Print this page
Saturday, 25 December 2021 12:56

“ፍሮም ‘ፈረንጅ አገር’ ዊዝ ላቭ!”

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(1 Vote)


                 እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ያው እንግዲህ ውጭ ያሉ ወዳጆቻችን ከዚህም፣ ከዛም እየተሰባሰቡ ነው፡፡
“ስማ ወንድምህ ሊመጣ እንደሆነ ሰማሁ።”
“አዎ ከነገ ወዲያ ይገባል፡፡”
“መጥቶ አያውቅም ሲባል ሰማሁ፡፡ ከሄደ ብዙ ጊዜ ሆነው እንዴ?”
“ወደ ሀያ፣ ሀያ አንድ ዓመት ይሆነዋል፡፡”
አዎ፣ በጣም ብዙ ዘመን በተለያዩ ምክንያቶች ብቅ ብለው የማያውቁ ዜጎቻችን በብዛት እየመጡ ነው፡፡ እነሱንም፣ አለፍ፣ አለፍ እያሉ ሲመጡ የከረሙትንም እንኳን ለሀገራቸው አበቃቸው፡፡ (እነ እንትና...እኔ የምለው ቦሌ ላይ ላትጠፉ ነው አይደል! ቆይማ...በፊት እኮ “መንገዶች ሁሉ ወደ ቦሌ ያመራሉ፣” አይነት ነገር የነበረው...አለ አይደል...በለጭለጭ ያሉ ነገሮች በርከት ያሉት እዛ ስለሆነ ነበር፡፡ አሀ...አሁን እኮ ቦሌን ‘ኦልድ ሲቲ’ የሚያስመስሉ ስንት ቦግ ቦግ ያሉ ቦታዎች አሉ፡፡ እናማ...ገና ለገና ዳያስፖራዎች በለጭለጭ ካለ ሰፈር አይጠፉም ብላችሁ ቦሌ፣ ቦሌ ስትሉ ‘እንዳትጠፋፉ ለማለት ያህል ነው፡፡)
እናማ፣ ምን መሰላችሁ... ሰው ሀገር አስራ ስድስት ሰዓት ምናምን እየተለፋ፣ ቤተሰብ በአንድ ጣራ ስር እየተኖረም ሳምንትና አስራ አምስት ቀን ሳይተያይ እየተነፋፈቀም፣ ከዚችም ከዛችም ተብሎ በሚላክ ገንዘብ እዚህ እንደ ቪ.አይ.ፒ. የሚያደርገንን፣ “አይደለም ሊተርፈኝ የአውሮፕላን ትኬት ለመግዛት እንኳን ከሁለት ዓመት በላይ ስቆጥብ ከርሜ ነው የመጣሁት፣” በሉንማ። ብዙዎቻችን አሁንም የተሳሳተ አመለካከት ነዋ ያለን! ቺዝ በርገር፣ ኬንተኪ ፍራይድ ቺክን ምናምን የመሳሰሉ ‘ፉዶች’ ‘የሀብታም ቀለቦች’ ይመስሉናላ!
“እኛ እዚህ የፈረንጅ ጎመን እንኳን ከቀመስን ስንት ጊዜያችን ነው፣ እነሱ እዛ የፈረንጅ በርገራቸውን እየገመጡ ከእነመኖራችን ረስተውናል፡፡ አሁን ማን ይሙት ሦስት መቶ ዶላር ለወር የሚልክልኝ ምን አድርጊበት ብሎ ነው!” የምንለው ደልቷችሁ የምትኖሩ ስለሚመስለን ነው። (እንትናዬ...ሰተት ብሎ ቦርሳ የገባ ሦስት መቶ ዶላር አነሰሽ! እንደው “ድሮስ ከአብሮ አደግ ጋር መሰደድ ትርፉ ይሄ ነው!” ምናምን አትበይኝና ዶላር የሚሉት ነገር ገንዘብ እንደሆነ ካወቅሽ ሦስት መቶ ቀንስ ሞልቷል! እናማ... እሷዬዋ ብቻ ሳትሆን...”እሱ ምን ያድርግ እዛ በርገሩን እየገመጠ፣ በመኪና እየተንሸራሸረ እዚህ ያለነው ሰውም አንመስለው!” የምንባባል በርከት ያልን መሆናችንን ለማሳበቅ ያህል ነው፡፡
ስሙኝማ... ዳያስፖራዎች አሁን መደባበቅ ምናምን የለም፡፡ እቅጭ፣ እቅጯን መነጋገር ነው፡፡ ምን መሰላችሁ...ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ...እውነቱን ማወቁ እነሱንም እዛ “ምን ይሉኝ ይሆን!” እያሉ ከመሳቀቅ ያድናቸዋል፡፡ በተለይ ደግሞ ከኮቪድ ወረርሽኝ መከሰት በኋላ ሁሉም ነገር እንደቀድሞው እንዳልሆነና ነገሮች መክበዳቸውን ንገሩንና በየሳምንቱና በየአስራ አምስት ቀኑ፣ “ይህን ላኪልኝ፣” “ያንን ላኩልኝ፣” የምንለው ነገር ላይ ቆጠብ እንበል፡፡ የምር ግን...ኮሚክ እኮ ነው፣ በዚህ ማንኛውም መረጃ እጅግ በጣም ቅርብ በሆነበት ዘመንም አሜሪካ ወይ ሌላ የፈረንጅ ሀገር መሄዱ ብቻ በራሱ ድሎት የሚመስለን አለን፡፡ እናማ...የእኛን ህልምና የእናንተን እውነት አንድ፤ ሁለት እያላችሁ መስመሩን አስምሩልንማ!
እናላችሁ...እኛ ደግሞ የሚላክልን ‘ዶላሬ’ እንዳይቋረጥብን ምክንያት በመደርደር የፈጠራ ችሎታችንን ያዳበርን... ‘ፌክ ኒውስነታችን’ እንዳይነቃ... አለ አይደል... “ታዲያ ሲቸግረኝ ምን ላደርግ!” ብሎ ፍጥጥ ማለት ነው፡፡ ዘመኑ ነዋ! የምር ግን...እንደው በሌላ አማርኛ ዘመኑ፣ የወጣቶቹን ቅላጼ ለመጠቀም፣ ‘የፈጣጤነት’ አይመስላችሁም! ጉድ እኮ ነው! ፊት ለፊታችሁ፣ ወይም በዓይናችሁ ስር የሆነ ነገር ሲሠራ አይታችሁት ትልቁም፣ ትንሹም ፍጥጥ ብሎ “ዓይኔን ግንባር ያድርገው!” ሆኗል። ‘ሂሳቡ’ ጥሩ እስከሆነ ድረስ እነ ሲ.ኤን.ኤንን የሚያስንቅ  ‘ፌክ ኒውስ’ መልቀቅ የማያሳፍር ዘመን ይመስላላ! 
ስሙኝማ... እንግዲህ ጨዋታም አይደል... በቀድሞ ጊዜ እኮ መሥሪያ ቤት ለሆነ ጉዳይ ፈቃድ መውሰድ ሲፈለግ የተለመደው ከአጎት ወይም ከአክስት አንድ መርጦ “አጎቴ አርፎ ነው፣” “አክስቴ አርፋ ነው፣” ምናምን ይባል ነበር፡፡ የሆነ ‘ኢንቬስቲጌቲቭ’ ምናምን ነገር ቢሠራበት ኖሮ እኮ በአጎትና በአክስት ብዛት ጊነስ ውስጥ ማግባት የሚገባን መአት ነበርን! ለነገሩ መአት ቂል አለቆች ስለነበሩ ለሰባተኛ ጊዜ “አጎቴ አርፎ ነው፣” ያለችውን ጸሀፊ “እንደው የሆነስ ሆነና በአጠቃላይ ስንት አጎቶች አሉሽ?” ምናምን አይባልም! ወይም “የአንቺ አጎቶች በየወሩ የሚሰናበቱት  የሆነ የተፈራረማችሁት ኮንትራት አለ እንዴ?” ምናምን አይባልም!  
ታዲያላችሁ...ዳያስፖራ ወገኖቻችንን “ታዲያ ሲቸግረኝ ምን ላደርግ!” ማለቱ ሁልጊዜ ላያዋጣ ይችላል፡፡ እዛ ሆነው ስለእኛ ከራሳችን በላይ የሚያውቁ ዳያስፖራዊች አሉዋ! ደግሞ...ጥያቄ ሊመጣ ይችላል፡፡ “በየት ሀገር ነው እንዲህ የቸገረው ሰው የሦስት ሺህ ብር ስኒከር የሚደርገው?” ሊባል ይችላል፡፡ ወይም “በምን አይነት ተአምር ነው በጣም የቸገረው ሰው የሠላሳ ሺህ ብር ሞባይል ስልክ የሚይዘው?” የሚል መስቀለኛ ጥያቄ ሊከተል ይችላል። ለነገሩ እንደነእንትና አይነት ጃኬታችሁ እላያችሁ ላይ እያለ እናንተ ሳታውቁት ለሦስተኛ ወገን ማሻሻጥ የሚችሉት፣ ለዚህም የሆነ ሰበብ አያጡም። “ታዲያ የሁለት ሺህ ብር ሞባይል ይዤ ቤተሰቤን ላሰድብ!” ቂ...ቂ...ቂ....
“ሀሎ!”...‘ከአማሪካን፡፡’
“ሀ...እ...ሀሎ...”... ከአፍሪካ ቀንድ፡፡  
“ምን ይጎትትሀል... ደህና አይደለህም እንዴ?”
“ምን ደህንነት አለ ብለህ ነው፡፡”
“ምን ማለት ነው! እንግዲሀ ይህን ጠማማ ንግግርህን አትጀምረኝ፡፡ የሆንከው ነገር ካለ በግልጽ ንገረኝ፡፡”
“እኔ እንጃ... ሰሞኑን ትንሽ አመም አድርጎኝ ነው...”
“ምን! ምን እያልከኝ ነው!”
“አይ.. ትንሽ የጤንነቴ ነገር...”
“አንተ ሰውዬ ትነግረኝ እንደሆን ንገረኝ፤ ዙሪያ አትጠምጠም!”
“ሰሞኑን አሞኝ ብዙም ከቤት አልወጣም።”
“ፕሮብሌሙ ምንድነው? ቼክአፕ አላደረግህም እንዴ?”
“ሰፈር ያለ አንድ አነስተኛ ክሊኒክ ሄጄ  ሀኪሞቹም አላወቁትም፡፡”
“አር ዩ ክሬዚ! አነስተኛ ክሊኒክ ምን ታደርጋለህ! ሆስፒታል አትሄድም እንዴ?”
“እ..እ..በምኔ! የሆስፒታሎቹ ዋጋ አገር አስጥሎ ነው የሚያስመንነው፡፡ ደግሞ ብታየኝ በጣም ቀንሼ እህል በልቼ የማድር አልመስልም፡፡”
“ኦ ማይ ጋድ! እንዲህ እስክትሆን ለምንድነው ያልተናገርከው!”
“ትሰጋላችሁ ብዬ ነው፡፡ ሶሪ...”
“አሁን በቃ! ለሲስ ቦስተን እደውልላትና ዊዚን ቱ፣ ስሪ ዴይስ ሳም ቱ ታውዘንድ እንልክልሀለን፡፡ ሆስፒታል ሄደህ እንደገና ቼክአፕ አድርግ...ደግሞ በደንብ ስማኛ፣ ዳየትህን አስተካክል...”
ስሙኝማ...ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ... “አመመኝ” የምትለዋ እኮ የመጣችው ሁሉም ‘ሰበብ’ አልቆ መደጋገሙ ያስነቃል ተብሎ ‘ቀይ መብራት’ ብልጭ ሲል ነው፡፡ ደግሞላችሁ...እነ ‘ብሮ’ እና ‘ሲስ’ እንዲህ ድንገት ይመጣሉ ብሎ አልታሰበም፡፡ “ከሳሁ...” ምናምን ሲል “ፎቶ ላክ፣” ቢባል፣ እድሜ ለፎቶሾፕ...ሸምበቆዋን ከእነፍጥርጥሯ መስሎ መላክ ነው፡፡ አሁን ታዲያ ድንገት ከች ያለው ብራዘር ምን ይገጥመዋል መሰላችሁ...“እህል ቀምሼ የማውቅ አልመስልም” ያለው ሰው... ምን አለፋችሁ...በቃ የቅቤ ቅል መስሎ በእኛ ሀገር እንደ ‘ምቾት ጥግ’ የሆነውና “ከዚህ በላይማ እንዳትወፍር!” የሚባል አይነት ቁመና ይዞ ቁጭ!
“አንተ! በቀደም እህል  ቀምሼ የማውቅ አልመስልም ብለኸን አልነበር እንዴ!”
“እ..እ... ምን መሰለህ...ገንዘቡን ከላካችሁልኝ ጀምሮ በቀን ሰባት ጊዜ ነው የምበላው!” (ይሄ ፌይር አይደለም... ዘለዓለም በቀን ሰባቴ እየጨረገደ አሁንም የምርኩዝ መዝለያ ዘንጓን የሚመስል መአት አለ አይደል እንዴ! እኔ የምለው...እንግዲህ ጨዋታም አይደል...አንድ ሰሞን አብዛኛውን ጊዜ ምሳውን በቀን እስከ አምስት ክትፎ ይመገባል ስለሚባል የስታዲየም በር የሚያስገባው ስለማይመሰል ሰው እንሰማ ነበር፡፡ በዚህ ዘመንም እንደዛው ይሆን እንዴ!)
እናማ... ዳያስፖራዎች በዘመድ አዝማድ፣ ፍሬንድ ምናምን “አሞኝ...” “በእዳ ተይዤ...” “የእንትን ስልጠና መውሰድ ፈልጌ...” እያልን ፌክ ኒውስ ስንልክ መክረማችንን ስትሰሙ አትብሸቁማ! 
ብቻ ዳያስፖራዎች፣ በቆይታችሁ ይመቻችሁማ!
ደህና ሰንብቱልኝማ!


Read 1713 times