Saturday, 18 December 2021 15:09

“ሕልሜን ንገሩኝ፤ ሕልሜን ፍቱልኝ”…የቸገረ ነገር!

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(1 Vote)

    አንዳንድ ሰው፣ የተበጣጠሰ ሕልም አይቶ፣ ያየውን ይናገራል - “እንት ይመስለኛል” እያለ ይተርካል። ሚስጥሩን ፍቱልኝ ብሎ ይጠይቃል። መፍትሄውን ከጠቢባን ይፈልጋል - እንደ ጥንቱ ፈርኦን፣ እንደ ጥበበኛው ዮሴፍ።
ለአንዳንድ ሰው፣ ፍንትው ብሎ ይታየዋል። “በራሱ ምርጫ ሕልም ያያል” ብንል ይሻላል። አዋቂ፣ ትናንትን አስተውሎ፣ የነገን ያልማል። እንደ ማርቲን ሉተር ኪንግ፣ I have a dream (ሕልም አለኝ) እያለ፣ ከነ ፍቺውና ከነ ትርጉሙ ይናገራል።
ጥበበኛ ሰው፣ ሕልሙን በትጋት እውን ያደርጋል - መልካም መልካሙን። ክፉው ሕልም ደግሞ፣ ሕልም ብቻ ሆኖ ይቀራል - “ሕልም እልም” በሚል ዜማ ታጅቦ። እውቀት የወለደው ሕልም፣ በጥበበኛ ትጋት፣ ተዓምርን ያመጣል። መዓትን ያስቀራል።
ለአንዳንድ ሰው፣ ሕልሙ ይጠፋበታል። የሕልም ጥላ ብቻ ይቀረዋል። መንፈሱ ይደፈርሳል። ወደ ሕሊና ካልተመለሰም፣ ይፈራርሳል። በሙሴ ዘመን እንደነበረው ፈርኦን። ወይም እንደ ናቡከደነፆር ዘመን። የዘመናችን መንፈስ እንደዚህ ነው።
የግል ማንነትን ያከበረ የስልጣኔ ሕልም ዛሬ ጨላልሟል። በእልፍ የዘረኝነት አይነቶችና ቅዠቶች ሳቢያ፣ መልካሙን ሕልም አጥተናል። አማራ፣ ኦሮሞ፣ ትግሬ፣ ሶማሌ፣ ምናምን የሚል ሆኗል - የቀን የሌት ቅዠታችን።
ዝናው ብዙ ነው። ንጉስ ነው። ግዛቱ እጅግ ሰፊ ከመሆኑ የተነሳ፣ አዋጅ ሲያወጣ፣ ለሁሉም አገር ነው። “በመላው ዓለም ለምትኖሩ ሁሉ….” በማለት ያውጃል። አንዳንዴ አስፈሪ ትዕዛዝ ነው፤ አንዳንዴ ደግሞ የምስራች ነው - ሰላም ይብዛላችሁ እያለ አዋጅ ያስነግራል።
“የነገስታት ሁሉ ንጉስ”፣ “ከአፅናፍ እስከ ጫፍ ዓለምን ሁሉ የሚገዛ”፣ …ተብሎ ተፅፈለታል።
ብዙ ጦርነት ያካሄደ፣ በየአቅጣጫው እየዘመተ ያሸነፈ መሪ ነው። ክብሩና ግርማ ሞገሱ ግን ሌላ ነው። በቤተ መንግስቱ ሰገነት ላይ ወጥቶ ዙሪያውን ሁሉ ሲቃኝ፤ ታላቂቷን ከተማና የሕንፃዎቿን ከፍታ ሲመለከት፣ ውስጡ ይፈካል። የክብር ዘውድ፣ የኩራት አክሊል ሆነው ይታዩታል።
ስሙ “ናቡከደነፆር” ይባላል። የዛሬ 2600 ዓመት፣ የዓለማችን ሃያል ንጉስ፣ የብዙ አገራት የበላይ ገዚ፣ ማን ነበር? በሉ። መልሱ፣ ሌላ ሳይሆን “ናቡከደነፆር” እንደሆነ በታሪክ ተፅፎለታል። በታሪክ አዋቂዎች ተመስክሮለታል።
ስሙ ከዘመን ዘመን እየተሸጋገረ፣ ወደ ብዙ ሰው የደረሰው ግን፣ በትንቢተ ዳንኤል ነው። “ሕልሜን ንገሩኝ” ብሎ ለአዋቂዎች ከባድ ትዕዛዝ ያስተላለፈ ንጉስ ነው - ለዚያውም ከነዛቻቸው። ከየአገሩ ተመርጠው የተሰባሰቡ ጥበበኞችና አዋቂዎች፣ ምን ይበሉ?
የሕልም ጭላንጭልና የጥበብ መፍትሄ - በፈርዖንና በዮሴፍ ትረካ።
በእርግጥ፣  ግራ የሚያጋባ ጥያቄና የሚያስፈራ የንጉሥ ትዕዛዝ፣ አዲስ ነገር አይደለም። በየዘመኑ ሞልቷል። “ሕልም አየሁ፤ ሕልሜን ፍቱ” ብሎ አዋቂዎችን መጠየቅ፣ የተለመደ ነገር ነው። ንጉሥ ደግሞ፣ መጠየቅ ብቻ ሳይሆን፣ ማዘዝም ይችላል።
የግብጽ ፈርዖን፣ “ሰባት የሰቡ ከብቶች፤ ከዚያም ሰባት የከሱ ከብቶች በህልም አየሁ። ሕልሜን ፍቱልኝ። ትርጉሙን ንገሩኝ” ብሎ ጠቢባንን ጠይቋል። በትዕዛዝ አስጨንቋል። ሕልሙን የፈታለት፣ ከእስራኤል አገር በባርነት ተሸጦ የመጣ ጥበበኛ ነው። ዮሴፍ የሚሉት ጥበበኛ። ሰባት የአዝመራና የጥጋብ ዓመታት ይመጣሉ።
ከዚያም፣ ሰባት የችግርና የረሃብ ዓመታት ይከተላሉ አለ ዮሴፍ።
ግን፣ በዚህ አላበቃም።  ፍቺውን ብቻ ሳይሆን መፍትሄውንም ጨምሮለታል።
ሕልምን፣ እንደ ፍንጭ እንደ ጠቃሚ መረጃ አስቡት።
ፍቺውን ደግሞ፣ በጥበበኞች ምርምር እንደሚገኝ እውቀት ቁጠሩት። በእርግጥም፣ ሕልምና መረጃ ብቻውን ምን ይረባል - ለእውቀት ካልጠቀመ።
ግን፣ የሕልም ፍቺና እውቀትስ፣ በተግባር ለኑሮ ካልፈየደ ምን ያደርጋል?
ደግነቱ፣ የፈርኦን ሕልምና የዮሴፍ ፍቺ፣ ሕይወትን ለማትረፍ ጠቅሟል። ጥበበኛው ዮሴፍ፣ የቅርቡን አስተውሎ፣ የሩቁን አገናዝቦ፣ መላ ፈጥሯል። በሰባቱ የአዝመራ ዓመታት፣ ብዙ እህል ማምረትና በመጋዘኖችም ቆጥቦ ማከማቸት አንድ መፍትሔ ይሆናል አለ። ለችግር ዓመታት ይጠቅማል። ዮሴፍ፣ በጥበቡና በብልሃቱ፣ ፈርኦንም ምክር በመስማቱና ከልብ አምኖበት በመትጋቱ፤ የእልፍ አእላፍ ህይወት ከረሃብ እልቂት ተረፈ። በባርነት የመጣው ዮሴፍ በፈርኦን ዘንድ ክብርን አተረፈ።
በሙሴ ዘመን የነበረው ፈርኦን ግን፣ ሕልም አልነበረውም። ሰዎችን እንደየ ጥበባቸው ከማክበር ይልቅ በዘር እየለየ በባርነት ይይዛል። ብዙ ከማምረትና ከማከማቸት ይልቅ፣ በባሮች ጉልበት ይተማመናል። ግብፅን የቅዠትና የውድቀት አገር አደረጋት።
የዳንኤል ትረካ፣ ከዮሴፍ ትረካ ጋር ይመሳሰላል።
እንደ ዮሴፍ፣ ዳንኤልም ጥበበኛ ነው። ሕልምንም የሚፈታ።
ዮሴፍ፣ በዘመኑ የአላማችን ሃያል ወደ ነበረው አገር፣ ወደ ግብፅ በባርነት የተሰደደ ነው። ዳንኤልም ከእልፍ ዓመታት በኋላ፣ እጅግ ሃያል ወደ ነበረው አገር፣ ወደ ዛሬዋ ኢራቅ በምርኮ የተሰደደ ነው።
ሁለቱም የቤተ መንግድት ቤተኛ ሆነዋል - ዮሴፍ በፈርዖን ዘንድ፣ ዳንኤል ደግሞ በናቡከደነፆር ቤተመንግስት።
ሁለቱም እጅግ ታላቅ ክብር ያገኙት፣ የንጉሶችን ሕልም በመፍታት ነው። ሌሎች አዋቂዎችና ጠቢባን ያልቻሉትን ነገር ሰርተው፣ ልህቀታቸውን አስመስክረዋል። በጣም ይመሳሰላሉ።
አንደኛ፣ የዳንኤል ፈተና ከባድ ነው። “ሕልሜን ፍታ” ተብሏል። ይሄ የተለመደ ነው። ግን፤ “ሕልሜን እወቅልኝ፤ ሕልሜን ንገረኝ” ተብሎ ታዟል። ከባድ ጥያቄ፣ ከባድ ትዕዛዝ ነው።
ሁለተኛ ነገር፤ የዳንኤል የህልም ፍቺ፤…. ለኑሮ በተግባር ቅንጣት መፍትሔ አያመጣም። ጉዳትን አያስቀርም፣ ጥቅምም አያስገኝም። ሕልም የጠፋበት ዘመን መፍትሄ የለውም። ቶሎ ወደ መልካም ሕልም ካልፈጠነ በቀር፤ እየዋለ እያደረ መውደቁና መፍረሱ አይቀርም።
የትኛው ዋዜማ ላይ እንደሆንን እንወቅ - በቅይጥ ዘመን።
የስኬትና የውድቀት ዋዜማ ይመሳሰላሉ። የቅይጥ አስተሳሰብ ዘመን ናቸው። ልዩነታቸው ምንድን ነው?
በስኬት ዋዜማ፣ እውቀት እየሰፋ ይውላል። ሕልም እየፀዳ እየፈካ ያድራል።
በውድቀት ዋዜማ፣ እውቀት እየሳሳ ይውላል። ሕልም እየደፈረሰ ያድራል፤ እንደ ጥላ የማይጨበጥ ይሆናል።
ትረካው እንዲህ ነው።
“በነገሰ በሁለተኛው ዓመት፣ ናቡከደነፆር፤ ሕልም አለመ። መንፈሱም ታወከ። እንቅልፍም ራቀው።”
ግን ችግር የለውም። አዋቂዎች በንጉሡ ዙሪያ ሞልተዋል። የጠቢባን መነሃሪያ ናት፣ ግርማዊቷ መናገሻ ከተማ፤ ታላቂቱ ባቢሎን። ምን ጎድሎ፣ ምን ጠፍቶ! አብዛኞቹን የአካባቢው አዋቂዎች፣ “ከላዳዊያን” ይሏቸዋል። ግን ከየአገሩ ለሚመጡ ጠቢባንም፤ ባቢሎን ቤታቸው ነበረች።
የንጉሡ ግዛት፣ እስከ ግብጽና እስከ ፐርሺያ ዳርቻ የተስፋፋ፣ ሶሪያና ፍልስጤምን፣ የእስራኤል ጉልላት እየሩሳሌምን ያስገበረ ግዛት ነው። ከግብጽ የተሰደዱ ጥበበኞች፣ በባቢሎን ምድር፣ የህግ አዋቂ ዳኛ፣ የቋንቋ ሊቅ የፅህፈት ባለሙያ፣ ወጌሻና መድሃኒት ቀማሚ ሆነው ሲሰሩ ነበር። በችሎታቸው ተከብረው፤ ለሹመት ተመርጠው።
ታዲያ፣የስነ ከዋክብትና የቀን ቆጠራ ጥበበኞች፣ የስነ ፍጥረትና የፍልስፍና ሊቆች የመኖራቸው ያህል፣ አስማትና መተት፣ ጥንቆላና ንግርት ሁሉ እንደ ጥበብ እየተቆጠሩ ይታመንባቸው ነበር። እውቀትና ጥበብ ቢስፋፋም፣ የጥንቱ ጭፍን እምነት ከነባር ዙፋኑ አልተነቃነቀም። ነባሩ የጥንቆላና የአስማት እምነት ላይ አዲስ እውቀትና ጥበብ መቀላቀሉ ነው የባቢሎን  ድንቅ የስልጣኔ ጅምር።
በነባር የፀሐይና የጨረቃ አምልኮ ላይ፣ የጨረቃን ኡደት በቁጥር የመመዝገብና የማስላት፣ የፀሐይን ዓመታዊ ዑደት የማጥናትና የቀን ቆጠራ ቀመር የማዘጋጀት ጥበብ ሲቀላቀልበት፣ “አስትሮሎጂ” ይሆናል።
ኮከብ ቆጠራ እንዲሉ-የአምልኮና የእውቀት፣ የእምነትና የጥበብ ድብልቅ።
ስር ምሶ ቅጠል በጥሶ፣ መድሃኒት የሚቀምም ጥበበኛ ሲመጣ፣ ከጥንቱ ጥንቆላና ምትሃት ሲቀላቀል፣ ሥራይ እና ሴረኛ፣ ጠቢብና ጠይብ፣ …. ትርጉማቸው ይደበላለቃል። መካሪና መተተኛ፤ ፀሐፊና ጠንቋይ… በደግና በክፋ ስሜት፣  “አዋቂ” ተብለው ይጠራሉ።
ለጥሩና ለመጥፎ የተቀመመ ስራ ስርና ቅጠላ ቅጠል፤ “ፈውስ” ተብሎ ይሰየማል-በሽታን ለመጥራት፣ ጤናን ለማምጣት ቢሆን ያለ ልዩነት ትርጉማቸው የሚምታታበት ጊዜ ነው- የስልጣኔ ጅምር።
“ሕልም እና ፍቺውስ”?
በጥንታዊ ጭፍን እምነት ካየነው፣ ሕልም ማለት፣ የሌላ ዓለም ሚስጢር፣ የሌላ ዓለም ሃይል ነው። የማይከራከሩት ዳኛ፣ የማይገዳደሩት እጣ ፈንታ ነው - የህልም ፍቺ።
በእውቀት አይን፣ በጥበበኛ ሕሊና ሲያጤኑት ደግሞ፣ ሕልምና ፍቺው፣ የስነ-ሕይወትና የስ-አእምሮ ጉዳይ ይሆናል።
ለጊዜው የደመቁ ሃሰቦችና ስሜቶችን፣ ስር የሰደዱ ጥልቅ አቋሞችንና ምኞቶችን፤… የዕለት ተዕለት ኑሮን፣ እንዲሁም በረዥም ጊዜ የተገነባ ውቅር ስብዕናን ሁሉ የሚያንጸባርቅ ነው - የሰው ህልም። በእስከዛሬ ማንነት የተቃኘ ነው።
ዶሮ ብታልም ጥሬዋን ነው ይባላል። ነባር የግል ማንነት ህልምን ይቃኛል። ያላዩት አገር አይናፍቅም እንዲሉ ነው።
የበዛወርቅ ዘፈን ምን ነበር የሚለው? “ትናንትናን ያየ፣ ስለ ነገ ያውቃል” የሚል መልዕክት አለው። “ታሪክን ያስተዋለ፤ ከጠቢብ ይልቃል” ይላል ዘፈኑ። የነገ ተስፋና ስጋት፣ ከትናንት ምኞትና ጥፋት፣ ከዛሬ ድክመትና ብርታት ጋር የተቆራኘ ነው። ህልምም፣ በትናንት ተቃኝቶ፣ ነገን በሰቀቀን ወይምና በጉጉት ያሳየናል። ባያሳይ እንኳ ሊጠቁም ይችላል።
በሌላ አነጋገር፣ በአንድ በኩል፣ ትናንት ባበጀነው ወይም ባበላሸነው ስብዕና የተቃኘ ነው - ህልምና ፍቺም።
በሌላ በኩል ደግሞ፣ በወደፊት ራዕይና ምኞት፣ በወደፊት ስጋትና ፍርሃት የተነደፈም ነው - የሰው ሕልምና ፍቺው። ይሄ፣ በእውቀትና በጥበብ ስናየው ነው።
ህልም በእያንዳንዱ ሰው ልቦና እየተቃኘ የሚሸመን ንድፍ ነው ማለት ይቻላል።
የህልም ፍቺስ? የልቦናን ቅኝት ከነአቅጣጫው ያመላክታል፤ ጭላንጭሉን ያሳያል - የሕልም ፍቺ።
የዳንኤል አባባል፣ ይህን የሚገልጽ ይመስላል። “የህልምህን ትርጉም ልንገርህ” ለማለት፣ “የልቦናህን ልንገርህ” የሚል አባባል ይጠቀማል - ዳንኤል።
ወደ “ስነልቦና” ወደ “ስነ አእምሮ” ሳይንስ፣ የሚያሸጋግር ጥሩ አባባል ነው። ባቢሎናዊ የስልጣኔ ጅምር ልንለው እንችላለን - እውቀትና ጥበብ የተስፋፋበት ዘመን። ነባሩ የጥንቆላና የጭፍን እምነት ጨለማ ላይ፣ የብርሃን ብልጭታዎችን የቀላቀለ የስልጣኔ ቡቃያ ነው። የባቢሎን ችግኝ በሉት። የስኬት ዋዜማ ነው።
የዳንኤል ብቃት የተገለፀበት መንገድም፣ ያንን ቅይጥ ዘመን የሚያመለክት ነው። “በትምህርትና በጥበብ ሁሉ” እጅግ የመጠቀ ሊቅ እንደሆነ በትረካው ተነግሮለታል። ከዚህ ጎን ለጎን፣ “በራዕይና በሕልም ሁሉ” አስተዋይ ነበር ተብሎለታል።
“በንጉሡ ግዛት ውስጥ ከሚኖሩ ሕልም ተርጓሚዎችና አስማተኞች ሁሉ”… የዳንኤል ጥበብ እጅጉን እንደሚልቅ፣ አስር እጅ እንደሚበልጥ ንጉስ ናቡከደነጾር ራሱ መስክሯል።
ብቻ ምናለፋችሁ። ንጉሡ ህልም ቢያይ፣ ትርጉሙን ተንትነው ሊያስረዱ፣ ገልጠው ሊያሳዩ የሚችሉ ጥበበኞች በባቢሎን ሞልተዋል- አገሩ የጥበብ አገር ነው። በዚያ ላይ፣
እንደ ዳንኤል፣ ከቅርብና ከሩቅ አገራት፣ ከዘመተባቸውና ካስገበራቸው ግዛቶች፣ በምርኮና በስደት፣ ከእስራኤልና ከግብፅ፣ በሶሪና ከፐርሽያ የመጡ ጠቢባን የተሰበሰቡባት ከተማ ናት። ንጉሡ ሲጠራቸው ይመጣሉ፤ ከፊቱ ቀርበው ትዕዛዙን ይፈጽማሉ። የትዕዛዙ አይነት ነው አሁን የቸገራቸው።
 ከስኬት ከግንባታ ዋዜማ፣ ወደ ውድቀት ዋዜማ።
ሕልሙን እንዲነግሩት፣ ንጉሡ፣ የሕልም ተርጓሚዎቹና አስማተኞቹን፣ መተተኞቹንና ከለማዳዊያኑን አስጠራ። እነሱም ገብተው ከንጉሡ ፊት ቆሙ።
ንጉሡም፣ “ህልም አልሜያለሁ። ሕልሜን ለማወቅም መንፈሴ ታውኳል። “ አላቸው።
“ንጉሥ ሆይ፤ ሺህ ዓመት ንገሥ። ለኛ ለአገልጋዮችህ ሕልምህን ንገር። እኛም ፍቺውን እናሳይሃለን” ብለው ተናገሩት።
ችግሩ እዚህ ላይ ነው። ሕልሙን አያውቀውም። ወይ ረስቶታል። ከአእምሮው ጠፍቷል። ወይም ከመነሻውም በግልጽ አልታየውም።
በድንግዝግዝና በብዥታ ያያችሁት ነገር፤ ሳይታወቃችሁ በአፍታ ደብዝዞ ይጠፋል። ይምታታል። የጠረን ሽውታው ብቻ ይታወሳችኋል። የጽልማሞት መንፈሱ ብቻ ይቀራል። ወይ የወገግታ ስስ ምልክት ብቻ ይታያችኋል።
“ቅር፤ ቅር አለኝ። ለምን እንደሆነ እንጃ። ደስ የሚል ነገር ተሰምቶኛል። ፍርሃት ፍርሃት አለኝ። ምክንያቱን እንጃ።” የሚያስብል ነገር አልገጠማችሁም?
ከነገሩ፤ እንኳን በህልም ቀርቶ፤ በእውን እና በቁም፤ የወደፊት ራዕይንና መልካም ምኞትን በግልፅ ማወቅ ቀላል አይደለም። የዘመናችንን መንፈስ፣ ተመልከቱ። በግልፅ የማይታይ ድፍርስ ረግረግ መንፈስ ነው። ድንግዝግዝ ብዥታና በትርምስ የታወከ መንፈስ አጥልቶብናል። ሕልም ጠፍቶብናል።
ናቡከደነፆርም፤ ሕልሙን ማወቅ ተስኖታል። ጠፍቶበታል፤ የሕልም ጥላ ብቻ ነው እንደ ጽልማሞት ያጠላበት።
“ነገሩ ከኔ ዘንድ ርቋል። ሕልሜንና ፍቺውን ባታስታውቁኝ፤ ትሰየፋላችሁ። መኖሪያችሁም፣ የጉድፍ መጣያ ይደረጋሉ። ሕልሜንና ፍቺውን ብታሳዩኝ ግን፤ ከኔ ዘንድ ስጦታ፣ ክፍያና ብዙ ክብርም ትቀበላላችሁ። ስለዚህ፤ ሕልሜንና ፍቺውን አሳዩኝ” አላቸው።
አዎ፣ እንደ ዛሬው ዘመን፣ የናቡከደነጾር ዘመን፣ ከስልጣኔ ግስጋሴ የተገኘ ድንቅ ዘመን ነው -የባቢሎን ዘመን። ነገር ግን፣ የስልጣኔን ህልም ከዘነጉ፣ ወይም በድፍረት ንቀው ከጣሉት፣ መጨረሻው አያምርም። ወደ ውድቀትና ጥፋት ያመራል።
ዛሬም፣ ይህ እየተደገመ ነው።
የግል ማንነትን ያከበረ የስልጣኔ ሕልም ዛሬ ጨላልሟል። በእልፍ የዘረኝነት አይነቶችና ቅዠቶች ሳቢያ፣ መልካሙን ሕልም አጥተናል።
In a famous speech, in 1963, Martin Luther King, Jr., said:
Even though we face the difficulties of today and tomorrow, I still have a dream. It is a dream deeply rooted in the American dream.
I have a dream that one day this nation will rise up and live out the true meaning of its creed: “We hold these truths to be self-evident—that all men are created equal.” . . .
… a desert state sweltering with the heat of injustice and oppression, will be transformed into an oasis of freedom and justice.
I have a dream that my four little children will one day live in a nation where they will not be judged by the color of their skin but by the content of their character.
ሁሉንም ሰው፣ ነጭ ይሁን ጥቁር፣ በግል ተግባሩ፣ እንደ የስራው፣ በትክክል የምንመዝንበትና የምንዳኝበት  የስልጣኔ ዘመን ይመጣል። ያንን ዘመን በአይነ ሕሊና አማትሮ የሚያይ፣ ነፃነትና ፍትህ በሕብር የተጣመሩበት የፍቅር ዘመንን የሚጣራ ነበር የያኔው ሕልም። የዛሬ 58 ዓመት በማርቲን ሉተር ኪንግ ንግግር የተገለጠው ሕልም።
የዛሬ ሕልምስ? ቅዠት ብንለው ይሻላል። ነጭ እና ጥቁር እያለ የሚናገር ነው - የዛሬው ቅዥት። Black Lives Matter እንዲሉ። በኛ አገር ደግሞ፣ የሕልም ጭላንጭሉ የለም። አማራ፣ ኦሮሞ፣ ትግሬ፣ ሶማሌ፣ ምናምን የሚል ሆኗል- ቅዠታችን።


Read 3056 times