Saturday, 25 December 2021 13:27

የ‹‹ወደኋላ›› ረጅም ልቦለድ የጭብጥ ትንተና

Written by  ከአንለይ ጥላሁን ምትኩ
Rate this item
(3 votes)

     ርዕስ= ወደኋላ
ዘውግ=ረጅም ልቦለድ
ደራሲ=ሊዲያ ተስፋዬ
ማተሚያ=ሜጋ ማተሚያ ኃ.የተ.የግ.ማህበር
የገጽ ብዛት= 174
ዋጋ=120 ብር( USD 10)

ጭብጥ በልቦለድ ውስጥ ሊተላለፍ የተፈለገው መልዕክት ነው፡፡ ‹‹ማንኛውም ልቦለድ የሚፃፍበት አይነተኛ ዓላማ አለው። ይህ ዓላማው በታሪኩ ሂደት፣ በገፀባህሪያቱ ህይወትና በመካከላቸው ባሉ እርስበርሳዊ ግንኙነቶች ውስጥ እሚፈስ ሲሆን አንድ አይነት ማህበራዊ ጉዳይ ወይም ቁምነገር ይዞ እሚነሳ ነው፡፡›› (ዘሪሁን አስፋው፣ገፅ 185) በህይወት ገጠመኝ አማካኝነት ዳብሮ የወጣ (የተንጸባረቀ) ማዕከላዊ ነጥብ ነው፡፡
‹‹ወደኋላ›› ረጅም ልቦለድ ሶስት መሰረታዊ ጭብጥ አለው፡፡ እነዚህን ጭብጦች ለመለየት የዋና ገጸባህሪዋን አመለካክት፣ ድርጊት፣ ስሜት እና እምነት (ጽኑ አቋም) በመፈተሽ መተንተንና መፈከር ላይ የተመሰረተ ነው፡፡ ማለትም ከሌሎች ገጸባህሪዎች ጋር ያላትን አቀራረብ፣ ንግግር፣ ገለፃ ወይም ግንኙነት ሊያሳዩ የሚችሉ ጉዳዮች እንፈክራለን፡፡ ይህንንም የምናደርገው የታሪኩ ባለቤትና ተራኪ ራሷ በመሆኗ ነው፡፡
የልቦለዱ ጭብጦች ፡-   ሀ. የዓላማ ፅናት፣
ለ. የርዕይ መነጠቅ (ስኬት አልባነት) እና
ሐ. አባዊ ስርዓት (የወንዶች ዓለም) ናቸው፡፡
ከላይ የተጠቀሱት መሰረታዊ ጭብጦችን ከልቦለዱ የተለያዩ ምዕራፎች የሚስማማቸውን እየጠቀስን እንተንትን፡፡                      
ሀ. የዓላማ ፅናት
ዓላማን ከግብ ለማድረስ ተከታታይነት ያለው ትግበራ፣ ግላዊ ውሳኔ እና ፅናት ይጠይቃል፡፡ ቆራጥ ውሳኔ ደግሞ ከጠራ ግብ ይመነጫል፡፡ ስለሆነም ‹‹ሶፊያ›› ለራሷ ያላት ግምት እጅግ ከፍ ያለ ነው፡፡ ሁሉንም ነገር በራሷ ማከናወን እንደምትችል የምታምን ጠንካራ አቋም ያላት ናት፡፡ ስለሆነም ብዙ ዋጋ ከፍላለች፡፡ በዚህ ጥንካሬዋ ራስን ችሎ መቆም እንደሚቻል ለመመስከር የተሳለች ሆና አግኝቻታለሁ፡፡ ከምትወደው የትዳር አጋሯ የተለያዩ ጫናዎች ደርሰውባታል፡፡ ለአብነትም፡-
‹‹አንተ ነህ አይደል የቀደድኸው?››
‹‹እና…››
ፋሲል ምንም ድንጋጤ አይታይበትም፡፡
‹‹ወረቀት ብቻ የቀደድክ እንዳይመስልህ… እኔንም ነው!››
… ነደድሁ…
የምተነፍሰው አየር አጠረኝ፡፡
‹‹በእኔና በአንቺ መሃል ከገባ እንኳን ወረቀት ሰውም ቢሆን ዕጣ ፈንታው ይኸው ነው!›› አለ በትክክለኛ ስሜት፡፡ (ገፅ 10)
የፋሲል ተፅዕኖ የህይወት ዓላማ ብላ የተሰማራችበት ነገር ላይ በመሆኑ ትዳሯን በአይነቁራኛ እንድትመለከተው አስገድዷታል፡፡ ሰዎችን የመርዳትና የማብቃት ፍላጎት ስለነበራት ድጋፍ ለሚያደርግ ድርጅት የሰራችውን ጥናታዊ ፅሁፍ ነው ቆሻሻ ገንዳ ውስጥ ቦጫጭቆ የጣለባት፡፡ ሆኖም ግን ሶፊያ ጉዳዩን ከባሏ አንፃር እንጂ ከራሷ ጋር አታገናኘውም። ለምን ሊረዳት እንዳልቻለም ደጋግማ ታስባለች፡፡ አልፎ ተርፎም ምንም ነገር እንደሌላትና የጓዳ ሃላፊነቷን ብቻ እንድትወጣ አስጠንቅቋታል፡፡
‹‹የአንቺ ኃላፊነት ቤት ውስጥ የሚያስፈልገንን ነገር ማዘጋጀት ነው፡፡ ገብቶሻል?››
‹‹መሆን የምፈልገውን መሆን የእኔ ውሳኔ መሰለኝ›› አልሁ ጫን አድርጌ
በእምነቷ ፀንታ በመቆም ለማስረዳት ብትሞክርም፣ ዝንፍ የማይለው ውሳኔ የባሏ ነው፡፡ ይህም ‹‹የራሴ አሻራ ያላረፈባቸው ድርጊቶች ሁሉ ዋጋ ያስከፍለኛል›› ብላ እንድታምን እና የልዩነታቸው ድንበር ቅጥ ያጣ እንደሆነ እንድትገነዘብ አድርጓታል፡፡
ሰዎችን የመርዳት፣ ሴቶችን ከወንዶች ተፅዕኖ የማላቀቅ እና ያለማንም ተፅዕኖ ህልሟን ከግብ ማድረስ ዋነኛ ዓላማዋ ነው፤ሶፊያ፡፡ ለዚህም በከፋ ችግርም ጊዜ ለዓላማ መቆም እንደሚቻል ለሴቶች በአርዓያነት የተሳለች ሆና አግኝቻታለሁ፡፡ በተለይም ደግሞ የሶሪያ ስደተኞች ጉዳይን የራሷ ሃላፊነት እንደሆነ የምታምን በመሆኗ ‹‹አይመንና ሰብሪናን›› ስራ ለማስቀጠርና ራሳቸውን ለማስቻል ብዙ ደክማለች። እስከ ታሪኩ መጨረሻ ድረስ  ከጎናቸው አልተለየችም፡፡
የሰብሪና በውጣውረድ የተሞላ ህይወት ልቧን ሰብሮታል፡፡ እጅጉን ስለምታዝንላትም ከወንዶች እጅ የጣላትን የገንዘብ እጦት ለመቅረፍ የመፍትሄ ሀሳቦችን ከመሰንዘር ባለፈ ስራ ለማስቀጠር ደክማለች፡፡ የስደትን አስከፊነት ተረድታበታለች፡፡ ከዚህ አንፃር የሀገሯ የወደፊት እጣ የጦርነት ሲሳይ መሆን በአእምሮዋ የሚመላለስ ጉዳይ ሆኗል፡፡
በመጨረሻም አንድ የአላማ ፅናቷን የሚያሳይ ነጥብ አንስቼ አጠናቅቃለሁ፡፡
…‹‹አይገርምህም ከውድቀት በፊት ወደ ነበረው የመጀመሪያው ሥርዓት እመልስሃለሁ፡፡›› አልሁት፡፡
‹‹ማለት?››
‹‹ፈቃድህ ወደ ሚስትህ ይሆናል››
‹‹ኪኪኪ… ኡህ…ሶፊዬ! አፌ ቁርጥ ይበልልሽ! ኪኪኪ…›› ሆዱን ይዞ እንባው እስኪወርድ ድረስ ሳቀ፡፡ (ገፅ 56)
ለ.የርዕይ መነጠቅ (ስኬት አልባነት)
ልቦለዱ እንደ አጠቃላይ ሲታይ የሶፊያ ታሪክ ነው፡፡ በእሷ እንቅስቃሴ ላይ ማተኮር የዓብይ ጭብጡን ለመለየት ከፍተኛውን ድርሻ ይወጣል፤የሚል እምነት አለኝ፡፡ ስለሆነም ይህ ሁለተኛው ነጥብ በይበልጥ ከሶፊያ ህልሞች እውን መሆን ወይም አለመሆን ጋር የጠበቀ ዝምድና አለው፡፡ ለምሳሌ፡-
‹‹…አዋሳ በሰላም ለመኖር ዋስትና የሚሆነን ምንድን ነው? አገሩ ይረጋጋ…እኔም የጀመርኩትን ስራ ልጨርስ…››
‹‹ምንም ጊዜ የለኝም! ጨርሻለሁ!››
‹‹ስማ ፋሲል! እስከዛሬ የከፈልኩት ጊዜና ጉልበት ብቻ አይደለም ሕይወትም ጭምር ነው፡፡ መልሼ ያንኑ ስህተት መድገም አልፈልግም!›› በጩኸት የተወጠረው ጎጆ እስፒል እንዳገኘው ፊኛ ሲረግብ ታወቀኝ፡፡(ገፅ 62)
ከዚህ ምልልስ የምንረዳው አለመግባባቱ ወይም አለመደማመጡ ከቁጥጥር ውጭ መሆኑን
ነው፡፡ ተስፋ የተጣለበት ትዳር ሲከስም ለሶፊያ ታይቷታል፡፡ በጎጆዋ ላይ ያላትን እምነት
ያጨለመ በመሆኑም ከፊኛ ጋር አመሳስላዋለች፡፡ ይህም ዋጋ የከፈለችበትን የህይወት ጉዞ
ያጨለመ አጋጣሚ ሆኖ ይታየኛል፡፡ ከፋሲል ጋር እንዳትቀጥል ያደረጋት ውሳኔ ነው፡፡ በእርግጥ
የራሷ ውሳኔ ቢሆንም ቅሉ ትዳሬ ብላ የገባችበትን ሰፊ ዓለም ችግሮች ተጋፍጣ የምትወጣበት
ጉልበት አላገኘችም፡፡ ከላይ ለመግለፅ እንደሞከርኩት ፅናቷ የሚገለፀው ከትዳር ህይወቷ ባሻገር
ነው፡፡ ማለትም የፋሲልን አመለካክት ከመቃረን የዘለለ ተግባር አልፈጸመችም፡፡ የአእምሮዋ
ትኩረት የወንዶችን አለም መተቸት ላይ ነበር፡፡ ይህም ቢሆን የተሳካላት አይመስልም፡፡ እስኪ
ከላይ የሰፈረውን ምልልስ በድጋሜ እንጥቀሰው፡፡
…‹‹አይገርምህም ከውድቀት በፊት ወደ ነበረው የመጀመሪያው ሥርዓት እመልስሃለሁ፡፡›› አልሁት፡፡
‹‹ማለት?››
‹‹ፈቃድህ ወደ ሚስትህ ይሆናል››
‹‹ኪኪኪ… ኡህ…ሶፊዬ! አፌ ቁርጥ ይበልልሽ! ኪኪኪ…›› ሆዱን ይዞ እንባው እስኪወርድ ድረስ ሳቀ፡፡(ገፅ 56)
እዚህ ላይ በመጽሐፍ ቅዱስ ሄዋንን ‹‹ፍቃድሽ ወደ ባልሽ ይሆናል›› ተብሎ የተጠቀሰውን በመገልበጥ የተነገረ መሆኑን ልብ ማለት ያስፈልጋል፡፡ ስለሆነም ይህ አካሂዷ እና ምኞቷ ከግብ ሳይደርስ ቀርቷል፡፡ ፋሲልንም ማስከተል አልቻለችም፤ግልበጣው በታሪኩ ውስጥ በግልፅ አልታየም፡፡ በእርግጥ በታሪኩ ፍፃሜ ፋሲል ተመልሶ ለማሳመንና ለማግባባት ቢሞክርም፣ አዲስ አበባን ለመልቀቅ ፈቃደኛ አልሆነችም፡፡ ይህ ማለት ግን አላማዋን ‹‹የማሰናከል›› ተግባር ያለውን የትዳር አጋሯን ቆርጦ እንደመጣል መቆጠር የለበትም፡፡ ምክንያቱም ፈተና የምታመጣበት እሷው ስለሆነች፡፡ ለአብነትም‹‹ …ድብልቅልቃችን ወጥቶም ዐይኑ በእንባ ሲሞላ ይከፋኛል፡፡ ስህተቱን እንዳያውቅ ደግሞም የሚፈልገውን ለማድረግ እንዳይጠቀምበት ስል አላባብለውም እንጂ፡፡›› የሚለው ተጠቃሽ ነው፡፡ እንዲሁም ፡- ‹‹የእኔ ዘመን መንገድ ይገርማል! ከመነሻው መድረሻው አይታወቅም። ውጤቱ ማለፍ ወይም መውደቅ ሆኖ ከመደምደሙ በፊት ያለው መሰናክል ብዙ … ነው፡፡ ድልድይ ሆኖ ሊያሻግረን የሚችለው መናበብ መቻል፣ መደጋገፍ፣ መተቃቀፍ፣ አይዞህ! አየዞሽ! መባባል ነበር፡፡ አልሆነም!›› በማለት ዘመኑን የምትተች ቢሆንም፣ መፍትሄው ላይ ስትተጋ አትታይም፤ይህም ገፀባህሪዋን ደካማ ያደርጋታል፡፡
ሌላኛው መነሳት ያለበት ነጥብ የጥናታዊ ፅሁፉ ጉዳይ ነው፡፡ ከቆመችለት አላማ አንፃር ስደተኞች ላይ ታደርግ የነበረው ተግባር ሲፈፀም አይታይም፡፡ ምናልባትም አንባቢው ከታሪኩ መገባደድ በኋላ በአእምሮው የሚያሰላስለው ካልሆነ በቀር፡፡ በጥናት ሰበብ የተዋወቀቻት ሰብሪናንም ቢሆን በግል ችግሮቿና ጉዳይ ላይ ተጠምዳ መቆየቷ ግብ  እንደሳተች የሚጠቁም ይመስለኛል፡፡ ማለትም የስደተኞች ጉዳይ በሀገር ደረጃ ያለውን ተፅዕኖ ለመፈተሽ የሚደረግ ጥናት እንደመሆኑ ሰፊ የመረጃ ምንጭ የሚጠይቅ ሆኖ ሳለ በአንድና በሁለት ሰው መረጃ ላይ የሚመሰረት አይደለምና ነው፡፡ በእርግጥ ከላይ የተጠቀሱ ችግሮች የተፈጠሩት ገጸባህሪዋ ከተላበሰችው ሰብዕና አንጻር ይመስለኛል፡፡ እንዲሁም የታሪኩ ማጠር ግልፅ ተፅዕኖ አለው፤ አልተፍታታምና ፡፡
ሐ. አባዊ ስርዓት (የወንዶች ዓለም)
ከላይ ከተጠቀሱት ዓብይ ጭብጦች በተጨማሪ ‹አባዊ ስርዓት › ተተችቶበታል። ሶፊያ፤ የወንዶች አለም በእጅጉ የሚረብሻት ገፀባህሪ ናት፡፡ ትችቷ የሚመሰረተው ክርስትያናዊ በሆነው የፆታ ምልክታ ላይ ነው፡፡ ስለሆነም ምንጩ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ነው፡፡ ምሳሌ እንጥቀስ። ‹‹የሔዋን ቅጣት መራራ ነው፡፡ ምሬቱ ከእግር እስከ ራሴ ይሰማኛል፡፡ አሁን ማን ይሙት አዳምና እባብ ተቀጥተዋል ይባላል? ጉልበታቸው  እንጂ ነፍሳቸው ምን ደረሰባት?›› የሚለው ገለፃና ሙግት ከመጀመሪያውም ምግባራዊ ተግባር አይደለም፤ ሔዋንን የኮነነ በመሆኑ። የነገሩን ክብደትና ህመሟን ለመረዳት በተከታይነት የሰፈረውን እንሆ፡-
ለእባብ - ‹‹በሕይወትህ ዘመን ሁሉ በደረትህ እየተሳብህ ትሄዳለህ አፈርም ትበላለህ›› አጭርና ግልፅ፡፡
ለአዳም - ‹‹ምግብህን ጥረህ ግረህ ከእርሷ ታገኛለህ፡፡ ምድርም እሾህና አሜከላ ታበቅልብሃለች … እንጀራህን በፊትህ ላብ ትበላለህ›› መጠኑ ቢለያይም ሁላችንም የምንበላው በላባችን አይደል?
ለሔዋን - ሔዋን እኮ ነፍሷን ነው የተቀጣችው፡፡ ተቀጣን ልበል እንጂ! ‹‹ፈቃድሽ ወደ ባልሽ ይሆናል›› ሲላት ኡ… ኡ… ማለት አልነበረባትም? ፈቃድን ያህል ነገር ከአስረከቡ ወዲያ የሚቀጥል ማንነት አለ? (ገፅ 19)
የህልውናዋ ምስጢር አዳም ስለመሆኑና ነፃነቷን መነጠቋ በእጅጉ ያበሳጫታል። ስለሆነም ታምጻለች፡፡ አመጿ ስር ነቀል ነው።
‹‹አዳምንም ደግሞ እጠይቀዋለሁ። ለምን እስከዛሬ አብረኸኝ ኖርህ? የምትፈልገውን የምታውቅ ከሆንህ ለምን ከእጄ ተቀብለህ በላህ? እሷ እውቀት ወዳ፤ እኔ ደግሞ በሆዴ መጨከን አቅቶኝ… ትዕዛዝህን ተላለፍን ብትል ምን ነበረበት? እለዋለሁ፡፡›› (ገጽ 20) ሴት በጥበቧ ፤ ወንድ ደግሞ በጉልበቱ (በሆዱ) ማደር የጀመሩት ቀድሞውኑ ነው፤ያለች ይመስለኛል፡፡ አሁንም ቢሆን የሚከተለው አዳም እንጅ ሔዋን አይደለችም፣እንደማለት ነው፡፡ ይህም ለወንዶች አለም የመረረ ጥላቻዋን ያመለክታል፡፡ ‹‹አዳም በኤደን ገነት ላሉት እንስሳት በሙሉ ስም ማውጣቱን እንደ ታላቅ ጀብዱ በየማታው ሲያወራላት እየሳቀችም ቢሆን ‹‹ለምንድነው በትንሽ ነገር ቶሎ የምትመሰጠው?›› ያለችው ይመስለኛል፡፡›› (ገፅ 55)
ከፆታ አንጻር ለተነሳው ጉዳይ ተጨማሪ ነጥብ እንጥቀስና እናጠቃለው። ‹‹…ያን አመሉን ሳስብ ወደ ቤተሰቦቼ ዘመን ይወስደኛል… ማለቴ ወደ አያቶቼ ዘመን። የሴትን ዓለም በጓዳ ልክ ወዳጠበቡት። ከቁርስ እስከ እራት ምግብ የመስራትና የማብላት፣ ልጅ የማሳደግ፣ ቤት የማሰናዳት ተግባር ውስጥ ብቻ መኖር፡፡ የባል ፈቃድ ብቻ የሚፈፀምበት፣ የሚስት ድምጽ የማይሰማበት ዓይነት ኑሮ፡፡›› (ገጽ 57) የሴቶች የአደባባይ ውሎ እየጎላ የመጣበት ዘመን ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ‹‹የባለቤቷ›› ጫና አሉታዊ መሆኑን አንፀባርቃለች፡፡ በዚህም የዘመኑ የሀበሻ ወንዶች ተተችተውበታል ማለት ይቻላል፡፡ ያው መቼቱ ባለፉት ሶስት የለውጥ አመታት ላይ የተመሰረተ ስለሆነ የፖለቲካው ውጥንቅጥም የወንዶች አለም ውጤት መሆኑን መጥቀስም ተገቢ ነው፡፡ በታሪኩ ውስጥ ያሉ ወንዶች በአብዛኛው ሴትን ከፆታዊ ፍላጎታቸው አንፃር የሚመለከቱ ሆነው ተገልፀዋል። በተጨማሪም ሴትን ዝቅ አድረገው የሚመለከቱና ሆድ አደሮች ናቸው፡፡
በአጠቃላይ ‹‹ወደኋላ›› ረጅም ልቦለድ፣›› በርካታ ይዘቶች ያቀፈ ቢሆንም፣ መሰረታዊ ጭብጦች ሆነው ያገኘኋቸው ግን ከላይ በዝርዝር የተመለከትናቸው ናቸው፡፡ ከዚህ ቀጥሎ ደግሞ ‹‹የትረካ ስልቶች ትንተና›› ክፍልን የምንመለከት ይሆናል፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጸሃፊውን በኢሜይል አድራሻው፡- This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል፡፡

Read 1814 times