Print this page
Saturday, 25 December 2021 13:49

ኮሮና በመላው አለም በየሳምንቱ 50 ሺህ ሰዎችን እየገደለ ነው

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

       -ናይጀሪያ 1 ሚ. ክትባት ስታስወግድ፣ ቻይና 13 ሚ. ሰዎችን ከቤት እንዳይወጡ ከልክላለች
         -አምና ብቻ ከ5 ሚ. በላይ የአለማችን ህጻናት ለሞት ተዳርገዋል

         በአሁኑ ሰዓት በመላው አለም በኮሮና ቫይረስ ሳቢያ በየሳምንቱ በአማካይ 50 ሺህ ያህል ሰዎች ለሞት እንደሚዳረጉና በመላው አለም በቫይረሱ ሳቢያ ለሞት የተዳረጉት ሰዎች ቁጥር ባለፈው የፈረንጆች አመት 2020 በኤችአይቪ ኤድስ፣ ወባና ሳምባ ነቀርሳ ከሞቱት ሰዎች ድምር ቁጥር እንደሚበልጥ የአለም የጤና ድርጅት ባለፈው ረቡዕ አስታውቋል፡፡
የኮሮና ቫይረስ ክትባቶችን በአለማቀፍ ደረጃ በፍትሃዊነት ለማዳረስ አለመቻሉ በተለይ በድሃ አገራት በርካታ ሰዎች በቫይረሱ ሳቢያ ለሞት እንዲዳረጉ ሰበብ መሆኑን ባለፈው ረቡዕ ከጄኔቫ በሰጡት መግለጫ ያስታወቁት የድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም፤ ወረርሽኙ ከተከሰተበት ጊዜ አንስቶ በመላው አለም ከ3.5 ሚሊዮን በላይ ሰዎችን መግደሉንም አስታውሰዋል፡፡
እስከዚህ ወር መጨረሻ ድረስ ከአጠቃላይ ህዝባቸው 40 በመቶ ያህሉን ለመከተብ እቅድ ይዘው ከነበሩት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አባል አገራት መካከል እቅዳቸውን ማሳካት የቻሉት ግማሽ ያህሉ ብቻ መሆናቸውን የጠቆሙት ዳይሬክተሩ፣ ክትባቶች በፍትሃዊነት ለመዳረስ ካለመቻላቸው ጋር በተያያዘ ድሃ አገራት ወደኋላ ለመቅረት መገደዳቸውን አስረድተዋል፡፡
በሌላ የኮሮና ቫይረስ ዜና ደግሞ፣ በቻይናዋ ዢያን ከተማ አዳዲስ የቫይረሱ ተጠቂዎች ቁጥር መጨመሩን ተከትሎ 13 ሚሊዮን ያህል ዜጎች ከቤታቸው እንዳይወጡ ባለፈው ረቡዕ የእንቅስቃሴ ገደብ እንደተጣለባቸው ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ፣ 2 በመቶ ህዝቧን ብቻ የከተበችው ናይጀሪያ በእርዳታ ያገኘቻቸውንና ሳትጠቀምባቸው ጊዜያቸው ያለፈባቸውን 1 ሚሊዮን የአስትራዜኒካ የኮሮና ቫይረስ ክትባቶችን ባለፈው ረቡዕ ማስወገዷ ተነግሯል፡፡
በሌላ ዜና ደግሞ፣ ባለፈው የፈረንጆች አመት 2021 በመላው አለም ከ5 ሚሊዮን በላይ ህጻናት በተለያዩ ምክንያቶች ለሞት መዳረጋቸውንና አብዛኞቹ ለሞት የተዳረጉት መከላከል ወይም ታክመው መዳን በሚችሉ በሽታዎች ሰበብ መሆኑን  የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አስታውቋል፡፡
ከሰሃራ በታች ያሉ የአፍሪካ አገራትና የደቡባዊ እስያ አገራት በአለማችን ከፍተኛ የህጻናት ሞት የተመዘገበባቸው መሆናቸውንም የተቋሙ ሪፖርት አመልክቷል፡፡

Read 1692 times
Administrator

Latest from Administrator