Monday, 20 December 2021 00:00

“የልቤ ክረምቱ” - የታገል መሰላል

Written by  ደረጀ በላይነህ
Rate this item
(0 votes)

 በየዘመኑ በጥበብ ዓለም የሚወለዱ የጥበብ ሥራዎቹ፣ በየድንኳናቸው የሚታዩ ሕልሞች በእርሻው የሚበቅሉ አበቦች፣ አምረውና ደምቀው፣ አብበውና ፈክተው፣ አሊያም  ጠውልገውና ደርቀው ይታያሉ። ከፊሉ ዘመን ተሻግረው ሌላውን ዘመን ዐውድ ሲያውዱ፣ ያላለላቸው ደግሞ እዚያው ከስመው ታሪካቸውን ዐመድ ውስጥ ያበቃሉ።
ጽሑፌን በዚህ ሀሳብ የተንደረደርኩት በዋዛ አይደለም፡- ሰሞኑን “የልቤ ክረምቱ” በሚል ርዕሰ ደራሲና ገጣሚ ታገል ሰይፉ፣ ከዛሬ 32 ዓመት ጀምሮ የጻፋቸውን ግጥሞች መርጦ ያካተተበትን መጽሐፍ መነሻ አድርጌ ነው።
በ100 ገጽ በሸጋና ማራኪ ሽፋን የተጠረዙት የታገል የግጥሞች መድበል፣ የገጣሚውን የዘመንና ጥበብ እርከን ከማሳየት ባሻገር፣ የረገጡትን የዘመን ፍልስፍና፣ ፖለቲካና ኢኮኖሚያዊ ገጽታ ያሳያሉ።
ግጥሞቹ በሀሳብም በቅርጹም ዥንጉርጉር ሆነው የሚታዩና በየዘመናቸው የነበሩትን የቃላት አጠቃቀም  የትረካ ስልት ወዘተ የያዙ ስለሆነ የአማርኛን ግጥሞች ዳና ለማጥናት ለሚፈልጉ ሰዎች ጥሩ አጋጣሚ የሚፈጥሩ ይመስለኛል።
“Literary Application” የተሰኘውን መጽሐፍ የጻፉት ፒተር ዌስት ላንድ፤  “… A thought is a child of the mind, and a word is the clothing of that child with a grament of flesh” እንዳሉት፤ ታገል የአእምሮውን ምጥ ውጤቶች በቃላት ሥጋ አልብሶ ከትውልድ ትውልድ እንዲዘልቁ አግዟቸዋል።
ከዚህ ቀደም ከጻፋቸው የግጥም መጻሕፍት ውስጥ ከአራቱ ማለትም ከፍቅር፣ ቀፎውን አትንኩት፣ የሰዶም ፍጻሜ እና በሚመጣው ሰንበት የመረጣቸውን ግጥሞች ወደ ዛሬና ቀጣዩ ጊዜ አንባብያን አሻግሯል።
“በ14 ዓመት ዕድሜዬ አሳትሜዋለሁ” የሚለው “ፍቅር” በሚል ርዕስ ከታትመው መጽሐፉ የወሰዳቸው ግጥሞች፣ በሃሳብና ቅርጽ ከዕድሜው  ዘለግ ብለው የሚታዩ ናቸው። ለምሳሌ ገጽ 6፤ “ሊስትሮ” በሚል ርዕስ የተጻፈው መንቶ እንዲህ ሰፍሯል፡-
 ሣጥን ቢጤ ይዞ፣ እዚያም!  ሲሮጥ ሁሉን እየቃኘ ለመኖር ሲዳክር፣ እንጀራው እግሩ ስር ተቀምጦ ተገኘ።
እኛ ሊስትሮን የምናውቀው፣ ከጣውላ የተሰራ ሰንዱቅ/ሳጥን እንዲ፣ ሆድ የሚገባ እንጀራ  አይደለም። ገጣሚው ግን በሌላ ዓይን አይቶታል። ዋው! መሰኘት ደግሞ የጥሩ ግጥም ባህርይ ነው።… እንጀራ ሰው እግር ስር ምን ይሰራል?... እንዴት እንጀራ ይረገጣል?... የእንጀራው መጋገሪያ የሕልውናው ቋትና ምጣድ ነው- ሣጥኑ!
አሜሪካዊው ፕሮፌሰር ሎረንስ ሪኔ እንደሚሉት በሌላ ዓይን፣ በአዲስ መንገድ - ማየት የገጣሚ አንዱ  የሥነ ግጥም ባለሙያው መመዘኛ ነውና… ይበል የሚያሰኝ ነው።…
ያ ዶሮዬ ጮኸ መንጋቱን ነገረኝ
በዛሬው ቀን ላርደው ቀጠሮ ነበረኝ።
የሚለውም ግጥም ከልጅነት መጽሐፉ ከ“ፍቅር” የተወሰደ ነው። ይህ ግጥም ሀሳቡ ሲተነተን የትና የት ነው! ከብዙ ጉዳዮችና ሕልሞች ጋር ልናነጻጽረው እንችላለን። … የነገ ጀንበራችን፣ የነገ የብርሃን ፋናችንን ዛሬ ልናዳፍነው ነው፤ ነገ ከቆፈኑ የሚያድነን ፍም፣ ውሃ፤ ልንደፋበት እንደምንችል የሚነግረን ግጥም ነው! ስለ አስተውሎት በብዙ አቅጣጫ ሊነግረን ይችላል። ርጋታ፣ ትዕግስት፣ ጥሞና፣ ከውሳኔ መቅደም እንዳለበት ሽንቁር ያሳየናል፤ ግን አይሰብከንም።
ከሌላኛውና ሁለተኛው የታገል የግጥም መጽሐፍ ከሆነው “ቀፎውን አትንኩት” ጥራዝ የተወሰዱት ግጥሞች በ1986 ዓ.ም እንደታተሙ ገጽ በመግቢያ ላይ ተጠቅሷል።
በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ከተካተቱት ግጥሞች ብዙዎች የሰው ልጆችን ስኬትና ውድቀት በሚመለከት አዝወትረው የሚጠቅሷት ግጥም የመጀመሪያው ገጽ ላይ ትገኛለች። ርዕሷ “ጠላቴን ስመርቅ” ይላል፡-
ከፍ በል ወደ ላይ፣
ከስልጣኑ ሰማይ፣
ከስም አደባባይ፤
በሃብት ከፍ ከፍ፣
በሹመት ከፍ ከፍ፣
ከፍ! ከፍ!
ከፍ! ከፍ!
ከዚያ የወደክ‘ለት፣
አጥንትህ እንዳይተርፍ!
ሽቅብ ወጥቶ ቁልቁል መፈጥፈጥ፣ ሞቱና ጉዳቱ የከፍታውን ያህል ነውና!... ይህ የታገል ግጥም “ምርቃት” ይሁን እንጂ ርግማን ነው። ላይ ላዩን ያጠለቀው ጭምብልና የሚጠቀምባቸው ቃላት አዎንታዊ ቢሆኑም፤ ግባቸው ጥፋትን መመኘት ነው። … ስላቅና ምፀት!
በዚህኛው መጽሐፍ ውስጥ በተራኪ ዘውግ የተጻፉ ግጥሞችም አሉ። ለምሳ ገጽ 28 ላይ “እኔና ወዳጄ” የሚለው ግጥም፤ በ”ኢሮስ” ፍቅር የተለከፈ ገጸ ሰብ የሚባትተውን መባተትና ግራ መጋባት ያሳያል። በግጥሙ ውስጥ ሁለት ገጸ ባህርያት በቁዘማና በግራ መጋባት ሲመክሩ እናያለን። አንዱን አንጓ ለማሳያነት እነሆ፡-
አቤቱ ወዳጄ ትዝታውን ታሞ፣
ማዶውን እያየ… ከዛፎች ስር ቆሞ፣
ዓይኖቹን ሳያቸው… ሰው እንደተራቡ
ምን ነክቶሃል ብዬ … ቆምኩኝ አጠገቡ፤
“አይጣል ነው ወዳጄ”… አለኝ በሰቀቀን፣
ያሳለፈው ጊዜ… ከፊቱ ቢደቀን
በሚቀጥለው አንጓ ላይ፣ በፍቅር የተያዘና ግራ የተጋባ እንደሆነ እናያለን፡፡ ማዶ ማዶ የሚያየውም፤ ዓይኖቹ ሰው የተራቡት… ልቡ በናፍቆት የነደደውም በፍቅር ነው።
ገጣምያን በወጣትነት ስለ ተቃራኒ ጾታ መጻፋቸው፣ የስሜቱን ግለት፣ የምድጃውን ነበልባል በቅርብ ስለሚያውቁት ነው። ፍቅር በወጣትነት ይንተከተካል፣ በጉልምስና ፍም ይለብሳል፣ በስተእርጅና ትዝታን ይንተራሳል!... ገጣሚም የዚህ ሕይወት አካል ነውና፤ ጣዕሙን ያጋራናል!... በእያንዳንዳችን ልብ ውስጥ ያለችውን ጽጌሬዳ አሽትቶ፣ መዐዛዋን ይተርክልናል!
ሦስተኛው የታገል መጽሐፍ “የሰዶም ፍጻሜ” ነው። ከዚህ መጽሐፍ በ”የልቤ ክረምቱ” 21 ግጥሞች ተመርጠው ተካትተዋል።
በዚህ እትም የበኩር ሆና የመጣችውን ግጥም በእጅጉ ግዙፍ ምስል አላት። ርዕስ “የፍቅር ቀጠሮ” የሚል ነው። የፍቅርን ቀጠሮ ፣ ቁመት፣ የጊዜን ሕግ ገፍትሮ መጣል የጣሪውን ሽቅብ መሸሽ! የግድግዳውን ድንዳኔ የቀመሰ ያውቀዋል። ይህ ግጥም ያንን ነው ድንች አልባ አድርጎ የሚያሳየው!
ጠበኩሻ ኔማ… እዚያው ስፍራ ቆሜ፣
በአክሱም ቁመና… በላሊበላ ዕድሜ፣
እግሮቼን ተክዬ… ቀኔን አስረዝሜ፣
የሔድሽበት መንገድ… ልቤ እንደነጎደ፣
ስንት ነገር መጣ… ስንት ነገር ሄደ?
ስንት ጊዜስ ነጋ… ስንቴ ጎህ ቀደደ፣
ስንቴ ዝናብ ጣለ… ስንት ጊዜ አባራ፣
ትመጫለሽ ብዬ… በቆምኩበት ስፍራ፣
ስንቴ አድማሱን ማተርኩ… ስንትና ስንት ዓመት?
አንገቴን አስግጌ… በራስ ዳሸን ቁመት፣
በአክሱም ቁመና …. በላሊበላ ዕድሜ
በቀጠርሽኝ ስፍራ…. ስጠብቅሽ ቆሜ፤
ስንት ሳቅ አለፈ…. ስንትና ስንት ዕንባ፤
ስንቴስ ክረምት ሆነ…. ስንት ፀደይ ጠባ?
ስንቱ ተገናኘ… ስንቱ ሰው ተጋባ?
ግጥሙ በግነት የተፃፈ፤ ጠባብዋን ቅድበት ዓለምን በሚሞላ ስፋት የሸፈነ፣ የሸረሪቷን ክር፣ የግዙፉ ዋርካ ግንድ ያህል ያተለቀ፣ ዓመታትን በደቂዎች ማህፀን ውስጥ ያጨቀ፤ የዘመን ልውውጥ በአንድ እፍኝ የቋጠረ ማንፀሪያ ነው፡፡
ይህ ሁሉ ግን ግቡ አንድ ነው፡፡ ይህ የፍቅርን ሃያልነትና ብርቱ ጡንቻ ማሳያ ነው፡፡ የተፈጥሮ ሕግን መሻር የሚችል፤ የሌለውን እንዳለ አድርጎ የሚከስት ጠባቡን የሚያሰፋ፣ ረቂቁን የሚያገዝፍ፣ ጊዜ የሚበቃው ራሱን የቻለ ሰፊ ዓለም መሆኑን ነው፡፡ … ረቂቅ ሆኖ፤ ግን በተጨባጩ ዓለም ፍጥረት የሚያናውጥ ምትሃት!
“የሰዶም ፍፃሜ” ውስጥ አንዱ-ግጥም የትሬያንግል-የሶስት ማዕዘን ቅርፅ ያለው ሲሆን፣ “ፍቅር” ውስጡ ካለው ተመሳሳይ፤ ቅርፅ በተለየ ትርጉም የሚሰጥ፤ “ግድያ ሲወፍር” የሚል ግጥም አለ፡፡ (ገፅ 38)
ቃየል
 መክኖ የለ
አንድ ሰው ሞቷል አይደል
ዐውቆ በሰራው ግፍ ባልፈጸመው በደል
ቃየልም በክፋት ሠራት ፈለሰፋት ጭካኔን
በክርኑ
ያኔ መቼ ገባው ግድያ ሲወፍር ጦርነት
መሆኑ
 አቤል አፈር ሲግጥ ቃየል ግን እንዳፈር
ምድርን መሸፈኑ
 ይህ አይነቱ  ገፅ ፅሑፋዊ ቅርፅ፣ በግሪክ ውስጥ ከክርስቶስ ልደት በፊት 4ኛው ክፍለ ዘመን ገደማ የተጀመረ ነው፡፡ በስነፅሑፍ ቃላትና ቲዎሪዎች ላይ የተፃፉ አንድ መፅሐፍ እንዲህ ይላል፡- this kind of poem has its lines arranged to represent a physical object  or to suggest  action /motion` mood/ feeling i but usually shape and motion Thus geometric figures are common`
ከላይ የተመለከተው ግጥም ሀሳቡና ድርጊቱ ከአንድ ቃየን ጀምሮ ግድያ ወፍሮና ሰፍቶ ጦርነት ክንፉን መዘርጋቱን፣ አንዱ ጠበኛ ሰው ደግሞ ተባዝቶ ዓለምን  መሙላቱ… ከሀሳቡ ጋር ያለው ግጥምጥሞሽ፣ ፈረንጆቹ ከሚሰሩት የተለያየ ቅርጽ፣ ክንፍ፣ የጠርሙስ ቅርጽ ወዘተ ይልቅ ትልቅ ትርጉም የሚሰጥ ሆኖ ተቀምጧል፡፡ … ይህ ትልቅ-ሀሳብ-በትልቅ-በሀዲድ እንደከነፈ-የሚያሳይ ስለሆነ በግሌ ከፍ ያለ ግነት ሰጥቸዋለሁ፡፡ ታገል በዚህ ጥራዝ ባካተታቸው ግጥሞች የመሰላሉን መርገጫዎች ከፍታ እየጨመረ መምጣቱን ለማሳየት ትልቅ መንገድ ነው ማለት ይቻላል፡፡
ብዙዎቻችን ለቴሌቪዥን ምስል የለበሱት የመመዘኛ ግጥሞች የሰጠናቸው ግምቶች ወደ ጎን ብለን ስናያቸው ታገል እየጨመረ እንጂ እየቀነሰ አልመጣም። ፊልም የለበሱ ግጥሞች በአድናቆት ብቀበልም፣ ወደ ወረቀት ሲመለስ እምቅነት፣ ሙዚቃዊነት፣ ድርድርነትና ምናባዊነት ላይ ችግር ይገጥመዋል የሚል ስጋት ነበረኝ፡፡… ይሁን እንጂ “በሚመጣው ሰንበት” መፅሐፉ ላይ በበለጠ ሀሳብና ልዕቀት (excellence) መጥቷል፡፡ በተለይ የቤት ዓመታት ስልቱ በእጅጉ ጣፍጦለታል።
የጋዜጣው ገፅ ስለሚገድበኝ “በጨለማ የሚያበራው ትል” ከሚለው ግጥሙ ጥቂት ስንኞች እዋሳለሁ፡፡ (ገፅ 89)
ካናታቸው ላይ ነግሰህ
ከፍ ብለህ ስለበራህ…
ተመሳጥረህ ከፅልመቱ
 ብትንጎማለል በግርማ
ብትብለጨለጭ በከንቱ
ውጧቸው ድቅድቅ ጨለማ፤
ገደል ገብተው ለሚሞቱ
ካልደረስክላቸውማ
ቅንጣት ብርሃን ካልተረፈህ
ከቁም ዳፍንት የሚያጠራ
ዋጋም የለህ ላይን ገዝፈህ
ሽቅብ ብትከንፍ እንዳሞራ፡፡
እያለ ይቀጥላል፡፡ ይህ ግጥም በቤት ዓመታቱ የተመረጠው “የሀለ-ሀለ” ቤት የሚጠቀም ሲሆን ሀሳቡም ግሩም የሚባል ነው፡፡ --- ማህበራዊ ኂሱም ዘመኑን የሚያሳይ፤ የሀገር ቀላም ነው። በዚህ መድብል ውስጥ ከዚህ ቀደም የህትመት ብርሃን ጨርሶ ያላዩ 3 ግጥሞች መካተታቸውን ሳልገልጽ ማለፍ አልሻም፡፡
በአጠቃላይ “የልቤ ክረምቱ” የገጣሚ ታገል ሰይፉ የሕይወት ዘመን ምርጥ ሥራዎች ስለሆኑ፣ ለጥናትም ለውበትም፣ በአንባቢዎች እጅ ቢገቡ እንደ በረከት እቆጥራቸዋለሁ፡፡ አንብቧቸው!!

Read 2867 times