Saturday, 25 December 2021 12:59

ሠላምን ባህል ማድረግን ያለመ ፕሮጀክት

Written by  መታሰቢያ ሳሣዬ
Rate this item
(0 votes)

  ለዓመታት የዘለቀ ግጭትና የሰላም ችግር ያጠላበት፣ ህጻናትና ሴቶች በእጅጉ ዋጋ የከፈሉበትና ከ200 ሺ በላይ ሰዎች የተፈናቀሉበት አካባቢ ነው- በደቡብና ኦሮሚያ ክልሎች ውስጥ የሚገኙት የአማሮ፣ ገላንና ሱሮበርጉዳ ወረዳዎች፡፡
ከ3 ዓመታት በፊት በአካባቢው በተቀሰቀሰ ግጭት ሳቢያ ለችግር የተጋለጡትንና ከመኖሪያ ቀዬአቸው የተፈናቀሉትን ወገኖች ለመደገፍና በአካባቢው የተቀሰቀሰውን ግጭትና  የሰላም ችግር በዘላቂነት ለመቅረፍ የሚያስችል አንድ ፕሮጀክት ሰሞኑን በዎርልድ ቪዥን ኢትዮጵያ ተጀምሯል፡፡
ይኸው ሰላም፣ ልማትና ሰብአዊ እርዳታን አጣምሮ የያዘውና በወርልድ ቪዥን ኢትዮጵያ ተግባራዊ መደረግ የጀመረው አዲሱ ፕሮጀክት፤ ሰላምና ማህበራዊ ትስስርን በሶስቱ ወረዳዎች ውስጥ እንዲሰፍን ማድረግ ዋነኛ ዓላማው አድርጎ መነሳቱን በወርልድ ቪዥን ኢትዮጵያ የፕሮጀክቱ አስተባባሪና የሰላም ግንባታ ሰራተኛ የሆኑት አቶ እዮብ ይስሃቅ ተናግረዋል፡፡
በደቡብ እና ኦሮሚያ ክልሎች አማሮ፣ ገላንና ሱሮ በርጉዳ ወረዳዎች ላይ ተግባራዊ የሚሆነው ይኸው የሰላምና እርቅ ፕሮጀክት በ3ቱም ወረዳዎች ውስጥ የሚገኙ 360 ወጣቶችን ተጠቃሚ የሚያደርግና የስራ ዕድልን ለመፍጠር የሚያስችል እንደሆነም ተገልጿል፡፡ በፕሮጀክቱ በአካባቢው ለሚገኙ 180 ወጣቶች ግጭትን በሰላም መፍታት ስለሚቻልበት መንገድ ስልጠና ይሰጣል ተብሏል፡፡ በግጭቱ ሳቢያ ከመኖሪያቸው ተፈናቅለው በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ  የአካባቢው ነዋሪዎችን ለማቋቋም ራሳቸውን እንዲችሉ ለማድረግ የሚያስችል ስራ እንደሚከናወንም ተገልጿል፡፡
በሁለቱ ክልሎች በሚገኙት ወረዳዎች ውስጥ የሚኖሩት በተለያዩ ጊዜያት በሚቀሰቀሱ  ግጭቶች  ሳቢያ ለጉዳት የሚዳረጉትን የአካባቢው  ነዋሪዎች ህይወት ለመቀየር የሚያስችለውና ግጭቶችን በዘላቂነት በማስቀረት በአካባቢው ሰላም እንዲሰፍን ለማድረግ ያስችላል የተባለው ይኸው ፕሮጀክት በወርልድ ቪዥን ኮሪያ ፈንድ የተደረገና ከ500 ሺ ዶላር በላይ ወጪ የሚደረግበት ፓይለት ፕሮጀክት እንደሆነም ተገልጿል፡፡
በአዋሳ ከተማ ውስጥ በተካሄደው በዚህ ፕሮጀክት ማስጀመሪያ ፕሮግራም ላይ የተገኙት የወርልድ ቪዥን ኢትዮጵያ ካንትሪ ዳሬክተር ሚስተር ኤዲ ብራውን እንደሚናገሩት፤ ይህ ዓላማውን ሰላምና ማህበራዊ ትስስርን በሁለቱ ወረዳዎች ውስጥ ማስፈን አድርጎ የተነሳው ፕሮጀክት ለቀረው የአገሪቱ  ክፍሎች አርአያ ሊሆን የሚችልና በሰላምና እርቅ  ጉዳዮች ላይ ትልቅ በጎ ተፅዕኖ ሊፈጥር የሚችል ፕሮጀክት ነው፡፡ ፕሮጀክቱ ሰላምን ባህል ማድረግን ያስተምራል የሚል እምነት አለኝ ያሉት ዳይሬክተሩ፤ ሠላም የሁሉም ነገር መሰረት በመሆኑና ከሰላም በፊት ሊተገበር የሚችል ብልጽግና ሊኖር ስለማይችል በዚህ የሰላምና የማህበራዊ ትስስር ጉዳይ ላይ አጥብቀን ልንሰራ ይገባል ብለዋል፡፡
የወርልድ ቪዥን ኢትዮጵያ ካንትሪ ዳይሬክተር ሚስተር ኤድ ብራውን፤ በአማራና አፋር ክልሎች በሽብርተኛው የህወኃት ሃይሎች የተጎዱ ዜጎችን ለመደገፍና ለደረሱት ችግሮች አፋጣኝ ምላሽ ለመስጠት የሚያስችሉ እንቅስቃሴዎች ለማድረግ ወደ ስፍራው ማምራታቸውን ተናግረዋል። በጦርነቱ የተጎዱ አካባቢዎች ላይ የደረሱ የምግብና የንጹህ መጠጥ ውሃ እጥረቶችን ለመቅረፍ የሚያስችልና በጦርነት የፈራረሱ ቤቶችን ለማደስ እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
በዚህ  የፕሮጀክት ማስጀመሪያ ፕሮግራም ላይ የተገኙት የሲዳማ ክልል ምክትል ፕሬዝዳንት እና የትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ በየነ በራሳ እንደገለፁት፤ አካባቢው ለዓመታት የዘለቀ የግጭት እንቅስቃሴዎች የሚታዩበት ስፍራ ሆኖ መቆየቱን አስታውሰው፤ ይህንን ችግር በዘላቂነት ለማስቀረትና በአካባቢው ሰላም እንዲሰፍን ለማድረግ በድርጅቱ እየተከናወነ ያለው ተግባር በእጅጉ ሊበረታታ የሚገባው ነው ብለዋል፡፡ በግጭቱ ሳቢያ ከመኖሪያ ቀዬአቸው የተፈናቀሉ ወገኖች ወደ መኖሪያቸው ተመልሰው ራሳቸውን እንዲችሉ ለማድረግ እየተከናወነ ያለው ተግባር የአካባቢውን ሰላም በዘላቂነት ለማረጋገጥ የሚያስችል ነውም ብለዋል፡፡
ይህ አዲሱ ፕሮጀክት ቀደም ሲል በጌዲዮና ጉጂ ዞን በ2010 ዓ.ም ተከስቶ የነበረውን ግጭት ተከትሎ የተጀመረው ፕሮጀክት ቀጣይና ሁለተኛው ፕሮጀክት ሲሆን ከዚህ ቀደም በ1.2 ሚሊዮን ዶላር ተግባራዊ የተደረገውና በአካባቢው ወጣቶች ላይ ያተኮረ የመጀመሪያው ፕሮጀክት ውጤታማ ሆኖ ተጠናቋል፡፡

Read 1044 times