Saturday, 25 December 2021 13:45

ዋልያዎቹ

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

  • ዛሬ ሽኝት ይደረግላቸዋል፤ነገ ወደ ያውንዴ በማቅናት የ12 ቀናት ዝግጅት ያደርጋሉ
       • ከሞሮኮ፣ ሱዳንና ዚምባቡዌ ጋር የአቋም መፈተሻ ግጥሚያዎች እንዲያደርጉ እቅድ ተይዟል
       • “የኳስ ቁጥጥራችንን በጎል እንዲታጀብ እንፈልጋለን፡፡ ከምድባችን ማለፍ አለብን፡፡” ዋና አሰልጣኝ ውበቱ አባተ


           ካሜሮን ለምታስተናግደው 33ኛው የአፍሪካ ዋንጫ 15 ቀናት ቀርተዋል፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን  ዛሬ በስካይ ላይት ሆቴል ሽኝት የሚደረግለት ሲሆን ሙሉ ቡድኑ ነገ ወደ ያውንዴ ከተማ እንደሚጓዝ ታውቋል፡፡ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ዋና ጸሐፊ  ባህሩ ጥላሁን በጋዜጣዊ መግለጫ ላይ  እንደጠቀሰው ለብሔራዊ ቡድኑ የአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎና ዝግጅት 51 ሚሊዮን ብር አጠቃላይ በጀት ከመንግስት  ተጠይቆ፤  በመንግስት የተፈቀደው በጀት 35 ሚሊዮን ብር ሲሆን  ለቡድኑ የሚያስፈልገውን ቀሪ የ16 ሚሊዮን ብር በጀት ከፌዴሬሽኑ በጀት፣ ከስፖንሰሮች ከሌሎች ገቢዎች ለማሟላት መሞከሩን አስታውቋል፡፡
ዋና ፀሀፊው እንደገለፀው ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ዛሬ በስካይ ላይት ሆቴል በሚካሄደው ልዩ  የሽኝት ፕሮግራም ላይ የተለያዩ መርሐ ግብሮች ተዘጋጅተዋል፡፡ የእግር ኳስ ፌዴሬሽኑ ያሰራው “የዋልያዎቹ አሻራ” የሚል ጥናታዊ ፊልም እንደሚመረቅ ፤በከፍተኛ  የመንግስት ባለስልጣናት በኩል የሰንደቅ ዓላማ ርክክብ እንደሚከናወንና ዋልያዎቹ በአፍሪካ ዋንጫ በሚኖራቸው ተሳትፎ ላይ በየጨዋታው የሚያስመዘግቡት ውጤት የተዘጋጀላቸው የቦነስ ክፍያ እንደሚገለፅ ይጠበቃል፡፡ ዋና አሰልጣኝ ውበቱ እንደተናገሩት ቡድናቸው በያውንዴ ከተማ ለ12 ቀናት የመጨረሻ ዝግጅቱን የሚሰራ ሲሆን ዓለም አቀፍ የእግር ኳስ ማህበር በሚያዘጋጀው የወዳጅነት ጨዋታዎች መርሓግብር መሰረት ከሞሮኮ፤ሱዳንና ዚምባቡዌ ጋር የአቋም መፈተሻ ግጥሚያዎች ለማድረግ መታቀዱን ፌዴሬሽኑ ገልጿል፡፡
ከትናንት በስቲያ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ ውበቱ አባተ በሰጡት መግለጫ ወደ አፍሪካ ዋንጫው 25 ተጫዋቾችን ይዘው እንደሚሄዱ ተናግረው ነበር፡፡ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን በአህጉራዊው ውድድር  ብሔራዊ ቡድኖች የሚያሰልፏቸውን ተጫዋቾች ብዛት ከ23-ወደ 28 ማሳደጉ ይታወቃል፡፡ ዋንኛው ምክንያት በኮቪድ ምርመራ እና ሌሎች ሁኔታዎች ቡድኖቹ እንዳይቸገሩ ታስቦ ነበር፡፡ የብሔራዊ ቡድኑ ዋና አሰልጣኝና የፌዴሬሽኑ ዋና ፀሐፊ በአስተዳደራዊና ቴክኒካዊ ጉዳዮች በሰጡት መግለጫ  25 ተጫዋቾችን ወደ አፍሪካ ዋንጫው ይዘው ለመሄድ ከጅምሩ ሲወሰኑ 23  ተጫዋቾች በካፍ ወጪ ሁለት ተጫዋቾች  ደግሞ በፌዴሬሽኑ ወጪ ለማጓጓዝ አቅደው ነበር፡፡ ሐሙስ ዕለት በብሔራዊ ቡድኑ የአፍሪካ ዋንጫ ዝግጅትና ተሳትፎ ዙሪያ ከቀድሞ አሰልጣኞች የቀድሞ ተጫዋቾችና ከሚዲያው ጋር በተካሄደ የፓናል ውይይትና ጋዜጣዊ መግለጫ ጋር ተያይዞ  የቀረቡትን አስተያየቶች በመንተራስ ውሳኔው ተቀይሯል፡፡ የተጫዋቾች ስብስቡን በተፈቀደው ብዛት የመያዝ ጥቅሙ ጎልቶ በመታየቱ አመሻሹ ላይ ፌዴሬሽኑ ወደ አፍሪካ ዋንጫ የሚያቀኑ ተጫዋቾችን ብዛት ከ25 ወደ 28 እንዳሳደገ ታውቋል፡፡ በውሳኔው መሰረትም በአፍሪካ ዋንጫው 23 ተጫዋቾች በካፍ እንዲሁም 5 ተጫዋቾች በኢትዮጵያ እገር ኳስ ፌዴሬሽን ሙሉ ወጭያቸው ተሸፍኖ በ33ኛው የአፍሪካ ዋንጫ የሚሳተፉ ይሆናል፡፡
ዋና አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ለ33ኛው የአፍሪካ ዋንጫ በመጀመሪያ የጠሯቸው  የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን 25  ተጫዋቾች የሚከተሉት ናቸው፡፡ ግብ ጠባቂዎች ተክለማርያም ሻንቆ (ሲዳማ ቡና)፤ ፋሲል ገ/ሚካኤል (ባህርዳር ከተማ) እና ጀማል ጣሰው (አዳማ ከተማ) ናቸው፡፡ ተከላካዮች አስራት ጡንጆ (ኢትዮጵያ ቡና)፤ ሱሌይማን ሃሚድ (ቅዱስ ጊዮርጊስ) ረመዳን የሱፍ (ወልቂጤ ከተማ)፤ ደስታ ዮሐንስ (አዳማ ከተማ)፤ አስቻለው ታመነ (ፋሲል ከነማ)፤ ያሬድ ባየህ (ፋሲል ከነማ)፤ ምኞት ደበበ (ቅዱስ ጊዮርጊስ) እና መናፍ አዋል (ባህርዳር ከነማ) ናቸው፡፡ አማካዮች አማኑኤል ዩሐንስ(ኢትዮጵያ ቡና)፤ጋቶች ፓኖም( ቅዱስ ጊዮርጊስ)፤ ሽመልስ በቀለ( ኤል ግዋና ግብጽ)፤ መስዑድ መሀመድ (ጅማ አባጅፋር)፤ ፍፁም አለሙ (ባህር ዳር ከነማ)፤ ፍሬው ሰለሞን (ሲዳማ ቡና)፤ በዛብህ መለዮ (ፋሲል ከነማ) ናቸው፡፡ አጥቂዎቹ አቡበከር ናስር (ኢትዮጵያ ቡና)፤ ጌታነህ ከበደ (ወልቂጤ ከነማ)፤ አማኑኤል ገ/ሚካኤል (ቅዱስ ጊዮርጊስ)፤ ሽመክት ጉግሳ (ፋሲል ከነማ)፤  ቃሲም ( ጂ ኤስ ካቤል አልጄሪያ) መስፍን ታፈሰ (ሃዋሳ ከነማ) እና ዳዋ ሂጤሳ (አዳማ  ከነማ) ናቸው፡፡ በሁለተኛው ምዕራፍ ጥሪ የተደረገላቸው 3 ተጫዋቾች ደግሞ ሱራፌል ዳኛቸውና ይሆን እንደሻው (ፋሲል ከነማ) ግብ ጠባቂው ፍሬው ጌታሁን (ድሬደዋ ከነማ) ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የተጫዋቾች ስብስብ  በግብጽ የሚጫወተው ሽመልስና በአልጀሪያ በሚጫወተው ሙጂብ አማካኝነት በዝውውር ገበያው ከምድቡ ዝቅተኛውን የዋጋ ተመን  በ750 ሺ ዩሮ መያዙን በትራንስፈርማርከት  ድረ ገፅ ላይ ተመልክቷል፡፡ “በተጫዋቾቹ ምርጫ ዋናው ዓላማችን የነበረው ጥሩ ቡድን መስራት ነው፡፡ በየቦታው የመረጥናቸው ልጆች ከቡድኑ ጋር የተላመዱና ከአጨዋወቱ ጋር የሚሄዱ ናቸው” ያሉት ዋና አሰልጣኝ ውበቱ ቡድናቸው ለዓለም ዋንጫ የመጨረሻ ማጣሪያ ጨዋታ ካደረገ በኋላ ከተጫዋቾቹ ጋር በቂ የመገናኛ ግዜ እንዳልነበራቸው ጠቅሰው፤ በመጀመሪያ ተጨዋቾች በዚሁ የዓለም ዋንጫ ላይ የነበራቸውን የግልና የቡድን እንቅስቃሴዎች በቪዲዮ እንዲመለከቱ አድርገናል ብለዋል፡፡ የፕሪሚየር ሊግ ውድድር በሚካሄድበት ሀዋሳ ላይ በብሔራዊ ቡድኑ እቅድ ያሉ ተጫዋቾች በቴክኒክ እና በአዕምሮ በሚደረጉት ዝግጅቶች ላይ ተመክሯል፡፡ ከሰውነት ክብደት  ተያይዞም መቀነስ ወይም መጨመር ያለባቸውን ተጫዋቾች ላይ  ክትትል  በማድረግ ለአፍሪካ ዋንጫ ብቁ የሆኑትን ለመመልመል መሰራቱንም አብራርተዋል፡፡ ዋና አሰልጣኙ ለብሔራዊ ቡድኑ ተጫዋቾች ምርጫ በሊጉ ከሚወዳደሩ ክለቦች ዋና አሰልጣኞች፤ የቀድሞ ተጨዋቾችና አሰልጣኞች ጋር ሰፊ ምክክር በማድረግ ግብዓቶችን በመቀበል መስራታቸው  በተጫዋቾች ምርጫቸው ቡድኑ ሚዛኑ እንዲጠብቅ ያስቻለ ነው ብለዋል። በሌላ በኩል ትውልደ ኢትዮጵያውያንን ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች በማሰባሰብ ወደ ቡድኑ ስለማካተት አስተያየት ሲሰጡ  “የውጭ ተጫዋቾች ለመጥራት ፍላጎት ነበረን፡፡  ሙከራም አድርገናል፡፡ በዴቪድ ባሻህ አማካኝነት የተወሰኑ ተጫዋቾችን የኳስ ታሪክና አጫጭር ቪዲዮዎችን ተመልክተናል፡፡ በቂ አይደለም፡፡ በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ብሔራዊ ቡድኑ የምንቀላቀልበት ሁኔታ ግን የለም፡፡ በአጠቃላይ  ሂደቱ  ለወደፊቱ የሚያግዝ ነው” ሲሉም ተናግረዋል። ለዋልያዎቹ ስብስብ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ለማካተት በዴቪድ በሻህ በተያዘው እቅድ ከ9 በላይ ተጫዋቾች ከእስራኤል፣ከስፔን፣ ከጀርመንና ከሌሎች ሀገራት ተጠቁመው ነበር፡፡ አንዳዶቹን  በ33ኛው የዓለም ዋንጫ ለማስገባትም ፍላጎት ነበር፡፡ ብሔራዊ ቡድኑ በአፍሪካ ዋንጫ ለመሳተፍ ከነበረው አጭር ጊዜ አንጻር፤ ስለተጨዋቾቹ በቂና የተሟላ ማስረጃ አለመቅረብ እንዲሁም በነኢትዮጲያ መንግስት የሁለት አገራት ዜግነት አለመፈቀዱ ሂደቱን አስተጓጉሎታል፡፡
በምድብ 1 ከኢትዮጵያ ጋር የተደለደሉት ሶስት ብሔራዊ ቡድኖችም የተጫዋቾች ስብስባቸውን ሰሞኑን አስታውቀዋል፡፡ የአፍሪካ ዋንጫን በምታስተናግደው ካሜሮን በኩል 28 ተጫዋቾች ተጠርተዋል፡፡ የሚገኝበትን የማይበገሩት አንበሶች ተብሎ የሚጠራውን ስብስብ ቪንሰንት አቡበከር በዋና አምበልነት ይመራዋል። ከምድብ 1 በተጫዋቾች ስብስብ ከ137.95 ሚሊዮን ዩሮ ዋጋ በመተመን ከፍተኛውን ዋጋ በያዘው የካሜሮን ቡድን ግብ ጠባቂው ኦንድሬ ኦናና ከሆላንዱ አያክስ፤ አማካዩ አንድሬድ ፍራንክ ዛምቦ ከጣሊያን ናፖሊ እንዲሁም አጥቂው ኤሪክ ማክሲየም ከጀርመኑ ባየር ሙኒክ ተካትተዋል፡፡ በካሜሮን ቡድን የተያዙ ተጫዋቾችከቤልጂየም፣ ከፈረንሳይ፣ ከአሜሪካ፣ ከቻይና፣ ከግሪክ እና ከኦስትሪያ የተሰባሰቡ ናቸው፡፡ “ሰማያዊዎቹ ሻርኮች” የሚባለው የኬፕቨርዴ ብሔራዊ ቡድን በተጫዋቾች ስብስቡ ከአገሪቱ ክለብ የተመረጠ ብቸኛው ተጫዋች ተቀያሪ ግብ ጠባቂ የሆነው ኬቨን ራሞስ ብቻ ነው፡፡ በዝውውር ገበያው 24.23 ሚሊዮን ዩሮ በትራንስፈር ማርካት የተተመነው የኬፕቨርዴ ቡድን  ከቆፕሮስ፣ ፓርቱጋል፣ አየርላንድ ሆላንድ ቱርክ፣ ስዊዘርላንድ፤ ምስራቅ አውሮፓ እና አረብ አገራት ላይ  ከሚገኙ ክለቦች የተውጣጡ ናቸው፡፡ የቡርኪናፋሶ ብሔራዊ ቡድን በትራንስፈር ማርካት 14.43 ሚሊዮን ዩሮ ዋጋ የተተመነ ስብስብ ነው በሰሜን አፍሪካ በአውሮፓ እና በተለያዩ የቡርኪናፋሶ ክለቦች የሚሰለፉ ተጫዋቾች ይገኙበታል፡፡ የቡርኪናፋሶ ቡድን  “ፈረሰኞቹ” በሚለው ቅፅል  ስማቸው የሚታወቁ ሲሆን ከግብፆቹ ክለቦች  ኢታድ ኦፍ አሌክሳንድርያ እና ፒራሚድ እንደቅድመ ተከተላቸው የሚሰለፉትን ሳይዱ ሲምፓሬ እና ኤሪክ ትሯውሬ ባላቸው ልምድ ቡድኑን ያጠናክሩታል ተብሏል፡፡
ዋና አሰልጣኝ ውበቱ በምድቡ ስለሚገጥሟቸው ካሜሮን፣ ቡርኪናፋሶ እና ኬፕቨርዴ ያሉበት ደረጃ ጠንካራ መሆኑን ሲገልፁ፤ በአጨዋወታቸው ቶሎ ቶሎ ወደ ግብ የሚደርሱ መሆናቸውን እንደተገነዘቡ ጠቅሰዋል፡፡
ካሜሮን ከአይቬሪኮስት፣ ኬፕቨርዴ ከናይጀሪያ ያደረጓቸውን ጨዋታዎች ቪዲዮ በመመልክት ቡድናቸው ጠንካራ የስነ ልቦና ዝግጅት አድርጓል  ብለው፤በስነ ልቦና በኩል በዓለም ዋንጫና በአፍሪካ ዋንጫ ኳስ ይዞ በመጫወት ያገኙትን ልምድ፤ከምዕራብ አፍሪካ ቡድኖች ጋር መፋለምን እየለመዱ በመምጣታቸውም የመንፈስ ጥንካሬያቸው አላቸው በማለትም አስረድተዋል፡፡ የቀድሞ ብሔራዊ ቡድን አስልጣኞች፤ ተጫዋቾችና የሚዲያ ባለሙያዎች የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎ ዙሪያ ከላይ በሰጧቸው አስተያየቶች ላይ ዋና አሰልጣኝ ውበቱ በሰጡት ምላሽ “ከኒጀር ጋር ካደረግነው ጨዋታ ጀምሮ የነበረንና አጨዋወት ጠብቀን ለአፍሪካ ዋንጫ ደርሰናል፡፡ በእያንዳንዱ ጨዋታ በአማካይ ከ600 በላይ የኳስ ቅብብሎች እናደርጋለን። ኳስ እንደምንጫወት ይህ ያሳያል። የኳስ ቁጥጥራችንን በጎል እንዲታጀብ እንፈልጋለን፡፡ ከምድባችን ማለፍ አለብን፡፡” ብለዋል።

“ኳስ ይዞ በመጫወት ላይ ጎል ካልገባ ትርጉም አይኖረውም፡፡ ብሔራዊ ቡድኑ የማጥቃት ባህርይው ከፍተኛ ቢሆን ጥሩ ነው፡፡” የቀድሞ አሰልጣኝ አስራት ኃይሌ (የአዲስ አበባ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት)
“በተለመዱ ስህተቶች ከውድድሩ መውጣት የለብንም፡፡ ኳስ ብንይዝም የማግባት አቅማችን ያነሰ ነው፡፡ ስለዚህም በግብ ማግባት ላይ የተመሰረተ እንቅስቃሴ ያስፈልገናል፡፡” ሰለሞን አባተ (የኢትዮጵያ እግር ኳስ አሰልጣኞች ማህበር ተወካይ)
“ብሔራዊ ቡድኑ በአጨዋወቱ ጥሩ ለውጥ አድርጓል፡፡ በብሔራዊ ቡድኑ ዙሪያ  የቪዲዮ ኦናሊስ ተሰርቶ መቅረቡን አድንቄዋለሁ፡፡ በቡድኑ ውስጥ በስነ ልቦና የሚያነሳሱ ተጫዋቾች ያስፈልጋሉ፡፡ ከምድብ ማለፍ ብቻ ሳይሆን እስከ መጨረሻው የምንሄድበት ሞራል ያስፈልጋል፡፡” ፍቅሩ ተፈራ (የቀድሞ ብሔራዊ ቡድን ተጫዋች)
“ቡድናችን በራሱ በተጋጣሚውም ሜዳ ላይ ብዙ ኳስ ይጫታል፡፡ በአፍሪካ ዋንጫው ቡድኑ የተጋጣሚውን የመከላከል አደረጃጀት ሰብሮ በመግባት ጎል የሚያስቆጠረር መሆን አለበት፡፡  ወደፊት የብሔራዊ ቡድኑ አጨዋወት ለማጠናከር ከክለቦች አጨዋወት ጋር የሚያግባባ ሁኔታ መስራት አለብን፡፡” ሚሊዮን ጉግሳ (የ4-3-3 የራዲዮ ፕሮግራም ተንታኝ)
በአፍሪካ ዋንጫ ላይ የሚተላለፈው ቡድን በምዕራብ አፍሪካ ቡድኖች የተፈተነ ምርጥ ስብስብ ነው፡፡ በትልቅ ውድድር ላይ ሲሳተፍ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በአጨዋወቱ የራሱ መግለጫ ሊኖረው ይገባል፡፡ ለወደፊቱ ብሔራዊ ቴክኒክ ኮሚቴው የአጨዋወት መንገድን ለይቶ ቢያስቀምጥ ጥሩ ነው፡፡” አልመዲን  ማህመድ (ከፕሮፌሽናል ተጫዋቾች ማህበር)

Read 12988 times