Tuesday, 21 December 2021 00:00

ሙያ ዘለል ንድፈሃሳብ

Written by  ከአንለይ ጥላሁን ምትኩ
Rate this item
(0 votes)


           "የቀጭኔ አንገት ምግብ ለማግኘት እየረዘመ መሄዱን ሲያብራራ፤ ‹‹ቀጭኔ በምግብ ፍለጋ ተግባር ተሰማርታ ሳለ፣ ተንጠራርታ ወይም አንገቷን ወጥራ ቅጠል ለመቀንጠብ በምትሞክርበት ጊዜ በአንገቷ የነርቭ ፈሳሽ ተንሸራሽሮ አንገቷን ያስረዝመዋል፤ አለ፡፡ ከዚያም አንገቷ የረዘመው ቀጭኔ፣ ረጅም አንገት ያላቸው ልጆች ትወልዳለች፡፡--
          
            የበርካታ ሙዎች ድንበር እየተናደ ከሚያለያያቸው ይልቅ የሚያቀራርባቸው ጉዳይ እየበረከተ መጥቷል፡፡ በአንዱ ሙያ (ጥናት) የዳበረ ንድፈሃሳብ በሚያዛምድ ጉዳይ ላይ ለሌሎች ግብዓት እየሆነ ድሩን ይዘረጋል፡፡ ለምሳሌ በሶሾሎጂ፣ በአንትሮፖሎጂ፣ በፍልስፍና፣ በስነጽሁፍ እና በሳይኮሎጂ ወዘተ… ሙያዎች መካከል ያለው የጠበቀ ዝምድና ጥሩ ማሳያ ነው፡፡ የጋራ ከሆኑት የሙያዎቹ ንድፈሃሳቦች መካከል ደግሞ መዋቅራዊነት (structuralism)፣ ትዕምርታዊነት (semiotics theory)፣ አዝግሞታዊ (evolutionary theory)፣ ስነልቦናዊ አስተንትኖት (psychoanalytic theory)  እና ሚቶሎጂ (mythology) ወዘተ… ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ለአሁኑ በአዝግሞታዊ ንድፈ-ሃሳብ ላይ ቅምሻ እናድርግ፡፡
አዝግሞታዊ ንድፈ ሃሳብ (Evolutionary Theory)፡-
‹‹የህይወት ባለፀጋ ሁሉ ከአንድ የዘር ግንድ በዘመናት ሂደት ሲወርድ ሲዋረድ የመጡ ናቸው›› ብሎ ያምናል፡፡ መሰረቱን የጣለው ቻርለስ ዳርዊን ነው፡፡ ዳርዊን (1809-1882) ፈር ቀዳጅ ቴዮሪውን በ19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን አጋማሽ ‹‹ስለ ብቸኛ ዝርያዎች አመጣጥ›› በሚል ርዕስ ባዘጋጀው መፅሐፉ አሰፈረ፡፡ ይህም ሀሳብ ለስነህይወት ዕውቀት መሰረት ሆነ፡፡ ስለሆነም የሰፈረው ሀሳብ የህይወት ባለፀጋዎች ግንኙነት ወይም ትስስር እንዲሁም  ልዩነት ለመረዳት አስችሏል፡፡
ይህ ቴዮሪ፣ በመሰረቱ ህያው ሁሉ ቅድመ ህያው ከነበረ ግዑዝ (ቁስ) አካል የተከሰቱና ሂደቱም ማንም ያለወጠው፣ ማንም የማይመራው፣ በማንም ያልታገዘ መሆኑን ያብራራል፡፡ ለውጡ በቢሊዮን ዘመናት ውስጥ ንዑስና አናሳ አካል ከነበራቸው መዋቅሮች ተነስቶ ቀስ በቀስ እያዘገመ ወደ ውስብስብ መዋቅሮችና  ተግባሮች እንዳደገ (እንዳስገኘ) ያስረዳል፡፡
በዝግመታዊ  ንድፈ ሃሳብ የለውጥ ሂደት አዳዲስ ሁኔታዎች እየተከሰቱ፣ እኒህን ለውጦች የሚቋቋሙ ወራሾች እየተፈጠሩ፣ ለውጦችን መቋቋም ያቃታቸው ደግሞ እየወደሙ፣ እየከሰሙ፣… በሂደቱ ውስጥ መሬት የብዙ ሕይወት መናኸሪያ ሆነች፤ ብሎ ያምናል፡፡
በእርግጥ በጥንታዊቷ ግሪክ አናክሲማንደር (Anaximander) የተባለ ፈላስፋ፤ ‹‹ሕያዋን ከግዑዝ አካል እንደመጡ፣ ሰውም ከእንስሳነት ወደ ሰውነት የተቀየረ ነው›› የሚል ንድፈ ሃሳብ አሰራጭቶ ነበር። ሆኖም ግን ቴዮሪው በቂ ማስረጃዎች አላቀረበም ነበር፡፡

ተፈጥሯዊ ምርጦሽ
(Natural Selection)
ቻርለስ ዳርዊን ፣ ዝግመታዊ ለውጥ በ‹‹ተፈጥሯዊ ምርጦሽ›› (natural selection) አማካኝነት ሊፈጠር እንደሚችል በግልፅ አስረድቷል፡፡ ይህ ቴዮሪ የሌሎችን ሙያዎች (ምሁራን) አስተሳሰብ አቃፊ (አዋሃጅ) በመሆኑ በአጭር ጊዜ ተቀባይነት አገኘ፡፡ በመላው ዓለምም ተሰራጨ፡፡
የተፈጥሯዊ ምርጦሽ (natural selection) ነጠላ መርሆ፣ አካላት ህያው ሆነው የሚዘልቁትና ዘር የሚተኩት ወይም ወራሽ ለማፍራት የሚበቁት በውድድር አማካኝነት ነው፤ የሚል ነው፡፡ ይህም ማለት ከሌሎች ጋር ተወዳድረው የአካባቢዎችን ተፅዕኖ በተሻለ ሁኔታ ለመቋቋም የሚችሉ፣ ተግዳሮትን የመቋቋም ዝግጁነት ያነገቡት ናቸው--- ከህልፈት የሚተርፉት፤ ዘርም መተካት የሚችሉት (survival of the fittest)፡፡
እናም  ታግሎ ከችግር መላቀቅ፣ ለአካባቢው ተስማሚ አቅም መላበስ ያስመርጣል፡፡
ሌላው በዳርዊን ዘመን የነበረ ‹‹ላማርክ›› (Lamark) የተባለ የስነሕይወት አጥኚ፣ የዝግመተ ለውጥ ሂደትን ለማስረዳት የተጠቀመው ምሳሌ የቀጭኔን አንገት ነበር፡፡ እንመልከተው፡-
የቀጭኔ አንገት ምግብ ለማግኘት እየረዘመ መሄዱን ሲያብራራ፤ ‹‹ቀጭኔ በምግብ ፍለጋ ተግባር ተሰማርታ ሳለ፣ ተንጠራርታ ወይም አንገቷን ወጥራ ቅጠል ለመቀንጠብ በምትሞክርበት ጊዜ በአንገቷ የነርቭ ፈሳሽ ተንሸራሽሮ አንገቷን ያስረዝመዋል፤ አለ። ከዚያም አንገቷ የረዘመው ቀጭኔ፣ ረጅም አንገት ያላቸው ልጆች ትወልዳለች። በአካባቢ ተፅዕኖ የተገኘው የአንገት ርዝመት ለውጥ ከዘር ዘር የሚወረስ ይሆናል። በዚህም ይህ ባህሪ የሚወረሰው ሙሉ በሙሉ በአካባቢ ተፅዕኖ ነው የሚል ድምዳሜ ላይ ደረሰ፡፡
ያ ባህርይ (አንገትን ረጅም ለማድረግ ያስቻለ) በቀጭኔ ተፈጥሮ ውስጥ እንደነበረ እና ሲያስፈልግ በተግባር የሚተረጎም መሆኑን ግን አላመነበትም፡፡
በአንፃሩ ቻርለስ ዳርዊን ከላይ እንደተጠቀሰው፣ በአካሉ ውስጥ የነበረና የሚወረስ ገፅታ፣ አዲስ ለተከሰተው ሁኔታ ተመቻችቶ የችግር መፍቻ ሆነ እንጂ፣ ከአካባቢው የተወረሰ ገፅታ አይደለም አለ። ቻርለስ ዳርዊን ለዚህ ሃሳብ ደጋፊ ይሆን ዘንዳ፣ ዳላፓጎስ ደሴቶች ላይ ያያቸውንና ለናሙና የሰበሰባቸውን ወፎች የአፍ አካባቢ ቅርጽ በማስረጃነት አቅርቧል፡፡
 
ስነፅሁፍ እና ዝግመተ
ለውጥ ንድፈ ሃሳብ
ሁለንተናዊ የሰው ልጅ ባህርይ በስነፅሁፍ የተገለፀ ሲሆን በተጨማሪም በተዋሀዱ ባህሎች፣ በተዳቀሉ ዝርያዎችና በጥልቅ ታሪካዊ ዕይታዎች አማካኝነት ዝግመተ ለውጥ እውን ይሆናል፡፡
ስነፅሁፍ ሳይንሳዊ በሆነ መንፈስ የሰውን ተፈጥሮ አይነታዊና መጠናዊ መረጃ (ማስረጃ) በማቅረብ በውስን ጊዜና ቦታ ላይ ተመስርቶም ሆነ ሳይመሰረት የሚገልፅበት መንገድ ሁነኛ ማሳያ ነው፡፡
ሌላው በስነፅሁፍ ውስጥ ዝግመታዊ ለውጥ የሚንፀባረቀው በተዋረድ በተገለፁ የተለያዩ ምልከታዎች አማካኝነት ነው፡፡ እነዚህም ምልከታዎች  ከሌሎች ሙያዎች ከሚንፀባረቁ እሳቤዎች ጋር የሚወዳደሩና ጎልተው የወጡ ናቸው፡፡

ስነሕይወታዊ
የዝግመተ ለውጥ፡-  
የሰው ልጅ ዝግመተ ለውጥ አሁን ካለበት ሁኔታ ላይ ለመድረስ የዘር ግንድ ከሚጋሩት ሌሎች እንስሳት ተለይቶ በሚሊዮን የሚቆጠሩ አመታትን ተጉዟል፡፡ ከዝንጀሮ መሰል ቅድመ አያቶቻችን ከጎሬላ የዘር ግንድ የተገነጠልነው ትንሽ ቀደም ብለን ሲሆን፤ የቅርብ ዘመዶቻችን ከሆኑት ከችንፓንዚዎች ጋራ እንጋራ ከነበርነው የዘር ግንድ የተገነጠልነው ደግሞ ከ7.5 ሚሊዮን ዓመታት  በፊት እንደነበር ይገመታል፡፡
የሰው ልጅ ከችንፓንዚዎች ጋር  ከ96-99 በመቶ የሚሆን ዘረመሎች (DNA) ይጋራል፡፡ ዘረመል የመጋራት ልኬት መጠን የዝምድና ቅርበት ማረጋገጫ ነው፡፡
በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ ወሳኝ የነበረው ለውጥ በሁለት እግሩ ቆሞ መሄድ የቻለበት አጋጣሚ ነው፡፡ ይህን ቀስ በቀስ ማድረግ የቻለው ከስድስት ሚሊዮን ዓመታት ጀምሮ ነው፡፡ ለውጡም የታየው በአፍሪካ ስምጥ ሸለቆ ሲሆን ለዚህም ሁነኛ ማረጋገጫዋ የአፋሯ ‹‹ሉሲ›› ናት፡፡
እንዲሁም በሁለት እግር መቆም መጀመሩ፣ የፊት እግር ሆኖ ያገለግል የነበረውን የአሁኑን እጅ ነፃ አወጣው። እጅም በሌላ ተግባር ላይ ተሰማራ፡፡ በሂደት በእጅ ላይ ከተፈጠሩት ለውጦ ዋነኛው በአውራ ጣት ላይ የተደረገው ነው። ይህም ነገሮችን ጠንከር አድርጎ መጨበጥ አስቻለው፡፡ በዚህም  ምክንያት የተለያዩ የአደን መሳሪያዎችን እንዲስል (እንዲሰራ) ቻለ፡፡ ስለሆነም አድኖ ስጋ፣ ቆፍሮ ደግሞ ስራስርን ፣ ከበፊቱ በቀለለ መንገድ ማግኘት ቻለ፡፡ ከ800-1000,000 ዓመታት አካባቢ እሳት ከፈጠረ በኋላ፣ ምግብን በቀላሉ አብስሎ ለማላም ቻለ፡፡ ይህም በምግብ ማኘክ ያጠፋው የነበረውን ጊዜ ቀነሰለት፤ የተገኘውን ትርፍ ጊዜም በሌላ ስራ ላይ ማዋል ቻለ፡፡
በመቀጠልም ከሁለት መቶ ሺ ዓመታት በፊት ቋንቋን ፈጠረ፡፡ በቋንቋ በመግባባትና በስራ በመሰማራት መንስኤ፣ የሰው ልጅ አንጎል (አእምሮ) በጣም ዳበረ፡፡ ተግባራቱም እየበረከቱ እና እየሰሉ ሄዱ፡፡ የሰው ልጅ ልዩ ችሎታውም ለ‹‹ጊዜ›› ያለው ልዩ ምልከታው ነው፡፡ (ከሕያው ፈለግ፣ ሽብሩ ተድላ፣ በምንጭነት ተጠቅሜያለሁ)
ማህበራዊ ሳይኮሎጂ፡-  
የማህበራዊ ስልቶችና ስርዓቶች ሁሉ መሰረታቸው ህልውናን ለማስቀጠልና ፆታዊ የግንኙነት እርካታን ለመጎናፀፍ በሚደረገው ሂደት ውስጥ ነው፡፡ ማለትም  በሴትና በወንድ መካከል ያለ ዓለማቀፍ ምስል (ፆታዊ ግንዛቤ)፣ የጓደኝነት ምርጫ ሂደቶች ሁሉ መሰረታቸው የህልውና ጥያቄ ነው፣ ብሎ ያምናል፡፡ በተጨማሪም የሰው ልጅ በቡድን መሰባሰብ፣ የተጠና የግብረስጋ ግንኙነት መንገድ፣ ሀይለኝነት፣ ቁጡነትና ግትርነት እንዲሁም የተፈጥሮን ጫና የመቋቋም ችሎታ የተላበሰው በዝግመተ ለውጥ ሂደት ነው፤ ብሎ ያምናል፡፡
በአጠቃላይ ሲታይ፤ ዝግመተ ለውጥን በተፈጥሯዊም ሆነ በማህበራዊ ተግዳሮቶች  ውስጥ ያለውን ጉልህ ሚና ማስተንተኛ ንድፈ-ሃሳብ  ነው፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጸሃፊውን በኢ-ሜይል አድራሻው፡- This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል፡፡


Read 7837 times