Sunday, 02 January 2022 20:43

33ኛው የአፍሪካ ዋንጫን በ33 ሁኔታዎች

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(1 Vote)

 በ33ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ለመሳተፍ ካሜሮን በመግባት የመጀመሪያው የሆነው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ላለፉት 7 ቀናት ዝግጅቱን እደረገ ነው። ከሱዳን አቻው ጋር የአቋም መለኪያ የወዳጅነት ጨዋታ አድርጎ 3 ለ 2 ሲያሸንፍ  ጎሎቹን አማኑኤል ገብረሚካኤል እና ሽመልስ በቀለ አስቆጥረዋል። ዋልያዎቹ በምድብ አንድ ከአዘጋጇ ካሜሩን፣ ቡርኪና ፋሶ፣ እና ኬፕቬርዴ ጋር ተደልድለዋል፡፡  ካሜሮን ለአምስት ጊዜያት በ1984፤በ1988፤ በ2000፤ በ2002 እና በ2017 እኤአ ላይ የአፍሪካ ሻምፒዮን ስትሆን፤  በ2013 እኤአ ላይ ቡርኪናፋሶ ሁለተኛ ደረጃ እንዲሁም ኬፕ ቨርዴ ለሩብ ፍፃሜ በመድረስ ከፍተኛ ውጤት አላቸው፡፡ ኢትዮጵያ ባለፉት 32 የአፍሪካ ዋንጫዎች በአስሩ ላይ ስትሳተፍ 27 ጨዋታዎችን በማድረግ 7 ድሎች 3 አቻ እና 17 ሽንፈቶች ተመዝግበዋል። 29 ጎሎች በተጋጣሚዎች መረብ ላይ ስታሳርፍ 61 ጎሎች ደግሞ ተቆጥረውባታል።  የኢትዮጵያ ከፍተኛውን ውጤት በ1962 እ.ኤአ ላይ የአፍሪካ ዋንጫ ሻምፒዮን ለመሆን የበቃችበት ሲሆን በ1ኛው የአፍሪካ ዋንጫ 2ኛ ፤ በ2ኛው የአፍሪካ ዋንጫ 3ኛ፤ በ4ኛው የአፍሪካ ዋንጫ 4ኛ ደረጃ ነበራት።
የ33ኛው የአፍሪካ ዋንጫ አዘጋጅ ካሜሮን በአምስት ከተሞች ያዘጋጀቻቸው  ስታዲየሞች ኦሌምቤ &ስታድ አህማዱ & ጃፖማ & ሊምቤ & ካውኮንግ እና ሩምዴ አድጂያ ናቸው።የውድድሩ መክፈቻ እና የፍጻሜ ጨዋታ አዲስ በተገነባውና 60,000 መቀመጫ ባለው ኦሌምቤ ስታዲየም ያውንዴ ከተማ የሚካሄድ ነው። የፌሊክስ ፎኩዋ የጥበብ ስራ የሆነው ወንድማማችነትን የሚያመለክተው ሞላ “Mola” ማስኮት ሲሆን “AfricaSmile” የተሰኘው የመዝሙር ዘፈን ተሰርቷል።
በ33ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ላይ ካሜሮን ለ20ኛ ጊዜ፣ ሴኔጋል ለ16ኛ ጊዜ፣ አልጀሪያ ለ19ኛ ጊዜ፣ ማሊ ለ12ኛ ጊዜ፣ ቱኒዚያ ለ20ኛ ጊዜ፣ ቡርኪናፋሶ ለ12ኛ ጊዜ፣ ጊኒ ለ13ኛ ጊዜ ፣ ኮሞሮስ ለመጀመሪያ ጊዜ፣ ጋቦን ለ8ኛ ጊዜ፣ ጋምቢያ ለመጀመሪያ ጊዜ፣ ግብፅ ለ25ኛ ጊዜ፣ ጋና ለ23ኛ ጊዜ፣ ኢኳቶሪያል ጊኒ ለ3ኛ ጊዜ፣ ዚምባቡዌ ለ5ኛ ጊዜ፣ አይቬሪኮስት ለ24ኛ ጊዜ፣ ሞሮኮ ለ18ኛ ጊዜ፣ ናይጀሪያ ለ19ኛ ጊዜ፣ሱዳን ለ8ኛ ጊዜ፣ ማላዊ ለ3ኛ ጊዜ፣ ኢትዮጵያ ለ11ኛ ጊዜ፣ ሞውሪታኒያ ለ2ኛ ጊዜ፣ ጊኒ ለ3ኛ ጊዜ፣ ኬፕቨርዴ ለ3ኛ ጊዜ እንዲሁም ሴራልዮን ለ3ኛ ጊዜ አፍሪካ ዋንጫውን ይሳተፋሉ።
 በ33ኛው የአፍሪካ ዋንጫ የሚሳተፉ 24 ብሔራዊ ቡድኖች የሚታወቁባቸው ቅጽል ስሞች  ደግሞ የሚከተሉት ናቸው። አልጀሪያ (የበረሃዎቹ ጦረኞች)፣ ቡርኪናፋሶ (ነጭ ፈረሶች)፣ ካሜሮን (የማይበገሩት አንበሶች)፣ ኬፕቨርዴና (ሰማያዊዎቹ ሻርኮች) ፣ ኮሞሮስ (አሳዎቹ)፣ ግብፅ (ፈርኦኖቹ)፣ ኢኳቶሪያል ጊኒ (ብሔራዊ መብረቆች)፣ ኢትዮጵያ (ዋልያዎቹ)፣ ጋቦን (አነሮቹ) ጋምቢያ (ጊንጦቹ)፣ ጋና (ጥቋቁር ክዋክብት)፣  ጊኒ (ብሔራዊ ዝሆኖች)፣ አይቬሪኮስት (ዝሆኖቹ) ማላዊ (ነበልባሎቹ)፣ ሞውሪታኒያ (ዘ አልሞራቫዲሶ)፣ ሞሮኮ (የአትላስ አትብሰት)፣ ናይጀሪያ (ንስሮቹ) ሴኔጋል ( የቴራንጋ አናብሰት)፣ ሴራልዮን (የሊዮኔ ክዋክብት)፣ ሱዳን (የናይል አዞዎች)፣ ቱኒዚያ (የካርታጌ ንስሮች) ተብለው ይጠራሉ።
 በአፍሪካ ዋንጫው  ላይ የሚሳተፉ 24 ብሔራዊ ቡድኖች በትራንስፈርማርከት TransferMarkt በተጨዋቾች ስብስባቸው የሚኖራው የዋጋ ተመን  ከዚህ ቀጥሎ በቅደም ተከተል እንደሰፈረው ነው። ሴኔጋል 339.40 ሚሊዮን ዩሮ፣ አይቬሪኮስት 302.93 ሚሊዮን ዩሮ፣  ናይጀሪያ 275.55 ሚሊዮን ዩሮ፣  ሞሮኮ 214.50 ሚሊዮን ዩሮ፣  አልጀሪያ 189.85፣ ግብፅ 174.60 ሚሊዮን ዩሮ፣  ማሊ 150.00 ሚሊዮን ዩሮ፣   ካሜሮን 142.45 ሚሊዮን ዩሮ፣  ጋና 135.75  ሚሊዮን ዩሮ፣  ጊኒ 95.85 ሚሊዮን ዩሮ፣  ጋቦን 52.28 ሚሊዮን ዩሮ፣  ጋምቢያ 44.65  ሚሊዮን ዩሮ፣ ቱኒዚያ 36.55 ሚሊዮን ዩሮ፣  ኬፕቨርዴ 24.28 ሚሊዮን ዩሮ፣   ጊኒ ቢሳዎ 22.93 ሚሊዮን ዩሮ፣   ዚምባቡዌ 15.45 ሚሊዮን ዩሮ፣   ቡርኪናፋሶ 14.83 ሚሊዮን ዩሮ፣   ሴራልዮን 12.68 ሚሊዮን ዩሮ፣   ኮሞሮስ 12.15 ሚሊዮን ዩሮ፣   ሞሪታኒያ 12.03 ሚሊዮን ዩሮ፣   ኢኳቶሪያል ጊኒ 4.60 ሚሊዮን ዩሮ፣  ማላዊ 3.75 ሚሊዮን ዩሮ፣  ኢትዮጵያ 750 ሺ ዩሮ፣ እንዲሁም ሱዳን 375 ሺ ዩሮ ናቸው።
 በ33ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ላይ ከሚሳተፉ ተጨዋቾች ገበያ ከፍኛውን የዋጋ ተመን ያላቸው የሚከተሉት ናቸው። መሐመድ ሳላህ ከግብፅ 100 ሚሊዮን ዩሮ፣ ሳዲዮ ማኔ ከሴኔጋል 80 ሚሊዮን ዩሮ፣ አሸረፍ ሃኪሚ ከቱኒዚያ 70 ሚሊየን ዩሮ፣ ቪክቶር ኦሺሜን ከናይጀሪያ 60 ሚሊዮን ዩሮ ፣ ዊልፍሬድ ኒዲሲ ከናይጀሪያ 60 ሚሊዮን ዩሮ፣  ፍሪንክ ኬሲዮ ከናይጀሪያ 48 ሚሊዮን ዩሮ፣ ካሊዶ ኩሊባሊ ከጋና 45 ሚሊዮን ዩሮ፣ ዊልፍሬድ ዛሃ ከአይቬሪኮስት 40 ሚሊዮን ዩሮ፣ ቶማስ ፐርቴይ ከጋና 40 ሚሊዮን ዩሮ እንዲሁም የሱፍ ኤንናሰሪዬ ከቱኒዚያ 40 ሚሊዮን ዩሮ ናቸው።
በ33ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ላይ ከ14 በላይ የትጥቅ አምራች ኩባንያዎች 24ቱን ብሔራዊ ቡድኖች በማልያ አቅርቦታቸው ስፖንሰር አድርገዋል።  ፑማ ከ6 ብሔራዊ ቡድኖች ጋር በመስራት ግንባር ቀደም ሲሆን አይቬሪኮስት፣ ጋና፣ ሞሮኮና፣ ግብፅ፣ ጊኒቢሳዎ እና ሴኔጋል ናቸው።  አልጀሪያ፣ ኬፕቨርዴና ግብፅ ከአዲዳስ፤ ኢትዮጵያና ዚምባዌ ከአምብሮ፣ ጋቦንና ቱኒዚያ ከካፓ ትጥቃቸውን አግኝተዋል። ቡርኪናፋሶ ከቶቪዮ፣ ካሜሮን ከሌከስ ስፖርቲፍ፣ ማላዊ ከሞቶ፣ ናይጀሪያ ከናይኪ ፣ ሱዳን ከኮሎ ስፖርት፣ ኢኳቶሪያል ጊኒ ከኢርያ፣ ማሊ ከኤርነስ፣ ሞውሪታኒያ  ከኤቢ ስፖርት እንዲሁም ጋምቢያ ከሶላር ስፖርት ማልያቸውን አግኝተዋል።
በ33ኛው የአፍሪካ ዋንጫ በሚሳተፉ 24 ብሔራዊ ቡድኖች ከ600 ተጨዋቾች ተመዝግበዋል። ከአምስቱም አህጉራት ወደ አፍሪካ የሚመለሱት ተጨዋቾቹ ለ1 ወር ያህል በአፍሪካ ዋንጫው ላይ በብሔራዊ ቡድኖቻቸው ቆይታ ያደርጋሉ።  ይህ በተለይ የአውሮፓ አምስት ታላላቅ ሊጎች ላይ የሚወዳደሩ  ክለቦችን አቋም ያናጋዋል።  በደንቡ መሰረት ለአህጉራዊ ሻምፒዮና ለዓለም ዋንጫ ጠጨዋቾች መልቀቅ ያለባቸው ከ14 ቀናት በፊት ነው። ካፍ ባሳለፈው ውሳኔ ተጨዋቾችን ውድድሩ ከመጀመሩ 6 ቀናት በፊት ቡድኖች እንዲለቁ  ለአውሮፓ ክለቦች ፈቅዶላቸዋል። የአውሮፓ ሊጎች ፎረምና የአውሮፓ ክለቦች ማህበር በውሳኔው ተደስተዋል።
ለአፍሪካ ዋንጫው በርካታ ፕሮፌሽናሎችን በመልቀቅ የመጀመሪያው ከ51 በላይ ተጨዋቾችን ለብሔራዊ ቡድኖች የሰጠው የፈረንሳይ ሊግ 1 ነው። ከግብፅ ፕሪሚዬር ሊግ  41፣ ከእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ 30፣ ከጣሊያን ሴሪኤ 22 ፣ ከስፔን ላሊጋ 11 እንዲሁም ከጀርመን ቦንደስሊጋ 11 ተጨዋቾች ወደ አፍሪካ ዋንጫው  መጥተዋል።
የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን በአፍሪካ ዋንጫው ላይ ለሽልማት ያዘጋጀው 12.2 ሚሊዮን ዶላር ነው። በውድድሩ አሸናፊነት ዋንጫውን የሚያነሳው 4 ሚሊዮን ዶላር፤ ለሁለተኛ ደረጃ 2 ሚሊዮን ዶላር፣ ለ3ኛ ደረጃ 1.5 ሚሊዮን ዶላር ይበረከታል። የግማሽ ፍጻሜ ተፋላሚዎች እያዳንዳቸው 1.5 ሚሊዮን ዶላር እንዲሁም የሩብ ፍጻሜ ተፋላሚዎች 800 ሺ ዶላር ይበረከትላቸዋል።
በአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌደሬሽን ስር የሚካሄደውን አፍሪካ ዋንጫ ትልልቅ ኩባንያዎች ስፖንሰር አድርገውታል። የውድድሩ አብይና የስያሜ ስፖንሰር ሆኖ የሚሰራው የፔትሮልየም ኩባንያው ቶታል ኤነርጂስ ከ2017-2025 በፈጸመው ውል ከ250 ሚሊዮን ዶላር በላይ ከፍሏል። 4 ኦፊሴላዊ  ስፖንሰሮችም ያሉት ሲሆን የቴሌ ኩባንያው ኦሬንጅ የፋይናንስ አገልግሎት ኩባንያው ቪዛ፣ የአቋማሪ ኩባንያው 1 ኤክስ ቤት እንዲሁም የአውቶሞቲቭ ኩባንያው ኮንትኔንታል ናቸው።
ታላላቅ የስፖርት ትጥቅ አምራች ኩባንያዎች ከብሔራዊ  ቡድኖች ባሻገር ምርጥ የአፍሪካ ፕሮፌሽናል ተጨዋቾችን በመጫወቻ ታኬታቸው ስፖንሰር አድርገዋል። የግብፁ መህመድ ሳላህ፣ የጊኒው፣ ናዲ ኪየታ፤ የአይቬሪኮስቱ ፍራንክ ኬሲ እና የሴኔጋሉ ኤድዋርድ ሜንዲ አዲዳስን & የሴኔጋሉ ካሊዱ ኩሊባሊ እና የአይቬሪኮስቱ ሴባስትያን ሆለር ፑማ & የአልጀሪያው ሪያድ ማህሬዝ ፣ የናይጄሪያው ዊልፍሬድ ኒዲዲ እና የጋቦኑ ኦቦ ሚያንግ ናይኪን እንዲሁም  የሴኔጋሉ ሳድዮ ማኔ ኒው ባላንስን ያደርጋሉ።
ባለፉት 7 የአፍሪካ ዋንጫዎች ሻምፒዮን የሆኑ ሀገራትን በትጥቅ አቅርቦታቸው ስፖንሰር ያደረጉት አዲዳስ፣ ናይኪ እና ፑማ ናቸው። በ2008 እና በ2010 ግብፅን ፑማ፣ በ2012 ዛምቢያን ናይኪ፣ በ2013 ናይጀሪያን አዲዳስ፣ በ2015 አይቬሪኮስትን ፑማ፣ በ2019 አልጀሪያን አዲዳስ ናቸው።
ግብፅ በአፍሪካ ዋንጫ ለ7 ጊዜያት (በ1957፣ በ1959፣ በ1986፣ በ1998፣ በ2006፣ በ2008 እና በ2010 እ.ኤ.አ ላይ) ሻምፒዮን በመሆን ከፍተኛውን የውጤት ክብረወሰን ይዛለች። ለ4 ጊዜያት ዋንጫውን በማሸነፍ ከተጨዋቾች ከፍተኛ የውጤት ክብረወሰን የያዙት ደግሞ ከግብፅ ብሄራዊ ቡድን ጋር በ1998፣ በ2006፣ በ2008 እና በ2010 እ.ኤ.አ ላይ ሻምፒዮን ለመሆን የበቁት አህመድ ሃሰን እና ኤሣም ኤልሃድሪ ናቸው።
ሶስት የአፍሪካ ዋንጫዎችን አከታትሎ በማሸነፍ ብቸኛዋ ሀገር በ2006፣ 2008 እና 2010 እ.ኤ.አ ላይ ያሸነፈችው ግብፅ ናት። ሁለት አፍሪካ ዋንጫዎችን በተከታታይ በማሸነፍ 3 ብሔራዊ ቡድኖች ይጠቀሳሉ። ግብፅ (በ1957 እና በ1959)፤ ጋና (በ1963 እና በ1965) እንዲሁም ካሜሮን (በ2000 እና በ2002) ናቸው። ለመጀመሪያ ጊዜ በተሳተፉበት የአፍሪካ ዋንጫ ሻምፒዮን ለመሆን የቻሉት 3 አገራት ግብፅ በ1957፣ ጋና በ1963 እንዲሁም ደቡብ አፍሪካ በ1996 እ.ኤ.አ ላይ ነው።
በአሁኑ ወቅት የካሜሮን እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት የሆነው ሳሙኤል ኤቶ በአፍሪካ ዋንጫ ታሪክ 18 ጎሎች በማስመዝገብ የምንጊዜም ከፍተኛው ግብ አግቢ ነው። የዲ.ኮንጎው ናዳዬ ሙሉምባ ግብፅ በ1974 እ.ኤ.አ ላይ ባዘጋጀችው የአፍሪካ ዋንጫ ላይ 9 ጎሎች በማስቆጠር ልዩ ክብረ-ወሰን አለው።
3 ተጨዋቾች በ6 የአፍሪካ ዋንጫዎች ተሳትፈው አንድና ከዚያም በላይ ጎሎች በማስመዝገብ  ስማቸው ይጠቀሳል። እነሱም የካሜሮኑ ሳሙኤል ኤቶ (በ2000 እና በ2010) ፤ የዛምቢያው ካሉሻ ቡዋሊያ (በ1982፣ በ1992 እና በ2000) እንዲሁም የጋናው ኦሳሞ ጊያን (በ2008 እና በ2017) ናቸው።
በአፍሪካ ዋንጫ ላይ ከፍተኛ ተሳትፎ ያደረጉት ሁለት ተጨዋቾች፣ (ከ1996-2010 እ.ኤ.አ) በ8 የአፍሪካ ዋንጫዎች በየብሔራዊ ቡድኖቻቸው ለመሰለፍ የቻሉት የካሜሮኑ ሪጎበርት ሶንግ እና የግብፁ አህመድ ሃሰን ናቸው።
እያንዳንዳቸው 3 የአፍሪካ ዋንጫዎችን ማሸነፍ ከፍተኛ የውጤት ክብረወሰን የያዙት ሁለት አሰልጣኞች የጋናው ቻርልስ ጊያምፊ (በ1963 ፣ በ1965 እና በ1983) እንዲሁም የግብፁ ሃሰን ሺሃታ (በ2006፣ 2008 እና በ 2010 እ.ኤ.አ) ላይ ነው።
ፈረንሳዊው ሔርቬ ሬናርድ ከሁለት የተለያዩ ብሔራዊ ቡድኖች ጋር  የአፍሪካ ዋንጫ በማንሳት ብቸኛው አሰልጣኝ ናቸው። በ2012 እ.ኤ.አ ከዛምቢያ ጋር እንዲሁም በ2015 እ.ኤ.አ ላይ ከኮትዶቯር ብሔራዊ ቡድኖች ጋር ነው።
በተጨዋችነትና አሰልጣኝነት በየብሔራዊ ቡድናቸው ዋንጫው መውሰድ የቻሉት ሁለት አፍሪካዊያን አሰልጣኞች ግብጻዊው መሐመድ ኤልጎሃሪ በ1969 በተጨዋችነትና በ1998 አሰልጣኝነት እንዲሁም ናይጀሪያዊው ስቴቨን ኬሺ በ1994 በተጨዋችነትና በ2013 እ.ኤአ ላይ በአሰልጣኝነት ነው።
ፈረንሳዊው ክላውድ ዲለሮይ በ9 የአፍሪካ ዋንጫዎች ላይ በመሳተፍ እና 6 የተለያዩ ብሔራዊ ቡድኖችን በሃላፊነት በመምራት ብቸኛው አሰልጣኝ ናቸው። ዲለሮይ በዋና አሰልጣኝነነት የተሳተፉባቸው የአፍሪካ ዋንጫዎች ከካሜሮን ጋር (በ1986 እና በ1988) ከሴኔጋል ጋር (በ1990 እና በ1992)፣ ከጋና ጋር (በ2008)፣ ከዴ.ሪ ኮንጎ ጋር (በ2006 እና በ2013  ከኮንጎ ጋር (በ2015) እንዲሁም ከቶጎ ጋር (በ2017) ነው።
በአፍሪካ ዋንጫ አዘጋጅነት ዋንጫውን ለማሸነፍ የበቁ አገራት ግብጽ (በ1959፣ በ1986 እና በ2006)፤ ጋና (በ1963 እና በ1978) ፤ ኢትዮጵያ (በ1962)፣ ሱዳን (በ1970)፤ አልጀሪያ (በ1990)፤ ደቡብ አፍሪካ (በ1996) እንዲሁም ቱኒዚያ (በ2004) ናቸው።
በ25 የአፍሪካ ዋንጫዎች ላይ በመሳተፍ ክብረወሰን የያዘችው ግብፅ ስትሆን ቱኒዚያ ደግሞ ከ1994-2021 እ.ኤ.አ  ባሉት ጊዘቴያት 15 የአፍሪካ ዋንጫዎችን በመሳተፍ  በማሸነፍ ትጠቀሳለች።
ባለፉት 64 ዓመታት በተካሄዱት 33 የአፍሪካ ዋንጫዎች 44 አገራት ለመካፈል በቅተዋል። በ33ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ላይ ጋምቢያና ኮሞሮስ  በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ይሳተፋሉ።
በአፍሪካ ዋንጫ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ይሳተፋሉ። በአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፈው የማያውቁ 10 አገራት መካከለኛው አፍሪካ ሪፓብሊክ፣  ቻድና፣ ጅቡቲ፣ ኤርትራ፣ ኤስትሞኒ፣ ሌሴቶ፣ ሰአቶሚና ፕሪንሲፒ፣ ሲሸልስ፣ ሶማሊያና ደቡብ ሱዳን ናቸው።
በአፍሪካ ዋንጫ ላይ በአንጋፋ ዕድሜ ክብረወሰን የያዘው ተጨዋች በ44 ዓመት ከ21 ቀናት ዕድሜው በ2017 እ.ኤ.አ የተሰለፈው የግብፁ ኤሣም ኤልሃድሪ ነው። በ2000 እ.ኤአ ላይ በተካሄደው የአፍሪካ ዋንጫ ላይ በ16  ዓመት ከ93 ቀናት ዕድሜውን  በመሰለው ደግሞ ጋቦናዊው ተጨዋች ሺቫ ጊዚንጉው ይጠቀሳል።
ናይጀሪያ አፍሪካ ዋንጫ ላይ ለ15 ጊዜያት ከ1-3 ባለ ደረጃ ገብታ ከተፍኛውን ውጤት በማስመዝገብ ግንባር ቀደም ናት። ለ3 ጊዜያት ዋንጫውን ስታሸንፍ 4 ጊዜ በ2ኛ ደረጃ 8 ጊዜ ደግሞ በ3ኛ ደረጃ ጨርሳለች።
በ2019 እ.ኤ.አ ላይ ግብፅ ባስተናገደችው 32ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ላይ በ52 ጨዋታዎች 102  ጎሎች መቆጠራቸው በውድድሩ ታሪክ ከፍተኛው የጎል መጠን ሲሆን፤ በ1957 በተካሄደው የአፍሪካ ዋንጫ በ2 ጨዋታዎች 7 ጎሎች መመዝገባቸው ደግሞ አነስተኛው የግብ መጠን ነው።
በአፍሪካ ዋንጫ ታሪክ 6 ተጨዋቾች 1 ጊዜና ከዚያ በላይ ኮከብ ግብ አግቢ  ሆነው ጨርሰዋል። የኮትዲቯሩ ሎረንት ፓኩ (በ1980)፣ የካሜሮኑ ሮጀር ሚላ (በ1986 እና በ1988)፣ የናይጀሪያው  ራሺዲ ያኪኒ (በ1992 እና በ1994)፣ የካሜሮኑ ፓትሪክ ምቦማ (በ2002 እና በ2004) እንዲሁም የካሜሮኑ ሳሙኤል ኤቶ (በ2006 እና በ2008) ናቸው።
የአፍሪካ ዋንጫን ለ5 ጊዜያት በማዘጋጀት ግብፅ (በ1959፣ በ1974፣ በ1986፣ በ2006 እና በ2019) መጀመሪያዋ ናት። ጋና ለ4 ጊዜያት (በ1963፣ በ1978፣ በ2000 እና በ2008) ኢትዮጵያ ለ3 ጊዜያት ( በ1962፣ በ1968 እና በ1976) ፣ ቱኒዚያ ለ3 ጊዜያት (በ1965፣ በ1994 እና በ2004)፣ እያንዳንዳቸው ለ2 ጊዜያት በማዘጋጀት ሱዳን (በ1957 እና በ1970)፣ ካሜሮን (በ1972 እና 2021) ናይጀሪያ (በ1980 እና በ2000 )፣ አይቬሪኮስት(በ1984 እና በ2023) ደቡብ አፍሪካ (በ1996 እና በ2013፣ ኢኳቶሪያል ጊኒ (በ2012 እና በ2015)፣ ጊኒ (በ2012 እና በ2017) እያንዳንዳቸው ጊዜ በማዘጋጀት ሊቢያ (በ1982)፣ ሞሮኮ (በ1988)፣ አልጀሪያ (በ1990)፣ ሴኔጋል በ1992፣ ቡርኪናፋሶ (በ1998)፣ ማሊ (በ2002)፣ አንጎላ (በ2010) እንዲሁም ጊኒ (በ2025) ናቸው።
በአፍሪካ ዋንጫ ላይ በብዙ ተከታታይ ጨዋታዎች  ባለመሸነፍ ክብረወሰን ያስመዘገበው ከ2004-2017 እ.ኤ.አ በተደረጉት የአፍሪካ ዋንጫ ጨዋታዎች በ24 ጨዋታዎችን ያልተሸነፈው የግብፅ ብሄራዊ ቡድን ነው። በተጠቀሱት ጊዜያት የግብፅ ቡድን 9 የአፍሪካ ዋንጫ ጨዋታዎችን በተከታታይ በማሸነፍ ይጠቀሳል።
በአፍሪካ ዋንጫ ላይ ሻምፒዮን ለመሆን የበቃ የመጀመሪያው አፍሪካዊ ያልሆነ አሰልጣኝ በ1959 እ.ኤ.አ ላይ ከግብፅ ጋር ዋንጫውን ያሸነፈው ግሪካዊው ፖል ቲታኮስ ነው። በሌላ በኩል 5 ፈረንሳዊያን አሰልጣኞች ከተለያዩ ቡድኖች ጋር አፍሪካ ዋንጫውን አሸንፈዋል።  


Read 26369 times