Print this page
Saturday, 25 December 2021 12:50

ኢትዮጵያን ለማፍረስ እስከ ሲዖል መድረስ

Written by  ነፃነት አምሳሉ
Rate this item
(1 Vote)

   ዓለም ካየቻቸው ዘግናኝ ጭፍጨፋዎችና ግድያዎች መካከል አንድም ከታሪክ አንብበን አንድም በግላጭ አይተን የሰው ልጅ እንዴት በዓይን እርግብግቢት ፍጥነት ወደ አውሬነት ሊቀየር እንደሚችል ምስክር ለመሆን ችለናል፡፡ የሰማናቸው የግፍ ታሪኮች በጥፍር የሚያስቆሙ፣ ያየናቸውም ሰቆቃዎች የደም ዝውውርን ቀጥ የሚያደርጉ ናቸው፡፡  
ስለቀሪው ዓለም ግፍ አውርተን አሊያም ሰምተን ብናልፈው እንዴት ደስ ባለን ነበር፡፡ አበው የፈሩት ይደርሳል የጠሉት ይወርሳል እንዲሉ በዘር የተቀነበበው ፖለቲካችን ዳፋው የህዝባችንን ክብር÷ የሃይማኖታችንን ልእልና÷ የሰውነታችንን ጥግ÷ የአብሮነታችንን ህብርና የእሴታችንን ጸጋ ተፈታትኖ ጫፍ ወደሌለው እልቂት  አስጠግቶናል፡፡ የሰው ልጅ ብርታቱ ለኑሮ ውጣውረድ መትጋቱ ብቻ ሳይሆን መከራና ሰቆቃን ባየበት ዓይኑ እንቅልፍ ይዞት ማደሩ አስገራሚ ያደርገዋል፡፡
በ1960ዎቹ የፖለቲካ ስንጥቃት በመጠቀም የበቀለ እንግዳ አረም እንዳለ በወቅቱ ያስታወለ ስለመኖሩ ያጠራጥራል። ለብሔር ብሔረሰቦች መብት አዲስ እይታ አለኝ ብሎ አራት ገጽ ወረቅት ጽፎ መድረክ ላይ የወጣው ዋለልኝ መኮንን የተባለ ተማሪ የብሄር ብሄረሰቦች ጥያቄ በኢትዮጵያ በሚለው ጽሁፉ፤ ኢትዮጵያ የምትባለው ሀገር እየተወከለች ያለችው በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል ባለ የማህበረሰብ ማንነት ነው ብሎ በመኮነኑ የብዙዎች ዓይን በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል ላይ ጠቆረ፡፡ ዋነኛ በርባን ሆኖ የቀረበው ደግሞ የአማራ ህዝብ ሆኖ ተገኘ፡፡ በዚህ ወርቃማ እድል በመጠቀም ትህነግ የተባለ ሴረኛ ድርጅት ከህቡእ መዋቅር ተላቅቆ ሥጋ ሲለብስ በድርጅቱ ሰነድ ላይ የአማራን ህዝብ እንደ ጨቋኝ በመሳል ለቀጣዩ እልቂት የአብርሃም በግ አድርጎት ለገበያ አቀረበው፡፡
ሕወሓት አማራ ጠል ይሁን እንጂ ለየትኛውም ብሔር የሚንሰፈሰፍ አንጀት የለውም፡፡ በአናቱም የኢትዮጵያና የኢትዮጵያዊነት እሳቤን አጥፍቶ እንደ ዩጎዝላቪያ የተበታተነችና የመሀረብ ቁርጥራጭ የሆነች ሀገር በመፍጠር በምትኩ ታላቂቱን ትግራይ የመመስረት ህልሙ በሌት አላስተኛ በቀን አላስቆም ብሎ ሲያቃዠው መኖሩ የትናንት ትዝታችን ነው።
ይህን ምኞቱን ለማሳካት የአማራን መሬቶች ወልቃይትና ጠገዴን ከህገመንግስት መጽደቅ በፊት በፖለቲካ ውሳኔ እንደ መሶብ እንጀራ ጠቅልሎ ሲወስድ ህዝቡን ከርስቱ ነቅሎ ገድሎ አባርሮ አሳድዶታል። የጸደቀውም ህገመንግስት ከነትሩፋቶቹ ጭምር ሰውነትን ንዶ ብሔርን በማጉላቱ÷ ግለሰባዊ ነጻነትን ገፍፎ ቡድናዊ ስያሜ በመቀበሉ ለሕወሓት ሠርግና ምላሽ ሲሆን ለአማራ ህዝብ ግብ ሰልስት የሌለው የዘመናት ልቅሶ እንዲሆን ፈርዶበታል፡፡
ወርሮ መደራደር÷ ሰርቆ መከራከር÷ ዘርፎ መነጋገር የሕወሓት ስልታዊ አካሄድ ነው፡፡ የአማራን ክልል የታሪክና የቅርስ ሀብት የሆኑትን የላሊበላን ውቅር አብያተክርስቲያናት የትግራይ ልጆች ስልጣኔ ነው ሲል÷ የራስ ዳሸን ተራራን በትግራይ ክልል አስገብቶ የቱሪዝም ገቢውን ለራሱ ለማድረግ ሲሰራ÷ የትግራይ ክልልን ካርታ እስከ ቤንሻንጉል አንደርድሮ የህዳሴ ግድብ ብቸኛ ባለቤት ለመሆን ሲሸርብ÷ ኦርቶዶክስን በማዳከም÷ እስልምናን በማድቀቅ ተንኮል ሲጎነጉን÷ የመጠጥ ውሃ ለቸገረው ህዝብና ሀገር ከፍተኛ ሚሊዮን ብሮችን በማውጣት የጥላቻን ሐውልት ሲያስገነባ÷ አማራን በትምክህት አሮሞን በጠባብነት ሶማሌን በአክራሪነት ፈርጆ ህዝብን ከህዝብ ሲያናክስ የኖረበት ዘመን እዳውን መክፈል አቅቶን ዛሬም ተቸግረንበታል፡፡
በዚህ ፍትጊያ መሀል የተንገሸገሸው የአማራ ህዝብ፣ የሕወሓትን አገዛዝ በራሱ ልጆች መስዋዕትነት ከላዩ ላይ አንከባልሎ ጥሏል፡፡ ውሎ አድሮም በመላ ሀገሪቱ የተዛመተው ተቃውሞ የስርዓቱን ግብዓተመሬት ሲያፋጥነው፣ ይህ ውርደት አጥንቱ ድረስ ዘልቆ የተሰማው ሽብርተኛ ቡድን መጋቢት 24 ቀን 2010 ቤተ መንግስቱን ጥሎ ወደለመደበት ጉድጓድ እንዲገባ ሲያስገድደው፣ ጎመን በጤና ብሎ ክልላዊ ስልጣኑን ይዞና በፌዴራል ያለውን ወንበሩን አስጠብቆ መኖር ባለመቻሉ ደም የለመደ እጁ አላርፍ ብሎ ወደ ቃታ መሳብ ሲሻገር፣ የማይነካውን ነክቶ የማይወጣው እዳ ውስጥ ለመነከር ተገዷል፡፡
የመከላከያ ሰራዊታችን ላይ የተፈጸመው ፍጅት፡- አሸባሪው የሕወሓት ስብስብ ጥቅምት 24 ቀን 2013 ላይ ለዳርድንበር ነፍሱን ሊገብር በተሰማራው መከላከያ ሰራዊታችን ላይ ፍጅት ፈጽሞ አስከሬኑ ላይ ጨፍሮበታል፤ መሬት ለመሬት እየጎተተ ተሳልቆበታል፤ አስከሬኑን በቤንዚን አንድዶታል፡፡፡
ከአማራ ህዝብ ጋር የምናወራርድው ሂሳብ አለ! ይህ ንግግር የሕወሓት የህይወት ዘመን መመሪያ አንቀጽ ነው፡፡ ሕወሓት የቆመበት የፖለቲካ ምሰሶ ርዕዮተዓለማዊ ትንተና ሳይሆን ጸረ አማራ ጥላቻ ነው፡፡ ያለ አማራ ስም የሚያካሄደው ትግል የለም። አማራ ባይኖር እንኳ የራሱን እስትንፋስ ለመቀጠል ሲል ምናባዊ አማራን ከመፍጠር ወደ ኋላ አይልም፡፡
ኢትዮጵያን ለማፍረስ ሲኦልም ቢሆን እንገባለን! ይህ እኛን ለመውረር ወደ ኢትዮጵያ የመጡ የጣሊያን ሰራዊቶችን  ንግግር ሳይሆን የሕወሓቶች ቃል ነው። ከእነዚህ ሃይሎች ጋር በየትኛውም አስተርጓሚ ተነጋግሮ መግባባት አይቻልም። ከዚህ መፈክር ማግስት ጀምሮ መንግስት ለትግራይ አርሶ አደር የማረሻ ጊዜን መስጠቱ እንደ ፈሪነት ተቆጥሮ ጦሩን በአማራ ክልልና በአፋራ ክልል ላይ አዘመተ፡፡
ጅምላ ግድያ- አንጾኪያን ንፋስ መውጫ ጠቅሰን በሁመራ በአጋምሳ በወልዲያና በደሴ የተፈጸሙት ግፎችን ይዘን በጋሸና ከ60 በላይ የሚሆኑ ንፁሓን ላይ የዘር ጭፍጨፋ ተፈጽሞባቸዋል! በአንድ ክፍል ውስጥ ተደብቀው የነበሩ 16 ሰዎችን ጨምሮ በአንድ ቀን ከሥልሳ በላይ ንጹሓን ደመ-ከልብ ሆነዋል፡፡ ሟቾቹ ራሳቸውን መከላከል የማይችሉ ህጻናት አዛውንት ሽማግሌዎች ነበሩ፡፡ በወልዲያ ከተማ ውሃ ለመቅዳት ወንዝ የወረዱ አምስት ለፍቶ አዳሪዎችን በሰልፍ እንዲንበረከኩ በማድረግ በጥይት እሩምታ ጨፍጭፏል። በራያ ቆቦ 120 ሰዎች በጅምላ መረሸኑም ታውቋል:: ጭናን ለቀው ከመውጣታቸው በፊት በነበሩ አምስት ቀናት በ15 የተለያዩ ስፍራዎች 26 ሰላማዊ ሰዎችን፣  በቆቦ ከተማ ጳጉሜ 4 ቀን 2013 ዓ.ም በአራት የተለያዩ ስፍራዎች ላይ 23 ሰዎችን ገድለው ሸሽተዋል፡፡
ጅምላ መቃብር- በአጋምሳ በጋሊኮማ በቆቦ በኮምቦልቻ አካባቢዎች በመቶዎች የሚቆጠሩ ዜጎችን በጅምላ መጨፍጨፋቸውንና አንፆኪያ ጋሸና እና የደብረዘቢጥ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ግቢ ደግሞ የጅምላ መቃብር መገኘቱ ለዚህ ምስክር ነው፡፡
ጾታዊ ጥቃት- ይህን ግፍ እንኳን ለመናገርና ለማሰብ ቀርቶ ለመጻፍ  ያስቸግራል፡፡ የትኛው ግፍ በምን ቃል እንደሚገለጽ ይከብዳል! እስከ ታህሳስ 9 ቀን 2014 በተገኘው መረጃ መሰረት፤ በአማራ ክልል ከ147 በላይ ሴቶች በሕወሓት አሸባሪዎች መደፈራቸውን የባሕርዳር ከተማ አስተዳደር ሴቶች፣ ህፃናትና ማኅበራዊ ጉዳይ መምሪያ ገልጿል፡፡
የልጄን ዓይን ከማይ ራሴን ማጥፋት ይቀለኛል! በሸዋሮቢት ከተማ የ02 ቀበሌ ነዋሪና እንጨት በመሸጥና እንጀራ በመጋገር የሚተዳደሩ እናት በሕወሓት የቡድን ደፋሪዎች ከተደፈሩ በኋላ “የ15 ዓመት ታዳጊ ልጄን ዓይን አላይም ብለው ራሳቸውን ያጠፉ እናት ናቸው፡፡ ሌላኛዋ አብረው የተደፈሩት እናት ሲናገሩ “መግደልም መድፈርም መብታችን ነው” እያሉ ነበር የደፈሩን ብለዋል፡፡ በራያ ቆቦም የ9 ወር ነፍሰጡር እስከ መድፈር የደረሰውን ይህን ጨካኝ ቡድን ምን ቃል ይገልጸዋል?
የወልዲያ ከተማ ነዋሪዋ “የ3 ዓመት ልጄ ላይ መሳርያ ደግነው ነው የደፈሩኝ” ስትል እርስዋ ጋር ለማደር የመጣችውን የ14 ዓመት ልጅ በተዘጋ የጎረቤት ቤት በመውሰድ ለአራት እንደደፈርዋት ተናግራለች። ግፉአኑ የአጣዬ ከተማ ነዋሪዋን የ14 አመት የደብረ ኃይል ቅዱስ ቴዎድሮስና አቡነ አረጋዊ አንድነት ገዳም ጸበልተኛን አግኝተው በቡድን ደፍረዋታል፡፡ የ85 አመቷ መነኩሲት የእድሜ ባለጸጋ 10 ልጆችን ወልደው፤ በከበሩበት ሸዋሮቢት ሲደፈሩ “ምንኩስናዬ ፈረሰብኝ” ብለው ወደ ፈጣሪ አልቀሰዋል። ጋይንት ላይ ከ70 በላይ ሴቶች ሲደፈሩ በአማራነታቸው ጭምር ተሰድበዋል፡፡ መርሳ ከተማ ላይ አልደፈርም በማለትዋ ብቻ በአራት ጥይት ተደብድባ የተረፈችው ዘኪያ አህመድም ምስክር ለመሆን ችላለች፡፡
ግድያ- የሽብር ቡድኑ ወደ ውጫሌ ከተማ ከባድ መሳሪያ በመተኮስ የሃምሳ አለቃ ፈንታዬን ባለቤት÷ የልጃቸውን ሚስት እንዲሁም የወንድማቸውን ልጆች በአንድ ጊዜ ነጥቋቸዋል፡፡ በዚህ ከተማ ወራሪ ሃይሉ ከህዝቡ ዘርፎ የጫነውን አተር ክክ፣ ጤፍና ሌሎች የምግብ እህሎችን ከታጣቂዎቹ ታግለው ያስጣሉትን ሚሊሻዎች በቂም በቀል ተነሳስቶ 11 የሚደርሱ የአካባቢውን አርሶ አደሮችና ንጹሃንን ገድለዋል፡፡ ይሄ ይገርማችኋለሁ ወይ ብሎም የአእምሮ ህሙማንን “ለተልዕኮ የተቀመጡ መረጃ አቀባይ ሰላዮች ናቸው” በማለት መግደላቸውን አስር አለቃ በላይ ምስክር ሆነው ተናግረዋል፡፡
የንብረት ውድመት- ይህን ውድመት ግምታዊ ካልሆነ በስተቀር ትክክለኛ አሀዙን ለመግለፅ አስቸጋሪ ነው፡፡ ለአፋር ክልልና በምስራቃዊ አማራ ለሚገኙ ዞኖች የሰብል ተባይና በሽታ መከላከል አገልግሎት ይሰጥ የነበረው የኮምቦልቻ እጽዋት ክሊኒክ ከ9 ቢሊዮን ብር በላይ የሚያወጡ ንብረቶቹ÷ በኮምቦልቻ ደረቅ ወደብ የሕዳሴ ግድብና የሌሎች ፕሮጀክቶችን ከ100 በላይ ኮንቴይነር እቃዎች÷ በዓመት 14 ሺህ ኮንቴይነር የሚያስተናግደው የመቀሌ ደረቅ ወደብ÷ በወደቡ ላይ የነበሩ 209 የባለሃብቶች ኮንቴይነሮችና ዋጋቸው እስከ 20 ሚሊዮን ብር የሚገመቱ ትላልቅ ማሽነሪዎች÷ በደቡብ ወሎ የኮምቦልቻ ደረቅ ወደብ ላይ ተከማችተው ከነበሩ 251 ኮንቴይነሮች÷ ከ100 በላይ የሚሆኑት የሕዳሴ ግድብን ጨምሮ የሌሎች የልማት ፕሮጀክቶችን እቃዎች የያዙት ንብቶች ወድመዋል፡፡ ወደ አመድነት ተቀይረዋል፡፡
ዘረፋ- አሸባሪው ሃይል በሰሜን ኢትዮጵያ በሚገኙ የንግድ ባንክ ስድስት ዲስትሪክት ስር ያሉ 238 ቅርንጫፎችን መዝረፉን የባንኩ ፕሬዚዳንት አቤ ሳኖ ገልጸዋል፡፡ ሆኖም በመቀሌ የሚገኙ 61 እና በሽሬ 59 የባንኩ ቅርንጫፎች ያሉበት ሁኔታ ግን እስካሁን አልታወቀም፡፡ የማህበረሰብ መርጃ የሆነው የሰዎች ለሰዎች ወረኢሉለገሂዳ የተቀናጀ ፕሮጀክትም የዝርፊያው ሰለባ ከመሆኑ ባሻገር ወደ መጸዳጃ ቤትነት ቀይረውታል፡፡
ቱሪዝም ላይ የደረሰ ውድመት- ቡድኑ በደቡብ ጎንደር በላስታ ላሊበላና በአፋር ክልል በቱሪዝም ሃብት ላይ ክፉኛ ጉዳት አድርሷል። በተለይም የደሴ ቤተመዘክር ውስጥ የሚገኙ መንፈሳዊ፣ ታሪካዊና ባህላዊ ተንቀሳቃሽ ቅርሶች መዘረፋቸውን፣ ቅርፃ ቅርፅ፣ በቁፋሮ የተገኙ ጥንታዊ የመገልገያ መሣሪያዎችና የእንስሳት ቅሪቶች እንዲሁም አፄ ሚኒሊክ ከጂቡቲና ከፈረንሳይ አገራት ጋር ግንኙነት ያደረጉበት የስልክ ቀፎ፣ በአድዋ ጦርነት ጊዜ ያገለገሉ የጦር መሣሪያዎች፣ በ1890 ከፈረንሳይ የተበረከተ መድፍ፣ በኢትዮ ጣሊያን ጦርነት ጊዜ የተማረከ የአየር መቃወሚያ፣ ከ450 ዓመት በላይ ያስቆጠሩ የሸክላ ውጤቶች፣ አፄ ሚኒሊክ የተጠቀሙባቸው የጦር ሜዳ መነጽሮች፣ ከወርቅና ከብር የተሰሩ ታሪካዊ ቅርሶች በሙሉ መዘረፋቸውና መውደማቸው ታውቋል፡፡
የኦርቶዶክስ ተዋህዶ መቅደሶች ውድመት- በኤፍራታ እና ግድም ወረዳ የሚገኘውና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የቆሬ ሜዳ ደብረ ከዋክብት አቡነ ገብረመንፈስ ቅዱስ ቤተ ክርስቲያን ሲወድም በሰሜን ወሎ ዞን ኮን ወረዳ ሐሙሲት ከተማ በምትገኘው በደብረጸሐይ ሐሙሲት ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን አገልጋይ የሆኑ ሁለት ካህናትን “ብልጽግና ናችሁ” በሚል ማረዳቸው በሚዲያ ተዘግቦ ሰምተናል፡፡
የመስጂድ ውድመት- ሕዳር 03 ቀን 2014 ዓ.ም የሽብር ቡድኑ ወራሪ ሃይሎች የጦር መሳሪያ ታጥቀው ወደ ካራቆሬ መስጂድ መግባታቸውንና ጥቃቱን መፈጸማቸውን የመስጅዱ ጠባቂ ሼህ ሁሴን ዑመር ተናግረዋል። በአፋር ክልል አሸባሪው ቡድን ከ30 በላይ መስጂዶችን በማፍረስ ከአገልግሎት ውጪ አድርጓል፡፡ ከአስር ሺህ በላይ ቅዱስ ቁርኣንን አቃጥሏል፤ የሀይማኖት አባቶች ላይ ጥቃት ፈጽሟል፤
የመካነ ኢየሱስ ማመለኪያዎች መውደም- የማዕከላዊ ሰሜን ኢትዮጵያ ሲኖዶስ መውደሙን የጽህፈት ቤት ፕሬዚዳንት ቄስ ዋኘሁ አንዳርጌ ገልጸዋል፡፡
የጤና ተቋማት ውድመት- ለጊዜው የተቆጠሩ 416 የግል ጤና ተቋማት፣ 453 የጤና ጣቢያዎች፣ 1850 የጤና ኬላዎች፣ 40 ግዙፍ ሆስፒታሎች ተዘርፈዋል! ወድመዋል።
የትምህርት ተቋማት ውድመት- ከመጀመርያ ደረጃ አንስቶ እስከ ዩኒቨርስቲ ያሉ ከ4ሺ በላይ ትምህርት ቤቶች ወድመዋል፡፡ ወሎ ዩኒቨርስቲ ብቻ 10 ቢሊየን ብር ኪሳራ  ሲደርስብት ወደ ሙሉ አገልግሎት ለመመለስ ቢያንስ 2 ዓመት ያስፈልገኛል ሲል፤ የክልሉ ትምህርት ቢሮ ደግሞ ተቋማቱን መልሶ ለማቋቋም ቢያንስ 11 ቢሊዮን ብር እንደሚያስፈልግ ገልጿል፡፡ በአፋር ክልልም 2ሺ115 ትምህርት ቤቶች ላይ ያደረሰው ኪሳራ ከ285 ሚሊዮን ብር በላይ መሆኑ ታውቋል።
የፋብሪካ ውድመት- ሌላውን ትተን ኮምቦልቻና ደሴ ከተሞች ብቻ ከ30 በላይ የጨርቃጨርቅ፣ የኬሚካል፣ የማኑፋክቸሪንግና የተለያዩ አግሮ ኢንዱስትሪ ፋብሪካዎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሷል። በዚህም በርካታ ንብረት ከመውደሙ ባለፈ በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎችን ያለሥራ አስቀርቷል።
መሰረተ ልማት ውድመት-  የሽብር ቡድኑ በሀይቅና ውጫሌ ከተሞች መካከል ያለውን ድልድይ አፍርሶ ከፈረጠጠ በኋላ በጣሊያን ጊዜ የተሰራውን ከወልዲያ ወደ ቆቦ የሚወስደው ጥንታዊውን የአልወሃ ድልድይበለመደ እጁ አፍርሶታል፡፡ የመብራት÷ የውሃ÷ የስልክና የአዉሮፕላን ማረፊያዎች ውድመት ገና በጥልቅ እይታ ተዳስሶ ካልቀረበ በቀር ለግምትም አስቸጋሪ ነው፡፡
የጸጥታ ተቋም ውድመት- አሸባሪ ቡደኑ በአማራ ክልል ያገኛቸውን 178 ፖሊስ ጣቢያዎችንና አምስት የዞን ፖሊስ መምሪያዎችን ወደ አመድነት ቀይሯቸዋል።
የፓርኮች ውድመት- አሸባሪው ቡድን ለዱር እንስሳትም የማይራራ ነው፡፡ 1ሺ ሄክታር የሚሸፍነው የጓሳ ማህበረሰብ አካባቢ ጥበቃ ስፍራ በ40 ዓመታት ታሪክ ውስጥ አጋጥሞት የማያውቀውን የእሳት አደጋ ተጋፍጧል፡፡ በዚህም በእንክብካቤና በጥንቃቄ ለተያዙ 75 ቀበሮዎች ህይወት አደጋ ፈጥሮባቸዋል፡፡
የእርሻ መሬት ውድመት- አሸባሪው ህወሓት በአማራና አፋር ክልሎች ከ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሄክታር በላይ የእርሻ መሬት ከልማት ውጭ አድርጓል፡፡ የታጨዱ እህሎች ተቃጥለዋል፡፡ እንስሳት በብሔር ዓይን ታይተው ተገድለዋል፡፡
የተረጂዎች ብዛት- እስከ አሁን ባለው ግርድፍ ጥናት 9.1 ሚሊየን የአማራና የአፋር ህዝብ እጅግ ለከፋ አደጋ ተጋልጧል። በመቶ ሺ የሚቆጠሩ ዜጎች ለስደት ተዳርገዋል። በአርሶ አደሮች ላይ በደረሰ ሁለንተናዊ ጥቃት ከ280-290 ብር ኪሳራ ተመዝግቧል፡፡ እኛም ለታሪክ ብለን ይህንን ሁሉ ሃቅ መዝግበናል፡፡
ሕወሓት የአማራ ክልልን የሶርያ እህት ከተማ አድርጎታል፡፡ ሰው ገድሎ÷ ንብረት አውድሞ አልበቃ ስላለው የቡሃቃ ሊጥ አስጭኖ ወስዷል፡፡ የደም ጥማቱ ገና ያልወጣለት ቢሆንም ለጊዜው ግን እርካታን አግኝቷል፡፡ በጦሱም የአማራን ክልል መልሶ ማቋቋም ማለት አዲስ ሀገር ገንብቶ የማስመረቅ ያህል ዘርፈ ብዙ ተግዳሮት የተጋፈጠበት ፈተና ሆኗል፡፡ ክልሉንም ከ30-50 ለሚቆጠር ዓመት ወደ ኋላ መልሶታል፡፡
ከቁሳዊ ውድመት በላይም በአማራና በአፋር ህዝብ ላይ ያደረሰው ስነልቦናዊ ጥቃት በየትኛው የመጽናኛ ቃል እንደሚፈወስ ግራ አጋቢ ሆኗል፡፡
የተደበቁ መረጃዎች በመንግስት÷ በመርማሪዎችና በሚዲያ አካላት እንደሚወጡ በማመን ይህ ቡድን ዳግመኛ ነፍስ ቢዘራ ለአጎራባች ክልሎች ለመላ ሀገሪቱና ለቀጣናው አስጊ በመሆኑ ያለምንም ቅድመ-ሁኔታ ለራሳችን ህልውና ስንል የምንዋደቅበት  ምእራፍ ላይ መድረሳችንን ማወቅ ብልህነት ነው፡፡

Read 2175 times