Print this page
Saturday, 25 December 2021 13:11

ከፌስቡክ ገጾች በጨረፍታ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

    ቁራ አሞራ አንሁን!

            (ለአማራ ህዝባዊ ኃይል1 ልዩ ኃይል፣ ፖሊስ፣ ፋኖና ሚሊሻ)
                    ዘላለም ጥላሁን


             ደማችሁን አፍሳችሁ፣ አጥንታችሁን ከስክሳችሁ፣ ውድ ነፍሳችሁን ሰጣችሁ ለከፈላችሁት ዋጋ በግሌ ታላቅ ክብር አለኝ። ዝቅ ብዬም አመሰግናለሁ።
ነገር ግን ጦርነቱ ገና ተጀመረ እንጂ አላለቀም።  መጪው ከባድና ውስብስብ ነው። ህውሃትም ቢሆን ከአማራ ክልል ገና ጠቅልሎ አልወጣም። የወጣው ኃይልም ተከዜ ዙሪያ እየተሰባሰበ ለሌላ ጦርነት ከፍተኛ ዝግጅት እያደረገ ነው።  ከወደ ጎንደርና ዋግ አካባቢ በነበረኝ ውይይት የተረዳሁት ይሄን ነው። የተከዜ ተፋሰስና የተንቤንን ተራሮች ተከትሎ ህውሃት ዝግጅት እያደረገ ነው። ከቻለ ወደ ሰሜን ጎንደር፣ ካልቻለ ግን የሁመራን መስመር ለመስበር የመጨረሻውን እስትንፋስ እያሰባሰበ ነው-ህውሃት። ድርድሩና ታንቲራው ማዘናጊያ ነው። ህውሃት በውጊያ እንጂ በጦርነት ገና አልተሸነፈም። ወደ ጋይንትና ደብረሲና ሊመለስ የሚችልበት እድል ዜሮ ፐርሰንት እስኪሆን ድረስ ከፍተኛ ዝግጅትና ስራ ይፈልጋል።
ሌላው ቀጣዩ የኢትዮጵያ ፖለቲካና የምስራቅ አፍሪካ ጂኦፖለቲክስ ውስብስብና ብዙ እጆች የሚንቦጫረቁበት የእድር ጠላ ነው። የአማራ ህዝባዊ ኃይል ከዚህ አንፃር ነገን በዛሬ መነፀር መመልከት ግድ ይለዋል። ከስሜት ወደ ስክነት መዞር አለበት።
በትንሽ ድል መስከር ድልን ያሳጣል። አንድ የቁራ ተረት ልንገራችሁ።
 “በአንድ ወቅት ቀበሮ ግዳይ ጥላ እየበላች ነበር። በአጋጣሚ ዞር ስትል ቁራ አሞራ ነጠቃት። በጣም ተናደደች። ቁራም ወደ ዛፍ ላጥ ብሎ ወጣ። ቀበሮ ንዴቷን ተቆጣጥራ መላ ዘየደች። “ቁራ ሆይ እኔ እኮ በጣም አደንቅሃለሁ። ወይ ድምፅህ ሲያምር። በእናትህ አንዴ ብቻ ጩህልኝ”አለችው። ቁራም በሀሴት ሰከረ። ደስ አለው። ከዚያም ጮኸ። ሲጮህ በአፉ የያዘው ሙዳ ወደቀ። ቀበሮም በዘዴ ግዳዩን አገኘች”
ስለዚህ ቁራ አሞራ ሳይሆን ቀበሮ እንሁን። በስሜት የምንጮህ፣ በትንሽ ነገር መሰረታዊውን ነገር የምንረሳ ቅርብ አዳሪ አንሁን። ከዛሬ እንሻገር። ነገን ብቻ ሳይሆን ብዙ ነገዎችን እናስብ። ለአማራው ለኢትዮጵያም ነገን አስቦ መስራት ይጠቅማል።  የአማራ የህዝብ ኃይል ማዕበሉን ጠብቆ፣ ነገን በተስፋ ሰንቆ በጀመረው መንገድ መሄድ አለበት። መከላከያና ልዩ ኃይልን በቻለው መጠን ማጠናከር አለበት። ህዝብን የማንቃት፣ የወጣት አደረጃጀቶችን የማጠናከር፣ ፋኖን የማደራጀት ስራውን መቀጠል አለበት። ነገር ግን ቅድሚያ ለመከላከያ መስጠት ጥቅሙ እጥፍ ድርብ ነው።
ከዚህ ባለፈ ውሃ በቀጠነ ከተማውን በተኩስ ማናወጥ ከቁራ ያለፈ ውጤት አይኖረውም። በቢሊዮን የተዘረፈ ሀብት ሳይመለስ፣ የእህትና እናቶች እምባ ሳይታበስ፣ ጠላት ለሌላ ጥቃት እየተዘጋጀ፣ በድል ተኩስ ከተማውን ማናወጥ ከትናንት አለመማር ነው። ከቻላችሁ ቀበሮ ሁኑ። እንደ ቁራ ሳጮሁ፣ እንደ ቀበሮ ዘዴኛ ሁናችሁ የነገውን የቤት ስራ፣ ውስጥ ለውስጥ ስሩ።
 ቁራ አትሁኑ!️
______________________________________


    ኑ ቀብዳችሁን ውሰዱ፤ ለአሸባሪውም አጥልቁለት
        በድሉ ዋቅጅራ

              የምእራባውያን የብዙሀን መገናኛዎች፣ አልጃዚራንም ጨምሮ የጠ/ሚንስትራችንን ወደ ግንባር መዝመት ‹‹የኖቤል ሽልማት አሸናፊው...›› በሚል አሹዋፊ ቅጽል አጅበው ዘገቡት፡፡
ለመሆኑ የሱዳንን ተቀናቃኞች አስማምቶ ሰላም ስላወረደ፣ ከኤርትራ እርቅ አውርዶ የሀያ አመት ባላንጣነትን ስለፋቀ፣ ደቡብ ሱዳንን ስላሸማገለ፣ ለአስርታት በስደት የቆዩ ተቃዋሚዎችን ያለ ቅድመ ሁኔታ ወደ ሀገራቸው ያስገባ፣ ዛሬ ሀገር ለማፍረስ የሰይጣን ፋስ ይዘው ያገኙትን የሚቆርጡ የህወሀት የሀያ ሰባት አመት መሪዎች በይቅርታ የዘረፉትን እንዲበሉ የፈቀደ፣ . . . ለዚህ አይደለምን ጠ/ሚንስትራችን ኖቤል የተሸለመው?
ለካ ኖቤሉ የሰላም ስራ ማረጋገጫ ሳይሆን፣ የቅኝ ግዛት ቀብድ ነበር። አዎ፣ መሪያችን ‹‹ለምእራባውያን ተላላኪ አልሆንም›› ሲል ለምእራባውያኑ እርግብነቱ አበቃ፣ ቁራ አደረጉት፤ የወይራ ዝንጣፊውን ወስደው ነፍጥ አስነክሰው ሳሉት፡፡ ወይራውን እሳት ለሚተፋው የህወሀት ሰይጣናዊ ድራጎን አስነከሱት፤ ተቃጠለ፤ ከሲኦል አመድ ተቀላቀለ፡፡
.ህወሀት በምንም መንገድ በመንግስትነት ወይም በሰው ሚዛን ሊቀመጥ አይችልም፡፡ በኢትዮጵያ ታሪክ እንደ ህወሀት የሚጠላትን ሀገር የመራ መንግስት የለም፤ ይኖራልም ብዬ አላስብም፡፡ መንግስት ሆኖ፣ ሀገሩን የ1000 ኪ.ሜ የባህር በር የነፈገ፣ ከ300 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር በላይ የዘረፈ፣ ህዝቦችን በእኩልነት ስም በብሄር ከፋፍሎ ለማፍረስ ህልሙ እርሾ ያስቀመጠ፣ አሸባሪ ሽፍታ ሆኖ ሲጠብቀው በኖረ ሰራዊት ላይ ጭፍጨፋ የፈጸመ፣ በተቀማው ለም መሬት እየተንገበገበ ከመኖር በቀር ለበቀል ያልተነሳው የአማራ ህዝብ ላይ አሰቃቂ እልቂትና ሰይጣናዊ ውድመት ያካሄደ፣ የአፋር ህዝብን የጨፈጨፈ፣ በመላው ሀገሪቱ የተካሄዱ የብሄር ግጭቶችን አቅዶ ያስፈጸመ፣ . . .  ወዘተ.  ይህ አሸባሪ ቡድን ዛሬ ለምእራባውያኑ ሰላማዊ እርግብ ነው፤ ህዝብ ባይኖረውም መንግስት ሊያደርጉት ተነስተዋል፡፡
አዎ! ጠ/ሚንስትሩ ኖቤል አይገባውም ነበር፡፡ ለአሜሪካ ፈቃድና ድርጎ የማያረግድ፣ ለግዳጃቸው የማይዘምት፣ በጦርነታቸው የማይሞት፣ አሸባሪ አሽከራቸውን በተባባሪ ባንዳዎች ሴራ ሸዋ ሮቢት ሲያደርሱት በመደራደር ወይም ሀገር ጥሎ በመፈርጠጥ ፋንታ ሊዋጋ የሚዘምት፣ እንዴት ለዚህ ሰው የምእራባውያን የቅኝ ግዛት ቀብድ፣ የኖቤል ሽልማት ይገባዋል? አይገባውም።
እና፣ እባካችሁ ኑ ቀብዳችሁን ውሰዱ፤ ለህወሀትም አጥልቁለት፡፡

__________________________________________________

  አገዋ እንዳይጎዳን
                           ሙሼ ሰሙ

           የባይደን አስተዳደር ለኢትዮጵያ ተፈቅዶ የነበረውን የአገዋ ከቀረጥ ነጻ ተጠቃሚነት ሰርዟል፡፡ እ.ኤ.አ በ2020 ኢትዮጵያ ከቀረጥ ነጻ የጨርቃ ጨርቅና የቆዳ ውጤቶችን ወደ አሜሪካ በመላክ 238 ሚሊየን ዶላር አግኝታለች፡፡ ይህ ማለት ከአጠቃላይ የሀገራችን ኤክስፖርት ውስጥ 7% ገደማ ሲሆን ወደ አሜሪካ ከምንልከው 525 ሚሊየን ዶላር ውስጥ 45.34 % ነው፡፡ በተቃራኒው አሜሪካ ወደ ኢትዮጵያ የምትልከው ምርት 868 ሚሊየን ዶላር የሚያወጣ ሲሆን የንግድ ሚዛኑ በ343 ሚሊየን ዶላር ወደ አሜሪካ ያጋደለ ነው፡፡
አሜሪካንን ከማማረር ይልቅ ከስራ ለሚሰናበተው በ100 ሺ የሚቆጠረው ሰራተኛ የስራ እድል ከመፍጠር ባሻገር ማዕቀቡ የሚያስከትለውን ጉዳት በመካከለኛና በረጅም ጊዜ ለማካካስ የሚያስችል አማራጭ እስክናገኝ ድረስ እቀባው በአጭር ጊዜ ሊደቅንብን የሚችለውን ፈተና እንዴት እንቋቋመው የሚለው ጥያቄ ዋነኛ መወያያችን መሆን አለበት፡፡
ለጊዜው ብዙ አማራጭ ያለን አይመስለኝም። ይህም ሆኖ፣ በመካከለኛ ጊዜ ሊሰሩ የሚችሉ አዳዲስ ገበያን የማፈላለግ፣ በረጅም ጊዜ ደግሞ የሚገነቡ የኤክሰፖርት አቅማችንን የማሳደግና በራስ አቅምና ምርት የመተማመን አማራጮች እስኪጎለብቱ ድረስ አንድ ሁለት ነገሮች ማመላከት ይቻላል፡፡
1) የውጭ ምንዛሬ አቅርቦቱን መሰረታዊ ለሚባሉ አቅርቦቶች ብቻ ማዋልና ጊዜያዊ ፍላጎቶቻችንን በመግታት የውጭ ምንዛሪ ፍጆታን መቆጠብ፡፡
2) ኤምባሲዎች፣ ቆንስላዎች፣ የተለያዩ የዲያስፖራ ኮሚኒቴዎችንና የኢትዮጵያ ተቆርቋሪ ማህበረሰቦችን በማስተባበር ከምንጊዜውም በላይ ገበያ የማፈላለጉን ስራ በስፋት፣ ተከታታይነት ባለው መንገድና በቁጭትና በተደራጀ መልኩ ማካሄድ፡፡
3) የኤክስፖርት ገበያው ላይ ያለውን ውስብስብ ችግር በጥናት ላይ ተመስርቶ መፍትሔ በመስጠትና በርካታ ዜጎች በኤክስፖርት ስራ፣ በተለያየ አቅምና የምርት አቅርቦት ሥራ ላይ እንዲሰማሩ የሚያበረታቱ የብድር፣ የታክስ፣ የቦታ አቅርቦትና ሌሎች የድጋፍና የማበረታቻ መንገዶችን ለአጭር ጊዜ በገደብ ማመቻቸት ሲሆን፤
ሌላውና መሰረታዊ ጉዳይ፤ እስካሁን 13 ሺ ከሚደርሱ ትውልደ ኢትዮጵያውያን 3 ሚሊየን ዶላር መሰባሰብ እንደተቻለ ተዘግቧል፡፡ ከአጠቃላይ የትውልደ ኢትዮጵያውያን ቁጥር አኳያ የፈቃደኞች ቁጥር ጥቂት ቢሆንም በነዚህ ጥቂት በጎ አሳቢ ዜጎች ተነሳሽነት ምክንያት ቀላል የማይባል ሀብት መሰብሰቡን መረዳት ይቻላል፡፡
አንዱ ችግሩ የማያቋርጥ የመዋጮ ጥያቄ መሆኑ ይመስለኛል (Donnior Fatigue)። መንግስት ይህንን አሰራር  በጊዜ ገደብ ወደ የሚመለስ የቦንድ ሽያጭ በማሳደግ የአንድ ዓመት የአጋዋ ኤክስፖርታችንን ያህል የውጭ ምንዛሪ በቀላሉ ማግኘት ይቻላል። በዘለቄታው የሚሰሩ ስራዎች መፍትሔ እስኪሰጡ ድርስ አንድ ሚሊየን ትውልደ ኢትዮጵያዊያን በማስተባበር እያንዳንዳቸው በአማካይ  500 ዶላር የሚያወጣና በተለያየ የግዢና የክፍያ ስርዓት የሚሰበሰብና ተመላሽ የሚሆን ቦንድ ቢገዙ፣ በአንድ ዓመት ውስጥ ከ500 ሚሊየን ዶላር በላይ ከዲያስፖራ በመበደር (Revolving Fund) የእፎይታ ጊዜ ማግኝት ይቻላል፡፡
የእፎይታ ጊዜው በሚሰጠው ትንፋሽ ውስጥ ሆነን ከላይ የቀረቡትን አማራጭ ስራዎች ያለማሰለስና በንቃት ከተሰራ በራስ አቅም የችግሩን ውስብስብነት ከመቀነስ ባሻገር አደጋውን እስከ መቀልበስ  የሚሻገር ዘላቂ ውጤት ማግኘት ይቻላል።

_______________________________________________


    "ለቀባሪው ማርዳት"
                 ጌታሁን ሄራሞ


           አሸባሪው ትህነግ በአማራና በአፋር ሕዝባችን ላይ ያደረሰው አደጋ በኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙሃን በየሰዓቱ እየተነገረን ነው። ሕዝብ የቡድኑን የክፋት ጥግ እንዲያውቀው መደረጉ መልካም ነው። ደግሞም “ሂሳብ አወራርዳለሁ” በሚል ዛቻ ወደ አካባቢዎቹ የዘለቀው ትህነግ ከዚህ የተለየ ተግባር ቢፈፅም ይደንቀን ነበር።
ትናንት ጌታቸው ረዳ “The Africa Report” ላይ የፃፈውን ተመለከትኩ። ትህነግን መልአክ ኢትዮጵያን ደግሞ ጭራቅ አድርጎአት እየሳለ ለምዕራባውያን በጥሩ እንግሊዝኛ በተባ ብዕሩ ከትቦላቸዋል።
በእኔ እምነት የኢትዮጵያ ሚዲያና የመንግስት ኮሚኒኬሽን ፅ/ቤቶች የትህነግን ገደብ የለሽ ጭካኔና የጄኖሳይድ ወንጀሎችን ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ለማጋለጥ ብዙ ርቀት የሄዱ አይመስለኝም። በእርግጥ ጉዳቱን ለዓለም አቀፍ ማህበረሰብና ተቋማት የሚያሳውቅ ኮሚቴ ተዋቅሯል ተብሎ ነበር፤ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎችም እንደተጋበዙ ተነግሮን ነበር። ከዚህ አንፃር የኢትዮጵያ መንግስት ምን ያህል ርቀት ሄዷል? ብቻ ግን ሳይንሳዊ ጥናት ገለመሌ እየተባለ አንድ ዓመት እንዳይፈጅ ስጋቱ አለኝ። ወያኔ እራሷ ጨፍጭፋ ፈጠን ብላ በዓለም አቀፉ መድረክ ተጨፈጨፍኩ ብላ እየጮኸች ነው። በመረጃው ዓለም ፍጥነት ወሳኝ ሚና አለው። እኛና ወያኔ ልዩነታችን እዚህ ላይ ነው...
ወያኔ ያለ የሌላ ክሷን ሪፖርት የምታደርገው ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ነው፤ እኛ ለትህነግ ወንጀል ሰፊ ሽፋን ሰጥተን ሪፖርት  የምናደርገው ለሀገሬው ሰው ነው...አንዱ ወዳጃችን እንደዚህ ዓይነቱን አዘጋገብ...”ለቀባሪው ማርዳት” በማለት ሰይሞታል።


Read 1782 times
Administrator

Latest from Administrator