Saturday, 18 December 2021 15:31

አንዳንድ ነጥቦች ስለ ስንቅነህ እሸቱ (ኦ’ታም ፑልቶ)

Written by  ሳሙኤል በለጠ (ባማ)
Rate this item
(1 Vote)


        “የልብወለድ ጸሐፊ ዐቢይ ተግባር የሰውን ልጅ ዘወትራዊ የህልውና ስንክሳር (existential condtion) እንደወረደ መዘገብ አይደለም፤ ከዚህ የህላዌ ቀመር ጀርባ ያለውን ስውር እውነት የተገነዘበበትን የፍልስፍና ዱቄት በገሀድ ማረጋገጥ በሚቻል ቋት ላይ ከስቶ የማሳየት ተግባር እንጂ፡፡ ልብወለድ የሰውን ልጅ ዘወትራዊ የሕይወት ስንክሳር ከነግብስብሱ የመክተብ ተግባር (reporting) ሳይሆን ላቅ ያለ ፍልስፍናዊ ርእሰ ጉዳይን በተዋበ ቋንቋ ሰንዶ የማቅረብ ተግባር ነው፡፡--;
            
              ያኔ በልጅነታችን በጥሞናው ጊዜ፣ እንደ አሁኑ ድህረ-ዘመናዊነት ዓለምን  ቱማታ  ብቻ ሳያደርጋት፣ የአባቶቻችንን የእነ ስብሐት ገብረእግዚአብሔርን፣ ሰለሞን ደሬሳን፣ ገብረክርስቶስ ደስታን፣ ዳኛቸው ወርቁን፣ አዳም ረታን፣ በዓሉ ግርማን ሥነ-ጽሑፋዊ  ሥራዎችን መርምረን፣ ተገርመናል፣ ተመስጠናል፤ አንቃዔዎቻችንም ነበሩ፡፡ አሁን ላይ የእኔ ትውልድን  ድህረ-ዘመናዊነት ከንባብ በእጅጉ አርቆታል፤ ስለሆነም  ከታላላቆቹ ቀጥሎ የመጡትን  የደራሲዎችና ገጣሚዎች ሥራ የመረመረ  አይመስለኝም፤ የእነ ስንቅነህ እሸቱ (ኦ ‘ ታም ፑልቶ) ፣ ሌሊሳ ግርማ፣ ዮሐንስ ኃብተማሪያም ፣ ዮናስ ኪዳኔ  የመሳሰሉ  ታላላቅ  ደራሲያንናና ገጣሚያን ሥራዎችን መመርመርና መወያየት አልቻልንም፡፡ ይህ  ደግሞ መሠረትና ቀለም እንዲሁም እግረ-ብዕርን  ያደናቅፋል። ውጤቱም  ሥነ-ጽሑፍን ማደብዘዝ ነው። እንደ እኔ  መፍትሔ  የሚሆነው የሚመስለኝ  የታላላቆቻችንን  ሥራ ማንበብ፣ መመርመር  ባገኘነው  ማስተላለፊያ መንገድ (media ) የሥነ-ጽሑፍ ውይይትና የሂስ ባህላችንን  ማዳበር ነው። የዚህ ጽሑፍ ዐቢይ ዓላማ  በዘመናዊው የአማርኛ ቋንቋ  ሥነ-ጽሑፍ ላይ  ትልቅ  አሻራ ባሳረፈው  በታላቁ  ደራሲና  ገጣሚ  ስንቅነህ እሸቱ (ኦ ‘ታም ፑልቶ) ተከታታይ  የልቦለድ (trilogy novels)  ሥራዎቹ ማለትም፡- በኤላን ፍለጋና በኬክሮስና  ኬንትሮስ ውስጥ  የሚገኙትን  የኢምፕሬሽኒዝም ፍልስፍና  ጽንሰ-ሃሳቦች መዳሰስ ነው፡፡ ስንቅነህ  እሸቱ (ኦ ‘ታም  ፑልቶ)፤ ደራሲና ኀያሲ ዓለማየሁ  ገላጋይ  በጥባጭ ደራሲዎች ከሚላቸው  የሚመደብ  ነው። ተለምዶአዊውን  የልብ-ወለድ ድርሰት አጻጻፍ ይትብሃል  ችላ  ብሎ  በምትኩም  አዳዲስ የአጻጻፍ  ዘይቤዎችን  ያስተዋወቀ ጎምቱ ደራሲና ገጣሚ ነው። በሥራዎቹ  ውስጥ  ሰው፣ ተፈጥሮ፣ ፍልስፍናዊ እሳቤዎች፣ ሥነ-ማህበረሰባዊና ባህላዊ ጉዳዮች፣ ሥነ-ተረት፣ የተፈጥሮ አወቃቀር -- ከሚመሰጥባቸው  ንዑስ ጉዳዮች መካከል ናቸው፡፡
የዘመናዊው የምዕራባዊያን ሥነ-ጥበብ  ንቅናቄዎች ከቀደሙት የሥነ-ጥበብ  ጥበባዊ  ጽንሰ-ሃሳቦችና  የአሠራር መንገዶች  የሚለዩባቸው መገለጫዎች ያላቸው  ሲሆን  አዳዲስ የሥነ-ውበት  እሳቤዎችን (aesthetic ideologies)  ማንሳት  ረቂቅ  እሳቦቶችን (የተፈጥሮአዊ  ቁሳዊ ነገሮችን  ቋሚ ገጽ ከመቅዳት  በዘለል) የሥነ-ጥበብ  ሥራዎች መሠረታዊ ጭብጥ አድርጐ  መነሳትና  አዳዲስ  ሥነ-ጥበባዊ ሥራዎች የሚሠሩባቸውን  የመሥሪያ  ቁሳቁሶች (media) ማስተዋወቅ  በዋናነት የሚጠቀሱት  ናቸው፡፡ ከእነዚህ  የጥብብ ንቅናቄዎች  መካከል አንዱ ኢምፕሬሽኒዝም  ነው። ኢምፕሬሽኒዝም ፈረንሳይ ውስጥ  የተነሳ ነባሩን የሥነ-ጥበብ  ውበት እሳቦትና ጥብቅ  የሥነ-ጥበብ አሠራር  ድንጋጌዎችን በመሻር በዘመናዊው  የሥነ-ጥበብ  ዘርፍ  አዲስ  ዕይታን  በማስተዋወቅ (የዚህ ሥነ-ጥበብ አቀንቃኝ ጠቢባን  የተፈጥሮአዊ  ነገሮችን ትክክለኛ  ገጽታ እንደወረደ ከመቅዳት በመቆጠብ ግብታዊ (spontanious) ግላዊ ዕይታቸውን  በሥራዎቻቸው  ውስጥ ይገልጹ ነበር) በኋላ  ላይ የተነሱት ዘመናዊና ድህረ-ዘመናዊ የሥነ-ጥበብ ንቅናቄዎች እንደ  መሠረታዊ  መርህ የሚጠቀሟቸውን የአሠራር መንገዶች  በመቀየስ ፈር ቀዳጅ  የሆነ የሥነ-ጥበብ  ንቅናቄ ነው፡፡ የዚህ ንቅናቄ ተጠቃሽ፣  ሠዓሊ ፈረንሳዊው ክላውድ  ሞኔት ነው፡፡ በኢምፕሬሽኒዝም  የሥነ-ጥበብ ንቅናቄ  ውስጥ  የሚገኝ  ዐቢይ  የኤግዚስቴንሻሊዝም ፍልስፍና ፅንሰ-ሐሳብ ፣ ግለሰባዊ ነጻ-ፈቃድ (individual autonomy) ነው፡፡ የዚህ  ሥነ-ጥበብ  አቀንቃኝ  ጠቢባን፣ ጥበባዊ  ሥራዎችን የሚሠሩት በቅፅበታዊ ውስጣዊ  ስሜት (immediate impression) መሪነት  ሲሆን  ይህም ግላዊ  ጥበባዊ ዕይታቸውን በጥበብ ሥራዎቻቸው  ውስጥ ለማንፀባረቅ  ነው። የራስን  ርዕዮተ-ዓለም  መሠረት አድርጐ ግላዊ  ኑሮን  መምራት፣ የኤግዚስቴንሻሊዝም ፍልስፍና አቀንቃኝ ፈላስፎች ቅድሚያ የሚሰጡት ዐቢይ መርህ  ነው፡፡
ኢምፕሬሽኒስት ደራሲያን የታሪክ ቅደም ተከተልን ተከትለው አይተርኩም፤ ጥቃቅን  ጉዳዮችን  በዝርዝር  መግለጥ  የሚወዱ ጸሐፍት ናቸው፡፡ ለዋቢነት የአዳም  ረታን (አብዛኞቹን ስራዎች)፣  የሄኖክ በቀለን (አገር ያጣ ሞትን)፣ በሥነ-ግጥም  ደግሞ ገጣሚ ፊርማዬ  አለሙን፣ ገጣሚና ሰዓሊ ከበደች ተክለአብን፣ ገጣሚና ሠዓሊ ገብረ ክርስቶስ ደስታን እንዲሁም ከባህር ማዶ ሄነሪ ጀምስን መጥቀስ ይቻላል። ኢምፕሬሽኒስት ደራሲያንና ገጣሚያን ብዙ ጊዜ በብዕራቸው ውስብስብ ልባዊ ንሸጣቸውን (subjective sensations) ስለሚጽፉ፣ ገለጻቸው ከሌሎች ግንዛቤ ሊርቅ ይችላል። የስንቅነህ እሸቱ (ኦ’ታም) ሥራዎች እንዲህ  ያለ ጠባይ  አላቸው። እጅግ  እሩቅ ናቸው። ለምሳሌ ያህል ከገጣሚና ሠዓሊ ከበደች ተክለአብ ግጥሞች መካከል አንድ  ግጥም  እንምዘዝ፡- “ይቀሰቀሰኛል” ትግሉ ሳያከትም /ሠማይ ሳይለብስ ቅላት/ ከጽልመት ማሕፀን /ብርሃን ሳይከሰት /ምጡ ሳያበቃ/ ንጋት ሳይወለድ / ጥቁር ሕዋ አካሉ / በቀይ እሳት ሳይነድ / ከጎህ ስርቀት በፊት / ከእኩለ ለሊት እልፈት / ይቀሰቀሰኛል! / መች ናፈቀኝ ንጋት / መች ናፈቀኝ ንቃት ! / ዕለትን መጎበኘት / የኑሮ ጽልመቱን / በብርሃን መመልከት / መች ናፈቀኝና / መች ሰለቸኝና? / በሌሊቱ ግርማ / የዕውን ዓለም መርሳት / በተምኔት እምርታ / በሕልም ዓለም መርካት/ ሐቁን ሕልም ብሎ / ሕልሙን ዕውን ማለት / መች ሰለቸኝና! / እንደ ብራ መብራቅ / ሕዋውን ሰንጥቆ / ጸጥ ባለው ሌሊት / የባዕድ ቃል ባርቆ/ ከሕልም ዓለም ሰላም / ሕሊናን መንጥቆ / ለዕውን ዓለም ሥቃይ / ለዕውን ዓለም ብካይ / በጥላቻ ልሣን ንጋቱን ቀድሶ / ለሙሉ ዕለት ለቅሶ / ድንገት አስበርግጎ / ቆሌ ገፎ -ገሶ / የሚባርቀው ድምፅ-ይቀሰቀሰኛል / በተዘጋው ዐይኔ በንቀት ክውታ / ምስልም ይታየኛል / ከግድግዳው ማዶ ! / ምን ይጋርደዋል? / ምንድን ያግደዋል! / ዐውቀዋለሁ እሱን / ግዙፉን ሰውነት / በጁ ከሚውለው / ከነቁልፍ ጨኸት / ዐውቀዋለሁ ምስሉን! /ከከዘራው ገራ / ገፋ ያለ ደረት / ረጅም የደንብ ልብስ / ቁጡ ገጸ ጽልመት / ፍቅር ያልዳሰሰው የጥላቻ ዕድሜ / መስመር ያሻከረው / እጅግ ዐውቀዋለሁ / ምንም አይጋርደው/ ይቀሰቅሰኛል! / የዕውን ዓለም ቁስል / በአዕምሮዬ እንዲሠርጽ / ተባዕታዊው ጩኸት “ኩሼኖ !” የሚለው / የዚያች የሕዋ ድምፅ ! /
(ሐርጌሳ በሰሜን ሶማሊያ የሴቶች እስር ቤት የዕለቱ ጅማሬ፤ ከበደች ተክለአብ፤ ሠዓሊና ገጣሚ፤ 1983፤ ገፅ 33-34 )
ገጣሚዋ ግጥሟን የቀረጸችው በስሜት ነው። የመጀመሪያውን ስንኝ ይዘው ቁልቁል ሲወርዱ የግጥሙ ቅዝቃዜ ይጨምራል፤ በእያንዳንዱ ምስልት ጽልመት፣ ባይተዋርነት፣ የጠነዘለ ቀቢጸ ተስፋ - የግጥሙን አንባቢ  ስሜት በጥቁር ክር ያከራሉ፤ በዑደት ‘ሚጦዘው ቁስልና ድምጽ  የሚቋጠረው  በአንባቢው  ልብ ውስጥ  ‘ሚሰርጽ ስሜት  አዳፍኖ  ነው። ፈረንሳዊው ሠዓሊና ቀራፂ ሄነሪ ማርሲ፤ “impressionism is the newspaper of the soul” [ስሜት አስራፂ  ጥበብ  የነፍስ  ጋዜጣ ነው።] ይላል። ትልቁ ደራሲ ሊዮ ቶሎስቶይም፤ “ሥነ-ጥበብ ግለ-ገለጻን (Self- Expression) እና የማሕበረሰብ-ገለጻን  (Social Expression ) አንድ ላይ በጥማሬ የያዘ ነው። ስለሆነም ጥሩ ሥነ-ጥበብ  የሚለካው በሚያስተላልፈው የስሜት ደረጃ  ነው ።” ብሎ  በሥነ-ጥበብ ውስጥ የስሜትን  ዋጋ ታላቅ ያደርገዋል። አዳም ረታ፤ አለንጋና ምስር በተባለው ልቦለዱ  ውስጥ “ከልጅቷ” የተሰኘው ትረካ ውስጥ በከፍተኛ  ደረጃ ኢምፕሬሽኒስት  እንደሆነ  ያሳያል። ሳናውቀው ያወቀን  ሐዘንና  ሞት የሕይወት አንድምታን ያዛባብናል፤ ህልውናችንን ያወዛውዘዋል። “ጨለማው አቅፎ ያባብለኛል። ወደምጠላው ተሸሽጌያለሁ፤ እምጠላው ውስጥም እሸሸጋለሁ። በቆሸሸ የትዝታዬ ድሪቶ ይቺ ትንሽ ዕድሜዬ ተጠቅልዬአለሁ፤ እንደጠወለገ የሸረሪት ድር ተጣብቄ ከነበርኩባቸው ጥጎቼ ተፈልቅቄ ወጥቼአለሁ። እግሮቼ ጥላሸት ተቀብተዋል። ምሁርነቴ በቀዳዳዎቼ እንደ ላብ ይወጣል። ከጥርሶቹ የማይማርክ ሳቅ ይፈልቃል። ፊቴ እንደ ቆሻሻ ምንጭ ደፍርሷል። የመነሻ ጽዳቴን ተጠራጥሬአለሁ....ከዋክብቶች ዐይን አላቸው? ዕንባ ያወጣሉ። እኔን ሲያዩኝ ያለቅሳሉ። ጠብታዎችን ነፋስ ወደ ውቅያኖስ ይወስዳቸዋል። ማንም አያያቸውም...” (አለንጋና ምስር፤ ገጽ-140)
በቅጽበት ትካዜና  ሐዘን  ውጦት  የሕይወትን  ትርጉም በትዝታው መሃል ሲፈልግ ለኛ ለምን ያሰኘናል፡፡ ደበበ ሰይፉ ለዚህ ስንክሳር ተጠየቃዊ ቅኔ ተቀኝቷል። የለምን ለምን… ነፋሱ ሣሩ ቅጠሉን አዋከበው.../ ሞገዱ ባህሩን አናወጠው.../ ግን የእኔን ልብ ምን አራደው? / ምንም የለ / ሚታወሰኝ / ድንገት እንጅ ሆድ የባሰኝ፡፡/ ለምን አልኩ ተጨብጨ/ ዕንባዬን በአፌ መጥጨ/ ሳውቅ ጥያቄ መልስ እንዳይሆን/ የለምን ለምን ለምን ሊሆን? /
(ደበበ ሰይፉ፣ 1961 ለራስ የተጻፈ ደብዳቤ)
ማዘኑ  አልቀረም፡፡ አዘነ፤ ምን  አሳዘነው? ሳርተር እንዳለው፤ "በተግባር ካልሆነ በስተቀር ምንም እውነታ የለም" ዐይነት የህልውናነት መቀጨጭ  በእውነት  ውስጥ ጥልቅ ሐዘንን  አስፈለቀቀው። “ያ አይደለም ግን የሰሞኑ የልቡ ክብደት ምክንያት። ሕይወቱ ትርጉም ዐልባ እንደሆነች አይሰማውም። ያለ ትርጉምም መኖር መቀጠል የለበትም። ግልጽ ነው ይህ። ስለዚህ መሞቱን በሚሞቁ እጆቹ ጨብጦት ጣ’ሙን ማየት አለበት። ወስኗልና። ርካሽ ሞት ግን አትሆንም ሞቱ፣ ባ’ሳ’ጥማጆች ሕይወት ውስጥ በቅሎ እረፍት እየነሳቸው ያለው ‘ርኩስ ዛፍ፣ አሁን የመርገምት ፍሬ አፈራ፤ ሕይወት ሊነቅል ያቆበቆበውን ዛፍ፣ ትነቅላለች ሞቱ። እሱን ከስሩ መንግሎ ጥሎት ይሄዳል፤ ወደ ሚስቱ ።” (የኤላን ፍለጋ፤ ገጽ-8)
 ስንቅነህ እሸቱ (ኦ ‘ታም ፑልቶ) ድርሰቶቹ የሚፈሱት በቅፅበታዊ ውስጣዊ  ስሜት (immediate impression) ኩሬ  ውስጥ  ነው። በመሃል ግላዊ ጥበባዊ ዕይታቸውን በድርሰቱ ውስጥ  ያንጸባርቃል። “የቻይናውያን ውርደት ኮንፊሸስና ላኦ ዙን፣ የራሺያውያን ስቃይ ፑሽኪንና ዶስቶየብስኪን፣ የደቾች ሰቆቃ ቫን ጎን፣ የህንዶችና የደቡብ አፍሪካውያን ወዮታ ጋንዲንና ማንዴላን፣ የጥቁር አሜሪካውያን ህማም የጃዝ ሙዚቃን ሲወልድ፣ ምነው የሃበሻ ረኃብና ድኅነት፣ ውርደትና ሐፍረት እንዲህ መከነ?”(ኬክሮስና ኬንትሮስ ገጽ-104) ይህ አይነቱ አጻጻፍ ለድህረ-ዘመናዊ አጻጻፍ የሚመጥን ነው።
ወዳጄ ሃያሲ መኮንን ማንደፍሮ እንዲህ ይላል፤ “የልብወለድ ጸሐፊ ዐቢይ ተግባር የሰውን ልጅ ዘወትራዊ የኀልውና ስንክሳር (existential condtion) እንደወረደ መዘገብ አይደለም፤ ከዚህ የኅላዌ ቀመር ጀርባ ያለውን ስውር እውነት የተገነዘበበትን የፍልስፍና ዱቄት በገሀድ ማረጋገጥ በሚቻል ቋት ላይ ከስቶ የማሳየት ተግባር እንጂ፡፡ ልብወለድ የሰውን ልጅ ዘወትራዊ የሕይወት ስንክሳር ከነግብስብሱ የመክተብ ተግባር (reporting) ሳይሆን ላቅ ያለ ፍልስፍናዊ ርእሰ ጉዳይን በተዋበ ቋንቋ ሰንዶ የማቅረብ ተግባር ነው፡፡ በሌላ አነጋገር፣ የሰው ልጅ የኑሮ ስንክሳር ስለተገለጠበት ብቻ አንድን የድርሰት ሥራ ታላቅ ሥራ አያደርገውም። አንድ የድርሰት ሥራ ታላቅ ሥራ የሚሆነው የሕይወት ዐቢይ ጉዳዮችን (ዐቢይ ፍልስፍናዊ ርእሰ ጉዳዮችን) ውበቱ በሰመረ አቀራረብ የሚዳስስ ሆኖ ሲገኝ ነውዉ፡፡” በዚህ አተያይ ስንቅነህ እሸቱ (ኦ ‘ታም ፑልቶ) የተሳካለት ደራሲ ነው ማለት ይቻላል።


Read 1372 times