Print this page
Sunday, 19 December 2021 00:00

ስዊዘርላንድ በእውቀት፣ አውስትራሊያ በስካር 1ኛ ተባሉ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 ሰሞኑን ይፋ የተደረገው የ2021 ግሎባል ኖሌጅ ኢንዴክስ፣ በእውቀት ደረጃ ስዊዘርላንድን ከመላው አለም አገራት በአንደኛ ደረጃ ላይ ሲያስቀምጣት፣ ሌላኛው ሰሞንኛ አለማቀፍ ሪፖርት የ2021 ግሎባል ድራግ ሰርቬይ ደግሞ አውስትራሊያን በስካር 1ኛ ደረጃ ላይ አስቀምጧታል፡፡
የአገራትን የዕውቀት ደረጃ ለመመዘን የሚያስችሉ 155 ያህል የተለያዩ መለኪያዎችን በመጠቀም የተደረገን አለማቀፍ ግምገማ መሰረት አድርጎ የወጣው የፈረንጆች አመት 2021 ግሎባል ኖሌጅ ኢንዴክስ፣ ዘንድሮም ስዊዘርላንድን ለ5ኛ ተከታታይ አመት ከአለማችን አገራት በ1ኛ ደረጃ ላይ እንዳስቀመጣት ነው ዘ ጋርዲያን የዘገበው፡፡
በአመታዊው አለማቀፍ የዕውቀት ደረጃ ዝርዝር ስዊድን፣ አሜሪካ፣ ፊንላንድና ኒዘርላንድስ እንደ ቅደም ተከተላቸው ከሁለተኛ እስከ አምስተኛ ያለውን ደረጃ የያዙ የአለማችን አገራት ናቸው፡፡ በዕውቀት ደረጃ ከአለማችን አገራት መካከል እጅግ ዝቅተኛውን ስፍራ የያዘችው አገር ቻድ ስትሆን ኒጀር፣ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ አፍጋኒስታንና የመን ይከተላሉ፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ፣ ባለፈው የፈረንጆች አመት 2020 በመላው አለም ከሚገኙ አገራት መካከል በብዛት የአልኮል መጠጦችን በመጠጣትና በመስከር አውስትራሊያውያንን የሚወዳደራቸው እንዳልነበር ሰሞኑን የወጣ አንድ ጥናት አመልክቷል፡፡ አንድ አስውስትራሊያዊ በአመቱ በአማካይ ለ27 ጊዜያት ያህል አልኮል ጠጥቶ መስከሩን በጥናት መረጋገጡን ሰሞኑን ይፋ የተደረገው የ2021 ግሎባል ድራግ ሰርቬይ አለማቀፍ ሪፖርት አመልክቷል፡፡
ዴንማርካውያንና ፊንላንዳውያን ቢያንስ በአማካይ በአመት 24 ጊዜ በመስከር የሁለተኛ ደረጃን ሲይዙ፣ አሜሪካውያን 23 ጊዜ፣ እንግሊዛውያን ደግሞ 22 ጊዜ በመስከር ተከታዮቹን ደረጃዎች መያዛቸው ተነግሯል፡፡
ጥናቱ በተደረገባቸው 24 አገራት ውስጥ የሚገኙ ሰዎች በአጠቃላይ በአማካይ በአመት 14 ጊዜ ያህል እስኪሰክሩ አልኮል መጠጣታቸውን እንደገለጹ ያመለከተው ሪፖርቱ፤ ምላሻቸውን ከሰጡት መካከል ጥንብዝ ብለው በመስከራቸው የድንገተኛ አደጋ ህክምና ድጋፍ እንደተደረገላቸው የተናገሩ እንዳሉም አመልክቷል፡፡ ጥናት በተደረገባቸው አገራት የአልኮል መጠጦች፣ የሲጋራና አደንዛዥ ዕጾች አጠቃቀም ካለፈው አመት ጋር ሲነጻጸር የተወሰነ ቅናሽ ማሳየቱን ነው ሪፖርቱ የጠቆመው፡፡

Read 2832 times
Administrator

Latest from Administrator