Saturday, 18 December 2021 15:37

የመለየት ሲቃ

Written by  አፀደ ኪዳኔ (ቶማስ)
Rate this item
(11 votes)


           "የምሰራበት ድርጅት ውስጥ ሁለታችንም የሂሳብ ባለሞያ ነን። አንድ ቀን በሙሉ ዓይኔ አይቻት አላውቅም። የምትለብሳቸው አጫጭር ቀሚሶች፣ የምትቀባው ሽቶ፣ ቀጥ ብሎ የወረደ አፍንጫዋ ስቦኝ አያውቅም። እሷ ውስጥ እራሴን ተመልክቼ አላውቅም። ስለ ስራ እናውራ እንጂ ሌላ ነገር አውግተን አናውቅም። አምስት አመት በዝምታ ሳያት፣ በትዝብት ስመለከታት ነበር የከረምኩት።--"
          
         ይሄ በ ”ነበር” ገፅ ላይ የተፃፈ የፍቅር ገድል ነው። በመሰልቸት  የተቋጨ፣ የትላንት ጣፋጭነቱ በመራር ግት የተጠናቀቀ የፍቅር ንዑስ  ድርሳን  ነው።
 ጡቷ ሥር ሆኜ የቀመስኩት የመውደድ ወተት፣ ህይወትነቱ ቀርቶ ሥስ ትዝታ ትቶ አልፏል። ደረቴ ላይ ዘለዓለም የመቅረት ምኞቷ አሁን እንደ ተቀደደ ወረቀት በቆሻሻ ቅርጫት ውስጥ አንቀላፍቶ “ልዋጤን” ያንኮራፋል። ከዚህ የዘመን መታያ ማህፀን የተማጠው ህያው እንባ፤በሰዎች ልብ ላይ ተንጠባጥቦ፣ ሁሉም ነገር ዝምታን እንኳን የሚረታ ብርታት የለውም።
ይሄ የህይወቴ ድስት ውስጥ የተቁላላ የፍቅር መረቅ ነው። ልረሳው፣ ልተወው፣ ልሸነግለው እንዴት ይቻለኛል? ባልስቅም እዚህ ድስት ውስጥ የመውደዴ ወዝ አለ። ባላለቅስም እዚህ ድስት ውስጥ የፍቅሬ እንባ አለ።
ዓለም እያየናት ትቀየራለች። ህይወት ዐይናችን ስር ሆና ሀመልማሎ ሳቋ ይወይባል። ሃዘኗም ለዛ በሌለው ክራር ተቃኝቶ “አትሂዱን” ይዘምራል። አታሞው የሚደለቀው በትዝታ ስልት ነው። ሽብሸቧው የሚገለጠው በዝምታ ወረብ ነው። እኛነት “እኔ” በሚል ግላዊነት ይቀየራል። አንድ አካል፣ አንድ አምሳልነት በጊዜ ስለት ተቆርጦ ሁለት ይሆናል። ሁሉም ነገር ይቀራል። ነበር ይሆናል ሩቅ ስሙ። ትላንት ነው የደስታ ምጡ።
“የቀረሁት ትላንት
የሞትኩት ዛሬ ነው
ዝምታ ሆኗል  ቁርሴ
አፈር ነው ትራሴ
አንቺን አንቺን እያልኩ አዝናለሁ በራሴ”
  የከተማ መሽታ ቤት ያለው አዝማሪ ያንጎራጉራል....
...ከዚያ ጠባብ ዐይኗ  ዐይኔ  ስትርቅ፣ ያ እቅፏ የጊዜን አቧራ ለብሶ ሰፊ የልቤ መንገድ ላይ ሲጓዝ ተመለከትኩ።  ... ፍቅራችን የመራራቅ ድር ሲያደራበት ፣ ሞት እኔ ላይ በመኖሬ  ሲቀልድ፣ ሲስቅ፣ ሲያሽካካ...ደግሞ ትከሻዬን ቸብ እያደረገ ሲያበረታኝ፣ ተስፋ የሚሉትን የነገን ሙቅ ሲያጠጣኝ አየሁ። እንቅልፍ እምቢ ሲለኝ... ናፍቆት ሩሄ ላይ የመከፋት ድንኳኑን ሲጥል፣ ህይወቴ ውሉ እንደጠፋበት ልቃቂት ሲወሳሰብ፣ የመኖሬ ሰማይ ሲጠቁር፣ ዳመኖች ናፍቆትን እንደ ዝናብ ሊጥሉ ሲያንዣብቡ፣ የዝናባቸው ጠፈጠፍ እምነቴን ሲያጨልም ቃኘሁ። ቀኖች እንደ ዔሊ ሲያዘግሙ፣  ዛሬም ከትላንት ሲነጠል... መውደድም ወደ ጥላቻ ሲቀየር፣ ሃቅ  በማስመሰል ሲተካ፣ በፍቅር መተያየት በግልምጫ ሲለወጥ አስተዋልኩ። የማልናገረውን መናገር ጀመርኩ። ያልጀመርኩትን መቋጨት አማረኝ። ፅልመትን በብርሃን ልተካ መቃብሬ ላይ ባጀሁ። ለለቅሶዬ ድንኳን ከጣሉ፣ ለእዝኔ ንፍሮ ከቀቀሉ፣ ለሞቴ ጥቂት እንባ ላፈሰሱ ሰዎች በህይወቴ መገኘቴን ለመናገር ትልቅ ጉብታ ላይ ወጣሁ። ቀና ለማለት በሞከርኩባቸው ቀናት ሁሉ ይበልጥ አቀረቀርኩ። ልስቅ ከንፈሬን በገለጥኩ ቁጥር ሃዘን እየተንጠባጠበ ድዴ ላይ ተነቅሶ አየሁ። ጓዜን ይዤ ለመራመድ ስሞክር ሁሉን ትቼ ለመሄድ ስነሳ፣ ከዚያው የሚያስቀር ምትሃት አንቆ ያዘኝ። ባለሁበት ቆሜ የምፅአት ቀንን የምጠብቅ ነኝ። መሄድ እንደ መቆም ያለ አድካሚ ነገር መሆኑ የሚገባችሁ እኔን ስትሆኑ ነው።  ሁሉም ነገር አደከመኝ።
ሁሉም ነገሮች እንደ ህልም፣ እንደ ቅዠት ይታዩኛል። እንባዬ ከዓይኔ ላይ ደርቆ፣ ልቤ ፍርሃትን እንደ ስልት ይመታል። ትንንሽ የምላቸው ዓለሞቼ ተቀይረው፣ ያንን የሳቅ ፍንደቃ በሃዘን ለውጠውት፣ ዓለም በእኔ ላይ ቂም የያዘች፣ እግዜር በእኔ ላይ በቀል ያሰበ እየመሰለኝ ነው።  ነገሮች አንዳንዴ ቅር ያስብላሉ። ትላንት በዛሬ ሲለወጥ፣ እምነት በክህደት ሲተካ፣ ሳቅ ሃዘንን ሲወልድ፣ እውነት ዋሾነት ሲያቅፍ...ሁሉም ነገሮች ቅር ይላሉ። ይመስለኝ ነበር። አብረን ስንሆን፣ ስታቅፈኝ...ደግሞ በሳቅ ታፍና ስታወራ፣ ደግሞ ከንፈሬን ስትስመኝ፣ ዐይኗን እያየሁ ዘላለም እንደማላጣት ገብቶኝ ነበር። ተያይዘን የሄድንበት መንገድ፣ ተቃቅፈን በፍቅር እንባ የታጠብንበት ቦታ ሁሉም መለወጥን ያቀነቅናሉ። ሁሉም ነገሮች ጊዜያዊ መሰሉኝ። አንዳንዴ ሰዎች የሚመጡት ለመሄድ ሲያስቡ ነው። የዛሬን አያድርገውና ፍቅሩን የጀመረችው እሷ ነች። አሁን ስለዚህ ሁሉ አልናገር። አሁን የድሮ በርኖስ ለብሼ በትዝታ ልኳትን። የእድሌ ገመድ  ከአንዲት እንስት ጋር ቢገመድም፣ አሁን ያ ገመድ ተበጥሶ ብቻውን ቀርቷል። የአርባ ቀን እድሌ ሲሉ እሰማለሁ። ምን እንደሆነ አላውቅም። አርባ እና እድል ምን እንደሚያገናኛቸው አልረዳም። ብቻ የአርባ ቀን እድሌ፣ የአርባ ቀን ሞቴን ይዞ እንደመጣ አውቃለሁ። እንደ ኢየሱስ አርባ መዓልትና አርባ ሌሊት ልፆም ይዳዳኛል። ኑሮዬ አንድ ሰሞን ከነበረችው በተቃራኒው ቆማለች። ሁሉም ነገር ልክ አይደለም። አምላክም ፍትህና ርትዕ አያውቅም። የጠቢቡ ሰለሞን እቁባቶችና ሚስቶች ከአንዲቷ መነጠልን፣ ከአንዲቷ ከመራቅ ያድናሉ? የአንዷ መሄድ በብዙዎች መምጣት አይተካም።  ህይወቴ ውብ ነበር፤ አሁን ግን ግራጫ የሃዘን ደበሎ ለብሷል። የፍቅር ለምድ የለበሰች በግ ነበረች፤  አሁን ግን ወደ የጥላቻ ቀበሮነት ተለውጣለች።
ብቻ ዝም ልበል። ስለዚህ አወዳደቄ ከምትሰሙ ስለዚያ ጣፋጭ የፍቅር ቀዳማይ፣ ስለዚያ የፍቅር ጥንስስ፣ ስለዚያ የመውደድ አባዜ፣ የማፍቀር ዛር ብትሰሙ ይሻላል.. ስለዚህ እንደ በረዶ የቀዘቀዘ መለያየት ከምትሰሙ፣ ስለዚያ ትኩስ ጣፋጭ ፍቅር ብትሰሙ ይሻላል...
እንዲህ ነበር የሆነው።
የምሰራበት ድርጅት ውስጥ ሁለታችንም የሂሳብ ባለሞያ ነን። አንድ ቀን በሙሉ ዓይኔ አይቻት አላውቅም። የምትለብሳቸው አጫጭር ቀሚሶች፣ የምትቀባው ሽቶ፣ ቀጥ ብሎ የወረደ አፍንጫዋ ስቦኝ አያውቅም። እሷ ውስጥ እራሴን ተመልክቼ አላውቅም። ስለ ስራ እናውራ እንጂ ሌላ ነገር አውግተን አናውቅም። አምስት አመት በዝምታ ሳያት፣ በትዝብት ስመለከታት ነበር የከረምኩት።
 አንድ ቀን መስሪያ ቤት ውስጥ ግብዣ ነበር። ውስኪው ወርዶ ፣ በጉ ታርዶና ተጠብሶ እየተበላ... አጠገቤ መጣችና አንድ መፅሐፍ ሰጠችኝ። “Things fall apart” ይላል። የአቼቤ መፅሐፍ ነው።
“አንብበው” አለችኝ።
“እሺ” ብያት መፅሐፉን ሳየው ውስኪ ቀድታ ይዛልኝ መጣች። እንደማልጠጣ ብነግራትም እሺ አላለችኝም። መጠጣቴን አምኜ ተቀበልኩ። ስቀምሰው አስጠላኝ። ውስኪ ደስ የማይል መጠጥ ነው። እና ከዚያ ጊዜ ጀምሮ አያት ነበር። እየጠጣን ብዙ አወራን። ስለምትወደው ድንቅ ደራሲ መናገር ጀመረች።
“ዶስቶቭስኪ የሰዎችን ስነ ልቦና በጥልቀት የተረዳ ደራሲ ነው። እሱ ስራዎች ውስጥ የሃሳብ ክምር አይታጣም። ነገሮችን በተለየ መንገድ የሚረዳ፣  በተለየ መንገድ የሚያስብ ደራሲ ነው። “notes from underground” የሚለው ስራው ውስጥ የሳለው ገፀባህሪ እድሜ ልክ ከአዕምሮዬ አይጠፋም። የሚናገራቸው ነገሮች ሁሉ እውነትን አታጣባቸውም። ሃቅን ያዘሉ ናቸው። ዶስቶቭስኪ ገፀ ባህሪ በደንብ አይስልም፤ በእርግጥ። ፅሁፎቹ ዝርክርክ ናቸው። አንዳንዴ ሳነባቸው በቲዮሪ የካበቱ እንቁ ይመስሉኛል። ቲዮሪውን እንዳለ ነው የሚያስቀምጠው። ለዚህ ሃሳቡን መሸከም የሚችሉ ገፀ ባህሪዎች ፈጥሬያለሁ ብሎ አይጨነቅም። አየህ አይደል ከዚህ እንዝላልነቱ ነው እኔ ፍቅር የያዘኝ። ቸልታው ነው ግርምት ውስጥ የከተተኝ። አደገኛ  ቁማርተኛ ነበር። ህይወቱም እኮ በቸልታ የተሞላ ነው። የሞት ፍርድ ተፈርዶበት ነበር። የሞት ፍርድ የሚፈረድባቸው ሰዎች አንዲት ጉጉት ታድርባቸዋለች። ህይወት ቢቀጥልስ ፣ ፍርዱ ቢሻርስ ወይም ቢሻሻልስ የሚል ጉጉት። ይህቺን ጉጉት አይቷታል። ምናልባት ድንቅ ደራሲነቱ የተፈለቀቀው ከዚህ ጉጉት ነው። የቁማር እዳውን ለመክፈል እንደሚፅፍ የሚናገሩ አሉ። ወንጅል እና ቅጣትን ሲፅፍ እንኳ በከባድ እዳ ውስጥ መዘፈቁን እራሱ ገልጿል። እና ዶስቶቭስኪ ድንቅ ደራሲ ነው ለእኔ።”. አለችና ውስኪውን መጎንጨት ጀመረች።
ስለምታወራው ሰው በእርግጥ ግድ አልነበረኝም። ግን ሰማዃት። መስማት አንዳች ተዓምር ውስጡ አለ። ከዚህ ግብዣ በኋላ መቁራረብ ጀመርን። ስለሰጠችኝ መፅሐፍ ስትጠይቀኝ አንድ ያስገረመኝ ነገር ነገርኳት። እዚህ የሰጠችኝ መፅሐፍ ላይ እናት ልጇን ለማዳን  ከአማልክት ጋር ስትተናነቅ ያሳያል። ምናልባት እናቴን ስለምወድ  የፅሁፉ ክፍል ላይ ልዩ ትኩረት አሳድሬ ይሆናል። ምናልባት እናት በልጇ ጉዳይ አምላኳን እስከማነቅ ትደርሳለች። የገብርኤልን ሰይፍ  እስከመጋፈጥ ያደርሳታል። በዚህ ጉዳይ ትንሽ አወራን። እሷ ግን እንዲህ አለችኝ፡-
“እናት ለልጇ ያላት ስሜት እንደ ሁኔታዎች ይቀያየራል። ልጇን ልትወድም ላትወድም ትችላለች። የእናትን ፍቅር ከመለኮት ጋር አዳብለው የሚናገሩ ደራሲዎች አሉ። ሌባ በላቸው -  ሲዋሹ ነው። ይሄ ታላቅ ቅጥፈት ነው። ብዙ መጥፎ እናቶች አሉ። ለገንዘብ ብለው ልጃቸውን ለውጪ ጥንዶች የሚሸጡ፣ ወልደው መንገድ ላይ የሚጥሉ፣ አንዳንዴ በግዴታ ልጃቸውን ስቃይ የሚግቱ ብዙ እናቶች አሉ። አንዳንድ ሰው ለእናት ያለው አመለካከት ጭፍን ነው። ሰው ጥሩ መጥፎ ይሆናል። እናትም እንደዚያ ነች። ለልጇ ጥሩም መጥፎም ትሆናለች።”
እንዲህ ስትለኝ ንግግሯን በዝምታ አለፍኩት።
ይሄ መግባባት እየዳበረና ደስ የሚል መስመር እየያዘ መጣ።  ስራ ቦታ ላይ ሆነን ዓይናችን ዓይናችን ላይ ያፈጣል። እና አንድ ቀን እራት እንድንበላ ጠየቀችኝ።
በዚህ እራት ላይ ሆነን አንዳንድ ደስ የማይሉ ነገሮች ነገረችኝ። ወይን ጠጣች። ውሃ ቀዳሁ ለራሴ። የምታወራው ነገር አንዳንዴ ግር ይላል። የምታፈቅረው ሰው ጥሏት ሌላ ሰው ጋር እንደሄደባት በታላቅ ቁጭት ነገረችኝ። ይሄም መራር ሃዘን ልቧ ላይ እንደጣለ ተናገረች። እና እንዲህ አለችኝ፡
“ይሄ ሃዘኔ ባንተ የሚቀር ይመስለኛል። እንባዬ ባንተ  ፍቅር  የሚታበስ እየመሰለኝ ነው። እና ጥሩ ስሜት አለኝ ላንተ። አንተ ምን ታስባለህ አብረን ብንሆን?”
“እስቲ ትንሽ ጊዜ ስጪኝ” ብያት ተለያየን...
ነገሩን በደንብ አሰብኩበት። እና አንድ መደምደሚያ ላይ ደረስኩ። በእርግጥ ይህቺ እንስት ወዳኛለች።  እኔ ግን ፍቅር ለሚባለው ስሜት እንግዳ ነኝ። ደግሞ እንደ ብርድ አጥንት ድረስ ሰርስሮ የሚገባ ብቸኝነት ይሰማኛል። እሺ ብያት በእቅፏ ልሞቅ ፈለግኩ። የፍቅር ማይ ልቀምስ ፣ የመኖር ጣዕም እንዲገባኝ ተመኘሁ። እና እሺታዬ በዚህ ውስጥ ፀና...
የተለያየ ቦታ እንሄዳለን። አንዳንዴ ቢሮ ውስጥ ከንፈሬን ትስመኛለች። ሁሉም ሰዎች አወቁና ታስቀናላችሁ አሉን።  በየዕለቱ መገባበዝ ጀመርን። ወይን አስለመደችኝ። ማንበብ አስለመደችኝ። በእኔ ውስጥ ገብታ ልቤ ላይ ነገሰች። ስቀርባት እየወደድኳት መጣሁ። ያ ጠይም ፊቷ፣ እነዚያ ነጫጭ ጥርሶቿ...የዐይኗ ማማር...የልቦናዋ ገርነት ያስገርመኝ ጀመር። አደባባይ አቀፍኳት። አደባባይ ሳምኳት። ፍቅሬን ፀሃይ አሞቅኩት። ዓለም የብርሃን ዘሃ መሆኗን እመንኩ...ጥርሴ ከመሳቅ ጋር ተሰፋ...ልቤ በፍቅር እሳት ሞቀ። ቸል ያልኩትን አምላክ ዝቅ ብዬ አመሰገንኩ።
“በህይወቴ ልጠላው የማልችለው አንድ ሰው ቢኖር አንተ ነህ” አለችኝ... ሳልጠራጠር  ዋጥኩት። ልቤ ላይ አረፈ። መንጋውን እንደሚከተል በግ ነበርኩ። በእሷ በኩል መጥቶ የምጠራጠረው አንዳችም ነገር አልነበረም።  በዚህ የፍቅር ሙቀት ሁለት ጥንድ አመታት አለፉ።
* * *
እንደ ዘበት ነገሮች መቀያየር ጀመሩ። ከእኔ ጋር ስትሆን ሳቋ እየደበዘዘ መጣ። ስሞሿ ከስንት አንዴ ሆነ። አስተቃቀፏ ተቀየረ። አትጨቅጭቀኝ ማለት አበዛች። ሰዎች ፊት እንደ ሩቅ ሰው ማስመሰል ጀመረች። ስልክ ማንሳት የስንት አንዴ ተግባሯ ሆነ። አነጋገሯ ተናገርኩ ለማለት ይመስል ጀመር። አንዳንዴ ፍቅሬን ስገልፅላት “ኡፍ” ማለት ጀመረች። ያሳየችኝ የፍቅር ዓለም ውብ እንደሆነ ልነግራት ታተርኩ። ከሷ ውጪ መኖር እንደማልችል፣ ባገባት ደስ እንደሚለኝ በዝግታ ነገርኳት። ሳቅፋት ፈጥና ከእቅፌ መውጣት ጀመረች። በዚህ ጊዜ ዐይኔ እንባ ያረግዝ ነበር። ጉንጬ ላይ የሚንጠባጠቡ የእንባ ዘለላዎች ሁሉም ነገር እንደተቋጩ ይለፍፉ ነበር። እንደበቃዃት ባላምንም ገብቶኝ ነበር።
ማን ነው እጁን ጎትታ ባስገባችው የፍቅር አለም ውስጥ መሸሿን የሚያምነው? ማን ነው የአልፈልግህምን አግቦ የሚያምነው? ማን ነው የሂድልኝን  ቅኔ  የሚያምነው? ማን ነው ፍቅሩ ሲከስም እያየ እውነታውን የሚቀበል? ማን ነው የሚወደው አበባ ተቆርጦ ሲጣል የሚያምነው? ማን ነው?
አንዳንድ ነገር እየተገለጠልኝ መጣ። ፍቅር ይወለዳል፣ ያድጋል፣ ይሞታል። ብዙ ጊዜ በፀብ፣ አንዳንዴ በዝምታ ከፈን ተገንዞ ይቀበራል። የመቃብሩ ሀውልት  ላይ የሚፃፈው “ሩጫዬን ጨርሻለሁ” የሚል ጥቅስ ነው። የምንወዳቸውን ሰዎች ሞታቸውን ያመንን ስንቶቻችን ነን? የወደድነው ወደ መቃብር ሲገባ ያላለቀስን እነማን ነን? እንደ ክርስቶስ በሶስተኛው ቀን እንደማይነሳ እያወቅን ይመጣል ብለን አልጠበቅንም? በህልም የሞተውን ሰው ስናየው ህልማችንን እውን አድርገው ብለን አልፀለይንም? የፍቅርም ይሁን የህይወት ሞት ሁሌም አስከፊ ነው።
እሷ ሥር የማቶሶቱስ ጅል ወንድ ሆንኩኝ።  ልቧ እየራቀ እንደሆነ ባውቅም ልረዳት ሞከርኩ... ፍቅሯ እየቀዘቀዘ እንደሆነ ቢገባኝም እራሴን  መሸንገል ጀመርኩ።
 አንዳንድ ወንዶች እንደ እኔ እድሜያቸው ሄዶ እንኳን አልበሰሉም። ዳዴ እያለ የሚርቅን ልብ መራቅ አይችሉም። ትግል ይወዳሉ። ልምምጥ ያበዛሉ። ምናልባት ፍቅራቸው ይሄን እንዲያደርጉ ገፍቷቸዋል። ቢሆንም የመብሰል ተቀዳሚ ተግባር...የሚወዱት ሰው ሲርቅ  በፈገግታ ተመልክቶ፣ አለመፈለጉን አምኖ በዝምታ መራቅ ነው። ብዙ ወንዶች አልበሰልንም። እና እኔም ያንን ማድረግ አልቻልኩም ነበር። ከዚያ ይልቅ ህመሜን መለማመጥ፣ ለህመሜ ማደንዘዣ መውሰድ ተቀዳሚ ተግባሬ ሆነ።
አንድ ቀን እንዲህ አለችኝ፡-
“የእኔ እና ያንተ ነገር አብቅቷል። ላንተ የድሮው ስሜት የለኝም። አዝናለሁ...ይቅርታ! “
እስቲ ተመልከቱ “በህይወቴ ልጠላው የማልችለው አንድ ሰው ቢኖር አንተ ነህ” ባለችው አንደበቷ ይሄን አለች። እንዲህ ነበር ሁሉም ነገር የተቋጨው። ከተቀመጥኩበት ወንበር ላይ በዝግታ ተነሳሁ። እሷ ፊት ሆኜ እንባዬን እንደ ምንም ዋጥኩት። መንገድ ላይ ስሄድ ሁሉንም ነገር እያሰብኩ ነበር።  ስራ ቀየርኩ...ከጊዜ በዃላ ያ ጥሎኝ ሄደ ካለችው ሰው ጋር አብራ እንደሆነች ሰማሁ። አላዘንኩም። አልተቀየምኳትም።  ይበልጥ አዘንኩላት።  ነገሮች እንደዚህ እንደሚጓዙ አመንኩ።
የመጠላላት ጉዳይ አይደለም። ሆን ብሎ ሰውን የመጉዳት አባዜ አይደለም። በክህደት ለማቁሰል የመፈለግ ግድም አይደለም። ፍቅራችን እንደ ቀለም አድሮ እንደሚደበዝዝ የተረዳንም አይመስለኝም።
ይሄ የነሲብ ጉዟችን ያስቀመጠው የማስመሰል ጡብ ነው። ሳናውቀው ተሸዋውደናል። ሳይገባን በግብታዊነት ለጥቅማችን የሰውን ልብ ተጠቅመናል። ሳንረዳ ለብቸኝነታችን መሸሻ ፈልገናል። ፍቅርን መጠቀሚያ አድርገናል። አላዋቂነታችንን በፍቅር ሳቅ ጋርደናል። አለመወደዳችንን ሳናውቀው ወደናል። አልፈለግንም ግን የሰው ልብ ውስጥ ነበርን። የአንድ ሰው የእንባ ምክንያት መሆን አንሻም ግን ሁነኛ ሰበብ ነን። ለእንባችን ማበሻ የፍቅር ጨርቅ ተጠቅመናል። የመኖር ጥሻችን ውስጥ አድብተን ፍቅርን ገለናል። አልገባንም ግን የሃዘን ምክንያታችን እኛው ነን።
ጥሏት ስለሄደ እኔን ፈለገች፣ ፈልጓት ሲመጣ ከእኔ እራቀች።
አሁን የሰዎች ልብ ውስጥ ቶሎ ለመግባት ፈሪ ነኝ። አሁን ወደ እኔ የሚመጡ ሰዎችን በጥሩ ዐይን አልመለከትም። አሁን ሰዎች ሲፈልጉኝ እጠራጠለሁ። አሁን ያላየችው የአውሬ መንጋ የሚያስበረግጋት ጥንቸል ሆኛለሁ። አሁን የችግሩ ምንጭ እኔ እንደሆንኩ ተረድቻለሁ። ሁሉም ይቀራል። ሁሉም ነገር ይረሳል። መምጣት እንደመሄድ ያለ አስደንጋጭ ውበት ነው።
አንድ ቀን መንገድ ላይ ስጓዝ አየዃት። አጠገቧ አንድ ወንድ አለ። የእኔን ወገብ እንደምትይዘው የእሱንም ይዛለች። አለፍ አለፍ ብላ እኔን እንደምትስመኝ እሱንም ትስመዋለች። የያዘችው  እኔ የሰጠዃትን ቦርሳ ነው። ስታየኝ ፈገግ አለች። ልቤ ትር ትር ማለት ጀመረ። አዕምሮዬ የተመሰቃቀለ መሰለኝ። አልፊያት ሄድኩኝ። ዞሬ ሳያት እሷም ዞራ አየችኝ።
ይህ መተያየት ጊዜ ነው። ይህ መተያየት እንደ ፍቅራችን አላፊ ነው። ይህ መተያያ ይመለካል፣ ጣዖት ነው። ይህ መተያያት እንባ ሆኖ ጉንጬ ላይ ወርዷል። ምናልባት እሷ ጋር ሳቅ ሆኖ ተቀምጧል። ምናልባት “የት አባቱ” የሚል ቃላት ይዞ ወጥቷል። ምናልባት ይህ መተያያ የቁጭት ህልም ነው። ባላያት እመኝ ነበር። ነገር ግን አጋጣሚ እንዳላያት እድል አልሰጠኝም። ባላስባት እመኝ ነበር፤ ነገር ግን ፍቅር ይሄን እድል ነፍጎኛል። ህይወቴ የእድል ሾተላይ ነው። አጋጣሚ ለእኔ መርዝ ነው።
ፍቅር መራሩን ግት አጠጥታኛለች። እንደ በኻ ግዑዝ ሆኜ ብኖር እንዴት እድለኛ ነበርኩ። እንደ ሽህር ለዕርድ ብቀለብና ያቺን የመጥፊያዬን ቀን ሳላውቅ ብጠፋ እንዴት ጥሩ ነበር።
አዎ! እውነታውን መቀበል ባልፈልግም እየኖርኩት ነው። ፍቅር ይወለዳል፣ ያድጋል፣ ይሞታል። የዓለም መጥፊያዋ በፍቅር በኩል የሚመጣ መሰለኝ።
አዎ! ፍቅር ይወለዳል፣ ያድጋል፣ ይሞታል!

Read 1559 times