Print this page
Monday, 03 January 2022 09:41

የህዝብ ደጀንነት በማገገሚያ ማዕከላት

Written by 
Rate this item
(1 Vote)


             ከአንድ አመት በላይ  በተሻገረውና በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል በአሸባሪው የህውሃት ቡድን በተቀሰቀሰው ጦርነት በርካታ መስዋዕትነት ተከፍሏል። የንፁሃን ህይወት ጠፍቷል፣ ንብረት ወድሟል፣ በርካታ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውሶች ተከስተዋል። ብዙዎችም ለከፍተኛ የስነ ልቦና ጫና ተዳርገዋል። ይህም ሆኖ የመከላከያ ሰራዊት ከአማራና አፋር ልዩ ሃይል ከፋኖና ከሌሎች ክፍሎች ከተውጣጡ ልዩ ሃይሎች ጋር በመሆን በህዝቡ ደጀንነት አሸባሪው ሃይል ከፍተኛ ሽንፈት ደርሶበት የሰሜን ወሎና የአፋር አካባቢዎች ነጻ ወጥተዋል። ይህ የሆነው ጥምር የጦር ሀይሉ በፈጸመው ገድልና በከፈለው መስዋዕትነት ነው። ለአገር ሉአላዊነት ሲሉ ህይወታቸውን የከፈሉ እንዳሉ ሁሉ ቆስለው በህክምና ላይ የሚገኙም አሉ፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ በአዲስ አበባ በጦር ሃይሎች ሆስፒታል ስር ከሚገኙ ማገገሚያ ማዕከላት መካከል በቤላ ማገገሚያ ማእከል ተገኝታ ቁስለኞቹን ጎብኝታ የቤላ ማገገሚያ ማዕከል የሰው ሀብትና የጠቅላላ አገልግሎት አስተባባሪ የሆኑትን ሌተና ኮሎኔል አብርሃም ጋሪን እንዲሁም ድጋፍ ለማድረግ በማዕከሉ የተገኙ የአዲስ አበባና የድሬደዋ ወጣቶችን አነጋግራለች።

                ማህበረሰቡ ለጦር ጉዳተኞቹ ከፍተኛ የሞራልና የቁሳቁስ ድጋፍ እያደረገ እያስደሰተን ነው
                            (ሌ/ኮ አብርሃም ጋሪ)

            ከአንድ ዓመት በፊት የተከፈተብን ጦርነት ለሁላችንም ግልጽ ነው። አብረን እየበላን አብረን እየጠጣን፣ እርሻቸውን እያረስን፣ እህላቸውን እያረምንና እያጨድን እነሱን እናትና አባት አድርገን አምነናቸው፣ ለእነሱ እየኖርንና እየሞትን ባለንበት መልሰው ከጀርባችን ወግተውናል። ይህም አልበቃ ብሎ መንግስታችን የትግራይ ገበሬ እርሻውን ይረስ የጥሞና ጊዜ ይኑረው ብሎ የተናጠል ተኩስ አቁም በማድረግ ውጊያ ሲያቆም ወራሪው ሃይል ይህንን አጋጣሚ በመጠቀም እስከ ሰሜን ሸዋ ድረስ በመግባት ወረራና ውጊያ ፈጽሞብናል።
በዚህ ሂደት አገሬን አላስደፍርም ያለው የኢትዮጵያ ቆራጥ ልጅ አገሩ እንዳትደፈር እንዳትበታተንና ለጠላት ተላልፋ እንዳትሰጥ ግንባሩን ለጥይት ሰጥቶ ተፋልሟል። ይህ ጀግና እዚህ እኛ ዘንድ ለህክምና መጥቷል። እኛም እያከምነው እያዳንነው እንገኛለን። ከዳኑና ካገገሙ በኋላ ወደ ግንባር የሚመለሰውና በጥሩ ጤንነት ላይ ያለውን እየላክን፣ ያንን ማድረግ የማይችለውን ወደየ ቤተሰቡ እየላክን ነው የምንገኘው።
ይህ አገር ወዳድ ወጣት ለሀገሩ የከፈለውን መስዋዕትነት ህዝቡ መጥቶ እያደነቀ፣ እያመሰገነ ድጋፍና ፍቅሩን እየገለጸ እያበረታታ ይገኛል። በጦር ሜዳ ቆስሎ እዚህ ያለ ወጣት የህዝብን ፍቅርና እንክብካቤ ሲመለከት ለዚህ ህዝብ እንኳንም መስዋዕትነት ከፈልኩ በሚል ደስታ ሲሰማቸው እንዲሁም አገግመውና ድነው ቶሎ ወደ ግንባር ለመመለስ ሲጓጉ እያስተዋልን ነው። እኛም በዚህ አጋጣሚ ህዝቡን ማመስገን እንፈልጋለን። አሁን ላይ እያገገሙ ላሉት ለእነዚህ ጀግኖች የህዝቡ አይዞህ ባይነት ከፍተኛ ሞራል እየሆናቸው ፍቅር እያገኙ ነው። ቀድሞም ቢሆን ከህዝብ ያራራቀን ይሄው አጥፊ ቡድን ይመራው የነበረው ሰርዓት ነው። አሁን ደግሞ ለሀገራችን እንሞታለን ያንን ስርዓት እንዋጋለን በማለት በከፍተኛ የሞራል መነቃቃት ውስጥ ይገኛሉ።
አሸባሪው ህውሃት በቀደሙት በርካታ አመታት ህዝቡን በጎጥ፣ በቋንቋ፣ በወንዝ እየከፋፈለ ውስጥ ለውስጥ ሲያባላን ኖረ፣ አሁን በግልጽ ያንን ሰይጣናዊ ተግባሩን አሳየን። በአሸባሪነት ተፈረጀ፤ አገር ሊያፈርስ ተነሳ። እንዲህ አይነት ግንባራቸውን ለጥይት የሚሰጡ ጀግኖች እያሏት ኢትዮጵያ ፈጽሞ አትፈርስም። ይህም በደንብ ታይቷል። በዚህ ሁሉ መሃል የህዝቡ ርብርብና ደጀንነት ይበልጥ ልብ የሚያሞቅ ሆኖ አግኝተነዋል። ራሳችንን አሳልፈን እንሰየፋለን እንጂ ሀገራችንና ህዝባችን በአሸባሪዎች አይዋረዱም። ጠቅላይ ሚኒስትራችን “በኢትዮጵያ ከመጡ አንገቴ ይቀላል እንጂ አገሬን አሳልፌ አልሰጥም” ያሉትን አባባል እንደ መፈክር በመውሰድ ለሀገራችን ህይወታችን እስክታልፍ እንዋደቃለን።አጠቃላይ ደጀንነትን በተመለከተ እንነጋገር ከተባለ ከ1997 ዓ.ም ጀምሮ ህዝብና ወታደር ተራርቆ ነበር። በአሁኑ ወቅት ግን ህዝብና ወታደር አይለይም። የኢትዮጵያ ህዝብ በአሁኑ ወቅት ከልጅ እስከ አዋቂ  ወታደር  ሆኗል። ለወታደሩ ወገናዊነቱንና ደጀንነቱን አረጋግጧል። አሁን የምንገኝበትን የማገገሚያ ማዕከል ከቢሮነት ወደ ሆስፒታልነት ስንቀይር እንኳን ከጽዳት እስከ ስራው ማጠናቀቂያ ድረስ ህዝብ ከጎናችን ሆኖ ነው ያጠናቀቅነው።
ህዝቡ የቁስለኞችን አመጋገብ በመከታተል፣ ልብሳቸውን በማጠብ፣ ጸጉራቸውን በማስተካከል፣ ሴቶቹ የሴቶቹን ጸጉር በመስራት እየተንከባከቡ ከጎናችን አልተለዩም። በዚህ አጋጣሚ በየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 3 አቶ ታደለ ተድላ የተባሉ የወረዳ አስተዳዳሪውን ላመሰግናቸው እወዳለሁ። ምክንያቱም እርሳቸው ለመጀመሪያ ጊዜ መጥተው ማገገሚያ ማዕከሉንና ታካሚዎቹን ከጎበኙ በኋላ ያዩትን ለክፍለ ከተማው በመግለጽ በሰሩት ስራ እስካሁን የየካ ክ/ከተማ ህዝብ አንድም ቀን ከጎናችን አልተለየም። ይህን ያየው የሰራዊቱ አባል አሁንም ለዚህ ህዝብ ወደ ግንባር ሄጄ እሞታለሁ እያለ ነው ያለው።“አንተ ለጡረታም ለቦርድም እዚህ ቆይ ትንሽ ተጎድተሃል” ሲባል እንኳን “ደህና ነኝ ሄጄ እዋጋለሁ” እያለ ነው እየሄደ ያለው። ይህን የሚያስብለው የህዝቡ ደጀንነትና ፍቅር ነው። ወገንተኝነቱን ህዝቡ በማረጋገጡ ነው። አሁን ዛሬ እዚህ ስትመጡ የድሬዳዋ ልጆች በማህበራቸው መጥተው ድጋፍ እያደረጉ ነው። “ኢትኸርባል” የተሰኘ የውበት መጠበቂያ አምራች ድርጅት ባለቤት ወጣት ማቲዎስም ይሄው በተደጋጋሚ እየመጣ የሚችለውን እያደረገ፣ ከባልደረቦቹ ጋር የሰራዊቱን አባላት እየጎበኘ ወገንተኝነቱን እያሳየ ነው ያለው። እናቶች ቡና እያፈሉ፣ የሰራዊቱን አባላት እየመረቁ፣ እያጫወቱና እየተንከባከቡ ይገኛሉ። ወጣቶች በየማህበራቸው ለምሳሌ የቤተክርስቲያን ማህበር፣ የበጎ አድራጎት ማህበራትና ሌሎችም ይመጣሉ፤ የሚችሉትን ነገር ሁሉ እያደረጉ ነው ያሉት። የጎደለብን ነገር የለም። በዚህ አጋጣሚ ለህዝቡ ያለኝን ክብርና አድናቆት መግለጽ እፈልጋለሁ፤ እጅግ እጅግ አመሰግናለሁ። አሁንም ለባንዳ ለተላላኪ፣ ለአሸባሪ አንንበረከክም፣ ኢትዮጵያና ህዝቦቿ ያሸንፋሉ፤ አሸንፈዋልም።

______________

              “አለን ከጎናችሁ ነን ለማለት ነው በማዕከሉ የተገኘነው”
                         (ወጣት ማቲዎስ መባ)

               ማቲዎስ መባ እባለሁ። የ”ኢትኸርባል” የውበት መጠበቂያ ምርቶችን በአገራችን በተፈጥሮ ዕፅዋቶች በማምረትና ለተጠቃሚ በማቅረብ ስራ ነው የተሰማራነው። ዛሬ እዚህ ቤላ የጦር  ሰራዊቱ ማገገሚያ ማእከል ስንገኝ ለሶስተኛ ጊዜያችን ነው። በተከታታይ ለሶስት ሳምንታት ለእኛ ሲሉ ለቆሰሉ ፣ የደሙ፣ ነፍሳቸውንም  ያለስስት ሊሰጡን ቆርጠው ለተነሱ ጀግኖች ወንድምና እህቶቻችን ያለንን አክብሮት፣ ፍቅርና ወገናዊነት ለመግለጽ ነው እየተገኘን ያለነው። እውነት ለመናገር እዚህ ይዘን ከምንመጣው የቁሳቁስ ድጋፍ ይልቅ እኛ መምጣታችን ይበልጥ ታካሚዎቹን ሲያስደስታቸው በመመልከቴ ነው፣ አሁን ከስራ ባልደረቦቼ ጋር በተደጋጋሚ እየመጣሁ ያለሁት።
እነሱ ለእኛ ከከፈሉልን መስዋዕትነት አንጻር  የእኛ እዚህ መገኘትም ሆነ የምናደርገው ድጋፍ ኢምንት ነው። ለዋሉልን ውለታ የምንከፍለው ባይኖርም እንኳን እዚህ መጥተን እንወዳችኋለን፣ ከጎናችሁ ነን በማለት ማበረታታትና ማመስገን አለብን። በተለይ ወጣቶች ይህን ማድረግ አለባቸው። እኔ አሁን ለቃለ መጠይቅ ስጋበዝ  ለመናገር የፈቀድኩት እንደኔ ያሉ ወጣቶች (እኔ በ30ዎቹ መጀመሪያ ላይ የምገኝ ነኝ) እዚህ እየመጡ እየጎበኙ፣ አይዟችሁ እያሉ እንዲያበረታቱና ድጋፋቸውን እንዲያሳዩ ለማበረታታት ነው።
ምን ይዛችሁ መጣችሁ፣ ምን ድጋፍ አደረጋችሁ ለተባለው “ኢትኸርባል” ከሚያመርታቸው የውበት መጠበቂያ ምርቶች በተለይ ለሴት የሰራዊቱ አባላት ለ50 ያህሉ ከእሬትና ከሌሎች የተፈጥሮ ዕፅዋቶች የምናዘጋጃቸውን ለጸጉር ተስማሚ የሆኑ ሻምፖዎችንና የጸጉር ቅባቶችን፣ ወደ 200 ሊትር መልቲ ፐርፐዝ የሆነ ላርጎ ፈሳሽ የልብስ ሳሙና እንዲሁም 270 ኪ.ግ ሙዝ፣ ይዘን ነው የመጣነው። ይሄ በጣም ትንሽ ነው። ነገር ግን ሌላውም ያለውን የሚችለውን እየያዘ  ቢመጣ የሚጎድል ነገር አይኖርም። ባለፉት ሁለት ሳምንታት ይህን ስናደርግ ነበር። አሁን ለሶስተኛው የጨመርነው ቅባትና ሻምፖዎቹን ነው። አሁንም ደግሞ የምለው እነሱ ከከፈሉን ዋጋ አንጻር እኛ የምናደርገው ድጋፍ ኢምንት ቢሆንም፣ እዚህ መገኘታችን አብሮነታችን ያስደስታቸዋል፤ ያበረታቸዋልና በተለይ ወጣቱ በዚህ መልኩ እንዲጎበኛቸው፣ ወገንተኝነቱንና ደጀንነቱን እንዲያሳይ እንዲያመሰግናቸው ጥሪ አቀርባለሁ። በግሌም እንደ አንድ ወጣት ኢትዮጵያዊ የምችለውን ሁሉ በማድረግ ድጋፉን እንቀጥላለሁ። የሰራዊቱ አባላት ለከፈለሉልኝ መስዋዕትነት እጅግ አመሰግናለሁ።
__________________

   “ወጣቱ የተከፈለለትን መስዋዕትነት እየመጣ ማየት አለበት”
                          (ወጣት በቃሉ ምስጋና)

              በቃሉ ምስጋና እባላለሁ፤ የድሬደዋ ልጅ ነኝ። “ድሬደዋ ህብረት የልማትና የበጎ አድራጎት ማህበር” የተሰኘ ያቋቋምነው ማህበር አለን። በማህበራችን በኩል የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን እናደርጋለን። አሁንም በቤላ የማገገሚያ ማዕከል መጥተን ድጋፍ ስናደርግ ለሶስተኛ ጊዜያችን ነው። በመጀመሪያው ዙር ለሴቶች የሰራዊቱ አባላት የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁዎችን፣ ሳሙናና የመሳሰሉትን አምጥተን ነበር። ፍራፍሬም ይዘን መጥተናል። ምክንያቱም የሰራዊቱ አባላት በጥሩ ሁኔታ አገግመው ወደ ቀደመ ጤናቸውና አቋማቸው እንዲመለሱ አትክልትና ፍራፍሬ ያስፈልጋቸዋል። ከምንም በላይ እዚህ መጥተን የተከፈለልንን ማየታችን ይበልጥ ስለ ሀገራችን እንድናስብ መስዋዕትነቱ እስከምን እንደተከፈለልን እንድናስላስል ያደርገናል። እነዚህ የሰራዊቱ አባላት የራሳቸው ህልም ያላቸው መኖር የሚፈልጉ፣ የሚደርሱበት ግብ ያላቸው ናቸው። እነዚህን ሁሉ ህልሞች ከሀገራቸው ክብርና ሉአላዊነት በታች አድርገው ለነፍሳቸው ሳይሰስቱ አጥንታቸውንና ደማቸውን ሰጥተውናል።
ይህንን ደግሞ ሌላው ወጣት በሩቁ ሆኖ ከመስማት እዚህ መጥቶ ቢያይ ይበልጥ የሀገርና የህዝብ ፍቅር ምን ማለትና እስከ ምን ድረስ እንደሆነ ይረዳል ብዬ አስባለሁ። እኛ በድሬደዋ ህብረት የልማትና የበጎ አድራጎት ማህበራችን እንደ ወጣት የሚጠበቅብንን እናደርጋለን። ለምሳሌ በልማት በበጎ አድራጎትና በሰላም ዙሪያ እንቅስቃሴ እናደርጋለን። እንደሚታወቀው ድሬደዋ ከለውጡ በኋላ የተለያዩ ችግሮች ሲፈራረቁበት የነበረ ከተማ ነበር። ህብረታችን “የፍቅር መንጋ” በሚል እንቅስቃሴ ህዝብ ለህዝብ ላይ ስንሰራ ቆይተናል። ድሬደዋ ያላትን የመፈቃቀር፣ የመተባበር፣ አብሮ የመኖር፣ የመተጋገዝ እሴት ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ የማስተዋወቅ ስራ ትልቁ ተግባራችን ነበር። በዲጅታል ወያኔ የሶሻል ሚዲያ እንቅስቃሴ ድሬደዋ ላይ የሀሰት ወሬ በማስራጨት ህዝቡ እንደተራቀና እንደተቃረነ በማረግ ብሄርን ከብሄር የማጋጨት ስራ ሲሰራ በነበረበት ወቅት እኛ እንደ ድሬደዋ ወጣት ተሰባስበን ከሶስት ዓመት በፊት ይህንን ህብረት በማቋቋም የድሬድዋን መልካም ገጽታዎች ለአለም በማሳየት የተከፈተብንን የዲጂታል ጦርነት ስናከሽፍ ነው የቆየነው። እኛም እንደ ወጣት ዘምተናል መክተናል ማለት ነው።
ነገር ግን ይሄኛው ጦርነት ላይ የዘመቱ የሰራዊት አባላት ደምና አጥንት እስከ መገበር ህይወትንም ሲከፍሉ ለተሰውት ነፍስ ይማር በማለትና ቤተሰቦቻቸውን በማገዝ፣ የቆሰሉትን እንደየ አቅምና ችሎታችን ያሉበት ድረስ በመምጣት የምንችለውን በማድረግና ፍቅርና እንክብካቤ በመስጠት በማመስገን፣ አለንታነታችንን መግለጽ አለብን። ወጣቱ ይህንን ልብ ማለት አለበት።
እዚህ ግቢ  ሰው እየመጣ ያለውን እየያዘ ሲጠይቃቸው፣ ሲንከባከባቸው ስመለከት በጣም ደስ ይለኛል። እንደኔ እንደኔ የተሻለ አልጋ ላይ እንዲተኙ አልጋ የሚለግሱ ቢኖሩ ጥሩ ነው እላለሁ። እንኳን የቆሰለና ህመም ያለበት፣ ምንም ያልሆነም ሰው ቢሆን ጥሩና ምቹ አልጋ ላይ መተኛት አለበት። እነዚህ ጀግኖች ወንድምና እህቶች  የሰራዊቱ አባላት አሁን ከሚተኙበት አልጋ የተሻለ ምቾት የሚሰጥ አልጋ ላይ ቢተኙ ቶሎ የማገገም ሁኔታ ያሳያሉ ብዬ አምናለሁ።
በተረፈ አሁንም ለሚያሳዩት የሀገርና ወገን ፍቀር እስካሁንም ላፈሰሱልን ደምና  ለከሰከሱልን አጥንት፤ የማይተካ ውድ ህይወት ለሰጡን ጀግኖቻችን እነሆ አክብሮትና ምስጋናዬ በድሬደዋ ህዝብ በተለይ በድሬ ወጣቶች ስም ምስጋና አቀርባለሁ። ለተሰውት ሰላማዊ እረፍትን ለቆሰሉት በቶሎ ማገገምን እመኛለሁ።        

Read 1552 times
Administrator

Latest from Administrator