Sunday, 02 January 2022 20:27

አዲስ መድኃኒት ሊነግዱ ፣ አዲስ ህመም ወለዱ

Written by 
Rate this item
(5 votes)

 ከኢራቅ ተረቶች አንዱ የሚከተለውን ይመስላል።
አንድ ሼክ በጣም ትልቅና የተከበሩ በአንድ ባለስልጣን ይታሰራሉ።
ሆኖም ሌላ ባለስልጣን ይፈታቸዋል። ይህም በተከታታይ ወራሪ ሰራዊት ግዛታቸውን በወረረ ሰዓት ነበር። ይህን መሰረት ያደረገ ነው።
ከእለታት አንድ ቀን፣ አንድ የማገዶ- እንጨት ሻጭ ሰው፣ ለኑሮው የሚያግዘውን እንጨት ለመቁረጥ ወደ ጫካ ይሄዳል። እዚያም አንድ አንበሳ ያያል። እንዲህም አለ ለራሱ፡-
“ይሄ አንበሳ ወዲህ ከመጣ ያለ ጥርጥር ይበላኛል።  ያ ከሆነ ደግሞ ቤተሰቤን ማን ይረዳል!” አለና በሙሉ ድፍረት ወደ አንበሳው ሄዶ፤ “እኔ ጫካ ውስጥ ምን ልታደርግ መጣህ?” አለው።
አንበሳው በሰውየው አጉል -ድፍረት ተገረመና፤
“ጫካዬ ነው ያልከው? ማነው ያንተ ያደረገው?
ይሄ ጫካ የዱር አራዊት ንጉሥ በመሆኔና የጫካዎች ሁሉ ጌታ በመሆኔ፤ የማስተዳድረው የኔ የራሴ ጫካ ነው!”
ሰውየውም፤
“ኧረ የለም። እኔ በየጊዜው እየመጣሁ እንጨት እየቆረጥኩ፣ ገበያ የምሸጥ ሰው ነኝ! እንፋለም ካልን ይዋጣልንና ያሸነፈ ይውሰደው!” አለ።
 አያ አንበሶ ኮራ ብሎ፣
“ይዋጣልን? ኧረ ድፍረት!” አለና ይብሱን ተደመመ። “ከእኔ ጋር ገጥመህ የት ለመድረስ ነው ያዋጣሃል ግን?”
“እርግጥ ነው” አለ ሰውዬው፤ “የእግሮች ጥፍሮችና ጠንካራ ጥርሶች አሉህ። እኔ ምንም መሳሪያ አልያዝኩም። ከፈቀድክልኝ ግን ወደ ቤቴ ሄጄ ፋስ-መጥረቢያ ይዤ ልመጣ እችላለሁ”
“ሆ! ሆ! ሆ!ሆ! “ አለ አያ አንበሶ  “ብለቅህ እንኳ መመለስህን በምን እርግጠኛ እሆናለሁ?”
ሰውዬውም፤
“ስሜ ፋስ-ፉስ ይባላል። የቤቴ አድራሻ ደግሞ ይህ ነው” ብሎ አድራሻውን ይሰጠዋል።  “ካልተመለስኩ ቤቴ መጥተህ ልትበላኝ ትችላለህ። ከዚህ ቅርብ ነው ቤቴ። በሌላ አንጻር ግን እኔ ገና መንገድ ስጀምር፤ እብስ ብለህ እንደማትጠፋ ምን ማረጋገጫ አለኝ?”
 አያ አንበሶ በሰውዬው አጉል ድፍረት አሁንም፤ “እኔ የአውሬዎች ሁሉ ንጉሥ ከእንዳንተ ዓይነት ምስኪን ፍጥረት ሸሽቼ ልጠፋ?! እኔ ሽሽትን ጨርሶ የማላውቅ አውሬም ነኝ! ብትፈልግ እሰረኝና ሂድ!”
ሰውዬው በትክክል እቺን ነው የፈለገው። በአስተማማኝ ሁኔታ ጌታ አንበሶን  አስሮ፣ እዛው ትቶት መጭ አለ።
አያ አንበሶ በዚያው ሁኔታ ለዘላለም በቆየ ነበር። ነገር ግን እመት አይጥ ደረሰችለት። ሲጮህ ድምጹን ሰምታ ኖሮ ወደሱ መጣች።
“ምን ሆነህ ነው አያ አንበሶ?” አለችው።
የሆነውን ነገራት።
“ግዴለም። እኔ የታሰርክበትን ገመድ ቀርጥፌ በጥሼ ነጻ አወጣሃለሁ”
አያ አንበሶም፤
“እንደዚያ ካደረግሽልኝማ፣ አንቺና ቤተሰቦችሽን ከእንግዲህ ማንም እንደማይነካችሁ አረጋግጥላችኋለሁ። የአውሬዎች ሁሉ ንጉስ ሁሌም ይጠብቃችኋል!”
እመት አይጥ ስራዋን ጀመረች። ገመዱን በጠሰችለት። አያ አንበሶ ነጻ ወጣ።
ከዚያም፤
“እኔ የምልሽ ስምሽን ካላወኩኝ ቃሌን እንዴት ላከብር ነው?”
“ስሜ  ፍሴይ-ፊስ ነው” አለች አይጢት። ከዚያ ወደፈለገችበት በረረች።
አያ አንበሶም፤
ፋስ-ፉስ አሰረኝ፤ ፍሴይ-ፊስ (ቱርካዊ ቋንቋ ነው) ፈታኝ። ፍሮይ- ፉስ የፋስ-ፉስ ውርድ (Diminuitive) ነው።
ይሄም በቱርክኛ፤ ውስጠ-ወይራ፤ እንደማለት መሆኑ ነው። ቢሮ ያለው ትልቁ ጃር ፤ ጆግ (Jug) ውስጥ ከተተኝ። ቢሮ ያለው ትንሹ ጃር ደግሞ አወጣኝ- አስፈታኝ፤ እንደማለት ነው። ይሄም አያ አንበሶ፣ “የዚህ ጫካ ነገር አንዳች አደጋ አለው፤ ማምለጥ ነው የሚሻለው” ብሎ ጫካውን ለአንዴም ለሁሌም ጥሎ ተፈተለከ።
***
ከጉልበት እንደሚሻል ተደጋግሞ ተነግሯል። ጠብ ከመጫር ተቆጠብ። ጠብ ሲጭሩብህ ተጠበብ፤ይላሉ አበው። አንድም፤ ጦርነት የሰላም መንገድ ሲሟጠጥና የዲፕማሎሲው መንገድ ሁሉ ሲነጥፍ የሚመጣ የህልውና መጠበቂያ  ዘዴ ነው። የሚቻለውን ብልሃት ሁሉ ለመጠቀም ጥረት ተደርጎ ሌላ አማራጭ ሲታጣ የሚካሄድበት ግዴታ ነው።
ምነው ቢሉ፣ የሰው ሃይልን፣ ንብረትን፣ የማቴሪያል ሃይልን ሁሉ፣ ሞራልንም ጭምር የምንገብርበት የእልቂት ክስተት ነውና። አንድም ደግሞ አገርና ህዝብ አሳር ፍዳውን እያየ፣ እጅን አጣጥፎ የሚቀመጡበት አልያም እንደ መዝናኛ የሚሄዱበት የጫጉላ ሽርሽር (HoneY moon) አይደለም። ይልቁንም ሼክስፒር እንደሚለው፤
“ፈጥነህ ጠብ ውስጥ አትስጠም፤
አንዴ ከገባህበት ግን፣ እጅህ ከባላንጣህ ይቅደም።” መባል ነው የሚኖርበት። ጊዜን ማወቅ የማጥቂያንም ሆነ የመከላከያን ጊዜ መለየት ዋና ነገር ነው።
“ጋሻ እንጂ ጦር አትስራ። ጋሻው ካህ ጦሩን ከጠላትህ ታገኘዋለህ” ይሏልና።
የሀገራችን አዙሪታዊ አካሄድ፣ ከጦርነት ወደ መልሶ ማቋቋም፣ ከመልሶ ማቋቋም ደግሞ መልሶ ወደ ጦርነት መሆኑ ሃይለ-አዙሪቱ የእርግማን ይሆንን? እስከማሰኘት የሚያጠያይቅ ነው። ዞሮ ዞሮ የኢኮኖሚ ውድመት የቆላ ቁስል እየሆነ እንደሚመጣ ጥርጥር የለውም። “ጅብ ከሚበላኝ፤ ጅብ በልቼ ልቀደስ” የሚባለው የሃይል ሚዛን ማስተካከያ ይሁንልን እንጂ ኢኮኖሚያችን ላይ የሚጥለው ጠባሳ በቀዶ ጥገና የማይወገድ ነው።
አገራችን በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚና በማህበራዊ መስክ ከገባችበት አረንቋ ትወጣ ዘንድ፣ ደስታዋን ብቻ ሳሆን መከራዋን ለመጋራት ዝግጁ የሆኑ ጽኑ ዜጎች ትፈልጋለች።
ርሃብ፣ ድርቅና ቸነፈር ዓመቱ አንዴ አበቅቴ ዘመን መቁጠሪያ ሲከሰት ቀበቶአቸውን ጠበቅ አድርገው ለዘላቂ ጉዞዋ የሚታደጓት ልጆች እንጅ የገና ስጦታ የሚያመጡ የጊዜያዊ ፍቅር ሰዎች (Part time lovers) የምትጠብቅ አይደለችም። በወቅቱ ደራሽነትን ከዘላቂነት ጋር ያቀናጁ (Timeliness and Timelessniss) ልባም ልጆችን ትፈልጋለች። እንደዲዮጋን የሰው ያለህ ትላለች። ባላንጦቻችን ከውስጥም ከውጭም ሆነው እንደ ሁልጊዜው  ከሃያላን ጋር  መስጥረው  በውስጥ ዓርበኛም፣ በድል አጥቢያ ዓርበኛም በመጠቀም አዳዲስ ችግር መፍጠራቸው ገሀድ ጉዳይ ነው። ጭር-ሲል አልወድም በሚሉም አያሌ ናቸው። ሁሉም ጥቅማቸውን ለማሳደድ እንቅልፍ አትተው የሚራወጡና አዲስ መድኃኒት ሊነግዱ አዲስ ህመም ወለዱ የሚባሉ ናቸው።

Read 12369 times