Saturday, 01 January 2022 00:00

የከበደው ካሣ - እውነትም ካሣ ከበደ

Written by  ከኢሳይያስ ልሳኑ
Rate this item
(2 votes)

 «የዓለም ታሪክ የታላላቅ ሰዎች ግለ ታሪክ ድምር ነው ይልቁንም» - ቶማስ ካርላይል
                           
            ይኼ ካሣ ይሉት ስም በእኛ ሀገር ባለታሪኮችን ይከባል፡፡ - መይሳው ካሳ - በዝብዝ ካሳ .... እና ዛሬ ደግሞ ካሣ ከበደ። - የከበደው ካሣ!
ነፍስ ሔር እንበል አስቀድመን፡፡
ፋሺስት ጥልያን ኢትዮጵያን በወረረበት ጊዜ፣ በማይጨው የጦር አውድማ ዘምተው የነበሩት አባቱ ቆስለዋል፡፡ እና በስደት ከቀዳማዊ ሀይለ ስላሴ ጋር አብረው ኢየሩሳሌምም ሄደዋል፡፡ እዛም የኢትዮጵያ ስደተኞች ማህበር ም/ሊቀ መንበር ሆነው ነበር፡፡ የአርበኝነቱ ትግል ሲግምና ሲፋፋም፣ በሱዳን በኩል ሰርገው ገብተው ጠላትን ቁም ስቅሉን ካሳዩት አርበኞችም መካከል ናቸው፡፡ ያኔ ታዲያ ደጃዝማች ከበደ ተሰማ ከባለቤታቸው ከወ/ሮ ይታጠቁ ጋር ክፉው ጊዜ ለያይቷቸውም ነበር፡፡ ወ/ሮ ይታጠቁ በሸዋ አውራጃዎች በምንጃርና ቡልጋ ውስጥ የጨለማውን የጠላት ዘመንን በችግር አሳልፈዋል.- የነፃነት ጎህ እስኪቀድ - የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ እስኪውለበለብ ድረስ፡፡
“አባቴ የወለጋ ግዳጃቸውን (ጣሊያን በተባረረ በዚያው ዓመት) በ1934 ዓ.ም. ፈጽመው የአዲስ አበባ ከንቲባ በሆኑበት ወቅት ስለተወለድኩ ወላጆቼ በነፃነት መደፈር ምክንያት ያሳለፏቸውን የችግርና የመከራ ዓመታት በማሰብ ‘ካሣ’ ብለው ሰየሙኝ” ይላል ካሳ (ጦቢያ ታህሳስ 1988)። - አምባሳደር ዶ/ር ካሣ ከበደ፡፡
ልደት የካቲት 18 ቀን 1935 ዓ.ም.፡፡ ጣሊያን ከተባረረ ሁለት ዓመታት በሁዋላ፡፡
ታላላቅ ሰብዕናዎች ምድር ላይ ሲታዩ ወይም ሲገኙ ጥንታውያኑ ግሪኮች ‹ነፍሳቸውን ከአማልክት የተዋስናቸው ግዙፋን (ጃይንትስ) ናቸው’ ይሏል። እውነትም ያሰኛል - የከበደውን ካሣ ታሪኩን ሲያውቁት፡፡ የታላላቅ ሰዎችን ታሪክ ቀንጭቦ ለማቅረብ የሚሞክር የእኔ ቢጤ ሰው ‘በዳገት ጫፍ የምትጓዝ አይነት አድርገህ አስበው’ ይለዋል አንድ የዚህ የእንግልጣር ሀገር ጸሀፊ። ‘እንዳይዳልጥህ - ምሉዕም ላይሆንልህም ይችላል’ እንደማለት ያለ ነው፡፡
አምበሳደር ካሣ (አንተ ብዬ ለትርክቱ ባወጋ ፍቅሬን ለመግለጽ እንጂ አክብሮቴን አያነቅስብኝም - ይህን ያዙልኝ) ከልሂቅ እስከ ደቂቅ - ከማይም እስከ ሊቅ - ከብላቴና እስከ አረጋዊ - ሁሉን በማግባባት እንደ መራሄ ሙዚቃ ሁሉንም አቀናብሮ አቻችሎ - ተስማምቶና ሰምቶ - ተምሮና አስተምሮ - ወዶና ተወዶ የኖረ ሰው ነበረ። ኢትዮጵያ በዘመናት ካፈራቻቸው የውጭ ዲፕሎማሲ ቀራጺያንና ተግባሪ፣ ጥበብንና መለኝነትን የተካነ፣ ወደውም ይሁን ሳይወዱ የሚያደንቁት የጂኦ ፖለቲካ ክሂሎት ያለው አዋቂ ጭምር፡፡ ደግሞ ባህላዊውን አስተምህሮ ከዘመናዊው አዋህዶ ‘አራዳ’ (በብስል አዎንታዊ ፍቺው) የተባለለት ሰው ነው፡፡
እስራኤል እየሩሳሌም ሂብሩ ዩኒቨርስቲ ዋና የጥናት አሳሽና የኢትዮጵያ አይሁድ አማኞች ጥናት ዘርፍ ማህበር ፕሬዘደንት ዶ/ር ሻላቫ ዌይል «በጣም ያሳዝናል» ብለው ጀመሩ «ሰውየው ሲናገር አይደለም አጠገብህ ሲሆን አንዳች የገዘፈ ተፅዕኖ ያሳድርብሃል። በሄደበትና በተሰበሰበበት ስፍራ የሚቃወሙት ሳይቀሩ እንዲያጨበጭቡ የማድረግ ልዩ ተሰጥኦ አለው» ይሉኛል፤ በስልክ የዚህን ታላቅ ሰው ህልፈት ስነግራቸው፡፡  እርግጥ ነው አምባሳደር ካሳ በበርካታ ድንገቴዎች ይህን ችሎታውን ያሳየባቸው አጋጣሚዎች ሲነበቡና ሲሰሙ - የሲኒማ ቅንብር ነው የሚመስሉት፡፡ የመረጃ አሰባሰብና አተናተን - ሀገራዊ በሆኑ ጉዳዮች አሰላለፍን ሰንጥሮ እለፍ ተቀደሙን የማገናዘብ ችሎታው ደግሞ የጥንካሬዎቹ መገለጫ ናቸው፡፡ በዚህ የተነሳ ‘የእስራኤል የስለላ ድርጅት አባል (ሞሳድ) ነው’ እያሉ ያሙታል፡፡ “የሞሳድ ሰው አይደለም እንዴ?” የሚሉ ይበዙ ይሆናል- ዛሬ ድረስ፡፡ ትንግርት መሳይ ክሰተቶችን በህይወቱ አልፏልና ያ ሲተረክ ‘የስለላ ተውኔት’ ቢመስልም አይገርምም፡፡ እዛው እስራኤል አንድ ‘ወግ ጠራቂ’ ጸሀፊ ከበርካታ ዓመታት በፊት ይህንኑ የእኛን የካሣን ቅንጫቢ ታሪክ፣ ሲኒማ አስመስሎ ያወጋበት ሀቲት ተጨምሮ ብዙ አስብሏል፡፡ አራት ኪሎ ያኔ የነገሱትንም የሕወሓት ሰዎች ጭምር አስበርግጎ - አምባሳደር ካሣን ባለበት ስሙን አጥፍተን ካልከሰስነው’ ብለው ብዙም ርቀት ያልተጓዘ ሙከራ አድርገው ነበር፡፡ ለምሳሌ ከሆነ  በ2005 (1997) የምርጫ ጊዜ ባህር ማዶ ከተከሰሱትም ዝርዝር አምባሳደር ካሣን አስገብተውት እንደነበረ መጥቀስ ይቻላል፡፡ ታዲያ አንዳንዴ ጥቂት ሰዎች የሚከብዳቸውንና አግዝፈው የሚያዩትን ሁሉ እንዲቀላቸው በ’ሴራና’ በ’አሉ’ ወሬ ጠልፈው ለመጣል መሞከራቸው አይቀርምና ‘ስለላ’ የሚለውን ከዚያ ቋት አስቀምጠነው እንለፍ፡፡
ከሶስት አስርታቱ ዓመታት በፊት ወደ ነበረው ሁኔታ መለስ እንበል፡፡ የኮለኔል መንግስቱ ሃ/ማርያም መንግስት አጣብቂኝ ውስጥ የገባበት ጊዜ፡፡ በግራ ዘመሙ ስርዓት ውስጥ ከጃንሆይ ዘመን ሚኒስትርነት የተሸጋገረው አምባሳደር ካሣ፣ በግራ ዘመሙ ስርዓት ውስጥ ሲቀላቀል፣ ሀገርን በማገልገል ስሜትና ብሔራዊ ራዕይ ይዞ እንጂ ‘ካድሬነቱ’ እጅግም አልዋሃድ ያለውና ባዕድ ሆኖ እንደኖረ የሚያውቅ ያውቀዋል። የዘይትና የውሀ አይነት ግንኙነት ነበር። እርግጥ የሀገር ነገር ከደሙ ውስጥ አለ፡፡ ገና በለጋነቱ ሲሰማና ሲነገረው ያደገውም የጀግንነት ታሪክ ለመሆኑ “ያደግሁት በፋሽስቶች የተፈጸመውን ግፍ እየሰማሁ” እንዳለው ነውና እርሱ የተቀረጸበት ብሔራዊ ደህንነትና ብሄራዊ ጥቅም የመጠበቅ ወንጌል አብሮት እንደጸና አስተውለናል፡፡ በደርግ በስተመጨረሻው ዘመን ላይ ውል ከውል ማገናኘት በከበደበት ጊዜ - በዲፕሎማሲው ዓለም ኢትዮጵያን ወደ ጭላንጭል ብርሃን ለመውሰድ የተጫወተው ሚና በልዩ የሚጠቀስ ነው፡፡ ከቶውንም የከበደው ካሳ ከታየባቸው አጋጣሚዎች አንዱ ነው፡፡
ዩኤስ አሜሪካ ከአዲስ አበባ ጋር ሆድና ጀርባ ናት ያኔ፡፡ ኢትዮጵያ ደግሞ የቀዝቃዛው ዓለም ጦርነት ውስጥ የ›ቀድሞዋን ሶቪየት ህብረት› ካምፕ ውስጥ ነኝ ብላለች፡፡ ዛሬ መልሰው ጫካና ወህኒ የገቡት ሕወሀቶች አዲስ አበባ ለመግባት ‹አጥፍቶ መጥፋቱን› እንደዛሬው ጊዜ ተያይዘውታል፡፡ በዚህ መሀል ‹ሶቪየት ህብረት› እንደእምቧይ ካብ መናድ ጀምራለች፡፡ ኢትዮጵያ ህልውናዋ ከአደጋ ወደቀ፡፡ አማራጭ ፍለጋ በሀሳቡ ይፍተለተል ገባ፡፡ ኢትዮጵያን ከአሜሪካ ጋር የማግባባትና የ›ተሀድሶ› እርምጃን በሀገር ውስጥ የማስጀመር ሀሳብ  - ከዚያ ጦርነት ሀገሪቱን ማዳን ከእጁ የወደቀ አደራ ሆነ፡፡ ዩኤስ አሜሪካ የሻከረ ግንኙነቱዋን የማለሳለሱ ስራ አዳጋች እንደሚሆን ለአምባሳደር ካሳ ግልጽ ነበር፡፡ አፍቃሬ ኢትዮጵያን ባዕዳን እንዲረዱት ለማድረግ ደግሞ ከታሪካዊ ትስስሩ ጋር ተዳምሮ የአሜሪካ አይሁዳውያን ነገር ከልቡ ጠፍቶ አያውቅም፡፡ ደግሞ በአሜሪካ የፖለቲካ አውድ ያላቸውን ተፅዕኖ በቅርብ ያውቀዋል፡፡ እግር ጥሎት - ወይም ለስራ ዋሽንግተን ዲሲን ከረገጠ፣ አብረውት የእብራይስጥ ዩኒቨርስቲ የተማሩ የክፍል ጓደኞቹን አፈላልጎ ያገኛል፡፡ ወዳጅነትን መጠበቅ ያውቅበታል፡፡ ደግሞ አምባሳደር ካሣ እብራይስጡን ቋንቋ - የይዲሹን ዳይሌክት (ዘዬ) ጨምሮ እንደ አንደኛው ቋንቋ ያቀላጥፈዋልና አይሁዳውያን አሜሪካውያኑ ይወዱለታል፡፡ ጨዋታውንም አብልጠው፡፡ ሁለቱ ባልና ሚስት የአይሁድ አሜሪካውያን ዶክተሮች ጃክ ዜለርና ዳያን ዜለር የርሱን መምጣት ሲሰሙ ስራ ትተው ሁሌም ይጠብቁታል፡፡ ያኔ በ1990 እ.ኤ.አ. የመጣበት ጊዜ ግን ከወትሮው የተወሳሰበ - አዳዲስ ክስተቶች የነበሩበት ነበር፡፡ እና በአይሁድ አሜሪካውያን ዘንድም ሩጫ ተይዟል፡፡
አምባሳደር ካሳ በዙሪያው ካለው የተለያየ ፍላጎት መካከል ለኢትዮጵያ የሚበጀውን እንደሰበዝ ነቅሶ ለገጠማት ፈተና መፍትሄ ማድረግ ለመቻል ያሰበው ቀላል አልነበረም፡፡ ለዚህ አይሁድ አሜሪካውያን ተሻግሮ ወይም ተመርኩዞ ከዋሽንግተን ጋር ኢትዮጵያን የማቀራረብ ብልሃት ተካቶበት ነበረ፡፡ ቀደም ሲል ታዲያ ‘አጣብቂኝ ማለቴ ያለምክንያት አይደለም፡፡ በሀገር ቤት  የ’ዋሽንግተን’ ነገር ጨው ቢነሰነስበት የማይቀምሱት ‘ኮለኔል መንግስቱ አሉ። በዚህ በኩል ቴላቪቭ ከኢትዮጵያ ‘ቤተ እስራኤሎችን’ ለመውሰድ ግልጽና ህቡዕ ስራ ጀምራለች፡፡ ዩኤስ አሜሪካ ደግሞ ከ’ሶቪየት ህብረት’ ጀርባ የተሰለፉትን ሀገራት ውልቃቸው እንዲወጣ በስለላ መረቧ ስታደርግ፣ ሕወሀትን የመሰሉትን አማጽያንን አይዟችሁ ማለት ጀምራለች፡፡ በዚህ መሀል ታዲያ ዲፕሎማቱ ካሳ አንዱን ባንዱ የማጣፋት ዘዴ ይዞ ዋሽንግተን ገብቷል፡፡ የእስራኤል ቴላቪቭና የአሜሪካ አይሁዶችን በቤተ እስራኤል ጉዳይም ሆነ ለኢትዮጵያ በሚሰጥ እርዳታ፣ ከአሜሪካ ጋር በማቀራረቡ ሂደት እንደየፍላጎቱ የማቻቻል ስራን ጀምሯል፡፡ መልካም ምልክቶችን እያየ መምጣቱን የሚገልጡ መልዕክቶችን ለአዲስ አበባም አስተላልፏል፡፡ መልዕክቱ ከኮለኔሉ ደጃፍ ደርሶ ተአማኒ ይሁን አይሁን የሚታወቅ ነገር ግን አልነበረም፡፡ እሱም ስጋት ነበረው፡፡
የአምባሳደር ካሣ ከበደ ከእስራኤል ጋር ያለው ግንኙነት- ኢየሩሳሌም ከሚገኘው የሂብሩ ዩኒቨርስቲ ተማሪነቱ ጎልቶ ይጀምራል። ከ1960-65 እ.ኤ.አ. እዛው ኢየሩሳሌም በትምህርት ቆይቷል። እስራኤል ገና ድክ ድክ የምትልበትና - ከግጭት ያልተላቀቀችበት ጊዜ ነበር ያኔ፡፡ ከሁለተኛ ዓለም ጦርነት በሁዋላ በ1947 ፍልስጤም የአይሁድና የአረብ በሚል እንደትከፈል በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሲወሰን፣ የአረቡ አለም አልቀበልም በሚል ውጊያ ያወጀበት ሁኔታ ተከሰተ፡፡ እና ከዚያ ጦርነት ወጥታ ውስጧን እንደአበባ ለማፍካት የምትጣጣር ነበረች እስራኤል፡፡ እንደውም  የአሜሪካ አይሁዳውያን ‘ኪቡትዝ’ እና ‘ማነው አይሁድ?’ በሚል ዲያስጶራውን ወደ ቃል ኪዳኗ ሀገራቸው የሚመለከቱበትም ጊዜ እንዲሆን የጦፈ ውይይት የሚደረግበትም ወቅት ነበር፡፡ እብራይስጥን አቀላጥፎ የሚናገረውና ከቶውንም የእስራኤላውያኑን የልቡና ውቅር የሚያውቀው ካሳ በዚያ ጊዜ መገኘቱ ትልቅ ፋይዳ ነበረው፡፡
ግን ካሣ እንዴት ብሎ ከዚህ አውድ ገባ?  በጃንሆይ ጊዜ እ.ኤ.አ. ከ1967 እስከ 1971 በኢትዮጵያ የእስራኤል አምባሳደር የነበረው ኡራየል (ኡሪ) ሉባርኒ ከካሳ አባት ደጃዝማች ከበደ ጋር የተገናኘበትን ጊዜና ሁኔታ ያስታውሳል፡፡ ከርሳቸው ጋር በሁለቱ ሀገራት ጉዳይ ካነጋገራቸውና ከጨረሰ በሁዋላ  “ጨርሼ ከባለስልጣኑ ቤት ስወጣ አንድ መልከ መልካም ዘለግ ያለ ወጣት ከጓደኞቹ ጋር ጨዋታ ይዞ አየሁት፡፡ ደጃዝማች ከበደ “አምባሳደር ተዋወቀው ልጄ ነው፣ ካሣ ይባላል” እንዳሉት ይነገራል፡፡
ወጣቱ ካሣ የአስራ ስምንት ዓመት ኮበሌ እያለ ነበር ወደ እስራኤል ለትምህርት የሄደው፡፡ በመጀመሪያ ለቋንቋ ጥናት ‹አኪቫ አልፓን› ከተሰኘ ተቋም ተሳተፈና ለዋናው ትምህርት ወደ መካነ ጥናቱ ገባ። በማህበራዊ ስራ ትምህርት ተመረቀ፡፡ በዚያ የኢየሩሳሌም የትምህርት ቆይታው ከተማሪዎችም ሆነ ከአካባቢው ነዋሪ ዘንድ ስሙ ታዋቂ ነበር፡፡ እንደውም ኒታ ኢፍሮኒ ከተሰኘች እስራኤላዊት (ነጭ) ጋር የከንፈር ወዳጅነት የመመስረቱ ዜና ከአፍ ለአፍ እየተዘዋወረ በኢየሩሳሌም ይወራ ጀመር። የወሬ ነገር እየተሳበ መጓዙ አልቀረምና አዲስ አበባ ከቤተ መንግስቱ ደረሰ አሉ። በዚያ ቅብጥብጥ ወጣትነት ምኞት ካሣ ከኒታ ኢፍሮኒ ጋር ጋብቻ ያስባል የሚል ወሬ ተወርቶበት ከአባቱ ጆሮ ዘንድ ደረሰ። አባት ‘እንዴት የሀገርህን ልጅ ሳታይ’ ብለው ቆጣ አሉና፣ በቀጭን ትዕዛዝ ወደ ሀገር እንዲመለስ ተደረገ የሚል ጉምጉምታ አለ፡፡ እሱም ይህን አይክድም፡፡ ብቻ ኢየሩሳሌምንና ኒታን ከልቡ ቢወዳቸውም ወደ ሀገሩ መመለስ ግን - ግድ ሆነ፡፡ በዚያ አፍላ ዘመን በነበረው ቆይታ ከብዙዎች ጋር የመግባባትና መልካም ግንኙነትን የመፍጠር ልዩ ስጦታውን ያሳየበትም ነበር፡፡ እስራኤል ገና ወገቧ ያልጠናበት ወቅት ቢሆንም የኋላ ኋላ - አሉ የተባሉት የሀገሬው ሰዎችን ለማወቅና ለመወዳጀት መልካም አጋጣሚ ነበር - ለካሣ፡፡ይህ የኢየሩሳሌም ተሞክሮውና ግንኙነቱን ከበርካታ ዓመታት በሁዋላ ሊጠቀምበትና ለሀገሩ ጥቅም ሊያውለው ይፈልግ ገባ፡፡ ኢትዮጵያና እስራኤል ታሪካዊ ግንኙነታቸው ጠንካራ ነው፡፡ ከ›ዮም ኩፐር› ጦርነት በሁዋላ ኢትዮጵያ በአፍሪቃ አንድነት ድርጅት አባል ሀገራት ግፊት ጭምር ከእስራኤል ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ባቋረጥችበት ክፉ ጊዜ ስንኳ የውስጥ ለውስጥ ግንኙነቱ ተቋርጦ አያውቅም ነበር። አምባሳደር ካሣ ኢትዮጵያ ከእስራኤል ጋራ “የማይነጠል ጂኦ ስትራተጂያዊ ግንኙነት አላት” ይላል፡፡ ከታሪክ ትስስሩ ጋር ይህን ለበጎ መጠቀምና ለክፉ ጊዜ መፍትሄነት ማዋልን ነበር አምባሳደር ካሣ የሰነቀው፡፡
የእስራኤሉ ሩይቫን መርኻቭ የቤተ እስራኤሎችን የማጓጓዝ ሁኔታ በርጋታና በዘዴ ስለመሆኑ ይጨነቃል፡፡ የአሜሪካዋ የያኔዋ ወጣት አይሁዳዊቷ ሱዛን ፖላክ ደግሞ ‘ፍጥነት’ ይታከልበት - የሚል ችኩልነት ተጠናውቷታል፡፡ ከቴላቪቭ እስከ ዋሽንግተን መረቡን የዘረጋው አምባሳደር ካሳ ከዩኤስ አሜሪካ ጋር የማግባባቱን ስራ ለማፋጠን የያዘውን ጥረት የቆዩ ወዳጆቹን ሳይቀር በይዲሽ እያማለለ ተያይዞታል። ፍንጮቹ አበረታች በሆኑበት ጊዜ ደግሞ የአዲስ አበባው የኮለኔል መንግስቱ ነገር አስግቶታል፡፡ ተለዋዋጭና ያልታሰቡ ክስተቶች እያደፈረሱት መሆናቸው ተስፋውን እየሸረሸረው እየሄደ ነው፡፡ እ.ኤ.አ. በ1975 እስራኤሎች የኢትዮጵያን ጦር ሀይል በመገንባቱ ረገድ እንዲያግዙ በሚል በምስጢር የተሞከረው በዚያው በእስራኤል የፖለቲካ ሰዎች ‘ወሬ የማይቋጥሩ’ (loose Cannon) በሚባሉት የዛን ጊዜው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሞሼ ዲያን በአደባባይ በመነገሩና በመጋለጡ የተነሳ እንደገና ኮለኔል መንግስቱ በአረቡም አለም ይሁን በሶሻሊስቱ ፊና መወቀስና መዋረድ እንዳይመጣ ስጋት እንዳደረባቸው ቆይቶ የወጡ መረጃዎች ይገልጻሉ፡፡ አምባሳደር ካሣ በወታደራዊው ይሁን በማህበራዊ ኑሮ ከቶም በሰውኛው ግንኙነት ስሉጥና ፈጣን የሆኑና ግራና ቀኙን የማጣጣም ልዩ ችሎታቸው ስለነበራቸው - የማግባባት ብልሃታቸውን አግባብ በሆነበት ቦታ ሁሉ እየተጠቀሙት ቆዩ፡፡
አምባሳደር ካሣ መረጃቸውና የመረጃ አውታሮቻቸው እጅግ እንደሚገርም የውጭ ጸሀፍት ጭምር ይገልጻሉ፡፡ በካሊፎርኒያ የአይሁድ አሜሪካውያን ማዕከል ፕሬዘደንት የነበሩት ማርሲ ፍሪድማን (ዶ/ር) አምባሳደር ካሳ “ስለእስራኤልም ይሁን ስለዲያስፖራ አይሁድ፣ ስለሀገሩ ቤተ እስራኤላውያን ታሪክ ያላቸው እውቀት ተንቀሳቃሽ ቤተ መጻህፍት አይነት ናቸው” ይላሉ፡፡ ሰውየው በሀገር ውስጥም ይሁን በዓለም በደረሰበት መረቡን የመዘርጋት ተሰጥኦው ድንቅ ነው፡፡ የሰው ንቀት አይገባውም፡፡ የመረጃ ትንሽና የማይረባ በእርሱ ዘንድ አይታወቅም፡፡ ከትንሹ አንሶ-  ከትልቁ ገዝፎ  - ማውጋትና መግባባት ይችላል፡፡ ይህ ሁሉ ግን የሀገሩን ገጽታና ይዘት ወደ መልካም ለመለወጥ ሲል ነው፡፡ በዚያን ውስብስብ አጋጠመኝ ወቅት እስራኤሎቹን የቸገረውና ግራ ያጋባው አምባሳደር ካሣ፣ መረጃውን (ወሬውን) በእስራኤል ሚዲያዎች ከመታወጁ አስቀድመው ያልተጠበቁ ጥያቄዎችን እያነሳ መሞገቱ ነው፡፡ እንደውም እርስ በርስ ቴላቪቭና ዋሽንግተን በመረጃዎቹ መሹለክና መደፍረስ ሳቢያ መገፋፋትና መጠቋቆም ጀምረው እንደነበር ውስጥ አዋቂዎች ይናገራሉ፡፡ አምበሳደር ካሣ ሁሉን ከወረቀት ላይ ይመዘግባል፡፡ ከኪሱ ብዕርና ወረቀት አይጠፋም፡፡ ቡና ለመጠጣት ሲገናኝ ወረቀትና ብዕሩ ይወጣል፡፡ የዚህ ጽሁፍ አቅራቢ አምባሳደር ካሳን ከኢትዮጵያ ውጭ ሜሪላንድ ቤተ ሳይዳ ከበርካታ አመታት በፊት ሲያገኘው ብዕሩን አውጥቶ ማመቻቸት መጀመሩን ይታዘባል፡፡
“እንዴ እኔው ልጠየቅ እንዳይሆን?” እላለሁ በቀልድ፡፡
“እናንተ ወጣቶቹ የሰማችሁትን ሁሉ ዛሬ ታስታውሱ ይሆናል! እኛ ግን ወረቀት ያስፈልገናል” ብሎኝ አለፈ፡፡ ሀሳብ የሚያጭሩ ነጥቦችን አለፍ አለፍ ብሎ ይከትባል፡፡ እና መረጃን መሰብሰብ ብቻ ሳይሆን ለሀገር እንዴት እንደሚጠቅም ነው ዘወትር የሚያስበው፡፡ ምንም እሳቤ ከሀገር ፋይዳ ውጭ እሱ ዘንድ ስፍራ የለውም፡፡ ለዚህ ሰብዕናው ታዲያ አባቱን ሁሌ በአክብሮት ያነሳል፡፡ ከአንደበቱ እንደሰማሁት አባቱ ክቡር ደጃዝማች ከበደ ከአጠገባቸው ሳይለዩ ከኮተኮቷቸው በወግና በስርዓት ካሳደጓቸው ልጆቻቸው አቢይ ነው፡፡ በስነ ምግባርና በግብረ ገብ የታነጸበት መሰረት ከዘመናዊው አስተምህሮና ከከተሜ (የአራዳነት) ጋር ተሰናስሎ ተዋህዶ አምባሳደር ካሣ ላይ ይስተዋል ነበር፡፡
የአሜሪካ አይሁዳውያንን በልዩ የማግባባት ብልሃት ተጠቅሞ ኢትዮጵያን ወደ ዋሽንግተን የማስጠጋቱ ሁኔታ፣ ከአዲስ አበባ ‹የቅይጥ ኢኮኖሚ› አዋጅ ጋር የፍትህ ጥያቄዎችንም ያገናዘቡ አዝማሚያዎችን ማሳየት የሚቻልበት ጭላንጭል መታየት ጀመረ፡፡ የቤተ እስራኤል ኢትዮጵያውያንን ጉዳይ የሚከታተሉ የአሜሪካ አይሁዳውያን ጊል ኩሊክና ኔት ሸፒሮ (AAEJ President) በአንድ በኩል አሰልፎ በሌላው በኩል ገጥ ደግሞ አምባሳደር ሉብራኒና አሸር ናሂም ከእስራኤል ይዞ ሚዛኑን ጠብቆ እየተጓዘ ኢትዮጵያን ሊታደጋት መንቀሳቀስ ጀመረ። በዚህ መሀል በአምባሳደር ካሣ ላይ ስሞታና በንዴት የሚንተከተኩ አልጠፉም። በደርጉ የማብቂያ ዘመን ላይ በአዲስ አበባ የአሜሪካ ኤምባሲ ጉዳይ አስፈጻሚ ሮበር ሁዴክን የመሰሉ “ካሣ የተሟላ እውነት ተናግሮ አያውቅም” እያሉ በንዴት ጠረጴዛ የሚደበድቡም ነበሩ።  በሀገር ቤት በመስኩ ላይ ያለው ወታደራዊ ሁኔታ ደግሞ ለኢትዮጵያ መልካም ዜና አልነበረም። የስነ ልቡና ጦርነቱ በዚያው እግር በእግር  ቀጥሏል፡፡ ከአሜሪካ የፖለቲካ ዳራ ውስጥ ‘አማጽያኑን’ የሚደግፈውም ግፊቱን ቀጠሏል፡፡
 አምባሳደር ካሳ መልካም የሚባሉትን ፍንጮች ለማስፋት ለሳምንታት እዚህ ዋሽንግተን ዲሲ መቀመጫው አድርጎ ሰነበተ፡፡ በዚያ መሀል በኢትዮጵያ በኮለኔል መንግስቱ ላይ መፈንቅለ መንግስት በማድረጋቸው በእስር በሚገኙ  ጄኔራሎች ላይ የሞት ቅጣት የመፈረዱ ዜና ይፋ ተሰራጨ፡፡ በቀናት ዕድሜ የ’ዋሽንግተን ፖስት’ ጋዜጣ “ዩኤስና ኢትዮጵያ የሚያደርጉት ስብሰባ ተራዘመ” (US - Ethiopia Meeting Postponed) የሚል ዜና ተነበበ፡፡ እና የፍጻሜም መጀመሪያ ሆነ፡፡ አምባሳደር ካሣ ከበደ ከቁጥጥሩ ውጭ በሆነ የሀገር ውስጥ ሁኔታ ተገዶ የጀመረውን ጥረትና ዶሴውን ዘጋ፡፡
እና ያለመው ተሳተበትና አዘነ፡፡ የሀገሩ እጣ ፈንታ አሳሰበው፡፡ እንጥፍጣፊ ተስፋም ብትሆን ብሎ ወደ አዲስ አበባ ተመለሰ፡፡ የቤተ እስራኤል ኢትዮጵያውያን ጉዳይ ጋር በውጭው ግንኙነት ከእስራኤል ጋር ግንኙነቱን ለመጠቀምና ኢትዮጵያን ለማዳን የሚቻልበት ጭላንጭል ይኖር ይሆናል በሚል ቀጠለ፡፡ ይሁንና ከታሰበው ያልታሰበው እየቀደመ - ሰኔና ሰኞ ለኢትዮጵያ እየገጠመ መጣ፡፡
ደግሞ የዴር ሱልጣን ገዳም ነገር ትዝ አለው፡፡ ሀገራዊ ፈተና የበዛበት ጊዜ ሆነና በአጋጣሚው የአባቱንም አደራ አስታወሰ። በኢየሩሳሌም ካሉት ገዳሞች መካከል የዴር ሱልጣን ተለይቶ በግብጻውያኑ ተንኮል የመወሰዱ ውዝግብ ለእስራኤል ባለስልጣኖች ደጋግሞ አነሳባቸው። እንደታሪኩ ዴር ሱልጣን ንግስተ ሳባ ከክርስቶስ ልደት በፊት በ1013 ዓመተ ዓለም ኢየሩሳሌም ከንጉሱ ሰለሞን ዘንድ ስትጓዝ ጓዟን ያሳረፈችበት ቦታ - ቀራንዩ (ጎልጎታ) አጠገብ የሚገኝ ነው ይሏል፡፡ ታዲያ የቀደመው መይሳው ካሣ
«ታጠቅ ብሎ ፈረስ ካሳ ብሎ ስም -
አርብ አርብ ይሸበራል እየሩሳሌም” የተባለበት - ታሪካዊው በዓት -  በስነ ቃላችንም በልቡናችንም የሰረጸችውን ይህችን ስፍራ ለኢትዮጵያውያን ክርሰቲያኖች እንዲታተምና እንዲጠበቅላት በዚያ አጋጣሚ ታገለ፡፡ አባቱ ክቡር ደጃዝማች ከበደ ተሰማ በስደት በኖሩባት ኢየሩሳሌም፣ የኢትዮጵያውያን ይዞታ የሆኑት ገዳሞችን ጉዳይ እንዳይረሳ ልጃቸውን ያሳሰቡትን እስከ ህልፈቱ አልረሳውም፡፡ በስደት ዘመኑ እንኳን በዋሽንግተን የ’ነፃነት ለኢትዮጵያ ራዲዮ መርሀ ግብር’ ላይ የ’ዴር ሱልጣንን ገዳም’ በተመለከተ ጥናታዊና ወቅታዊ ተከታታይ ጽሁፍ አምባሳደር ያቀረበበት በአድማጮች ዘንድ እስካሁን የሚታወስ ነው፡፡
ያኔ አማጽያኑ አዲስ አበባን እየከበቡ በነበበረበት ጊዜ አምባሳደር ካሳ እስከመጨረሻዋ መውጫ ደቂቃ ድረስ አደራውን ለመወጣት ደፋ ቀና ሲል ቆየ። የኢትዮጵያ ጠላቶች ደግሞ አምባሳደር ካሳ ስሙን ‹በይፈለጋልና በቁጥጥር ስር እንዲውል› በሚል ትዕዛዝ አስተላልፈው አውሮፕላን ማረፊያ ላይ አፋኝ መድበው ይጠብቁ ያዙ፡፡ ቀድመው ያሴሩት ተባብረው እርሱን ማፈላለጋቸውን አጤሱት፡፡
ነገር ግን ብዙም አልቆየ - ታሪኩ ትንግርት እንደሆነባቸው ሳያስቡት አምልጦ - ከውጭ ሀገር ሆኖ ጋዜጣዊ መግለጫ ሲሰጥ ከንፈራቸውን ነክሰው ሰሙት፡፡  
ባዕዳኑ ብለው ብለው  ሁሉም በአንድ ነገር በአምባሳደር ካሣ ዙሪያ ይስማማሉ፡፡ ፈጣን - ንቁ - አስተዋይ - ጎበዝ - ብልህ ዲፕሎማት፡፡ የቀረቡት ሁሉ በታላቅ ፍቅር ይመለከቱታል፡፡
ኢትዮጵያን ከልቡ ይወዳታል፡፡ በተግባሩ ሲመሰክርም ኖሯል። እንደ ዲፕሎማት እንደ ባለስልጣን ብቻ ሳይሆን - በስደት እንደ አንድ ስደተኛ ለፍቶላታል፡፡ ስለኢትዮጵያ ሲናገር፣ ሲጽፍ፣ ሲመክርና ሲያስተምር ኖሯል፡፡ የቀረበው ሰው ከየትም ይሁን የት አምባሳደር ካሣን ሳይወደው አይለየውም፡፡
 አምባሳደር አሸር ናሂም ‘ካሣ ለእስራኤልና ለአይሁድ ፍቅር አለው” ይላል፡፡ የኢትዮጵያው የዲፕሎማሲው ዋርካ አምባሳደር ካሣ - የከበደው ካሣ ሩጫውን ጨርሶ በፈረንጆቹ ልደት ቀን አረፈ፡፡ እጅ ነሳን፡፡




Read 2469 times