Print this page
Saturday, 25 December 2021 13:34

ምኞት

Written by 
Rate this item
(0 votes)

“ንጹህ ልብ ፍጠርልኝ” - እያልኩ ስማጸነው
የስንቱ ቆሻሻ
እኔ ላይ ተደፍቶ - ጠዋት አየዋለሁ
ልቤን ላጥራ ብዬ - ስደክም ስለፋ
ደፋር እጣቢውን
የስሜ ምንጣፍ ላይ - እያየሁት ደፋ!
-*-
አንዳችን ላንጠራ - እንዲህ እየተግማማን
እንዶድ አይችለንም - ፈትጎ ሊያጠራን !
ነውራችን ሲገለጥ - በዘመን ቆዳ ላይ
ጭቅቅት ሆነናል - ደግ ዘመን ላናይ !
-*-
የግብራችን ክፋት - ላይጠፋ በእጣኑ
ተረግሞ ከሰመ - የእግዜር ደግ ቀኑ !
ልቻለው እያልኩኝ - ያለፍኩት በመላ
ፊቴ ላይ ተጥፎ
ጠባሳ ሆነብኝ - በስተርጅናዬ ገላ !
አቃቂር አውጥቶ - ስም ሳያወጣ ከቶ
ሽብሽብ ቆዳዬ ላይ .......
ብልዝ ዓይኖቼ ላይ .......
ሽበት ጸጉሮቼ ላይ .........
ፊቴን ያነበበ - ደርሶ ያዝንልኛል - መጠቃቴን አይቶ!
-*-
ቅንነት ላይበቅል - በልባችን እርሻ
ረግጦ ማለፍ ሲሆን - የፍርዳችን ድርሻ
እኔ እንደምን ብዬ - ንጹህ ልብ አንጥፌ
መኖር እችላለሁ - ጠላቴን አቅፌ ?
እንክርዳድ ሲወረው - ሀገር ምድሩ ሁሉ
ወይ አብሮ መቃጠል .......
አልያም መረገጥ ነው - የስንዴ እድሉ!
-*-
እናማ አምላኬ - ድካሜን እይልኝ
ክፉ በመሆኔ - ከቶ አትፍረድብኝ!
ጥላቻን ጠልቼ - መኖር እያማረኝ
በሰው ክፉ ተንኮል - መራመድ አቃተኝ!
-*-
እጄን ባልዘረጋም - ለበቀል ጨክኜ
ብድር ባልመልስም - ስውር ስፍራ ሆኜ
እስቲ ለወዳጄም - ምህረት ስጠውና
ከማያልቀው ጸጋህ - ጥቂት ይቅመስና
ይቅር ባይ - ደግ ሰው - ትሁት የዋህ ቀና
እንዲሆን አድርገው - ልቡን እጠብና
አንተን በማወቁ ........
አትራፊ ነው እንጂ .......
“ከሰርኩኝ” እያለ - ደጁን የሚዘጋ - ከቶ የለምና!
-*-
እኔም በስተርጅና - ይህን ቀን ልይበት
በከዘራ ዘመን - ቀና ልበልበት
በሽብሽብ ቆዳዬ - ወዝቼ ልውጣበት
ሁለት ጸጉር ይዤ .......
መቃብር ላይ ቆሜ .......
በሞቴ ላይ ስቄ - ነገ ልሙበት!
(ነፃነት አምሳሉ)


Read 1277 times
Administrator

Latest from Administrator