Sunday, 02 January 2022 20:18

ወደ አገር ቤት የመጡ ዳያስፖራዎች ምን ይላሉ

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(5 votes)

አገሬ እንዲህ ሰላም ሆና የማገኛትም አልመሰለኝም ነበር
   ከኖርኩባቸው 47 ዓመታት ሰሞኑን ያሳለፍኳቸው 7 ቀናት ለኔ ትርጉም ያላቸው ነበሩ
  ወደ አገራችን የምንመጣው ስለተጠራን ብቻ አይደለም፤ ለአገራችን አሁን ስለምናስፈልጋትም ነው
                    
               ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ በውጪ አገር ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ባቀረቡት ጥሪ መሰረት በርካቶች ወደ አገራቸው እየገቡ ነው። የቦሌው አለም አቀፍ አየር ማረፊያ ገቢ እንግዶችን በመቀበል መጨናነቅ ከጀመረ ቀናት ተቆጥረዋል። ወደ አገራቸው እየገቡ የሚገኙት ዲያስፖራዎች ፊት ላይ ከፍኛ ደስታ፣ ጉጉትና ተስፋ ይነበባል። አየር መንገዱ ገቢ መንገደኞችን በአደይ አበባ ምንጣፍ በልዩ ሁኔታ የእንኳን ደህና መጣችሁ ሞቅ ያለ አቀባበሉን እያደረገላቸው ይገኛል።
ታህሳስ 20 ቀን 2014 ዓ.ም በመንግስት ደረጃ በይፋ የተጀመረው የአቀባበል  ስነስርዓትም በተለያዩ አካባቢዎች በልዩ ልዩ ፕሮግራሞች ቀጥሏል። እንግዶቹም እየተደረገላቸው ባለው አቀባበል መደሰታቸውንና ወደ አገራቸው ሲመጡም ብዙ ተስፋ ሰንቀው መምጣታቸውን ይገልጻሉ።
ናሆም ተስፋዬ ኑሮውን በካናዳ ኦቶአ ከተማ ካደረገ 17 ዓመታትን አስቆጥሯል። ከአገሩ ከወጣ በኋላ ወደ አገር ቤት የመመለስ ዕድሉን አላገኘም። ለብዙ ጊዜያት ወደ ኢትዮጵያ የመምጣት ፍላጎት ቢኖረውም ሁኔታዎች ሳይመቻቹለት በመቅረታቸው ዓመታን በናፍቆት እየተብሰከሰከ አሳልፏል።
በመጪው ፋሲካ ወደ አገሩ ለመምጣት ዕቅድ ይዞ ነበረ ቢሆንም በጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ ተደረገው ጥሪ ሃሳቡን ቀይሮ ጉዞውን ለገና እንዲያደርግ ይህም ትክክለኛ ውሳኔ እንደሆነ ይነገራል። “ወደ አገሬ ለመምጣት ያቀድኩት ለትንሳኤ  በዓል ነበር። ነገር ግን ኢትዮጵያ ትንሳኤዋ በሚበሰርበት በዚህ ወቅት እዚህ አለመገኘት ስህተት መስሎ ተሰማኝ። የአገሬን ትንሳኤ ከምወዳቸው ወገኖቼ ጋር አብሬ ለማክበር መጥቻለሁ። ወደ አገሬ በመምጣቴም በጣም ደስተኛ ነኝ” ብሏል።
በኢትዮጵያ በሚኖረው የሰባት ሳምንታት ቆይታ ወደ ሰሜኑ የአገራችን ክፍል በመንቀሳቀስ በጥፋት ሃይሎች የወደሙትን አካባቢዎች ለማየትና ጉዳት የደረሰባቸውን ወገኖች ለማጽናናት ዕቅድ መያዙንም አጫውቶኛል። ከአሜሪካ ቴክሳስ ከተማ በቡድን ወደ አገራቸው የመጡት 6 የህክምና ባለሙያዎች ዕቅዳቸው በሙያቸው ለወገኖቻቸውና ለአገራቸው የበኩላውን ድጋፍ ለማድረግ ነው። በዶክተር  ኤርሚያስ ዳንኤል ተመራውና 6 አባላት ያሉት ይሄው ቡድን፤ ኢትዮጵያ የደረሰው ታህሳስ 9 ቀን 2014 ዓ.ም ነበር ቡድኑ ወደ ሸዋሮቢት፣ ደብረብርሃንና፣ ደብረሲና አካባቢዎች በመንቀሳቀስ በጦርነቱ ሳቢያ ጉዳት ለደረሰባቸውና ህክምና ለሚስፈልጋቸው በርካታ ሰዎች ቀዶ ህክምናን ጨምሮ የተለያዩ አይነት ህክምናዎችን ሲሰጡ ቆይቶ ተመልሷል። ቡድኑ ለሰባት ቀናት ባደረገው ቆይታም አሸባሪው የህውኃት ኃይል በንፁሃን ላይ ያደረሰውን ዘግናኝ ጥቃት በስፋት ለማየት ዕድል ማግኘቱን የቡድኑ አስተባባሪ ዶ/ር ኤርሚያስ ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል።
“አገራችን እገዛችንን በምትፈልግበት ጊዜ ልንደርስላት እንደሚገባን በማመናችን በተለያዩ ስቴቶች ውስጥ የምንገኝ የሙያ አጋሮች ተነጋግረንና ሁኔታዎችን አመቻችተን በአንድ ላይ ወደ አገራችን ለመምጣትና ትንሽ እገዛ ለማድረግ ሞክረናል። ይህ እኛ ለአገራችን ልናደርግላት ከሚገባን እጅግ ትንሹ ነገር ነው። በቀጣይ ሁኔታዎችን እያመቻቸን በቡድን በመምጣት የምንችለውን እገዛና ድጋፍ ልናደርግ ተስማምተናል።” ብሏል- ዶ/ር ኤርሚያስ።
በምንኖርበት አካባቢ የሚገኙ ኢትዮያውያንን በማስተባበርም ትርጉም ሊኖረው የሚችል ድጋፍ እናደርጋለን። ለጊዜው የመጣንበትን ዓላማ አሳክተን ወደየመጣንበት እንመለሳለን። በልባችን የያዝነው ግን ገና ከፍ ያለ ስራ ነው ይላሉ- የህክምና ባለሙያዎቹ። በዚህች ምድር ከኖርኩባቸው 47 ዓመታት ትርጉም ያለው ህይወት ኖርኩ ብዬ የማምነው አሁን ኢትዮጵያ ያሳለፍኩትን 7 ቀናት ነው። ለምትወጃት አገርሽ አቅምሽ የሚችለውን ከማድረግ በላይ ምን የሚያስደስት ነገር ይኖራል ይላሉ ዶ/ር ኤርሚያስ።
ከስዊድን ስቶክሆልም ከተማ የመጡት ዮሐንስ ፍቃዱና ሔርሜላ ዘሪሁን የተባሉ ሁለት ትውልደ ኢትዮጵያውያን፤ ወደ አገራችን  የመጣነው ስለተጠራን ብቻ አይደለም። በዚህ ወቅት ለአገራችን ስለምናስፈልጋትም ጭምር ነው። በምንኖርበት አገር በተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን የምንሰማው ኢትዮጵያ ፈራርሳ ህዝቦቿ ተፈናቅለውና ተሰደው የሞት ምድር እንደሆነች ነበር። ስንመጣ ያየነው ግን እጅግ አስገራሚ ለውጥ ውስጥ ያለች ሰላማዊና የተረጋጋች ሆና ነው። የጠቅላይ ሚኒስትራችን ጥሪና የዲያስፖራው ምላሽ የኢትዮጵያን ውድቀት ለሚመኙላት ምዕራባውያን ትልቅ ኪሳራ ነው። አገራችን ዛሬም ከፍ እንዳለች መሆኗን ለዓለም ምናረጋግግጥበት ጥሩ አጋጣሚም ነው ብለዋል።ከአውስትራሊያ ሜልቦርን የመጣችው ትውልደ ኢትዮጵያዊቷ ገነት አማረ ደግሞ እንዲህ ትላለች። ወደ አገሬ የመጣሁት በአቅሜ ማድረግ የምችለውን ድጋፍ ለማድረግ ነው። ራሴና በአውስትራሊያ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ጓደኞቼን አስተባሬ የገዛኋቸውን ዊልቸሮችና የህክምና ቁሳቁሶችም ይዤ ነው መጣሁት። እነዚህ ቅሳቁሶች በአሁኑ ወቅት እጅግ አስፈላጊና ጠቃሚ   ናቸው። ወደ ኢትዮጵያ ስመታ ቁሳቁሶቹን ለማጓጓዝ መክፈል ይኖርብኛል ብዬ አላሰብኩም ነበር። ነገር ግን የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለእቃዎች ጭነት 20% ቅናሽ ብቻ በማድረግ አስከፍሎኛል። አየር መንገዱ እነዚህን እቃዎች በነጻ እንዲጓጓዙ ማድረግ ነበረበት ብዬ አስባሁ። ምክንያም ዕቃዎቹን ለማሰባሰብ የሚደረገውን ጥረት ከግምት ማስገባት ስለሚስፈልግ ነው። ያም ሆኖ ይዤው የመጣሁት ነገር በትክክል ለተጠቃሚ ወገኖቼ ሲደርስ ካየሁ ለእኔ ትልቁ ነገር  እሱ ነው።
ኢትዮጵያውያኑና ትውልደ ኢትዮጵያውያኑ በአገራቸው በሚኖራቸው ቆይታ ያለምንም የፀጥታ ችግር መንቀሳቀስ እንዲችሉ በቂ የደህንነት ጥበቃ እንደሚደረግላቸው በአገር አቀፍ ደረጃ የተቋቋመው ጥምር የፀጥታ ሃይል አስታውቋል።
ከአገር መከላከያ ሰራዊት ፣ ከሪፐብሊካን ጋርድ፣ ካፌ ደራል ፖሊስ፣ ከአዲስ አበባ ፖሊስ፣ ከኦሮሚያ ክልል ፖሊስና ከብሄራዊ መረጃና ደህንነት የተውጣጣው ጥምር የፀጥታ ሃይል ኢትዮጵያውያኑና ትውልደ ኢትዮጵያውያኑ ወደ አገር ቤት በሚመጡበትና በሚቆዩበት ጊዜ ያለምም የሰላምና ፀጥታ ስጋት መንቀሳቀስ እንደሚችሉም ገልጿል። ወደ አገራቸው የሚመጡ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያንን ለመቀበል የተቋቋመው ብሔራዊ ኮሚቴ በበኩሉ፤ እንግዶቹ ታህሣስ 24 ቀን 2014 በአዲስ አበባ የሚገኙ ፕሮጀክቶችን የማስጎብኘት፣ ከታህሳስ 25 ቀን 2014 እስከ ታህሳስ 27 ቀን 2014 ዓ.ም ድረስ ደግሞ በጦርነቱ የተጎዱ አካባቢዎችን የማስጎብኘት ፕሮግራሞችንና ሌሎች መርሃ ግብሮችንም ማዘጋጀቱን ይፋ አድርጓል።



Read 12760 times