Sunday, 26 December 2021 00:00

ይልቁንስ ይቻላልን ተዉና አይቻልምን መርምሩ!

Written by  ያዕቆብ ብርሃኑ
Rate this item
(0 votes)

     "--በእርግጥ ምንም ተስፋ የለህም፡፡ ምንም፡፡ አይገርምህም ምንም ተስፋ የለህም፡፡ ሆኖም ለምን ታመነታለህ? ይልቅ መለየትን ሳትፈራ አፍቅር፤ ስለማጣት ሳትጨነቅ ምላሽም ሳትጠብቅ ለድሆች ስፈር፤ የመሰለህን ሳትሸማቀቅ ተናገር፤ ሌሎች በሚናገሩት አትሸበር፤ ቅጥሩን፣ ድንበሩን፣ ነውሩን፣ ቅጥፈቱን፣ ቅብጥርጥሩን ሁሉ ስበር፤ ድፈር፡፡--"
                
                 ቁምነገር እናውራ! በምስራቅ የምትወጣውን ፀሐይ በምዕራብ ማውጣት ከተቻለ ንገሩኝ? ወይም በዚህች ጨረቃ ምትክ ሌላ ውብ ዘወትር የምትበራ ጨረቃ መፍጠር ከተቻለም አስረዱኝ? ወይም የጊዜን ስልጣን ሽሮ ትናንት፣ ዛሬና ነገ የሌለበት ምንጊዜም አሁን የሆነበት የዝንተዓለም  የጊዜ ልኬት ውስጥ መኖር ከተቻለም አብረን ይቻላል እንበል? የእናንተ ድሪቶ ዘይቤማ ዋጋ ልከፍልበት የተገባ ሆኖ አላገኘሁትም። ለነገሩ ይሄንንም ማድረግ ቢቻል እንኳን ውጤቱ በሳሙኤል ቤኬት አንደበት ሲገለጽ፤ ‹‹failing better›› ብቻ ነው፡፡ ከውድቀት አያመልጥም፡፡
ያም ያም እየተነሳ ይቻላል ይልሃል። እሱማ ይቻላል፡፡ ከጥቂት ሯጮች ጋር ተፎካክሮ አንደኛ መውጣት ይቻላል። ከድሃው ላይ ነጥቆ ቅንጡ ቤቶችን መገንባትም ይቻላል፡፡ ቱጃር መሆንም ቀላል ነው፡፡ ብዙ ከተሞችን ወርሮ ሺህ ተቋማትን እንዳልነበር አውድሞ፣ በእልፍ ምስኪኖች ሬሳ ላይ መሸለል እንደሚቻልም አይተናል። ይቻላል! ይሄው ሂደት ጥቂትም ቢሆን ዋጋ ማስከፈሉ ባይቀርም ቅሉ ይቻላል፡፡ የጎረስከውን ምግብም እንኳን የማኘክ ትግል ካላደረግክ ልትውጠው አትችልም፡፡
ሆኖም ጥቂት ቤሳ ሳንቲሞችን ለቃቅሞ ከሌሎች በልጦ ለመታየት የሚደረግን አጉል ጀብድ እፀየፋለሁ፡፡ ጥቂት መደዴ ስንኞችን ቋጥሮ በብዙ የሚያንቧትር ገጣሚ ሳይ ሳቄ ይመጣብኛል፡፡ ሌላም ሌላም … ለእኔ ጥበብ እንደ አደገኛ ወጀብ፣ እንደ ማዕበል፣ እንደ የጨረቃና ምድር መጋጨት ዓይነት ከፍተኛ ነውጥ ካልፈጠረ ከልጆች እቃቃ ጨዋታ ለይቼ አላየውም፡፡ ገጣሚዎቻችሁ፣ ሞዛቂዎቻችሁ፣ ጠቢባኖቻችሁ፣ ሁሉ ግን የነገር ሀቲታቸውን የሚያዘነግጉት፣ ከሚያነውሩ፣ ከሚያሳቅቁ፣ ዋልጌ፣ ዋዘኛ፣ ቧልት መሳይ ግንትር የሕይወት ክፋዮቻችሁ ላይ ብቻ መሆኑን ሳይ ዘወትር ይገርመኛል። ምናባቸው ክንፏ እንደተሰበረ ቢራቢሮ ሥርሥር ከመውተፍተፍ ባለፈ ፈቀቅ ማለት አይችልም፡፡
ለመሆኑ እናንተስ ንጉሥ መሆንን የተመኛችሁት ስለምን ነበር? ሌሎች እልፍ አዕላፋት ድሆችን ረግጣችሁ ለመግዛት?! አሸናፊ ለመሆን የቋመጣችሁትስ ስለምንድን ነው? በተሸናፊ ወንድሞቻችሁ ሽንፈትና ሀፍረት ርካሽ ክብርና ዝና ለመሸመት?! ቱጃር ለመሆን የማሰናችሁት ለምን ነበር? ከሌሎች አዕላፍት አዳፋ ለባሽ ድሆች በልጣችሁ ለመታየት! እነዚህ በሙሉ ለእኔ ዶሮ ብታልም ጥሬዋን ዓይነት መናኛ ህልሞች ናቸው፡፡                       
በምንኖርበት ዓለም ውስጥ የምንወርሰው ተፈጥሮ የምታስታጥቀን አንድ ዓይነተኛ መላ አለ፡፡ ትግል! በበኩሌ ለመሸነፍ ተሰልፌ አላውቅም፡፡ ግን እስከ ሞት ታግሎ መሸነፍን አቤት ስወደው! በመሸነፍ ውስጥ፣ ተስፋ፣ እልህ፣ ቁጭት አለ፡፡ ትርጉም ያለው ሕይወት ለመኖር እና ኑረትህን ለማሻገር መሰረታዊ መሰላሎች እኒሁ ናቸው፡፡ በማሸነፍ ውስጥ ግን እብሪት ብቻ... ሆኖም አሸናፊዎችም በእርግጠኝነት የሚሸነፉበት ዕለት ይመጣል፡፡ ይሄው ሂደት ምንጊዜም ሲያልቅ ውጤቱ የዜሮ ብዜት ነው፡፡
እናም አስቀድሞውኑ እንድትታገላት እንጂ እንዳታሸንፋት ሆና በተሰራች ዓለም ውስጥ እስከ ጅልግግናህ እየኖርክ ይቻላል አትበለኝ! በእርግጥ መቶ ሜትርን በ5 ሴከንድ ሮጦ ማጠናቀቅ ሊገርም ይችላል! ይሄም ቢሆን የሚያስገርመው እናንተን እንጂ እኔን አይደለም፡፡ እኔና የአልበርት ካሙው ንጉሥ ቄሳር ካሊጉላ ይህች ውጥንቅጧ የወጣ ዓለም እያየናት በሴከንዶች ልዩነት ሟሽሻ ብትጠፋ እንኳን መገረማችንን እንጃ፡፡ ለምን? ካልኽ ጥሩ… ሁሉም  ነገር፣ ምንም ነገር አስቀድሞውኑ በጊዜ ውስጥ እውን ስለሆነ፡፡ በጊዜህ ውስጥ መሸለም፣ መጋዝ፣ መታሰር፣ መዋረድህ አስቀድሞውኑ የታሰበ ነው፡፡ ትላንት ዛሬና ነገን ሳይሸራርፍ ሳይከፋፍል ለሚኖር ሠው፣ በጊዜ ውስጥ ሁሉም የሚሆን ነው፡፡ በትጋትህ ወይ በስንፍናህ አንዳንዱን ምርጫ የምትወስነው አንተው ብትሆንም ቅሉ፡፡
ነገር ግን የብቻህ ዓለም የለህም፡፡ እንደ በረት ሙሉ አሳማ ተፋፍጎ የሚላፋ የዓለም ሥርዓት አካል ነህ፡፡ የቱንም ያህል ለመነጠል፣ ለተፈጥሮ እውነተኛ ጥሪ ለመገዛት ብትፈልግ ሚዛንህን ላለመሳት ስትል በተደጋጋሚ ለሌሎች ቅኝት በቀረበ እርምጃ ጉዞህን ለማድረግ ትገደዳለህ። የምንለካውስ ለሌሎች በገባናቸው፣ በታሰብነው፣ በታየነው በተረዱን ልክ እንጂ በአዕምሯችን ውስጥ በምናውጠነጥነው ሃሳብና የብቻ ትግል እኮ አይደለም፡፡
ይሄኔ ነው ተስፋ ማጣትህ ብቅ የሚለው። ጣፋጭ ‹Bed time Story› አስነብቤህ የሚጠይቅ ደመነፍስህን ዝም ማሰኘት አልፈልግምና እባካህን ይህንን አባባሌን ከሌጣነት ባሻገር ተመልከተው። በእርግጥ ምንም ተስፋ የለህም፡፡ አንተ ተስፋ የምታደርጋቸው ነገሮች እንኳን ተስፋ መሆናቸውን አላውቅም፡፡ ዛሬም ዓለም በመሲሓን ከተጎበኘች ከሺህ ዓመታት በኋላ የባሰ ውጥንቅጥ ውስጥ ነች፡፡ አየህ ለሰው ልጅ የሚያስፈልገው ትግል እንጂ ተስፋ አይደለም፡፡ ተስፋ እንደ እንቅልፍ ነው። ስቃይህን ያዘገየዋል እንጂ ሊያጠፋልህ አይችልም፡፡ ትግል ግን እንደ ሲሲፐስ ወትሮ ለሚመለስብህ ፈተና እንኳን ያጸናሃል፡፡
ለምሳሌ የዛሬ ዓመት ትመረቃለህ እንበል። ወይም ከሁለት ወራት በኋላ ልታገባ ነው፤ ከመንፈቅ በኋላ ወደ ውጭ ልትሄድ ዕድል አግኝተሃል፤ ሰሞኑን የኖቤል ሽልማትን አሸንፈሀል፤ በቅርቡ ለሀገር መሪነት ታጭተሃል፤ ነገ ዕቁብ ሊወጣልህ ስለሆነ ደስ ብሎሃል... እነዚህን ነው ተስፋ አድርግ የምትለኝ? በበኩሌ እነዚህን ያንተን ቀቢጸ ተስፋዎች እያባበልኩ፣ እንደ ትል ደቃቅ ፍጥረት ሆኜ መኖርን አልሻም፡፡
ይልቅ ልንገርህ ስማኝ፡፡ በእርግጥ ምንም ተስፋ የለህም፡፡ ምንም፡፡ አይገርምህም ምንም ተስፋ የለህም፡፡ ሆኖም ለምን ታመነታለህ? ይልቅ መለየትን ሳትፈራ አፍቅር፤ ስለማጣት ሳትጨነቅ ምላሽም ሳትጠብቅ ለድሆች ስፈር፤ የመሰለህን ሳትሸማቀቅ ተናገር፤ ሌሎች በሚናገሩት አትሸበር፤ ቅጥሩን፣ ድንበሩን፣ ነውሩን፣ ጥፈቱን፣ ቅብጥርጥሩን ሁሉ ስበር፤ ድፈር። ክነፍ፣ ሸልል፣ ቆዝም፣ ብረር…ሲያሻህ እንደ ትንኝ እንደ ዓሳ፣ ስትፈልግ እንደ ንስር ቅዘፍ፣ ማስን፣ ታትር… በመጨረሻ በልብህ ላይ የሚቀረው ጥልቅ ሀዘን ብቻ መሆኑን ስነግርህ ግን እንዳትደነብር፡፡ አዎ ጊዜና ሞትን ለማሸነፍ ባያስችልህም እንኳን ሕይወትን በሙላት ለመቀበል የተሻለው መንገድ ይሄኛው ይመስላል፡፡ ነገር ግን ከልብ በመነጨ ንጹህ መሻት ሁሉንም ከከውንከው (ምንም ነገር ሊሆን ይችላል) አማልክቱ ሳይቀር ከአንተ ጋር እንደሚያብሩ ማሰብ ትችላለህ፡፡ ከልብ በመነጨ ንጹህ መሻት ክፋት ሊታሰብ አይችልም መቼስ አይደል?
እናስ ጓድ ውጣ እንጂ ለምን ታቀረቅራለህ? ለምን ጽንፍ የለሽ ህልምህን በአራት ማዕዘናት ግንቦች ትቀብራለህ? ጀግና ለመባልስ ስለምን በሰላም ከተኛ አንበሳ ጋር ትጋተራለህ? ይልቅ ከንጋት እስከ ምሽት አስስ፤ ጠርጥር፤ ተመራመር፤ የትም ውለህ የትም እደር፤ እንደ ጀብደኛ ሰው ኑር፡፡ ምንም ተስፋ የሚሆን ነገር ባይኖርም ምንምን ተስፋ ለማድረግ ታትር። በእርግጥ ምንም ተስፋ የለህም ስልህ ተስፋ ቆራጭ እንዳልመስልህ፡፡ ምንምን ተስፋ የማደርገውን እኔን ተስፋ ቆራጭ ለማለት አንተ ማን ነህ? በእርግጥ ምንም ተስፋ የለህም፡፡ ግን ስለምን ከጭልፊት እንደሚደበቁ ጫጩቶች ተስፋ ይሉት መጠለያ ፍለጋ ትፈረጥጣለህ? ተስፋ ማጣት ራሱ እኮ ተስፋ ነው፡፡ በል ይልቅ ድፈር…
በጉዞህ ሂደት ስንቅ የሚሆን ኩርማን እውነት ይኼውልህ... የዚህ ዓለም ቁልፍ ቀመሮች ጊዜና ሞት ይሰኛሉ፡፡ ሌላው ሁሉ ከትንኝ ያነሰ ከላባ የቀለለ ትርኪምርኪ እኮ ነው! ጊዜ እና ሞትን የማሸነፊያ መንገዶቹ ደግሞ ከማይታየው፣ ከማይዳሰሰው፣ ከተረሳው ወለል ስር ናቸው፡፡ በሉ ይቻላልን ተውና አይቻልምን መርምሩ፡፡ ያኔ የተረሳውን ፅንፍ የሚያስሱ ምናቦቻችሁ ካንቀላፉበት ይነቁ ይሆናል፡፡ ምናልባት!  


Read 2896 times