Print this page
Saturday, 25 December 2021 13:24

ወጥቶ - አደር

Written by  ደረጀ ይመር
Rate this item
(1 Vote)

  የጎጇችን ዐይን ማረፊያ የሆነችው ክንብንቧ ራዲዮናችን፣ ሰንበት ማለዳ  ላይ ቆፈን ውስጥ የሚከት ወሬ ይዛ መጣች።  አባቴ የወሬው ፍሬ ነገር እንዳያመልጥው በአንክሮ እየተከታተለ ነው፡፡ ጋዜጠኛው በነጎድጓድ ድምጹ፣ ኃይለ ቃል የበዛበትን መግለጫ ያነበንባል፡፡ በየመግለጫው መሀል “ጎራው ናና” የሚል ስሜት ቀስቃሽ ሙዚቃ ይለቀቃል፡፡  
“የወራሪዎቹ ጦር ቀጠናውን እያሰፋ ወደ መዲናዋ እንደተቃረበ ነው፡፡ ስለሆነም፤ ያንዣበበውን አደጋ በጋራ ለመመከት  የአባት ጦረኞች ለዳግም ዘመቻ እንዲዘጋጁ፣ ከመንግሥት ትዕዛዝ ተላልፏል፡”  አለ ጋዜጠኛው በማሳረጊያው፡፡
“እነኚህን የጋኔል ፈረሶችን፣ ልክ ሳላሰገባማ ክንዴን አልንተራስም፤” አለ አባቴ፤ ከንፈሩን በቁጭት እየነከሰ።
አባቴ ለእናት ሀገሩ የሚሰስተው ነፍስ ኖሮት አያውቅም፡፡ በመጀመሪያው ዙር ዘመቻ ቆስሎ ነው የተመለሰው፡፡ ከግራ እግሩ ላይ በቀዶ ጥገና የወጣችው ጥይት፣ አረማመዱን አዛንፈዋለች፡፡ የበቀለባት የወሎ አፈር፣ ጀግንነትን ብቻ ሳይሆን ጥበብንም አድለዋለች፡፡ በተለይ፤ ከውሃው ከወሳሰደ  የጥበብ ሐድራው ይደራለታል፡፡
 ቦረና ቦረና ገነቴ፣
አብረኽረኽችኝ ገባች በጉልበቴ፤
እንግዲህ ቀንሽ  ነው አዋቂ አትጠይቂ፣
እንደው ዝም ብለሽ ቡርግድሽን ሙቂ፤
ስንኞቹን በአንደበቱ ሲያንቆረቁር፣ እንደ ኩታራ እየቦረቀ ነው፡፡ ፍንደቃው ኑሮ ባጣነናት ጎጃችን ላይ፣ አንዳች የቅለት ካራማን ያነግሳል፡፡
ከቀናት በኋላ
አንድ ሀሙስ የቀራት ሎንችን፣ የመንደራችንን አባት ጦረኞችን በከርሷ ሰብስባ ለመውሰድ ከቆመች ሰዓታት ነጉደዋል፡፡ አባቴ እየተንኳተተ ሎንችኗ ላይ ከመሰቀሉ በፊት፣ ዞር ብሎ እኔንና እናቴን በስንብት ፈገግታው ጎበኘን፡፡  የልጅነት አንጀቴ ሲላወስ ይሰማኛል፡፡ እንባ ያቆረዘዙ ዐይኖቼን፣ እናቴ በመዳፏ አበሰቻቸው፡፡ እንባው ለአባቴ እርም ማውጪያ እንደሆነ የገባኝ ነፍስ ባወቅሁ ጊዜ ነው፡፡
አባቴ የተፋለማቸው ጣውንቶች፣ አሁንም አላረፉም፡፡ ከደጃፌ አሰፍስፈው ቆመዋል፡፡ የአባት ውርስ ሆኖብኝ፤ እጅ መስጠት አልተማርኩም፡፡ በቀለም መግፋቴ ለባርነት ሸብርክ እንድል አላደረገኝም። ሐሞቴን ኮስተር አድርጌ፣ ለፍልሚያ መዘጋጀት እንዳለብኝ ወስኛለሁ፡፡ በቅድሚያ ግን የምሰናበታቸው የቀለም ልጆች አሉኝ፡፡
“ዛሬ እንደ ድግምት የማነበነበው፣ የአእምሮ ጓዝ ይዤላችሁ አልመጣሁም፡፡”  በእግሬ ሥር   የተኮለኮለውን ቀለም ቆጣሪ አንድ በአንድ ሰለልኩት፡፡
“ምን ይቀባጥራል?” የሚል ተግሳጽ ያረገዘ ገጽታን፣ ቀለም ቆጣሪው በምላሹ ለአውደ ርዕይ አቀረበልኝ፡፡
“ከባርነት ምቾት ....የነጻነት እንግልት ይመረጣል” መፈክር ቢጤ አሰማሁ እና የመልእክቱን  አሻራ ነጩ ሰሌዳ ለይ አተምኩት፡፡
“መምህር እንደየሰዉ  ይለያያል፡፡ “ አለ አንድ ቀጥረ ቀላል ተማሪ
መልስ ሳልሰጥ ማብራሪያውን ቀጠልኩ፡፡
“ባርነት አሳሳች ነው ጎበዝ፡፡ ጊዜያዊ ሙቀት ይለግሳል፡፡ ልክ እንደ እንቅራሪቷ ማለት ነው፡፡ እንቁራሪቷ እስከ 99 ዲግሪ ሴንትግሬድ ድረስ፣ በውሃ ሙቀት እየተዝናናች ትቆያለች፡፡ ሙቀቱ ዘላለማዊ ይመስላታል፡፡ በቀሪዋ 1 ዲግሪ ሴንትግሬድ ያደፈጠውን ሞት አታስተውለውም፡፡ መቶኛ ዲግሪ ሴንትግሪድ ላይ ስትደርስ፣ ሁሉም ነገር ያከትማል፡፡ ባርነትም አሳስቆ የሚወስደው እንዲህ ነው፡፡ በነፍስ መቃብር ላይ የሥጋ አበባ ያኖራል፡፡”
ተማሪው በሙሉ ስሜቱ ቀዝቅዟል፡፡ ኦና ቤት የምለፈልፍ መሰለኝ፡፡ ትንሽ መነቃቃት ለመፍጠር ስንኝ ቢጤ ደረደርኩኝ፤
በሥጋ አበባ ባርነት ለምድ ለብሶ፣  
ነፍስ ግዞት ወርዳ በቁም አጎንብሶ፣
ይኽን ኑሮ ብሎ ውዳሴ ከመድገም፣
የጀግና ሞት ሞቶ አለምን መለጎም፤
“ከዚህ በላይ አለፍፍም ጎበዝ፡፡ ነገ ከጀግኖቹ አምባ ቀጠሮ አለብኝ፡፡ ባርነትን በሞቴ ላሸነፍ፤ ልክ አንደ አባቴ ከባላንጣዎቼ ጋር በጦር ሜዳ ልተናነቅ ነው፡፡ ነጻነቱን የሚሻ፣ አንድም ሰው ቢሆን ይከተለኝ።” አልኩኝ እና  መማሪያ  ክፍሉን በጥድፊያ ትቼ ወጣሁ፡፡
***
የባርነትን ግዳይን ለመጣል ከተመሙ ወጥቶ አደሮች መሀል በክብር ተገኝቻለሁ፡፡  አሁን የተኩስ ድምጽ ከመለማመዴ የተነሳ፣ አንደ ሞባይል ጥሪ እየቆጠርኩት ነው፡፡ በአውደ ውጊያው የተሰለፈው ጀግና፣ ስቆ ነው ይህቺን አለም የሚሰናበተው፡፡ ወጥቶ አደር፣ ሞትን መናቅ ያስተምረሃል፡፡ ሞትን ከናቀህ ሌላው ዕዳው ገብስ ነው፡፡
ጥቂት አውደ ውጊያዎችን ከተሳተፍኩ በኋላ፣ ዘማች አንቂ የሚል ማእረግ ተጫነብኝ፡፡  የጥይት እርሳስ ብቻ ሳይሆን፣ ጥይት ሐሳብም ለማስወንጨፍ በደጀንነት ተሰለፍኩ፡፡
ሕይወት በዚች ሰዐት ስቃልኛለች፡፡ ኮቾሮ እየበላሁ፣ አፈር ላይ እየተንከባለለኩ፣ አይቼ የማላቀው ደስታን መጎናጸፍ ጀምሬያለሁ፡፡ ለካስ የመንፈስ ልምላሜ፣ የሥጋ ጉስቁልናን ያስዘነጋል፡፡

Read 1138 times