Saturday, 18 December 2021 15:44

ዝክረ በገና በብሔራዊ ቴአትር

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

     “ዝክረ በገና” ባለፈው ሰሞን በብሔራዊ ቴአትር የተከናወነ ልዩ የበገና ምሽት ነበር።  ኬብሮን የዜማ መሳሪያዎች ማሰልጠኛ ተቋም፤ ከጠልሰም ሚዲያና ኮሚኒኬሽን ጋር በመተባበር ነው ያዘጋጁት፡፡ በዚህ ምሽት ላይ የበገና ደርዳሪና መምህር ኤርሚያስ ኃይላይ  (ኤርሚያስ በገና)፤ የበገና  ታሪክ አጥኚው ምንተስኖት ተስፋዬ እንዲሁም ፒያኒስትና የሙዚቃ ባለሙያው ቴዎድሮስ አክሊሉ ጥናታዊ ፅሑፋቸውን ያቀረቡ ሲሆን አንጋፋና ወጣት የበገና  ደርዳሪዎችም  በዝማሪያቸው ተሳትፈዋል፡፡
ኃይማኖታዊ ስርዓቱ እንደሚያዘው ዝክረ በገናው በቲያትር ቤቱ አዳራሽ ከመቅረቡ በፊት ወንዶች በስተቀኝ ሴቶች ደግሞ በስተግራ እንዲቀመጡ ተደርገዋል፡፡ በክብር እንግድነት የተገኙት የባህረ ሃሳብና የቅዳሴ መምህር አባ ሃብተማርያም፣ ስነ-ስርዓቱን በፀሎት አስጀምረዋል፡፡ ወጣቱ የበገና ደርዳሪና መምህር ኤርሚያስ ኃይላይ (ኤርሚያስ በገና) “ዝክረ በገና” የተዘጋጀበትን ምክንያት  ለአዲስ አድማስ ሲናገር “ዝክረ በገና የተዘጋጀበት ዋነኛ ዓላማ፣ በገናን ከእነ ክብሩ ለማቆየትና ታዋቂ በገነኞችን ለመዘከር ነው።” በተጨማሪም ሁላችንም በገናን እንድናውቀው፤ እንድንረዳው፣ እንድንመረምረውና ከመንፈሳዊ ፀጋው ጥቅም እንድናገኝበት ለማነቃቃት እንደሆነም ገልጿል።
ኤርሚያስ በገናን መስማትና መደርደር የጀመረው ገና በ15 ዓመቱ ነው። በቀን ከስምንት ሰዓታት  በላይ በመለማመድና በማጥናት በ5 ወራት ውስጥ  የበገና ትምህርቱን ተከታትሎ ድርደራውን እንደተካነበት ይናገራል። ትምህርቱን የተከታተለውም በቂርቆስ ወልደብርሐን  ሰንበት ትምህር ቤት ነው።
ከዚያም በቂርቆስ ሰንበት ትምህርት ቤት “ትንሹ የበገና መምህር” እየተባለ ለ1 ዓመት ከመንፈቅ አስተምሯል። አዲስ አበባ ውስጥ በሚገኙ የተለያዩ የሰንበት ትምህርት ቤቶች እንዲሁም በግልና በአንዳንድ ዓለም አቀፍ ትምህርት ቤቶች የበገና መምህር ሆኖ ከ3 ዓመታት በላይ አገልግሏል። በተለይ በቅዱስ ማርቆስ ት/ቤት በቅጥር ደረጃ የበገና መምህር ሆኖ ሰርቷል። 18 ዓመት ሲሞላው “ኬብሮን የዜማ መሳሪያዎች ማሰልጠኛና ማምረቻ” የተባለ የግል ተቋሙን  መሰረተ። ከ3 ወራት እስከ 2 ዓመት  የሚወስዱ የስልጠና  መርሐ ግብሮች በማዘጋጀት፣ ከ200 በላይ በገና ደርዳሪዎችን ለማፍራት እንደበቃ ኤርሚያስ ይናገራል፡፡
የበገና መምህርና ደርዳሪው ኤርሚያስ፣ በኮሮና ሳቢያ ያቋረጠውን የማስተማር ተግባር በአዲስ መልክ አጠናክሮ ለመቀጠል ዕቅድ አለው፡፡ ኬብሮን የዜማ መሳሪያ ማሰልጠኛና ማምረቻ ተቋሙን አስፋፍቶ፣ ተከታታይ ዝግጅቶችን ለማቅረብ እየሰራ መሆኑንም አብራርቷል። በበገና ዙሪያ ትልቅ ለውጥ ለመፍጠርና በገና ያለውን  አቅም ለማሳየት አልሟል። ተቋሙ አሁን የሚገኘው በደጃች ውቤ ሰፈር  ብልጭታ ት/ቤት ግቢ ውስጥ መሆኑን ጠቁሟል።
“በገና ጥንታዊና ታላቅ የዜማ መሳሪያ ነው። ሙያውን ከቀደምት አባቶች በወረስነው ትውፊት ጠብቀን ማቆየት ይኖርብናል። ኃይማኖታዊ ስርዓቱን ሳይለቅ ለመላው ዓለም ልናስተዋውቀው እንፈልጋለን። የበገና ታሪክን ማስታወስና መዘከር  ይገባል። የቀደመውን የበገና አደራደር፣ የዜማ ስልትና አለባበስ ለትውልድ የማሳወቅ ኃላፊነት አለብን።” ሲል ከሱ ዓይነት ባለሙያ የሚጠበቀውን አስረድቷል - ኤርሚያስ፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ ከጥንት ጀምሮ በገና ደርዳሪነት የተከበረ ሙያ መሆኑን የገለፀው መምህሩ ከቀደምት አባቶች የተገኘውን ትክክለኛ ትውፊት ለመጭው ትውልድ ማቆየት፣ የዜማ መሳሪያውን ለዓለም ምሳሌ በሚሆንበት አቅጣጫ ማስቀመጥ እንዲሁም ከበገና የሚገኘውን መንፈሳዊ እውቀት ማሳደግ የብሔራዊ ቴአትሩ የ”ዝክረ በገና” ዝግጅት ዓላማ መሆኑን አመልክቷል።
“ከበገና የሚገኘውን መንፈሳዊ እውቀት  ለማሳደግ ነው ስንል፣ የዜማ መሳሪያውን ወደ ዓለማዊ ሙዚቃ ውስጥ ለመቀላቀል፤ በአሰራሩ ላይ አዳዲስ ቁሳቁሶችን ለመጨመርና ጥንታዊነቱን  ለመቀየር አይደለም፡፡  በገና በአጨዋወቱ፤ በአለባበሱና በዜማው ያለውን ለመጠበቅ ነው፡፡” በማለትም የበገና መምህሩ ኤርሚያስ ያስረዳል፡፡
በብሔራዊ ቲያትር አዳራሽ በተካሄደው የ”ዝክረ በገና” ላይ ዝማሬያቸውን ያቀረቡት ባለሙያዎችም፣ በመርሃ ግብሩ  ጅማሮዎች መደሰታቸውን ገልጸዋል፡፡ አንጋፋው የበገና ደርዳሪና መምህር ዲያቆን ድርሻዬ በምሽቱ ካቀረበው ልዩና መንፈሳዊ ዝማሬ በኋላ በሰጠው አስተያየት፤ “ይህን የመሰለ ምሽት ብዙዎች ሲመኙት ነበር፤ በሙያው ውስጥ ለሚሰሩት ሁሉ ትልቅ ትርጉም ስላለው  ወደ ፊትም መቀጠል ይኖርበታል” ብሏል፡፡ “በገና ከአባቶቻችን የወረስነውን ትውፊት ይዞ እንዲቀጥል ትኩረት ሰጥተን የምንሰራበት ነው። በገና የቤተ-ክርስቲያን የዜማ መሳሪያ ነው፡፡ ዋሽንት፣ ክራርና መሰንቆም እንዲመለሱ ነው የምንፈልገው” በማለትም ዲያቆን ድርሻዬ አክሏል፡፡
አንጋፋዋ የበገና ደርዳሪ የትምወርቅ ሙላት በበኩሏ፤ “ኢትዮጵያ ውስጥ በበገና ደርዳሪነት  የሚታወቁት በጣት የሚቆጠሩ ናቸው፡፡ በተለይ ስለ ሴት በገና ደርዳሪዎች  ምንም የሚታወቅ ነገር የለም፡፡ እኔ በገናን የተማርኩት ሶስና ገ/እየሱስን  ተከትዬ ነው።  በዚህ ዓይነት ዝግጅት በገና ትንሳኤውን እያገኘ መምጣቱ ደስ ብሎኛል፡፡” ስትል አስተያየቷን ሰጥታለች።
በገና ሁሉም ሰው ሊወደው የሚገባ፤ ሁሉንም ሰው የሚመስጥ ነው ያለችው በገና ደርዳሪዋ፤ በመፅሃፍ ቅዱስ ላይ ከኦሪት ዘፍጥረት እስከ ዮሀንስ ራዕይ በ53 ቦታዎች ላይ የተጠቀሰ የዜማ መሳሪያ እንደሆነም ተናግራለች፡፡”
በገና በየትኛው የዓለም ክፍል ተፈጠረ በሚለው ጉዳይ ሁለት ዓይነት የታሪክ መላምቶች መኖራቸውን በምሽቱ ባቀረበው ጥናታዊ ፅሁፍ ላይ የጠቆመው ደግሞ ምንተስኖት ተስፋዬ ነው፡፡ ቀዳማዊ ምኒልክ ከታቦተ ፅዮን ጋር ከእስራኤል  ወደ ኢትዮጵያ ይዞ መግባቱ የመጀመሪያው መላምት ነው ይላል፡፡ በሌላ በኩል ግን የዜማ መሣሪያው ከኢትዮጵያ መገኘቱን አሥሩ የዜማ አውታሮችና አራት ማዕዘን ቅርጹ እንደሚያመለክቱ ይገልፃል። የጥንታዊቷ ግብፅ ንጉስ አኬናተን መቃብር ስፍራ ላይ በድንጋይ ላይ ተስሎ የተገኘው የበገና ቅርፅ የትም አገር የሌለ ለኢትዮጵያ ብቻ የሚደረደር ነው፡፡ በመካነ መቃብሩ ላይ የተፈለፈለው የበገና ደርዳሪ ምስል  በዚያን ዘመን በግብጽ  ከነበሩ የሌላ አገር ህዝቦች ጋር እንደሚመሳሰል፤ አለባበሳቸው ፍፁም ኢትዮጵያዊ እንደሚመስል አመልክቷል፡፡
በምድር ላይ ከ4000 ዓመተ ዓለም አንስቶ በገና አገልግሎት ሲሰጥ መቆየቱን የምንተስኖት ጥንታዊ ፅሁፍ ያመለክታል። በ18ኛው ክፍለ ዘመን “ነገረ ማርያም” የተባለ ጥንታዊ መፅሐፍ ላይ የተገኘው ምስል  (አሁን በብሪትሽ ሙዚየም ይገኛል)፤ የዜማ መሳሪያው ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን ጥንታዊ ትስስር እንደሚጠቁም በጥናቱ ዳስሶታል። “በነገረ ማርያም” ላይ ከሰፈረው ጥንታዊ ምስል ጋር ተያይዘው የሚነሱ የበገና ስንኞችን በተመለከተ፤ “እዝራ በመሰንቆ ዳዊት በበገና እያጫወቷት፤ ሳታውቀው አለፈች ያን መልአከ ሞት፡፡” የሚል ፅሁፍ መስፈሩን ጠቅሷል። የበገና ታሪክን በስፋት እያጠና የቆየው ምንተስኖት ተስፋዬ ስለ ዜማ መሳሪያው ያሰባሰባቸው ያልተሰሙ ታሪኮችን፣ በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ተበታትነው የሚገኙት የፎቶ ማስረጃዎችን  ሌሎች ታሪካዊ በገናዎችና ቅርሶችን የሚያስቃኝ ልዩ መፅሐፍ በማዘጋጀት ላይ መሆኑን ተናግሯል። ዝክረ በገናን መነሻ በማድረግም ለዜማ መሳሪያው ልዩና ቋሚ  ሙዚየም ኢትዮጵያ ውስጥ የማቆም እቅድም ይዟል። በምንተስኖት ጥናታዊ ፅሁፍ ላይ እንደተገለፀው፤ በገና ከጥንት ጀምሮ ከኢትዮጵያ ጋር በተሳሰረበት ልዩ ታሪክ ለመጭው ትውልድ ሊዘከር የሚችል ነው። በገና ለመንፈሳዊና ለተመስጥኦ አገልግሎት ይውል እንደነበር እንዲሁም በሀዘን፣ በለቅሶ፣ በብሶትና በቁጭት፣ በድርቅና በጦርነት እንዲሁም በአገራዊ ኩነቶች ላይ ሲያገለግል የቆየ የዜማ መሳሪያ መሆኑን ያስገነዝባል። ከአድዋ ጦርነትና ከዚያም በኋላ በ5 ዓመቱ የፋሽስት ጣሊያን ወረራ ላይ የበገና ደርዳሪዎች ከኢትዮጵያ አርበኞች ጎን በመሰለፍ የታሪክ ውለታ እንደፈጸሙም በጥናቱ አውስቷል።
ምንተስኖት በጥናታዊ ፅሑፍ ላይ እደጠቆመው ከታዋቂ ኢትዮጵያውያንና ነገስታት መካከል ሳልሳዊ ዳዊት፣ ደጃች ሳሪስ፣ራስ አሊ፣ ራስ ወሌ፤ አፄ ምኒልክ፣ አፄ ዩሀንስ፣ አፄ ቴዎድሮስና እቴጌ ጣይቱ በበገና ደርዳሪነታቸው ይታወቃሉ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የበገና ባህል በመላው ኢትዮጵያ ተስፋፍቶ እደነበር የሚያመለክቱ የፎቶ ማስረጃዎች እንዳሉም በጥናቱ ጠቁሟል። በ1869 ሃረር ላይ የተሰራ የበገና ደርዳሪ ምስል፤ በ1925 ጉራጌ ውስጥ እንዲሁም በ1930 ትግራይ ውስጥ የበገና ደርዳሪዎች የተነሷቸው ፎቶዎች ተገኝተዋል ብሏል ምንተስኖት። በ”ዝክረ በገና” ምሽትም ኢትዮጵያ ውስጥ  በበገና ደርዳሪነት አስደናቂ ታሪክ ያላቸውና የተነገረላቸው በገናኞች ተወስተዋል፡፡ ከእነዚህም ውስጥ አለቃ ተሰማ ወልደ አማኑኤል፤ መጋቢ ስብሐት አለሙ አጋ፤ መምህር ገ/እየሱስ አየለ፤ ጋሽ ታፈሰ ተስፋዬ፣ ጋሽ ደምሴ ደስታ፣ጋሽ ዘርፉ ደምሴ፣ አቶ ተገኝ ጫኔ እንዲሁም ጋሽ ስዩም መንግስቱ ይገኙበታል።
የበገና ደርዳሪና መምህሩ ኤርሚያስ፣ በሙያው ተምሳሌት ሆነውኛል በሚል የጠቀሳቸው ጋሽ ደምሴ ደስታን  ነው፡፡ ጋሽ ደምሴ በገና በመደርደር ብቻ ሳይሆን በመስራትም ጭምር የሚጠቀሱ ናቸው። ይህም በሙያው ሀብተ-በገና ተብሎ የሚገለጽ ፀጋ መሆኑን ይናገራል፡፡ ኤርሚያስ  “አባት” ብሎ የሰየመውን ግዙፍ በገና በባለሙያዎች ማሰራቱና መደርደሩም ከዚሁ ተሞክሮ በመነሳት ነው።  በ”ዝክረ በገና”   ግዙፉን በገናውን እየደረደረ ዝማሬውን አቅርቧል። ልዩ ችሎታ እንዳለው ያሳየውም ጥንታዊ የበገና ግርፉን በመድረክ ላይ በማቅረብ ነው።  
“አባት” ተብሎ የተሰየመው የኤርሚያስ በገና 2 ሜትር ከ30 ሴ.ሜ ርዝመት አለው፣  ገበቴው በሁለት የበሬ ቆዳ የተሸፈነ  80 X 80  ሆኖ ተዋቅሯል። 10 አውታሮቹን ለመስራት ደግሞ  30 በጎች   ለጅማታቸው ታርደዋል፡፡ በገናውን ሠርቶ ለማጠናቀቅ 6 ወር ፈጅቷል ተብሏል። ኤርሚያስ ለዝክረ በገና ታዳሚዎቹ  እንዳወጋው በአርአያነት የተከተላቸው የበገና ደርዳሪ ጋሽ ደምሴ በገና ይሰሩ የነበሩት በቢላ የመረጡትን እንጨት እየፈለፈሉ ነበር፡፡ የእጅ መዳፋቸው በስለታማው ቢላ  ከመሸላለቱ የተነሳ ጠባሳ የበዛበት እንደነበር ያስታውስና በቢላ  እንዲያ ለፍተው የሚሰሯቸውን በገናዎች ታዲያ በ20 ብር ብቻ ይሸጡ እንደነበር ተናግሯል፡፡
 በኢትዮጵያ ሙዚቃ ላይ ከፍተኛ ጥናትና ምርምር ያደረገበትን መፅሐፍ በማዘጋጀት ላይ የሚገኘው ፒያኒስትና የሙዚቃ  ባለሙያ ቴዎድሮስ አክሊሉ፣ በምሽቱ ባቀረበው ጥናት፣ የዜማ መሳሪያውን በሳይንስ አቀፍ ጥናቱ በጥልቀት ዳስሶታል፡፡  
በሰው ልጆች ታሪክ ሁሉም የዜማ መሳሪያዎች መነሻና አገልግሎታቸው ፀሎትና ምስጋና እንደነበር የገለፀው የሙዚቃ ባለሙያው፤ ዋሽንትና መሰንቆ በዓለማዊ ሙዚቃ በሳክስፎንና በፒያኖ የሚቃኙበት ዘመን ላይ ቢሆኑም፤በገና ግን መንፈሳዊ ይዘቱን ያልቀየረ፤ የተፈጥሮን ቅኝት ለዓለም የሚያስታውስ  የዜማ መሳሪያ ነው ብሏል።
 የበገና ንዝረት ወደ ተፈጥሮ ቅኝት ያመዘነ በመሆኑ በድርደራውና በዜማው ፈውስ ያስገኛል የሚለው ቴዎድሮስ፤ የሙዚቃ ፅንሰ ሃሳብ እያንዳንዱን አውታር በሚያወጣው ድምጽ ለክቶ በመተንተን ይህን መገንዘብ እንደሚቻልም ይገልፃል፡፡ የሰው ልጅ በተክለ ሰውነቱ ከተፈጥሮ የሚገናኝባቸው ሰባት በሮች አሉ፡፡ (በምስሉ ላይ እንደተመለከተው) ከተፈጥሮ የሚወጣው ደቂቅ ኃይል ወደ ሰውነት ውስጥ እእንዲገባና የበገና ንዝረት እነዚህን በሮች ይከፍታቸዋል። የሙዚቃ ባለሙያው ቴዎድሮስ አክሊሉ ካቀረበው ሰፊ  ሳይንሳዊ ትንታኔ ለመገንዘብ እንደሚችለው በገና ሁሉም ሰው በቤቱ ቢጠቀምበትና ሠልጥኖ ቢሰራበት መንፈሱን ከማደስ ባሻገር ህክምና ያገኝበታል፡፡
በበገና ድርደራ የንዝረት ህክምና መስጠት እንደሚቻል ለካንሰር፣ለኮቪድ፣ለአዕምሮ ህሙማን…. የዜማ መሳሪያውን በመጠቀም የፈውስን ሀይል ማግኘት እንደሚቻል አስረድቷል፡፡
በአንጋፋና ወጣት በገና ደርዳሪዎች በዝክረ በገና ምሽቱ ላይ የቀረቡ ዜማዎች በእጅጉ መሳጭ  ለሁሉም ህዝብ መዳረስና መቅረብ ያለባቸው ናቸው፡፡ በዜማ መሳሪያው ላይ የሚያተኩሩ ተመሳሳይ ዝግጅቶች በየጊዜው እንዲቀርቡም  ባለሙያዎቹ አሳስበዋል፡፡ የዜማ መሳሪያውን ከእነ ታሪካዊ ክብሩ ለትውልድ ለማስተላለፍ ቤተክርስቲያኗም ሙሉ ድጋፍ መስጠት ይኖርበታል። ለመጀመሪያ ጊዜ በቀረበው የ”ዝክረ በገና” ምሽት ላይ በገናን ከደረደሩት መካከል የ12 ዓመቷ ታዳጊ አዲስ ትጠቀሳለች፡፡ የጎሮ ገብርኤል ሰንበት ት/ቤት ተማሪ የሆነችው አዲስ፤ ሞገስ የሞላበትን የበገና አደራደር በመድረኩ ላይ አቅርባ ከታዳሚዎች አድናቆትን አትርፋለች። የበገና መምህሩ ኤርሚያስም እንደገለጸው፤ ልጆችን ታላቅ የሆነውና መንፈሳዊ የዜማ መሳሪያ ማስተማሩ፣ ወደ አገር  በቀሉና መንፈሳዊው እውነት የበለጠ ማቅረብ ስለሆነ፣ ሁሉም ታዳጊዎች ይህን ታላቅ መሳሪያ ቢማሩ ከፍተኛ ውጤት የሚያስገኝ ይሆናል ብሏል። በገናን ለልጆች ብናስተምራቸው እነሱው ይጨርሱልናል። ስለ በገና እውቀት መቅሰም በገናውን ማገዝ ነው።
የዜማ መሳሪያው ባህሉ ሳይበረዝ ጠብቆ ለማቆየት ነው ማሳደግ የምፈልገው። የዜማ መሳሪያው በባህሪው አርምሞና የተመቸ ቦታ ለመደርደርም ለማስተማርም ስለሚያስፈልገው በሚመለከታቸው ሁሉ ትኩረት መሰጠት ይኖርበታል በማለት ኤርሚያስ በገና ተናግሯል።Read 374 times