Tuesday, 04 January 2022 00:00

የኢትዮጵያ ምጣኔ ሀብት:- ለጊዜው እንዲያገግም ለዘለቄታው እንዲለመልም

Written by  እፁብድንቅ ስለሺ
Rate this item
(1 Vote)

(ክፍል ፩)
ነፍሰጡር  በወለደች ጊዜ የፈሰሰ ደሟን እንድትተካ፣ በምጥ የደከመ አኳሏ እንዲያገግም፣  በእርግዝና የዛሉ ጡንቻዎቿ እንዲጠገኑና ለህፃን የሚሆን ወተት ጡቶቿ ያመነጩ ዘንድ ዘመድ አዝማድ በተቻለው መጠን ልዩ ልዩ ምግብ  ያቀርባል። እርሷም  ምግቡ እየጠገናት፣ የልጇ ሳቅ ቁስሏን እያስረሳት  በወራት ውስጥ ወደ ቀደመ ጤንነቷ ትመለሳለች። ከዚህ አለፍ ሲልም ቆይታ ሌላ ልጅ ልታረግዝ ትችላለች። በፈተና ውስጥ ያለች አገር ምጣኔ ሀብት ጉዳይም ከዚህ ተለይቶ አይታይም። አገር አንድነትን አርግዛ፥ በተጋድሎ  ምጥ  ነፃትን ወልዳ፥ ክብርን  በታሪኳ ወተት እያፋፋች እንድታሳድግ “አራሳዊ” እንክብካቤ ያስፈልጋታል። የጭካኔ መድረክ፣ የውድመት አውድማ፣ የውጊያም ቀጠና  ሆኖ በቆየው የአገራችን  ክፍል  የምግብ እጥረት እንዲቀረፍ፣ የውሃና የመብራት አገልግሎት ዳግም እንዲሳለጥ፣ የጤና፣ ትምህርትና መሰል መሠረታዊ አገልግሎቶች ቢያንስ  በፍጥነት  ወደ ነበሩበት እንዲመለሱ የሚያስችሉ የበጀታዊ (ከመንግሥት ወጪና ገቢ ጋር የተያያዘውን ሁሉ) እና ገንዘባዊ (ከብድር፣  ወለድ፣ የውጭ ምንዛሪ አቅርቦትና ድልድል፣ የዋጋ መናር ጋር የተሣሠረው ጉዳይ) መንግሥታዊ የምጣኔ ሀብት እርምጃዎች ያስፈልጋሉ። ማህበረሰቡ በአጠቃላይ እንዲሁም መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የሚያደርጉት የመልሶ መገንባት ርብርብ  በአጋዥነት የሚወሰዱ እንጂ የመንግሥትን  በጀታዊና ገንዘባዊ እርምጃዎች የሚተኩ አይደሉም። በነዚህ ጉዳዮች ላይ ዘርዘር ያለ ሀሳብ ቀጥሎ ይቀርባል።
1) በጀታዊ የአፋጣኝ መልሶ መገንባት መንገዶች። የውድመትን ግምት የሚያጠኑ ጉባኤያት ተሰይመው  በመለስተኛ ጥናት በሚደርሱበት  የሰዎች ሕይወት ጥፋትን ብዛት፣ የግለሰቦች ሀብትና ንብረት ውድመት መጠን፣ የህዝብና የመንግሥት መሠረተ ልማት  ላይ የደረሰ ኪሳራ መጠን  ሁሉ የሚያሳይ ውጤት  ላይ ተመሥርቶ  የነፍስ አድን ሥራ መጀመር ይቻላል (ከጊዜ በኋላ ግን ጥልቅ ጥናት በማካሄድ የደረሰውን  የጥፋት አድማስ ለመማሪያም  ለመመሪያም እንዲያገለግል ተደርጎ ሊዘጋጅ ይችላል)።  የጦርነቱ ግንባር ቀደም ሰለባ የሆኑ የአገራችን አካባቢዎችን በተጨማሪ በጀት (ድጎማ)፣ ወይም ካልተጎዱ   ዘርፎች በጀት በማዛወር (ለምሣሌ  ቴሌ የትምህርት ዘርፉን ሊያግዝ ይችላል። በግምገማው ውጤት መሠረት  በጤና ተቋማት ላይ የደረሰው ጉዳት አባሽ ከሆነ) ፣ አንድም ካልተጎዱ አካባቢዎች “አንድ ሰላማዊ ወረዳ ለአንድ የተጎዳ ወረዳ” በስጦታ መልክ  ዳጎስ ዳጎስ ያለ  የበጀት ዝውውር በማድረግ   ውድመት የደረሰባቸውን ጤና ጣቢያዎች፣ ኮምፒውተሮቻቸው ተነቃቅለው የተወሰዱባቸው ትምህርት ቤቶች፣ ወና የቀሩት  የምግብና  ማምረቻ ቤቶች  ሁሉ ቶሎ ብለው ወደ ሥራ እንዲመለሱ መዋቅራዊ አቅጣጫና  መንግሥታዊ ድጋፍ ማግኘት አለባቸው። ከዚህ ሁሉ የከፋው ጥፋት  ሰብአዊ ጉዳት ነው። ቤተሰባቸውን ያጡ አሉ። እራሳቸው የቆሰሉም አሉ፣ ዘግናኝ ፆታዊ ጥቃት የደረሰባቸው  ብዙዎች መሆናቸውን ዘገባዎች ያሳያሉ፤   እህልና ከብቶቻቸው የተጋዙባቸው፣  በየቤታቸው ከግድግዳና ጣሪያ በስተቀር ዕድሜ ልክ ያፈሩት የቤት እቃ ሁሉ ተዘርፎ  እንዲሁ የሚቆዝሙ ብዙ አሉ። የነዚህ ሁሉ ድምር የሚያደርሰው ስነ ልቡናዊ ጠባሳ አለ። ታዲያ ጦርነቱ ባወደማቸው አካባቢዎች የምግብ እህሎች በድጎማ  ዋጋቸው ቀንሶ እንዲሸጡ፣ ከተቻለም  እንደየ አካባቢው ጉዳት መጠን ለተወሰኑ ወራት የሚያዘልቅ የምግብ እህል በነፃ እንዲሰጡ ማድረግ ይበጃል። ምርታማ ከሆኑና በጦርነት ካልተጎዱ የኢትዮጵያ አካባቢዎች  እህልና እንስሳት(የእርሻ በሬዎቻቸው ታርደው የተበሉባቸው ብዙዎች ስለሚኖሩ) ጉዳት ወደ ደረሰባቸው አካባባቢዎች  ባሉ ገበያዎች ባልተጋነነ ትርፍ ለገበያ የሚቀርቡበት መንገድ ቢመቻች  ሻጭም ገዢም የተሻለ ገበያ ያገኛሉ። የእርሻ መሬትም በቀጣይ ጦም አያድርም። ለዘር የሚሆን እህል ማቅረብንም ሊጨምር ይችላል፤ እገዛው።  የግብርናው ዘርፍ ከአጠቃላይ አገራዊ ምርታችን ወደ አርባ በመቶ የሚሆነውን ስለሚሸፍንና   ከአምሥት ለአካለ መጠን የደረሱ ሰዎች አራቱ የተሠማሩበት የሥራ መስክ በመሆኑ  እነዚህ እርምጃዎች የአጠቃላይ አገራዊ ምርትም በቶሎ እንዲያገግም ይረዳሉ። ታዲያ ነጋዴዎችም በዚህ  አጣብቂኝ ሰዓት የተጋነነ ትርፍ ማጋበስ  ላይ ሳያተኩሩ ማህበረሰባዊ ሃላፊነታቸውን የሚወጡ ከሆነ  በጊዜ ሂደት  ከሚያገግመውና ከሚያድገው ምጣኔ ሀብት  የዘሩትን  በብዙ እጥፍ  ከገበያ ላይ ያጭዳሉ።
 እንግዲህ ይህ ሁሉ  ሰብአዊ ፣ ቁሳዊና ስነ ልቡናዊ ችግር  መንግሥት የሚጠበቅበትን፣ ህዝብም ማድረግ ያለበትን ፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ማህበራትም ሚናቸውን የሚወጡ ከሆነ   ከዓመት ባነሰ ጊዜ  ከጦርነት በፊት ወደ ነበረው ቁመና መመለስና በቁጭት ላቅ ወዳለ ልማታዊ ምህዋርና ማህበራዊ መስተጋብር መገሥገሥ ይቻላል። በተያያዘ፣ መቼም በነዚህ አካባቢዎች ዘንድሮ የግብር ምህረት መደረጉ አሌ የማይባል ነው። ገበሬው፣ ነጋዴውና ሠራተኛው  ኑሮና ሥራው  ታውኮበት ስለሚገኝና የወደመው ንብረቱ ከገቢዉ በላይ ስለሚሆን የመሬት ኪራይ፣ የገቢ ግብርና መሰል የዜግነት አውጫጭኞች ለመሰብሰብ አይቻልም። ምናልባት በሌላ አካባቢ ባለው ዜጋ  ላይ መጠነኛ የግብር ጭማሪ በማድረግ  የመንግሥት ገቢና ወጪ ሚዛንን መጠበቅ ይቻላል። ካልሆነም በየትኛውም አገር  ብሔራዊ አደጋ ባጋጠመ ጊዜ እንደሚደረገው  ለተወሰነ  ወቅትም ቢሆን የበጀት ጉድለትን ማስታመም ያስፈልጋል።  የበጀታዊ እርምጃዎች ሲጠቃለሉ  የወደሙ ሀብት ንብረቶችን እንዲሁም የመንግሥት የልማት አዉታሮችን ወደ ቀደመ ጤናቸው ለመመለስ ከመንግሥት ካዝና ወጪ የሚደረጉትን  እንዲሁም በተጎዱ አካባቢዎች የግብር ምህረት ማድረግ የመሳሰሉ  የምጣኔ ሀብቱ ቁስል እንዲጠግን የሚያደርጉ ፈዋሽ ተግባራት ናቸው።
 2) መልሶ ግንባታን የሚያግዙ ገንዘብ ነክ እርምጃዎች። ይህ በተራ ቁጥር አንድ ከተጠቀሱት ጋር የሚገናኝበት  መንገድ አለው። መንግሥት በብሔራዊ ባንክ በኩል የግምጃ ቤት ሰነድ ሸጦ   ካገር ዉስጥ ብድር ሊያገኝና ከላይ ለጠቀስናቸው  የነፍስ አድንና የመልሶ ማቋቋሚያ ሥራዎች ሊያውል ይችላል።  ብሔራዊ ባንክ አሁን ያለውን ችግር የሚያቃልሉ ሌሎች ብዙ እርምጃዎችንም የመውሰድ አቅም አለው።  ሊወሰዱ ከሚገባቸው ገንዘባዊ እርምጃዎች ውስጥ፣ ለወደሙ ፋብሪካዎች መልሶ  ግንባታ የሚበቃ  በዝቅተኛ ወለድና ባልተጋነነ ዋስትና  እንዲቀርብ ማስቻል፤ እነዚህ ፋብሪካዎች  ከውጭ የሚፈልጓቸው ግብአቶች ሲኖሩ ደሞ  የምንዛሪ ድልድል ላይ  ቅድሚያ እንዲሰጣቸው ማድረግ፣ ከዚህ ቀደም ተበድረው   በጦርነቱ ምክንያት ያልከፈሉት ወለድ ወይም ዋና ቢኖር  የምህረት ጊዜ እንዲሰጣቸው ማድረግ  ሊጠቀሱ ይችላሉ።  ገንዘባዊ  እርምጃዎች  ከብሔራዊ ባንክ ጀምሮ ፣ የመንግሥትና የግል ንግድ ባንኮችን፣ ልማት ባንክን፣ በየአካባቢው የሚገኙ አነስተኛ የብድርና ቁጠባ ተቋማትን ሱታፌ በማቀናጀት የሚከናወን ነው።  ብሔራዊ ባንክ በቅርቡ ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ጋር የተጣሉ አንዳንድ  ክልከላዎችን  ማንሳቱ ትክክል ነው።
  በጦርነት ቀጠና ውስጥ  ገፈት ቀማሽ ለሆኑ ዘርፎች በተለየ ያደረገው እንቅስቃሴ ግን እስካሁን የጎላ እንቅስቃሴ ሲያደርግ አላየንም። እዚህ  ላይ  ብሔራዊ ባንክ የሚወስዳቸው እርምጃዎች በተፈጥሯቸው አጠቃላይ ምጣኔ ሀብቱን እንጂ አንድን አካባቢ  ኢላማ አድርገው ለመተግበር ያስቸግራሉ የሚል ሙግት የሚያነሳ ሊኖር ይችላል። በአንድ አገር ምጣኔ ሀብታዊ ሥርዓት ውስጥ፣ ብሔራዊ ባንክ የልብን ሚና ሲጫወት፣ ገንዘብ ደሞ እንደ ደም ነው። ልክ የልብ ሥራ ወደ ሁሉም የሰውነት ክፍል  ደም መላክና መቀበል እንደሆነው ሁሉ፣ ከሰውነት አንዱ ክፍል በደማ ወይም በተዉሳክ በተጠቃ ጊዜ፣ ልብ  ያን ቀጠና ጤነኛ ለማድረግ  የሚረዱ የሰውነት መከላከል አቅም፣ ሃይላትን ወደዚያ በመላክ ላጠቃላዩ አካልም፣ ለተጎዳው ክፍልም  ሥራውን ይሠራል። ባንኩም እንዲሁ የገንዘብ ሥርዓቱን ስልተ ምት በመቆጣጠር   በእጃችን የምንይዘውን ገንዘብ፣ በባንክ የምቆጥበውን መጠን፣ ለንግድና ሥራ የሚውለዉን ሁሉ ልጓም እያጠበቀና እያላላ (ለምሳሌ፡- የወለድ መጠን በመቀያየር፣ የገንዘብ ተቋማት እንዲስፋፉ በማድረግ፣ የብድርና የምንዛሪ ህግጋትን በማስተዋወቅና በማሻሻል ወዘተርፈ)  ሲቆጣጠር ይኖራል። ስለሆነም ብሔራዊ ባንክ የሚወስዳቸው እርምጃዎች አገራዊ አድማስ ያላቸው መሆኑ  ይበልጥ  ምጣኔ ሀብቱን ያነቃቁታል እንጂ  በስሌት እስከተተገበሩ ድረስ አሉታዊ ውጤታቸው ያይላል ለማለት አይቻልም ( በሀብት ንብረት ላይ የደረሰው ውድመት  ከፍተኛ በመሆኑ  የመግዛት ፍላጎት ከአቅርቦት በላይ ሊሆን እንደሚች ለመገመት ይቻላል። ቢያንስ ለጥቂት ጊዜ። ይህ ወደ አካባቢዉ  የሚፈስ ገንዘብ ሲታከልበት  የዋጋ መናር ማስከተሉ አሌ የሚባል አይደለም። ሆኖም ጉዳቱ የሚያካልላቸው ቦታዎች የአጠቃላይ አገራዊ ምጣኔ ሀብቱ ክፍልፋይ ስለሆኑ፣ በዚህ ሰበብ የሚመጣ የዋጋ ግሽበት በብሔራዊ ደረጃ  ሲመዘን አይጋነንም ባይ ነኝ)።  ስለዚህ   ብሔራዊ ባንክ  ለመልሶ ግንባታ የሚያግዙ አቅጣጫዎችን በማስቀመጥ የገንዘብ ዘርፉ ሚናውን እንዲወጣ ማስቻል አለበት። እንግዲህ ከላይ የተዘረዘሩት መንግሥታዊ  የበጀትና ገንዘባዊ እርምጃዎች፣  የህዝቡና የማህበራት ሚና  ለጊዜው እሳት ለማጥፋት የሚያግዙ ቅጠሎች እንጂ ለዘለቄታዉ  ምጣኔ ሀብታችን እንዲያንሠራራ ሠፊና ሥር ነቀል አገራዊ ንቅናቄ ያሻናል።
3) አብነቶች፦ በዘመናዊው የዓለም ታሪክ ውስጥ በጦርነት ምክንያት (ርእደ መሬት፣ የጥፋት ውሃ/ሱናሚ፣ ወዠቦ፣ በረድ ፣ አንበጣ   የመሣሰሉ ተፈጥሯዊ አደጋዎችንም ይጨምራል)   አፈር ልሰው  የተነሡ፣  ዘመው የተቃኑና ተቆርጠው ያቆጠቆጡ ብዙ ምጣኔ ሀብቶች አሉ።
 ለዚህ ትምህርት ይሆነን ዘንድ ዓይኖቻችን ድንበር ቢሻገሩ ምናቦቻችንም  ወደ ታሪክ ቢሠግሩ  አሁን እኛን የገጠመን አውዳሚ ጦርነትና ፈተና ሌላው ዓለምም በተለያየ መልክና ጊዜ ቀምሶት ነበር ወይም እየቀመሰው ያለ ነገር ነው ለማለት ይቻላል። ከእንደዚህ ዓይነት ችግሮች ማግሥት አስደናቂ ልማታዊ ግሥጋሤ በአጭር ጊዜ ያስመዘገቡ አገሮች ብዙ ናቸው። ጃፓኖች በሁለተኛው የዓለም ጦርነት እስከ ዘጠና በመቶ የሚሆነው የማምረቻ አቅም ወድሞባቸው ሳለ በኋላ  በጥቂት ዓመታት  የጠራ ግብ አልመው፣ የማይነጥፍ ትጋት አሳይተው፣ እጅግ በተሣለጠ  አገራዊ መናበብ “የምጣኔ ሀብት ተዓምር”ሊከውኑ ችለዋል። ዛሬ ሦስተኛው ታላቅ የዓለም ምጣኔ ሀብት የነሱ ነው።
 በ1980ዎቹ  ጀምሮ እድገታቸው በልዩ ልዩ ምክንያት ተቀዛቀዘና  ወደ ዝግመት ገባ እንጂ  እንዳያያዛቸው  ከየትኛውም አገር  ቀዳሚ የሚሆን ምጣኔ ሀብት ለመገንባት ችለው ነበር።  ከደቡብ ኮርያ እስከ ጃፓን፣ ከጀርመን እስከ ጣሊያን ፣ ከቬትናም እስከ ከህንድና ቻይና አንድም ከውስጣዊ  ድህነትና ግጭት፣ አንድም  ከውጫዊ ግጭት ማግሥት ባደረጓቸው  የምጣኔ ሀብት ማሻሻያዎች  በአጭር ጊዜ  ህዝባቸውን  ወደ ተድላ ሰገነት ሊያወጡ ችለዋል።
ለመሆኑ ምን ምን አደረጉ? እኛ አሁን ያለንበት የችግር ደረጃና ዐውደ ዓለም እንዴት ከነሱ የያኔው ዓለም ይለያል?  ኢትዮጵያስ ተጣብቷት የቆየውን የጠማማ ርእዮተ ዓለም ትብታብ፣ የምጣኔ ሀብት ድቀት፣ ማህበራዊ መንገራገጭ፣ ባህላዊ ተቸንክሮና መንፈሳዊ ድህነት እንዴት እንዴት ልትቀርፋቸው ትችላለች?  በቀጣይ ከነዚህ  አንዱን ዘለላ መዝዤ የማቀርብ ይሆናል።
ቸር ያሰንብተን!
ከአዘጋጁ፡- ጸሃፊውን በኢሜይል አድራሻው፡- This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል፡፡


Read 12369 times