Print this page
Saturday, 25 December 2021 13:29

ስደተኛው ነብይ

Written by  ሲራክ ወንድሙ
Rate this item
(2 votes)

  እውነተኛ የከያኒ ነብስ የህመም ማድጋ ናት!”
                         
            ..... በ፲፱፺፯ ዓ.ም የህትመት ብርሃን አግኝቶ ለአንባቢ የቀረበ አንድ መፅሀፍ አለ።
ሚስጥረኛው ባለቅኔ የሚል!
ሚስጥረኛው ባለቅኔ በደራሲና አርክቴክት ሚካኤል ሽፈራሁ የተዘጋጀ መፅሐፍ ሲሆን መፅሐፉ የብላቴን ጌታ ሎሬት ፀጋዬ ገ/መድህን ስራ የሆነውን “ሀ ሁ ወይም ፐ ፑ” ን መሰረት ያደረገ የስነፅሁፍ ምርምር ወይም (ዳሰሳ) መፅሐፍ ነው።
መፅሐፉን ባነበብኩት ወቅት ስመኝ የነበረው ነገር ቢኖር፣ አብዬ ፀጋዬ ከማለፋቸው በፊት ይህንን መፅሐፍ አንብበውት ቢሆን የሚለውን ነበር። የሚካኤል ሽፈራውን ድንቅና የማይጎረብጥ እይታ መመልከት ቢችሉ እና ለአንዲት ቅፅበት ከዘመን ህመማቸው ተናጥበው ፈገግ እንዲሉ ተመኘሁ።
ይህንን የምኞት ቋጠሮ ባሰርኩበት በዚያው ልደታዎች አንድ ቀን በማህበራዊ ድረ- ገፅ ላይ ይህንን መሰል መልዕክት አዘል ፅሁፍ አነበብኩ።
ፀሀፊው ሱራፌል አየለ ነበር።
“ሚካኤል ሽፈራሁ አብዬ ፀጋዬ ከማለፋቸው በፊት በአካል እንዳገኛቸው ተሰማና ‘ስታገኘው ምን አለህ ?’ ተብሎ ተጠየቀ።
ሚካኤልም  ‘በቃ ይነጫነጫል!’ ሆነ መልሱ “  የሚል ነገር ለጥፎ ተመለከትኩ።  ማን ? (ሱራፌል አየለ)
በመፅሐፉ አዘጋጅ መልስ ውስጥ ‘ከያኒን ከስራው ባለፈ ማግኘት፣ የግል ህይወቱን መበርበር፣ የምናቡን ንድፍ በእሱ ውስጥ ለመመልከት መሞከር ነፋስ የመጨበጥ ያህል ነው! ‘ ያለኝ መሰለኝ።
ብዙሃኑ የተደራሲ ክፍል በደራሲው የምናብ አለም ውስጥ ያየውን (የሚያየውን) ምስል በተደራሲው ህይወት ውስጥ ለማግኘት ይለፋል። ያቺ የደራሲው የምናብ አለም፣ የምኞት ሽል ናትና በደራሲው ማንነት ውስጥ ዝር አትልም።
ደራሲው በእውኑ አለም ልውለዳት ቢል እንኳን ካለበት ከአኗኗር ስርዓት እና ከማህበረሰብ የመንፈስ ከፍታ ጋር ስለሚጣረስ እንዲሁ ህልም እንደዘራ ይኖራል።
እንደብኩን መፃተኛ!
የዘራው ህልም አለ አጫጅ የትም ስለሚቀር፤ ያ ደራሲውን ወደ ብስጭት ጎተራ ይሰደዋል።
ዘውትር ባለበትና በሚኖርበት ስርዓት ይማረራል።
ብዙ የሚደንቀውና የሚሞቀው አይሆንም።
ሸክላ ሰሪ ...... ብሎ ቢቀድስ፤ የራሷ እያረረ.... ብሎ ቢደግም ነገረ ብሂሉ፤ ከያኒው ኑሮ ግራ ህይወት እዳ በሆነበት ማህበረሰብ ውስጥ በኪነት ብርቱ ጦስ እየተንገላታ በምኞቱ ጎለጎታ ላይ በኑረት መስቀል ተቸንክሮ ደሙን እያዘራ ‘ አቤት! ‘ ይላል።
ከእያንዳንዱ ከእውነተኛ የጥበብ ሰው ጀርባ የተቸነከረበት መስቀል እንዳለ አምናለሁ።
የእሱን ያህል የአስተሳሰብ ወሰን ..... የንቃት ደረጃ .... የመታተር ወኔና ህልም ካጣ ዝንጉ ሰው ጋር መኖር በራሱ ለጥበብ ሰው ብርቱ ህመም ነው።
ርጋፊ የመኖር ተስፋውን በሱስ ፣ በአልባሌ ወጪና ማስተንተን በራቀው እሳቤ መደብ ስር ራሱን ጨቁኖ የሚኖር ህዝብ መሀል የተፈጠረ ሀሳበኛ (ከያኒ)፣ ምድር ጥሮ ግሮ መኖሪያ አምባው ሳትሆን፣ ነዶ ጭሶ ማለቂያ ገሀነሙ ናች።
ተደራሲ ደራሲውን የሚለካበት ትልቁ ነጥብ በፀነሰው የምናብ የምኞት ሽል ሲሆን እሱ ካሰመረው እይታ ፈቅ ካለ ቀድሞ ይሰጠው የነበረው ቦታ በውስጡ መናድ ይጀምራል።
በምናቡ የአድማስ ጥግ ከመላዕክት በላይ ያገነነውን ሰው በአካል ሲመለከተው፣ የሰይጣን ያህል ሲሆንበት፣ የንቀቱን ስውር መርፌ የሀሜቱ ድሪቶ ላይ እየጣፈ፣ ጀምበርን የሚገድለው ጥቂት አይደለም።
በዚህም የተነሳ ማህበረሰቡ ‘ለካ እሱ እንዲህ ነው!’ እያለ ከልቡ ዙፋን ፊት አሽቀንጥሮ ይጥለዋል። አንቅሮ ይተፋዋል። በሰው ፊት ሞገስ ማጣት ለሰው ልጆች የህመም ሁሉ የበላይ ነውና ከያኒው በዚህ አለም በባይተዋርነት ይቃትታል።
ላልተቀበለው ማህበረሰብ መፃፍ ፤ ላልወደደው ተደራሲ መጨነቅ ይሰለቸዋል።
ግን .... በኪነቱ ቡዳ የተበላች ነፍስ እረፍት የላትምና እከከኝ ትለዋለች።
ያኔ ..... አመነም ከዳ ለማን እንደሚፅፍ ግራ እየገባው የነፍስ እከክ ዜማውን በመቀመር የህይወቱን ጀንበር ይባጃል።
በአንድ ወቅት አንድ ደራሲ በከፍተኛ ድባቴ ( Depression ) ውስጥ ገብቶ ነብሱ ስትጨነቅበት በከተማዋ አለ ወደ ተባለ የስነ-ልቦና አማካሪ ጋ ቀርቦ የደረሰበትን አስረዳ። የስነ - ልቦና አማካሪው በጥሞና ሰምቶም ሲያበቃ እንደመፍትሔ እንዲስቅ፣ ራሱን ዘና እንዲያደርግ በማሰብ በከተማቸው ውስጥ ያለ የአንድ እውቅ ደራሲን ስም ጠቅሶ የእሱን መፅሐፍቶች እንዲያነብ ይመክረዋል።
ያ የተባለው እውቁ ደራሲ ራሱ ነበርና ደራሲው የራሱ መፅሐፍ ለራሱ ሲጋበዝ በቆመበት ደንግጦ ቀረ።
ከዚህ የበለጠ የራስ እያረረ ..... ከየት ይመጣል?
ህልም ዘሪዎቻችን ያሳዝኑኛል። እሱ የቀመሳትን መራር ፅዋ አንተ ካልቀመስካት አለም ወድማ ካላደረች የሚል ዘራሰብ እንደክረምት ጉም ሀገር ባለበሰበት አለም ውስጥ እየተኖረ ለሰው ልጅ ጥሩ ማሰብ ይደንቃል።
ኪነት ትልቁ ፀጋና መገለጧ የሰው ልጅ ፍቅር ነው።
የሰው ልጅ ፍቅር ደግሞ ውቡ የአምላክ ዜማ ሲሆን ለነብስ ያደረ ከያኒ የዚህች ዜማ ዘማሪ ይሆናል።
እሱ ግን ዜማውን የመስማት ፀጋን የተነፈገ ነው። ይዘምረዋል እንጂ አይኖረውም።
ከገደሉ ውስጥ ስለመውጣት ሰብኮ እልፍ ነብሶችን ቢያሻግርም፣ ተግተው ለፈለጉት መኖሪያው ገደሉ ውስጥ ነው። በወዙ ጠፈጠፍ ሀገር ይሰራል። እሱ ግን ሀገር አልባ ስደተኛ ነብይ ነው።
ዘወትር በምኞቱ የፅንሰት ሽል ውስጥ እየተገላበጠ በጥቂት መሰሎቹ መከበብ ካልቻለ በእሱ የህይወት ሰማይ ላይ ብቅ ያለችው ደማቅ ፀሀይ ደሙስ ጋርዷት በፅልመት ትዋጣለች።
እናም .... እውነተኛ የከያኒ ነብስ የህመም ማድጋ ናት።
ዘመንና ትውልድ የግዞቱ ማደሪያ ሲሆኑ ሀገርና ሰው የአይኑ ማረፊያዎች ናቸው።
መዳፍ አህላ በጠበበችው አለም እየኖረ ከባህር በሰፋ የምናቡ ጥልቀት ሩቅ ይሰደዳል።
ወዴት እንደሚሄድ አያውቅም ግን መሄድ ነው ሀሳቡ .... ሩቅ ነው ድንበሩ!
ሀገር አለው ግን አይኖርበትም። ባይተዋር ነው።
የስደተኛው ነብይ መዳረሻ የት ነው? እያልኩ መጮህ ያምረኛል።
ግን ለማን ?
ምናልባት መዳረሻው በደሙ፣ በመረቀዙና መፈጠርን በጠሉ የነፍስ የቁስል ስንጥቅ (ንቃቃት) ውስጥ አለምን መስርቶ መኖር ይመስለኛል።                    


Read 569 times