Tuesday, 28 December 2021 00:00

የዱባዩ ገዢ ለ6ኛ ሚስታቸው 730 ሚ. ዶላር እንዲከፍሉ ተወሰነ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

    ባይደን ቸር ቢያደርሰኝ በቀጣዩ ምርጫ እወዳደራለሁ አሉ

              የዱባዩ ገዢ ሼክ ሞሃመድ ቢን ራሺድ አል-ማክቱም በቅርቡ በፍቺ ለተለዩዋቸው የቀድሞዋ ባለቤታቸው ለልዕልት ሃያ ቢንት አል-ሁሴን እና ለሁለት ልጆቻቸው በካሳ መልክ 730 ሚሊዮን ዶላር እንዲከፍሉ በፍርድ ቤት እንደተወሰነባቸው ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
የ72 አመቱ ሼክ ሞሃመድ ቢን ራሺድ አል-ማክቱም በፍቺ ለተለዩዋቸውና በአሁኑ ወቅት በእንግሊዝ ለሚገኙት የ47 አመቷ ልዕልት ሃያ ቢንት አል-ሁሴን የጥበቃና የጌጣጌጦች ግዢን ጨምሮ ለተለያዩ ወጪዎች የተጠቀሰውን ገንዘብ እንዲከፍሉ በእንግሊዝ የሚገኝ ፍርድ ቤት ባለፈው ማክሰኞ መወሰኑን ነው ዘገባው ያመለከተው፡፡
የተባበሩት አረብ ኤሜሪቶች ጠቅላይ ሚኒስትርና ምክትል ፕሬዚዳንት ለሆኑት ሼክ ሞሃመድ ቢን ራሺድ አል-ማክቱም በ2004 ካገቧቸው ስድስተኛ ሚስታቸው ልዕልት ሃያ ቢንት አል-ሁሴን የ14 አመት ሴትና የ9 አመት ወንድ ልጆችን መውለዳቸውን ያስታወሰው ዘገባው፣ ልዕልቷ በ2019 #የተለያዩ በደሎች ያደርሱብኛል ለደህንነቴ እሰጋለሁ; በማለት ወደ እንግሊዝ መሄዳቸውንና የፍቺው ሂደት መጀመሩን አክሎ ገልጧል፡፡
በሌላ ዜና ደግሞ፣ የጤናቸው ጉዳይ አሳሳቢ ደረጃ በመድረሱ ለቀናት ከስራ ገበታቸው ርቀው የሰነበቱት የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን፤ ጤና ከከረምኩ በቀጣዩ ምርጫ እወዳደራለሁ ሲሉ መናገራቸውን ሲጂቲኤን ዘግቧል፡፡
ባይደን ባለፈው ረቡዕ ከኤቢሲ ኒውስ ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ፣ የጤናቸው ጉዳይ ካላሰናከላቸው በስተቀር በመጪው የ2024 የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ የመወዳደር እቅድ እንዳላቸው መናገራቸውን ነው ዘገባው ያመለከተው፡፡

Read 9837 times