ቢሊየነር ፓትሪክ ዳሪ እ.ኤ.አ በ2019 ሱዝቤይ ኩባንያን በ3.7 ቢሊዮን ዶላር ገዝተው የግላቸው ማድረጋቸውንም ዘገባው አክሎ አስታውሷል፡፡

Read 983 times