Saturday, 01 January 2022 00:00

አለማችን በተሸኘው የፈረንጆች አመት 2021

Written by 
Rate this item
(0 votes)

ከፖለቲካ እስከ ኢኮኖሚ፣ ከንግድ እስከ ሳይንስና ቴክኖሎጂ፣ ከባህልና ስነጥበብ እስከ ተፈጥሮ አደጋዎች በአለማችን በየአቅጣጫው እጅግ በርካታ መልካምና መጥፎ ክስተቶችን ያስተናገደው የፈረንጆች አመት 2021 ትናንት ተጠናቅቋል፡፡
የአለማችን ስመጥር መገናኛ ብዙሃን በአመቱ ትኩረት ሰጥተው ሽፋን ከሰጧቸው የአመቱ ዋና ዋና ደግም ሆነ ክፉ ክስተቶች መካከል የተወሰኑትን በወፍ በረር እናስቃኛችሁ ዘንድ ወደደን - እነሆ!

ዘንድሮም ኮሮና
ባለፈው የፈረንጆች አመት 2020 የአለማችን ዋነኛ መነጋገሪያ ክስተት ሆኖ ያለፈው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ፣ በ2021ም አቻ ያልተገኘለት አለማቀፋዊ ጉዳይ ሆኖ ማለፉን ነው መገናኛ ብዙሃን የሚገልጹት፡፡
ቫይረሱ በወረርሽኝ መልክ ከተቀሰቀሰበት ጊዜ አንስቶ 5.4 ሚሊዮን ሰዎችን ለሞት መዳረጉ የተነገረ ሲሆን፣ አመቱ ሊሸኝ በጣት የሚቆጠሩ ቀናት ብቻ ሲቀሩት የተሰማው ወሬም ነገርዬው እንዳምናውና ዘንድሮው ሁሉ ለመጪው አመትም ግንባር ቀደሙ የአለማችን ትኩሳት ሆኖ እንደሚቀጥል የሚያሳይ ነው፡፡
አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ረቡዕ ዕለት እንዳለው፤ ባለፈው ሳምንት ብቻ በመላው አለም 7.3 ሚሊዮን ሰዎች በኮሮና ቫይረስ የተጠቁ ሲሆን፣ ይህም ቁጥር ወረርሽኙ ከተከሰተበት ጊዜ አንስቶ የተመዘገበ ከፍተኛው ሳምንታዊ አለማቀፍ የቫይረሱ ተጠቂዎች ቁጥር ነው ተብሏል፡፡

ከፖለቲካው ጎራ
የፈረንጆች አመት 2021 በገባ በ6ኛው ቀን ላይ ነበር፣ የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ደጋፊዎች ነጩን ቤተ መንግስት እንደ አሸን በመውረርና ጥፋት በመፈጸም ለ5 ሰዎች ሞት ምክንያት በሆነው ጋጠወጥ ድርጊታቸው የዲሞክራሲ ፈር ቀዳጅ የምትባለዋን አሜሪካ በመላው አለም አፍ በሃሜት እንድትብጠለጠል ያደረጉት፡፡ ይህ ከሆነ ከሁለት ሳምንታት በኋላም አሸናፊው ጆ ባይደን ስልጣን በይፋ ተቀብለው ካማላ ሃሪስን የመጀመሪያዋ ሴት ጥቁር አሜሪካዊት ምክትል ፕሬዚዳንታቸው አድርገው ሾመዋል፡፡
እስራኤልና ፍልስጤም አስከፊ ወደተባለ ፍጥጫ የገቡትና እስራኤል ጋዛን ከ3 ሺህ 200 በላይ ሮኬቶችን በማስወንጨፍ በአየር ጥቃት ዶግ አመድ ያደረገችውና ከ240 በላይ ሰዎች ለሞት የተዳረጉትም ባለፈው አመት ግንቦት ወር ላይ ነበር፡፡
በእስራኤል ታሪክ ለረጅም ጊዜ በጠቅላይ ሚኒስትርነት ያገለገሉት ቤንያሚን ኔታኒያሁ ለ12 አመታት ከቆዩበት ስልጣናቸው የተነሱት በሰኔ ወር ላይ ነበር፡፡
የአሜሪካ ጦር ለ2 አስርት አመታት ከቆየባት አፍጋኒስታን ለቅቆ መውጣቱን ተከትሎ፣ ታሊባን መዲናዋን ካቡል ዳግም የተቆጣጠረውም በዚሁ አመት ነሃሴ ወር ላይ ነበር፡፡
በተሸኘው የፈረንጆች አመት 2021 በአፍሪካ አራት ስኬታማ ወታደራዊ መፈንቅለ መንግስቶች የተደረጉ ሲሆን፣ በመፈንቅለ መንግስት የስልጣን ንጥቂያ የተደረገባቸው አገራትም ቻድ፣ ማሊ፣ ጊኒ እና ሱዳን ናቸው፡፡
በአፍሪካ በአመቱ አልቃይዳን ጨምሮ በተለያዩ ጽንፈኛ ቡድኖች አማካይነት የተለያዩ የሽብር ጥቃቶች መፈጸማቸው የተነገረ ሲሆን፣ የሽብር ጥቃቶች ከተፈጸሙባቸው አገራት መካከልም ሶማሊያ፣ ሞዛምቢክ፣ ኒጀርና ኡጋንዳ እንደሚገኙበት ለማወቅ ተችሏል፡፡ በአመቱ አለማችን ካስተናገደቻቸው ሌሎች አቢይ ክስተቶች መካከልም የቤላሩስና ፖላንድ የድንበር ቀውስ ይገኙበታል፡፡
ኢኮኖሚ
በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝና በተለያዩ ምክንያቶች ሲፈተን የከረመው የአለማችን ኢኮኖሚ በ2021 የ5 ነጥብ 5 በመቶ ዕድገት ማስመዝገቡ የተነገረ ሲሆን የሸቀጦች እጥረት፣ የማጓጓዣ ችግር እና መሰል ተግዳሮቶች በአመቱ በአለማቀፍ ደረጃ የዋጋ ግሽበት እንዲፈጠር ሰበብ መሆናቸው ተዘግቧል፡፡
ከቀናት በፊት ይፋ የተደረገ አንድ አለማቀፍ ጥናትም፤ የአለም ኢኮኖሚ በመጪው የፈረንጆች 2022 ለመጀመሪያ ጊዜ ከ100 ትሪሊዮን የአሜሪካ ዶላር በላይ ይደርሳል ተብሎ እንደሚጠበቅ አመልክቷል፡፡
የአለማችን አጠቃላይ ሃብት ከ20 አመታት በፊት ከነበረበት 156 ትሪሊዮን ዶላር በሶስት እጥፍ ያህል በማደግ በአመቱ 514 ትሪሊዮን ዶላር መድረሱና ቻይና አሜሪካን በመብለጥ ቁጥር አንድ የአለማችን ሃብታም አገር ለመሆን መብቃቷም በአመቱ ከተሰሙ የኢኮኖሚው ዘርፍ ዋነኛ ጉዳዮች መካከል ይገኙበታል፡፡

የተሸኙ መሪዎች
ለ16 አመታት በስልጣን ላይ የቆዩት የጀርመኗ መራሂተ መንግስት አንጌላ መርኬል አመቱ ሲገባደድ ስልጣናቸውን ማስረከባቸው ተሰምቷል፡፡ ያልታወቁ ታጣቂዎች የሃይቲውን ፕሬዚዳንት ጆቬኒል ሞይሴን ቤተመንግስታቸው ድረስ ገብተው በእሩምታ ተኩስ የገደሉትና ባለቤታቸውን ክፉኛ ያቆሰሉትም በ2021 አመት ነበር፡፡
በማይንማር የጦር ሃይሉ በየካቲት ወር የመጀመሪያዋ ቀን የአገሪቱን መሪ አን ሳን ሱኪን ከመንበረ ስልጣናቸው በማንሳት እስር ቤት ወርውሮ ስልጣኑን መያዙን ያወጀ ሲሆን፣ ሚያዝያ ላይ ደግሞ ራኡል ካስትሮ ለአስርት አመታት የያዙትን የኩባ ኮሚኒስት ፓርቲ መሪነት ድንገት መልቀቃቸውን አውጀዋል፡፡

ተቃውሞና አመጽ
በኮሮና ቀውስ አሳር መከራዋን ስታይ የከረመችው አለማችን በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ በፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ሰበቦች በተለኮሱ የተቃውሞና የአመጽ እሳቶች ስትለበለብ ነው አመቱን ያሳለፈችው፡፡
አገራት በኮሮና ስጋት ዜጎችን እንዳይሰባሰቡ ቢከለክሉም ከአሜሪካ እስከ አውሮፓ፣ ከእስያ እስከ አፍሪካና መካከለኛው ምስራቅ ክልከላውን ከመጤፍ ያልቆጠሩ በርካታ ተቃዋሚዎች ጎዳናዎችን አጥለቅልቀዋል፣ የአመጽ እሳቶችን አቀጣጥለዋል፡፡
በህንድ ገጠራማ አካባቢዎች አርሶ አደሮች የአገሪቱ መንግስት ያወጣውን የእርሻ ህግ በመቃወም ለወራት የዘለቀ ተቃውሟቸውን ያሰሙ ሲሆን፣ ከ700 በላይ የሚሆኑት ከመንግስት ሃይሎች በተከፈተባቸው ጥቃት ለሞት ተዳርገዋል፡፡
የዘመናት ገዢዋን ኡመር አልበሽርን በመፈንቅለ መንግስት ካስወገድችበት ጊዜ አንስቶ ፖለቲካዊ ቀውስ ውስጥ እንደተዘፈቀች የቀጠለችው ሱዳን፣ አመቱን ሙሉ በተቃውሞና በአመጽ እሳት ስትለበለብ ነበር የገፋችው፡፡
አመቱ በተለያዩ አገራት ከአየር ንብረት ለውጥ፣ የውርጃ ህጎች፣ የመብት ጥሰቶችና ሌሎች ጉዳዮች ጋር በተያያዘ በርካታ ተቃውሞዎችና የአመጽ እንቅስቃሴዎች የተቀጣጠሉበት እንደነበርም ዘገባዎች ያመለክታሉ፡፡

ከዚህ አለም በሞት የተለዩ
በአመቱ ይህቺን አለም ተሰናብተው ወደማይቀርበት ከሄዱ የአለማችን ዝነኞች መካከል የንግስት ኤልሳቤጥ 2ኛ ባለቤት ልዑል ፊሊፕ አንዱ ሲሆኑ፣ የታንዛኒያው ፕሬዚዳንት ጆን ማጉፉሊ በልብ ህመም ሳቢያ በ61 አመታቸው ለሞት መዳረጋቸው የተሰማውም በዚሁ አመት ነበር፡፡
የዛምቢያ መስራች እንደሆኑ የሚነገርላቸውና ከአፍሪካ የቅኝ አገዛዝ ታጋዮች አንዱ የሆኑት የቀድሞው የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ኬኔት ካውንዳ በተወለዱ በ97 አመታቸው ከዚህ አለም በሞት የተለዩት በሰኔ አጋማሽ ሲሆን፣ የ10 ሺህ ሜትር የአለም ክብረ ወሰን ባለቤቷ ኬንያዊቷ ዝነኛ አትሌት አግነስ ቲሮፕ በስለት ተወግታ መሞቷ የተሰማውም በጥቅምት ወር ላይ ነበር፡፡
የቀድሞው የአልጀሪያ ፕሬዚዳንት አብዱላዚዝ ቡተፍሊካ እና የቀድሞው የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት ፍሬድሪክ ዴ ክለርክ መሞታቸው ከተሰማ ከሳምንታት በኋላ፣ አመቱ ሊሸኝ የቀናት ዕድሜ ብቻ ሲቀሩት ደግሞ፣ በደቡብ አፍሪካ የቀለም ልዩነትንና አፓርታይድን ለማስወገድ በተደረገው ትግል ቁልፍ ሚና መጫወታቸው የሚነገርላቸውና የሰላም አቀንቃኝና አስታራቂ የሆኑት የኖቤል ሰላም ተሸላሚው ሊቀጳጳስ ዴዝሞን ቱቱ በ90 አመታቸው ከዚህ አለም በሞት መለየታቸው ተሰማ፡፡

የተፈጥሮ አደጋዎችና ሌሎች ክስተቶች
በአመቱ ሰደድ እሳትና የመሬት መንቀጥቀጥን ጨምሮ በርካታ የተፈጥሮ አደጋዎች በተለያዩ የአለማችን አካባቢዎች የተከሰቱ ሲሆን፣ ከፍተኛ ጥፋት ማስከተላቸው ተነግሯል፡፡
እ.ኤ.አ እስከ 2050 ድረስ በመላው አለም በአየር ንብረት ሳቢያ 216 ሚሊዮን ሰዎች ከመኖሪያ አካባቢያቸው ይፈናቀላሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም ከሰሞኑ የወጣ ሪፖርት አስታውቋል፡፡
በአመቱ በአሜሪካ፣ በቱርክና በአውስትራሊያ በሰደድ እሳቶች ሳቢያ በርካታ ደኖች መውደማቸውም ተነግሯል፡፡
በአፍሪካ የሙቀት መጠን ከተቀረው አለም በባሰ በከፍተኛ ሁኔታ በመጨመር ላይ እንደሚገኝና በዚህም ሳቢያ በአህጉሪቱ የሚኖረው 1.3 ቢሊዮን ህዝብ በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ ለሚፈጠሩ አደጋዎች በከፍተኛ ሁኔታ ተጋላጭ መሆኑንም ተመድ በቅርቡ ባወጣው ሪፖርት አስጠንቅቋል፡፡
በመጪዎቹ አስር አመታት ውስጥ 118 ሚሊዮን ያህል እጅግ በከፋ ድህነት ውስጥ የሚገኙ አፍሪካውያን ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር ተያይዘው ለሚከሰቱ የድርቅ፣ ጎርፍና የከፍተኛ ሙቀት ሰለቦች ይሆናሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም ይሄው ሪፖርት አሳስቧል፡፡
አደገኛ የሆነ እጅግ ከፍተኛ የሙቀት ክስተት ከአለማችን ከተሞች መካከል ግማሽ ያህል በሚሆኑት በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ እንደሚገኝና ክስተቱ በአለም ዙሪያ የሚገኙ ከ2 ቢሊዮን በላይ የከተማ ነዋሪዎችን ተጎጂ ማድረጉም ተነግሯል፡፡
በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ስጋት ሳቢያ ከተያዘለት መደበኛ ጊዜ ለአንድ አመት እንዲራዘም የተደረገው የ2020 የቶኪዮ ኦሎምፒክ በሃምሌ ወር መጨረሻ ላይ ተጀምሮ በነሃሴ አጋማሽ መጠናቀቁም አለም በበጎ ከምናስታውሳቸው የአመቱ ክስተቶች የሚጠቀስ ነው፡፡

የፈረንጆች አመት 2021 - በቁጥሮች
245 ሚሊዮን
በአመቱ በአለማችን የተለያዩ ጥቃቶች የደረሱባቸው ሴቶች ቁጥር
84 ሚሊዮን
እስካለፈው ወር ድረስ በመላው አለም በተለያዩ ምክንያቶች ከመኖሪያቸው የተፈናቀሉ ሰዎች ብዛት
9 ቢሊዮን
በመላው አለም በሚገኙ 184 አገራት የተሰጡ የኮሮና ቫይረስ ክትባቶች ብዛት
168 ሚሊዮን
በመላው አለም በኮሮና ሳቢያ ትምህርታቸውን ያቋረጡ ህጻናት ቁጥር
30 ሚሊዮን
ኮሮና ቫይረስ ከተከሰተበት ጊዜ አንስቶ ከስራ የተፈናቀሉ አፍሪካውያን ቁጥር
1.3 ቢሊዮን ቶን
በየአመቱ በመላው አለም ጥቅም ላይ ሳይውል ወደ ቆሻሻ ማጠራቀሚያ የሚጣለው ምግብ
48 ሺህ
በአመቱ በአፍሪካ አህጉር የደረሱበት ሳይታወቅ ደብዛቸው ጠፍቶ የቀሩ ሰዎች ቁጥር
1.3 ቢሊዮን
በመላው አለም የሚገኙ የሲጋራ አጫሾች ቁጥር
39 ሚሊዮን
በአመቱ ለከፋ ድህነት ሊጋለጡ ይችላሉ ተብለው የሚገመቱ አፍሪካውያን ቁጥርRead 792 times