Saturday, 25 December 2021 13:03

የወር አበባ…ለአንዳንዶች የህመም ስሜት አለው፡፡

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ ከኢሶግ
Rate this item
(0 votes)

 የወር አበባን በሚመለከት ከአሁን ቀደም የተለያዩ መልእክቶችን ለአንባቢ ማለታችን አይዘነ ጋም፡፡ ነገር ግን የህትመቱ አንባብያን ቀደም ሲል የነበሩት ብቻ ሳይሆኑ ትውልድ ቀጣይነት ስላለው ከአ መት አመት አዲስ የሆኑ እና በነገሮች ግራ የሚaጋቡ አይጠፉም። ስለዚህም በተከታይ የምታነቡት የአንዲት ተማሪን ጥያቄ ሲሆን እስዋም የወር አበባን ለማስተናገድ እንግዳ እንደሆነች ነው የተረዳነው፡፡ ጥያቄዋን ያቀረበችው በስልክ ነበር፡፡
ኢሶግ    ሄሎ…ኢሶግ
እንግዳ    …. እንደምን አላችሁ ?
ኢ    እግዚአብሔር ይመስገን… ማን እንበል
እን    ..አ..አ..ይ ..ስሜ ይቅር…ግን ከካዛንቺስ አካባቢ ነኝ፡፡
ኢ    እሺ….. ምን እንታዘዝ ?
እን    የላንቺና ላንተ ህትመት አቅራቢዎች ….እ….እኔ…እኔ ዘንድሮ በእድሜዬ ወደ 13 አመት የገባሁ ሲሆን አንድ የማይቀር… ነገር ግን አስቸጋሪ የሆነ የተፈጥሮ ነገር ገጥሞኛል። እሱም የወር አበባ ነው፡፡
ኢ    የወር አበባሽን ስታዪ የመጀመሪያ ጊዜሽ ነው?
እን    አ…አ…ይ...አሁን ወደ ስድስተኛ ጊዜ ሆነኝ …
ኢ    እሺ…ምንድነው አስቸጋሪ የሆነ ነገር ያልሽው..?
እን    እኔ. .በጣም ጤነኛ.. ከወር እስከወር እንደልቤ የምሯሯጥ… ምንም አይነት ሕመም ገጥሞኝ የማያውቅ…. ጤነኛ ሴት ነበርኩ
ኢ    ታድያ አሁን ምን  ተፈጠረ?
እን    አሁንማ..ልክ የወር አበባዬ ሲመጣ አንድ ቀን ሲቀረው ጀምሮ… የተለያዩ ስሜቶች ይመጡብኛል፡፡
ኢ    ምንድናቸው… ስሜቶቹ?
እን    እራስ ምታት… ሆድ ቁርጠት…ትኩሳት… የመሳሰሉት ሁሉ ይመጡብኛል…
ኢ    እሺ…
እን    በትምህርት ክፍል በሰላም ተቀምጬ መማር አልችልም፡፡ ዝም ብዬ እቤቴ ብተኛ ደስ ይለኛል፡፡ ግራ ገብቶኛል፡፡
--///--
በአንድ ወቅት ለዚህ እትም ማብራሪያ የሰጡት ዶ/ር መብራቱ ጀምበር የጽንስና ማህጸን ሕክምና እስፔሻሊስት እንዳብራሩት የወር አበባ ማለት አንዲት ሴት ልጅ በእድሜዋ ከፍ ስትል ማለትም ወደ አስራዎቹ ክልል ስትገባ ጀምሮ ከማህጸንዋ መፍሰስ የሚጀምር ንጹህ ያልሆነ ደም ነው። በተፈጥሮ በወር በወሩ የማህጸን ግድግዳ ጽንስ ይፈጠራል በማለት የሚዘጋጅ ሲሆን ጽንሱ ሳይፈጠር ሲቀር ግን ይፈራርስና ወደፈሳሽነት ተለውጦ ይወርዳል፡፡ የወር አበባ ከ3-5 ቀን ድረስ ሊፈስ የሚችል ነው፡፡ የወር አበባ ተፈጥሮአዊ የሆነ እና በመፍሰሱም ምንም የሚቀ ንሰው ነገር የሌለው እንዲሁም ጉዳት የማያስከትል ነው፡፡ ነገር ግን የወር አበባ መፍሰስ በሚጀምርበት ጊዜ አንዳንድ ሴቶች መጠነኛ በሆነ ደረጃ ያልተመቻቸ ስሜት ሊኖራቸው የሚችል ሲሆን አንዳንዶች ደግሞ በከፍተኛ ሁኔታ ለህመም የሚዳረጉ መሆኑ እሙን ነው ብለዋል፡፡
ዶ/ር መብራቱ አክለውም የወር አበባ የሚበዛባቸው ሴቶች ከማህጸን ችግር ጋር የተያያዘ ምክንያት ሊኖራቸው እንደሚችል መጠርጠር ይገባቸዋል፡፡ ለምሳሌ እጢ፤ መመረዝ፤ ጭንቀት  የመሳሰሉት ነገሮች የወር አበባ በሚመጣት ጊዜ ሕመምን ሊያስከትል የሚችል ነው፡፡ ከወር አበባ ጋር በተያያዘ የሚከሰተውን የህመም ስሜት በተለያየ መንገድ መግለጽ ይቻላል፡፡ ለህክምና የሚመጡት ሴቶች እንደሚገልጹት ከሆነ የወገብ መከትከት፤ ማህጸን አካባቢ ጭብጥ ማድረግ፤ የእግር ማበጥ፤ የጡት ሕመም፤ ራስ ምታት፤ የባህርይ ለውጥ የመሳሰሉ የጤና ጉድለቶች ሊከሰቱ ይችላሉ፡፡
የወር አበባ ህመም በምንም አይነት ምክንያት ሊከሰት ይችላል፡፡ ለምሳሌም…የማህጸን በር ጠባብ መሆን የሚፈሰውን ደም እንደልብ ስለማያስተላልፍ ማህጸን ደሙን ለማስወጣት ሲል የሚያደርገው ትግል በሴቶቹ ላይ ሕመም ሊያስከትል ይችላል፡፡
ይህ አይነቱ ህመም ምንም አይነት ምክንያት ሳይኖር የሚፈጠር የህመም ስሜት ሲሆን እንደ እጢ የመሳሰሉ ችግሮች ባሉበት ሁኔታ ግን ምክንያታዊ የሆነ ሕመም ይባላል ብለዋል ዶ/ር መብራቱ ጀምበር የጽንስና ማህጸን ሕክምና እስፔሻሊስት፡፡
በወር አበባ ጊዜ የሚከሰተው ሕመም በሁለት ይከፈላል፡፡ እሱም primary dysmenorrhea እና “secondary dysmenorrhea በመባል የሚታወቅ ነው። የመጀመሪያው 90% በመሆኑ ሴቶች ላይ የሚከሰት ሲሆን እሱም በአብዛኛው ልጅ በመውለድ መፍትሔ የሚያገኝ ነው። በመቀጠል የተመለከተው ደግሞ ብዙ ሴቶች ላይ የማይከሰት ነገር ግን ሕመሙ በቀላሉ መፍትሔ የማያ ገኝ ነው፡፡ መፍትሔ የሚገኘው ምናልባት በህክምና እርዳታ ከተደረገ ሊሆን ይችላል፡፡  
ማንኛዋም ሴት በግልዋ በወር አበባ ጊዜ የሚሰማትን ሕመም ለማስታገስ የምትችልባቸው መንገዶች አሉ፡፡  
ቅዝቃዜን ማስወገድ፡-
ሰውነት እንዲፍታታ ለማድረግ እግርን ወይም መላ የሰውነት አካልን በሙቅ ውሀ ውስጥ መዘፍዘፍ፤ ልብስ ደርቦ መልበስ ወይንም ከጥጥ የተሰሩ የውስጥ ሱሪዎችን ማዘውተር ሙቀት ለማግኘት ይረዳል፡፡
የጀርባ ግፊት (Counter Pressure)
አንዲት ሴት በወር አበባ ጊዜ ሕመም ሲሰማት ጀርባዋን በእጅ እንደማሸት ጫን ጫን በማድረግ ህመሙን ማስታገስ ይቻላል።
ማረሳሳት፡-
አንዲት በወር አበባ ምክንያት የህመም ስሜት ያለባትን ሴት ስለሕመሙዋ ረስታ ስለሌላ ነገር እንድታስብ ለማድረግ ማጫወት ወይንም የተለየ ነገር መጋበዝ በመሳሰለው መንገድ መርዳት ህመሙን እንድትረሳው የሚያደርጋት መሆኑን እና ስቃዩንም እንደሚቀንስላት የህክምና ባለሙያዎች ይመሰክራሉ፡፡
መረጋጋት፡-
በወር አበባ ወቅት ሕመም የሚሰማት ሴት እንድትረጋጋ የሚያስችላት የመዝናኛ መንገዶችን ብታስብ ሕመሙዋን ከማሰላሰል ስለምትቆጠብ ጭንቀትዋን ያስወግድላታል።
ጤናማ የአመጋገብ ልምድ፡-
በወር አበባ ጊዜ ፍራፍሬዎችን ማዘውተር፤ ከ6-8 ብርጭቆ ውሀ በየቀኑ መጠጣት፤እንደ ቡና፤ ቸኮላት የመሳሰሉትን ምግቦች መቀነስ፤ ስኩዋር እና ሶዲየም ያላቸውን ምግቦች መቀነስ ሕመሙን ለማስታገስ ይረዳል፡፡
አካላዊ እንቅስቃሴ ማድረግ፡-
አንዲት ሴት በወር አበባዋ ወቅት ብቻ ሳይሆን ምንጊዜም የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ወይንም የእግር ጉዞ ብታደርግ በጣም ይጠቅማታል፡፡


Read 13141 times