Saturday, 25 December 2021 13:04

ወርቃማ የግንባታ ዘመን፣ ወይስ አፍራሽ የሸክላ ዘመን።

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(1 Vote)

  • ለመገንባትም ጊዜ አለው። ለማፍረስም ጊዜ አለው። ወይስ፣ የሰዎች ይሆን ምርጫው?
   • ወርቁም ሸክላውም፣ ብረቱም ዝገቱም፣ በኛው በሰዎች እጅ ውስጥ ነው።
                  
                “አየር መንገድ” የሚለው ስያሜ፣ ትንግርተኛ አባባል ነበር - በዘመኑ። “አየር ላይ”፣… በሰው ልጅ የእልፍ አእላፍ አመታት ታሪክ ውስጥ፣ መንገድ ኖሮ አያውቅም። ለዚህም ነው፤ “ገንዘብ ካለ፣ በሰማይ መንገድ አለ” ተብሎ የተተረተው። የገንዘብን ሃያልነት ተመልከቱ። ተዓምረኛ ነው። ያልነበረና የሌለ ነገር፣ ይኖራል፤ ይፈጠራል - በገንዘብ ምትሃት። ገንዘብ ካለ፤ በሰማይ መንገድ አለ።
ገንዘብ ከሌለ ደግሞ፤ የነበረ ነገር ሁሉ ይጠፋል። “ከሌለህ፣ የለህም” ተብሎ የለ። ገንዘብ ከሌለህ፣ አንተም አትኖርም። ደግነቱ፣ አንተ ከሃያልም ሃያል ነህ። ከገንዘብ ትልቃለህ። ገንዘብን መፍጠር ትችላለህ። ሰው ተዓምረኛ ነው፤ በሰማይ መንገድ አለው። በአውሎ ነፋስ መሃል መመላለስ ይችላል።
ውቅያኖሱ በማዕበል ይናወጣል። ሰው ግን መንገድ አላጣም። ከአህጉር አህጉር፣ ባህሩንና ውቅያኖሱን ይሻገራል። ሰው ብርቱ፣… አለምን ይዞራል። ቀላል ሆኖ አይደለም።
ከንግስቷ ወርቃማ ዘመን በኋላ፣ የአፈር የአቧራ ዘመን።
በባሕርና በአየር ቀርቶ፣ ምድር ለምድር መጓዝም ከባድ ነው። ያደክማል።
በበረሃ አሸዋ ላይ መጓዝ፣ እንደ ሕልም ሩጫ ነው። እግር ላይ እንደታሰረ አሎሎ ነው - አሸዋ። የኋሊት ያንሸራትታል። ቁልቁል ይጎትታል። አቧራውና ሃሩሩ፣ ረሃቡና የውሃ ጥሙ ሳያንስ፣… አቅጣጫን እያሳሳተ በአዙሪት ያስቀራል - የበርሃ ጉዞ።
የጫካው የገደሉ፣ የጋራ ሸንተረሩ፣ የጎርፍ የረግረጉ ጉዞም፣ ይብሳል እንጂ አይሻልም። ክብረ-ነገስት እንደሚተርከው፣ ንግስተ ሳባ፣ ከኢትዮጵያ ወደ ኢየሩሳሌም ለመጓዝ ብዙ ወራት ፈጅቶባታል። ሊብስም ይችል ነበር። የያኔው ዘመን ጥበበኛ ኢትዮጵያውያን፣ ባለ ብዙ መርከብ፣ ባለ ብዙ ግመል፣ ጎበዝ ተጓዦች ስለነበሩ እንጂ፤ ጉዞውስ ከባድ ነው።
የሆነ ሆኖ፣ ንግሥተ ሳባ፣ በኢየሩሳሌም ቆይታዋ አርግዛ፣ ወደ አገሯ ስትመለስ ብዙ ወራት አልፈዋል። እናም፣ አገሯ ብትገባም፣ ወደ ቤተ-መንግስትዋ ሳትደርስ፣ “ማይበላ” በተሰኘ ቦታ እንደወለደች በአፈታሪክ ተተርኳል። ለወሊድ ጊዜ፣ “ውሃ አምጡ” የሚል ትዕዛዝ ይበዛል። ከዚህ ጋር የተያያዘ ነው ይባላል - የቦታው ስያሜ።
የይባላል ትረካው በዚህ ይብቃን። በፅሁፍ ወደተመዘገቡ፣ የሩቅ ዘመንና የቅርብ ጊዜ ታሪክ እናምራ።
የዛሬ 2000 ዓመት ግድም፣ የኋሊት ተመልሰን፣ የታሪክን ጉዞ እንመልከት። የኢትዮጵያውያን መርከቦች፣ በያ ዘመን፣ የቀይ ባህር ንጉሦች ነበሩ። በየብስም፣ እስከ ግብፅ ድንበር የጉዞ መንገድ እንደጠረገ፣ የያኔው ንጉሥ በኩራት አውጇል። ትልቅ ወርቃማ ስኬት ነው።
ከዚያ በኋላ ግን፣ የጉዞ ነገር፣ ለሺ ዓመታት አልተሸሻለም - በመላው ዓለም።
በኢትዮጵያ፣ የአፄ ምኒልክ ጦር፣ ከመሃል አገር ወደ አድዋ ለመድረስ፣ ለሦስት ለአራት ወራት በጉዞ ደክሟል።
የአትላንቲክ ውቅያኖስ ጉዞ፣ በጣም ረዥም ነው። ነገር ግን ኢትዮጵያን አንዴ ከመዞር፣ ብዙ አይበልጥም። እንዲያም ሆኖ፣ የአትላንቲክ የመርከብ ጉዞ፣ ከ40 ቀን በላይ ይፈጅ እንደነበር Vaclav Smil ይገልፃሉ (ከ180 ዓመታት በፊት፣ በነዳጅ የሚሰራ መርከብ ከመምጣቱ በፊት)።
ከሶሪያ፣ ለሃጅ ጉዞ ወደ መካ የሚሄዱ አማኞች፣ በግመል 40 ቀን በረሃ ለበረሃ ተንከራትዋል፤ አፈር መስለው ለብሰው። (ከዛሬ 120 ዓመት በፊት፣ የባቡር መንገድ ከመምጣቱ በፊት ማለት ነው)።
ከ1830 እስከ 1930 ባሉት ዓመታት ግን፣ ሁሉም ነገር ተቀየረ። አሁንስ?
ከወርቃማ የግንባታ ዘመንና  የዓለም ንዝረት ወዲህ፤ እስከ ዛሬ።
በወርቃማው የግንባታ ዘመን፣ ምን ያልተፈጠረ ተዓምር አለ? በሞተር ሃይል፣ ውቅያኖስን የሚያቋርጡ መርከቦች፣ ድንበር ዘለል የባቡር መንኮራኩሮች መጡ። ከዚያም በተከታታይ፣ በነዳጅ የሚሰሩ መኪኖችና አውሮፕላኖች።
ዓለምንና የሰውን ኑሮ የሚቀይሩ እነዚህ ሁሉ ወርቃማ ተዓምሮች የተከሰቱት፣ በጥቂት ዓመታት ውስጥ ነው። ኤሌክትሪክ ማመንጫ ማሽን፣ በኤሌክትክ የሚሰራ ሞተር፣ ስልክና ሬዲዮ፣ ካሜራና ፊልም፣ የሙዚቃ መቅረጫና ማዳመጫ፣… ምኑ ይቆጠራል!
ኤሌክትሪክ ያልነካው የዓለም ክፍል፤ በኤሌክትሪክ ያልነዘረ የኑሮ ቅርንጫፍ የት ይገኛል? ዓለም፣ እንዲሁም በውስጧ ያለው ነገር ሁሉ፣ በኤሌክትሪክ ንዝረት፣ እንደ አዲስ ነቃ፤ እንደ አዲስ ተነቃነቀ ቢባል ይሻላል።
የነዳጅ መኪኖች ከመምጣታቸው በፊት፣ በኤሌክትሪክ የሚሰሩ መኪኖች ናቸው የተፈበረኩት። የሀዲድ መንገድ ተደላድሎ፤ እንደ መንገድ መብራትም የኤሌክትሪክ ገመድ ተዘርግቶ፤  በበርሊን፣ በለንደን እና በኒውዮርክ ከተሞች፣ ስራ ጀመሩ። የእንግሊዞቹ፣ “ways”  በሚል ቅጥያ ይታወቃሉ። የአሜሪካዎቹ ደግሞ Streetcar lines:: “የመኪና መንገድ” እና “የመኪና መስመር” ልንላቸው እንችላለን። መኪኖቹ ከዚህ ውጭ አይሰሩም። በዚያው መንገድ በዚያው መስመር ብቻ፡፡
የአውሮፕላን ጉዞ፣ ግን ከዚህ ይለያል፡፡ “ways” እና “ lines”  የሚለው ስያሜ ግን፣ ወደ አውሮፕላን አገልግሎት ተሸጋግሯል፡፡ በእንግሊዝ፣ Airways በሚል ስያሜ፣ በአሜሪካ ደግሞ Airlines።
የኢትዮጵያ ደግሞ፣ ሁለቱን ስያሜዎች ያቀላቅላል፡፡ “የኢትዮጵያ አየር መንገድ” ተብሏል - ኤርወይስ እንደማለት፡፡ ግን ደግሞ፣ “ኢትዮጵያን ኤርላይንስ” ይባላል - የአየር መስመር እንደ ማለት ነው። ያው ነው። የባቡር መንገድ፣ የባቡር መስመር እንል የለ! ለመርከብ አገልግሎትም፤ “ሺፒን-ላየንስ”፡፡ አየር ላይና በባህር ውስጥ የተዘረጋ መስመር ወይም መንገድ ባይኖርም፤ ስያሜውን ተጋርተዋል፡፡ ተከታትለው የመጡ አዲስ የቴክሎጂ ተዓምሮች ናቸውና፣ ስም ቢጋሩ አይገርምም፡፡
“ሰው ምን ይሳነዋል?” ያሰኛል፡፡ አፈሩ፣ ወርቅ ይሆናል። አተላውም፣ ነዳጅ።
ነገር እየሰመረ ሲሄድ፣ የሰው እጅ የነካው ነገር ሁሉ፣… አፈሩ ጠጠሩ ሁሉ፣ ወርቅና እንቁ የሚሆንለት ይመስላል፡፡
የእርሻ ማሳዎችን ሲያበላሽ የነበረ “ጥቁር ቆሻሻ” ነው፤ የአለማችን አንቀሳቃሽ ሃይል የሆነው፡፡ “የአንድ በርሜል ድፍድፍ ነዳጅ ዋጋ”፣ የሚል ዜና የእለቱ የምንሰማው፣ በሌላ ምክንያት አይደለም፡፡ የእርሻ ጠንቅ የነበረው ጥቁሩ አተላ፤ የሰው እጅ  ሲነካው፣ ወርቃማ ነዳጅ ሆኗል፡፡
“ነዳጅ” የምንላቸው ፈሳሽ ወርቆች፣ በሰው እጅ ተጠምቀውና ተጣርተው ባይፈጠሩ ኖሮ አስቡት፡፡ ዓለማችንን ያጥለቀልቁ ከ1.3 ቢሊዮን በላይ መኪኖች ባልተፈጠሩ፡፡
በየእለቱ ከ10 ሚሊዮን በላይ ተሳፋሪዎችን፣ ከከተማ ከተማ፣ ከአገር አገር ለማጓጓዝ፣ በየእለቱ የሚያደርጉ ከ100ሺ በላይ የትልቅ አውሮፕላን በረራዎችስ?  ይህ ሁሉ ተዓምር፣ ለምኞት የሚያስቸግር የምናብ ምትሃት መስሎ ይቀር ነበር፡፡ ያለ ነዳጅ አይሆንማ።
ደግነቱ፣ የእህል ፀር የነበረው ፈሳሽ ጥቀርሻ፣ በሰው እጅ ገብቶ፣ ወርቃማ ፈሳሽ ሆነ፡፡ በየእለቱ ከ95 ሚሊዮን በርሜል የሚበልጥ ድፍድፍ ነዳጅ ይመረታል፡፡ የዚያኑ ያህልም፣ በየእለቱ እየተጣራ፣ ቤንዚንና ናፍታ፣ እንዲሁም ነጭ ጋዝ (ወይም ኬሮሲን የተሰኘው የአውሮፕላን ነዳጅ) ይመረታል፡፡
 ከአሸዋ የተቀመመ ወርቅ፤ ዓለምን የሚያንቆጠቁጥ።
ኤሌክትሮኒክ ነክ ቁሳቁሶችን ተመልከቱ፡፡ ሞባይልና ኮምፒዮተር፣ ቴሌቪዥንና ዲኮደር፣… አሁንማ ኤሌክትሮኒክስ ሳይገባበት የሚሰራ ነገር የለም ማለት ይቻላል። ይሔ ሁሉ ደግሞ፣ ያለ “ትራንዚስተር” እውን ሊሆን አይችልም፡፡ ትራንዚስተር ደግሞ፣ የተነጠረ፣ የተሞረደ፣ የተሸመነ “አሸዋ” ነው ማለት ይቻላል፡፡
አሸዋ ነው፤ በሰው እጅ ውስጥ ገብቶ፣ ዓለምን የሚያቆጠቁጥ ወርቃማ ቁሳቁስ ለመሆን የበቃው። “ትራንዚስተርስ” ማለት በግርድፉ፣ “ማብራሪያ ማጥፊያ” ነው፡፡ አሸዋ ቀልጦ ተጋግሮ፣ ከመስተዋትም በላይ ተቦርሾ፣ እልፍ “ትራንዚስተሮች” ይታተሙበታል፡፡ እልፍ “ማብሪያ ማጥፊያ”፣ በስርዓት አጣምሮ ቀጣጥሎ ማተም፣ “ትራንዚስተርስ ጋጋሪ” እንደመሆኑ ቁጠሩት፡፡ “አነባብሮ ጋጋሪ”፡፡
በእርግጥ፣ ምጣዱ እንደልብ የሚያዝናና አይደለም፡፡ ከመስታዋት የላቀ እንከን የለሽ መሆን አለበት - ንጣፉ (ምጣዱ)። እንደ እንጀራ ምጣድ በሰፊው ይጀምሩታል፡፡ ከዚያ ውስጥ፣ እንከን የለሹን ብቻ እየመረጡ፣ እየቆረጡ፣ ትናንሽ የትራንዚስተር መጋገሪያ፣ ቁራጭ ንጣፎችን (ቁራጭ ምጣዶችን) ያዘጋጃሉ፡፡
ከቆርኪ አይበልጥም ስፋታቸው። ማይክሮቺፕ ይሏቸዋል፡፡ ረቀቅ ያሉት ደግሞ፣ “ማይክሮፕሮሰሰር”። (በአራት ማዕዘን ተቆርጠው የተዘጋጁ ንጣፎች (ምጣዶች) ላይ  ነው፣ ትራንዚስተሮች የሚታተሙት፡፡
አሁን ልብ በሉ።
እስካሁን፤ የንጣፎቹን ስፋት ለማሳደግ የሚያስችል ቴክኖሎጂ ብዙም አልተገኘም። “ጨዋታው” ምንድነው? ከአውራጣት ጥፍር ብዙም በማትበልጥ ምጣድ ላይ፣ ስንት “ትራንዚተሮችን” መጋገር ወይም ማተም ይቻላል? ይሄ ነው ፈተናው፡፡ ይሄ ነው ተዓምረኛው ውጤትና ወርቃማው ስኬት። (ከአሸዋ የተሰራ ተዓምር በሉት። የትሪሊዮን ዶላር ኩባንያዎች፣ ማይክሮሶፍት፣ ጉግል፣ አፕል፣ አማዞን፣… የዚህ ተአምር ተወላጅና ተሳታፊ ናቸው።
የዛሬ 50 ዓመት ገደማ፤ በአንድ ቁራጭ ላይ ስንት ትራንዚስተሮችን ማተም እንደተቻለ እናስታውስ።  ከ2000 እስከ 5000 ብቻ።
የዛሬ 40 ዓመትስ? ከ50 ሺ በላይ፡፡
የዛሬ 30 ዓመትስ?  ያኔ ነው፣ ከ1 ሚሊዮን በላይ ትራንዚስተር የያዘ ማይክሮፕሮሰሰር የተሰራው፡፡
የዛሬ 20 ዓመትስ? 100 ሚሊዮን ትራንዚስተሮችን ወደማተም ተደረሰ።
ዛሬስ? ከ10 ቢሊዮን እስከ 50 ቢሊዮን ትራንዚተሮችን ለማተም የሚያስችሉ፣ አዳዲስ ፈጠራዎች መጥተዋል፡፡
በሃምሳ ዓመት ልዩነት፤ ቴክኖሎጂው፣ ሚሊዮን እጥፍ ተራቅቋል፡፡ ከዚያም በላይ ነው እንጂ፡፡ ከ5 ሺ ወደ 50 ቢሊዮን መጥቋል - የትራንዚስተሮች ቁጥር። በዚያችው ቅንጣት ምጣድ፣ ከአውራጣት ጥፍር ብዙም በማትበልጥ ቁራጭ ንጣፍ፡፡
ይሄ፤ ከተዓምር የሚልቅ ድንቅ ክስተት ነው። የኮምፒዩተር፣ የሞባይል፣ የኢንተርኔት፣…. የዲጅታል ቴክኖሎጂ ሁሉ አስኳል ይሄው ነው። ለምን ቢባል? “የማይክሮፕሮሰሰር” አቅም ማለት፣ የዲጅታል ቴክኖሎጂ አቅም ማለት ነው። የኮምፒዩተርና የሞባይል ዘር ሁሉ አቅም፣ ስረ-መሰረቱ ይሄው ነው። “በቁራጭ ዲጂታል ምጣድ ላይ ስንት ትራንዚተሮችን ማተም ይቻላል?” የሚል ሆኗል ቁልፉ ጥያቄ።
በእርግጥ ሌሎች በርካታ ተሳቢዎች ይኖራሉ። የንጥረ ነገሮች መረጣና ቅመማ፣ የኤሌክትሪክ ጥንቅሩና ንድፉ… ቴክኖሎጂው፣ የብዙ መላ፣ የብዙ ፈጠራ ሱታፌ እንደሆነ አያጠራጥርም። እንዲያም ሆኖ፣ የዲጅታል ቴክኖሎጂ ልቡ ማይክሮፕሮሰሰር ነው - ከቆርኪ የማይበልጥ የጥበብ ውጤት። ስንት ትራንዚተሮችን ይዟል የሚለው ጥያቄ ደግሞ የልቡ ልብ ነው። በሌላ አነጋገር፣ የኮምፒዩተር ቴክኖሎጂ፣ የዚያኑ ያህል ነው የሚራመደው፡፡
እናም፣ በ50 ዓመት ውስጥ ከሚሊዮን እጥፍ በላይ ተመነደገ፡፡
በእርግጥ፣ ሁሉም ነገር እንዲህ አይፈጥንም።
የእህል ምርት፣ በ50 ዓመት ውስጥ ሶስት ወይም አራት እጥፍ ብቻ ነው ያደገው፡፡ ግን ቀላል አይደለም፡፡ 10 ቢሊዮን ኩንታል የእህል ምርት፣ ወደ 30 ቢሊዮን ኩንታል ሲጨምር፣ ትልቅ ለውጥ ነው። ወደ ጥጋብ ዘመን የተቃረበ ነው።
በሌላ በኩል ግን፣ ከዚህ የፈጠኑ ወርቃማ የሰው ጥበቦችና የስኬት ግስጋሴዎች አሉ።
አሳዛኙ  ነገር፣ እየዛገ፣ በዝግመት የመፍረስ ጉዞም አለ።
ተጠፋፍተው ተፈረካክሰው፣ አፈር ለመሆን የሚቸኩሉና የሚፈጥኑም ሞልተዋል።
በዝግታም ሆነ በጥድፊያ፣ ከብረት ወደ ዝገት፣ ከወርቅ ወደ አመድ ያመራሉ። በአላዋቂነትና በየዋህነት፤ አልያም፣ በጠማማ የጥፋትና የክፋት መንገድ፣ ነባር ወርቃማ ስኬቶችን ያፈርሳሉ።
የእውቀትና የጥበብ ሰዎች ግን፣ በቀና መንገድ፣ አፈርን ወደ ወርቅ ይለውጣሉ።
ከመድቀቅ መራቀቅ፣ ከዝገት ብረት፣ ከአመድ ወርቅ።
የዓለምን ዳርቻ ያቀራረቡ፣ የሰውንም አድማስ ያስፋፉ፣…
ዓለምን የሚያፈኩና በብርሃን የሚያደምቁ፣ የሰውንም ሃይል የሚያበረክቱ…
ዓለምን የሚያሾሩና የሰውንም እርምጃ የሚያፈጥኑ ወርቃማ ተዓምሮች በሙሉ፣… ግሩም ድንቅ ናቸው - ባሰብናቸው ቁጥር የሚያስደምሙ።
ግን ደግሞ፣ ከተራ አፈርና አሸዋ፣ ከባዶ  አየርና ከብናኝ እንፋሎት፣ ከተራ ውሃና ከጥቀርሻ ፈሳሽ የመጡ ናቸው። ወደ ወርቅ የቀየራቸው፤ ጥበበኛ የሰው እጅ ነው።
የሕንፃው የድልድዩ ብረታብረትና ሲሚንቶ ከየት መጡ? ከተራ አፈርና አለት፣ በሰው ጥበብ የተፈጠሩ ናቸው። በእሳት ጠብሶና ፈጭቶ፣ ወይም አቅልጦና አጣርቶ፣ በቀመርና በስሌት፣ ቀምሞና አዋህዶ ያበጃቸው ናቸው።
የብረት ማዕድን፣ ከተወሰነ የከሰል ድንጋይ ጋር፣ በተመጠነ ሙቀት ተዋህዶ፣ በተለካ መንገድ ሲቀዘቅዝ ተዓምር ይወለዳል። ለግንባታ አገልግሎት የሚውለው የብረት ዓይነት ይፈጠራል - Steel የተሰኘው። አለበለዚያ፣ ሰማይ ጠቀስ ህንፃ አይታሰብም። የጄት ሞተር አይፈጠርም።
በነዳጅ ሃይል ወይም በግድብ ወራጅ ውሃ አማካኝነት የሚሽከረከሩ  የመዳብ ሽቦዎች ናቸው - ኤሌክትሪክን የሚያመነጩት። በረዥም ርቀት፣ ኤሌክትሪክ ለማስተላለፍ የሚጠቅሙ ትራንስፎርመሮችም፣ የመዳብ ሽቦዎች ሹርባ ናቸው። በብረታ ብረት አስኳል የተጠመጠሙ፣ በብረታ ብረት ቀፎ የተቀነበቡ። መዳቡም ብረቱም፤ ከአፈር ከአለት ተጣርቶ፣ ቀልጦ፣ ነጥሮና ተቀርጾ የተሰራ ነው - በሰው እጅ።
አውሮፕላኑ፣ መርከቡ፣ ባቡሩ፣ መኪናው ሁሉ ከብረታ ብረት የተሰሩ ናቸው። ነዳጅን፣ ከአየር ጋር በተመጠነ መንገድ በማንደድ ነው የሚንቀሳቀሱት።
በምኒልክ ዘመን፣ ከኢትዮጵያ ወደ ጅቡቲ የተዘረጋውን የባቡር መስመር፣ የያኔውን ወርቃማ ዓለም የሚያሳይ  አንድ ምሳሌ ነው።
በ1830 ዓ.ም፣ ከእንግሊዝ ወደ አሜሪካ የተጓዙ የመጀመሪያዎቹ ባለሞተር መርከቦችም፣ ያንን ወርቃማ ታሪክ ይመሰክራሉ። 40 ቀን ይፈጅ የነበረውን የአትላንቲክ ውቅያኖስ ጉዞ፣ ከ16 ቀን ባነሰ ጊዜ ማጠናቀቅ ችለዋል። ጉዞውን ከእጥፍ በላይ አፈጠኑት። ወይም ርቀቱን ከግማሽ በላይ አሳጠሩት ማለት ይቻላል። ቴክኖሎጂው በዚያው አልቀረም።
በ1900 ዓ.ም፣ ከለንደን ወደ ኒውዮርክ በ5 ቀን የሚያደርስ መርከብ ተሰርቷል።
በ1945 ዓ.ም ደግሞ፣ የመርከብ ጉዞው፣ የሦስት ቀን ተኩል ጉዞ ሆኗል።
ወርቃማውን ታሪክ የሚያፈጥን፣ ሌላ ወርቃማ ስኬት የመጣው፣ በጄት አውሮፕላኖች ነው። በ1950 ዓ.ም፣ ቦይንግ 707 አውሮፕላን፣ መንገደኞችን  በ8 ሰዓት አትላንቲክን በማሻገር፣ አዲስ ታሪክ አስመዝግቧል። ዛሬስ?
ዘመናዊው ቦይንግ 787፣ በሰባት ሰዓት ተኩል፣ ከለንደን ወደ ኒውዮርክ ያደርሳል። በ70 ዓመት ውስጥ የተመዘገበው የፍጥነት እድገት፣ ብዙ አይመስልም። የግማሽ ሰዓት ነው ለውጡ። ነገር ግን ከ200 ዓመት በፊት፣ የ40 ቀን ጉዞ እንደነበር አትርሱ።
የባቡር ፍርጎ፣ ምሽግ ሆነ። ሃዲዱም ቀልጦ ጥይት ማምረቻ።
ዘኢኮኖሚስት መጽሔት፣ በሰሞኑ የገና በዓል እትሙ ያቀረበው አስገራሚ ትረካ አለ። የባቡር መስመር ወርቃማ የግንባታ ዘመንን ያስታውሳል። ግን፣ የሸክላ እና የዝገት ዘመንንም ያሳያል - የፍርስራሽ ዘመንን። ታሪኩ፤ ከ1900 ዓ.ም እስከ ዛሬ ድረስ ይዘልቃል።
የአፍሪካ፣ የአውሮፓና የመካከለኛው ምስራቅ አገራት፣ በጥቂት አመታት ውስጥ ነበር፤ በባቡር መስመሮች የተገናኙት፤ የተቀራረቡት።
ከጀርመን እስከ ኢራቅ፣ ከእንግሊዝ እስከ ሶሪያ፣ ከሳውዲ አረቢያ እስከ ቱርክ፣ ከኢራን እስከ ሊባኖስ፣ ከፍልስጥኤምና ከእስራኤል እስከ ግብፅ፣… ወደ ሱዳን ካርቱም፣ ወደ ቱኒዚያና ሊቢያም፣ ሞሮኮና አልጀሪያም፣… የግንባታው ውጤት አጃኢብ ነው። የወራትና የሳምንታት ጉዞዎችን፣ ወደ ጥቂት ሰዓታት፣ ያሳጥራል።
ቁርስ፣ በእስራኤል እና በፍልስጥኤም ነው - ሃይፋ እና ጋዛ ላይ። ምሳ ግን ካይሮ ላይ። እራት ደግሞ ካርቱም ላይ?…
ቢበዛ ደግሞ የ 3 ቀን ምቹ ጉዞ ይሆናል - ያለ ድካም ያለ አቧራ። “ከእንግሊዝ ወደ ሶሪያ በሦስት ቀን ብቻ!”
ይሄ፣ የያኔው ማማለያ ማስታወቂያ ነው። ድንቅ ነው።
አህጉራትን ያገናኘው ድንቅ የባቡር አውታር፣ ለማመን የሚከብድ አዲስ ታሪክ ነበር - ያኔ በዘመኑ።
አሳዛኝ ገፅታም አለው።
ያንን ታሪክ የሚሰሙ ብዙ የዛሬ ሰዎች፣ ታሪኩን ለማመን ይቸገራሉ። ለምን እንበል።
ዛሬ፣ የባቡር መስመሮቹ የሉም። ፈራርሰዋል፤ ተነቃቅለዋል፤ በአሸዋ ተቀብረዋል።
አንዳንዶቹ የብረት ፉርጎዎች፣ የምሽግ ማጠናከሪያ ሆነዋል።
የባቡር መስመር ሃዲዶች እየተነቀሉና እየቀለጡ፣ ጥይት ተሰርቶባቸዋል።
ዛሬ ከአንድ አገር ወደ ሌላ የሚሻገር የባቡር ጉዞ የለም።
ከሶሪያ አሌፓ ከተማ፣ ወደ ቱርክ የሚመላለስ የባቡር አገልግሎት፣ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ፣ በእንፉቅቅ እየሰራ ነበር። ጦርነቱ መጣና ይሄው መስመርም አለቀለት።  የአሌፓ የባቡር ጣቢያ፣ የጦር ካምፕ ሆኗል፡፡
ብረታ ብረቱ እየዛገ ወደ አፈርነት ተለውጧል። ወደ አፈር ተመልሷል።
ምናለፋችሁ። ባለፉት 80 ዓመታት ውስጥ፣ በዘመናችን እስከተከሰተው የሶሪያ ጦርነትና ትርምስ ድረስ፣ የባቡር አገልግሎቶችና መስመሮች፣ ቀስ በቀስ እየተቋረጡ፣ እያረጁ፣ እየዛጉ፣ እየፈረሱ ነው ሲያዘግሙ የቆዩት - ወደ ዘገምተኛ ውድቀት።
አንዳንዴ ደግሞ፣ በድንገት ይወድማሉ። አመጽና አምባገነንነት በበረከተበት አካባቢ፣ ጦርነትና ውድመት፣ በእልፍ ሰበብ ይከሰታል።
ጎረቤት አገራት ሲጣሉ፣ የባቡር መስመሩ ድንገት ተቋርጦ፣ በዚያው ይሞታል። በአሸዋ ተቀብሮ ይቀራል። ኢራንን ከኢራቅ፣ ሞሮኮን ከአልጀሪያ፣ ግብፅን ከእስራኤልና ፍልስጥኤም የሚያገናኙ አውታሮች፤… በድንገት ታሪካቸው ተበጥሷል። ሌላም አለ።
አንዱ አማፂ ቡድን፣ 60 የባቡር ድልድይ በማፍረስ ይፎክራል። ሌላ ተቀናቃኝ ቡድን ደግሞ፣ በ1 ሰዓት ውስጥ፣ ከ60  በላይ ድልድዮችን በማፈንዳት፣ አዲስ “ሪከርድ” ያስመዘግባል። ሲመቸውም፣ የባቡር ጣቢያዎች ላይ ይዘምታል።
“አፍራሽ የዝገት ዘመን ነው” ቢባል አልተጋነነም።
ወርቃማው ወይም ብርማው ስኬት፣ ትንሽ እየቆየ ወደ ነሃስና መዳብ ብቻ፣ ቀጥሎም ወደ ብረት ብቻ፤ ከዚያም ወደ ሸክላ ብቻ፣ እያነሰ እየወረደ ከመጣ፣ ከፍፃሜው አይተርፍም። ፍርስራሽ አፈርና አቧራ መሆን አይቀርለትም።
የኢትዮጵያ የባቡር መስመር፣ ከወርቃማ የስኬት ዘመን፣ ቀስ በቀስ ወደ ውድቀት ለማዝገም ስንት አመት እንደፈጀ ማሰብ ትችላላችሁ። የመንገደኞች አገልግሎቱ ተስተጓጎለ፣ ከዚያም ሙሉ ለሙሉ ተቋረጠ። የጭነት ጉዞው፣ እያሰለሰ እያነከሰ፣ ለማገገምም ለማንሰራራት የማይችልበት ውድቀት ላይ ደረሰ።
እንደገና ወደ ባቡር መስመር ግንባታ ለመመለስ ስንት ዓመት ፈጀ? ምዕተ ዓመት።

Read 1547 times