Saturday, 25 December 2021 12:49

ባል ሳይገኝ ሚዜ ታማርጣለች

Written by 
Rate this item
(5 votes)

የዛሬ ርዕሰ አንቀፃችንን ሁነኛ በምንለው ግጥም እናቀርበዋለን።
አባቴ ለኔ አልነገረኝ…
የታሪኬን ቅኔ ስንኝ
አባቴም ለእኔ አልነገረኝ
እኔም ለልጄ አልነገርኩኝ፡፡
ታሪካችን…….
እንደ ጽላታችን ሩቅ
እንደ ልቦናችን ድብቅ
እንደ ነጻነት ቅጥልጥል
እንደባርነት ጭልምልም
እንደ ጨዋነት ስልምልም
እንደ አበሽነት ግብረ ገብ
እንደ ገበራችን ድርብ
ታሪካችን……
ተጓዥ እንደ ዓባይ ውሃ
ጦረኛ እንደ መሳፍንት
እንደ ቋጥኝ ጥርብ ደንጊያ፤ እንደ ላሊበላ ፍልፍል
እጅ ስራ አያውቅ ኦርጅናሌ የአልማዝ የተፈጥሮ ጌጥ
በውብ የተጻፈ ፊደል፡፡
ታሪካችን….
ፍልቅልቅ እንደ ኤርታሌ
እንደ ድህነት ባተሌ
እንደ ሰሜን ውብ አቀበት
እንደ ተራራው ሰንሰለት
እንደ አክሱም ወጥ ቅርፅ- አለት
ብዙ ባለ እጅ፣ ብዙ ጥበብ፣ብዙ ላብ ያፈሰሰበት
……..እነማ ሰሩት? ሲባል
አባቴም ለኔ አልነገረኝ
እኔም ለልጄ አልነገርኩኝ!
አያቴም ለአባቴ አልነገረው
ታሪካችን እንደዚህ ነው!
እንደ ፅላታችን ሩቅ
እንደልባችን ድብቅ
በሚስጢር የተለበደ
በጥበብ የተቀየደ
ሾላ- በድፍን ተወልዶ፣ሾላ በድፍን ያደገ
ቀን የጣለውን ክዶ፣ለደላው ያደገደገ
ይህም ለምን ሆነ? ሲባል፤
   አባቴም ለኔ አልነገረኝ
እኔም ለልጄ አልነገርኩኝ
ሁሉ አንደበቱን ከዘጋ፣ ከቶ ማ ምኑን፣ለማን ይስጥ?
ሁሉ ሚስጢር፣ሁሉ ቅይጥ
ረዥሙ ታሪካችን፣መቼ ይሆን አይኑን እሚገልጥ?
*   *   *
 አገራችን ዘመናት ታሪክ ያላት ታሪከኛ ሀገር ናት፡፡ ብዙ መንገድ የመጓዝን ያህል ብዙ እቅድ አካብታለች፡፡ ነቢብ- ወገቢር እንዲሉ፣እውቀትን ከስራ ግን ገና ሙሉ በሙሉ እጇ አላስገባችም፡፡
ገና ከመንደር ስድብና ከአሉባልታ አልተላቀቀችም፡፡ ህዝባችንም ያለፍርሀት ዲሞክራሲያዊ መብቱን መጠየቅ ደረጃ አልደረሰም፡፡ ውስጣዊ መንፈሱን ቨ  ስናጤነውም፣ ዛሬም “እናውቃለን ብንናገር እናልቃለን” ከሚለው አስተሳሰብ አልተላቀቀም፡፡ ሌላው ቢቀር ያወቀውን በድብቅ ለመነጋገርም አልታደለም፡፡
ዛሬም ብቃት አልተጎናጸፍንም፡፡ ዛሬም ጥራት  አልሆነልንም፡፡ ዛሬም ጊዜ- ገደብ አናከብርም። በኢኮኖሚ ረገድ የግዢህጋችን  ለቋሳ ነውና ከአንዳንድ ቁሳቁሶች በስተቀር፡፡ ብክነታችን ከጠዋት እስከ ማታ የተንሰራፋ ነው፡፡ ህገወጥ ንግድ አናታችን ላይ ከወጣ ቆየ፡፡ የአድር ባይነት፣የተጠራጣሪነት፣የፈሪነት፣የልፍለፋ ባህላችን በቅራኔ፣በእልህ መወጫ ዘዴዎች፣በቂም በቀል እና በደባ እየተወሳሰበ ቢብሮክራሲያዊ እንቅፋት (beureaucratic red-tape) እየታገዘ የመሰናክል እሩጫ (hurdles) ከሆነ ከራርሟል፡፡ የሁሉም ማጠንጠኛ የሆነው ግልጽነት አለመኖር፣በየቦታው ግጭት መበራከትና ጦርነት ለሰላማችን ጠር ሆኖ ይኸው ነግ ሰርግ የምንሰማው ዜና ሆኗል። እንደ ሰላምታ ተለምዷ፡፡
 በየስራ መስኩም ስራ አስኪያጆች እየተባረሩ፣ በጓሮ በር ግን ወደ አማካሪነት (consulatancy) እየተቀየሩ እያየን ነው፡፡ የመንግስት መዋቅርና  የመንግስት አንቀሳቃሽ-ፈፃሚ-ሀይል (state apparatus and state machinery) አንድም እያሽመደመደ፣ አንድም ለቋሳ እየሆንን እድገታችንን እየሸበበና እያሽመደመደ ይገኛል፡፡ ይህ ሁሉ ሆኖ ሀገር ትኖራለች፡፡ “መቼም ከትናንቱ ይሻላል” በሚለው ህዝቧም በአወንታዊ ተስፈኝነት (optimism) ይኖራል፡፡ ፈጣሪም ይታደጋታል፡፡
“ተመስገን ይለዋል፣ሰው በአያሌው ታሞ
ካማረሩትማ ይጨምራል ደግሞ!”
እያለ የሰነበተ ህዝብ ነው የምንለው ለዚህ ነው፡፡
አገራችን ከሙያ ይልቅ ጦርነት መቀፍቀፍ ይቀናታል፡፡ ከሳይንቲስቶች ይልቅ የብዙ ጀነራሎች ሀብታም የሆነችው ለዚህ ነው፡፡ ከልማት ጋር ከተጣላንባቸው ምክንያቶች አንዱ ይኼ ነው። ልማትን እንደ ዘፈን እናቀነቅነዋለን እንጂ በውል ያልጨበጥንበትም ምክንያት ይኼ ነው፡፡ አፋችን ልማት፣ልባችን ጦርነት፣ኑሮአችን ልፋት ሆነ፡፡ የእናት ሀገራችን ፖለቲካዊ ኢኮኖሚ (political economy) እናቱም አባቱም ይኼው ነው!
በተደጋጋሚ ያየነውና ያጋጠመን ነገር የበላይና የበታች ሹማምንት አመራረጥ ችግር ነው፡፡ በዚያ ላይ ከወንበሩ ከማባረር ይልቅ እንደ ካርታ መበወዝን (reshuffle ማደረግን) እንመርጣለን። ከአንድ የሥራ ሃላፊነት አንስተን ሌላ የስራ ሀላፊነት ላይ እናስቀምጣለን፡፡ ከድጡ ወደ ማጡ እንደማለት ነው፡፡ ያ እንዳለ ሆኖም ዋናው አውራ፣ መሪው፣ በትክክል ሳይመደብ በዙሪያው የሚመደቡ  ሰዎችን ፍለጋ መሯሯጥ ይዘወተራል፡፡ ይኼም የችግራችንን አይነተኛ ባህሪ ሆኗል፡፡ “ባል ሳይገኝ ሚዜ ታማርጣለች” ማለትም ይኼው ነው!


Read 13758 times