Tuesday, 04 January 2022 00:00

የሃይማኖት ፍልስፍና

Written by  ብሩህ ዓለምነህ
Rate this item
(1 Vote)

 ክፍል-2

የእግዚአብሔር ህላዌ ላይ የተነሱ ሐሳቦች
              
            በክፍል አንድ ፅሁፌ በሃይማኖትና በፍልስፍና፣ በእምነትና በአመክንዮ፣ በማመንና በመረዳት መካከል ያለውን ግንኙነት ተመልክተናል፡፡ ዛሬ ደግሞ የሃይማኖት ፈላስፎች ‹‹የእግዚአብሔርን መኖር በእምነት ብቻ ሳይሆን በአመክንዮም ልንደርስበት እንችላለን›› በማለት የሚያቀርቧቸውን መከራከሪያዎች የአሞን በቀለን ሌክቸር መሰረት አድርገን እንመለከታለን፡፡
ወደ መከራከሪያዎቹ ከመሄዳችን በፊት ግን በሃይማኖት ፍልስፍና ውስጥ ‹‹የእግዚአብሔር ህልውና›› ላይ የሚደረጉ ክርክሮች ለምን በጣም አንገብጋቢ እንደሆኑ ማንሳት አለብን፡፡
መቼም ‹‹እግዚአብሔር›› የሚባል ኃይል ስለመኖሩ እርግጠኛ ሳንሆን ስለ ፀሎት፣ ስለ ሃይማኖትና በሃይማኖቱ ውስጥ ስላሉ አስተምህሮዎች ልናወራ አንችልም፡፡ ፈላስፋው ዘርዓያዕቆብም ያደረገው ይሄንኑ ነበር፡፡ ዘርዓያዕቆብ ሁለት ዓመት ሙሉ በዋሻ ውስጥ ተደብቆ ሲፀልይና ሲመራመር ‹‹ጌታዬ! ፈጣሪዬ! አስተዋይ አድርገህ የፈጠርከኝ ሆይ፤ አሳየኝ፤ ትእዛዝህን እማር ዘንድም ልቦና ስጠኝ፤ ስውር ጥበብህንም ግለጽልኝ፤›› እያለ አብዝቶ ይፀልይ ነበር። ዘርዓያዕቆብ ፈላስፋ ነው፤ ይሄንን ፀሎት ሲያቀርብ የነበረው ግን እግዚአብሔር ስለመኖሩ በመጀመሪያ በአመክንዮ ሳያረጋግጥ ነው፡፡ እናም አካሄዱ የተሳሳተ ነበር፡፡ ወደ እግዚአብሔር መፀለይ ያለብን እግዚአብሔር ስለመኖሩ በመጀመሪያ እርግጠኞች ከሆንን በኋላ ነው፡፡ ዘርዓያዕቆብ ፀሎቱ ላይ ፍልስፍናዊ የአካሄድ ስህተት እንዳለበት ያወቀው ዘግይቶ ነበር። ዘግይቶም ቢሆን ግን ስህተቱን ሲያምን እንዲህ ብሏል:- ‹‹እኔ ግን ወደማን ዘንድ ነው የምጸልየው? ለመሆኑ የሚሰማኝ እግዚአብሔር አለ ወይ?›› ዘርዓያዕቆብ ለዚህ ጥያቄ መልስ ለማግኘት የሞከረው በእምነት ሳይሆን በአመክንዮ ነው፡፡ እንደ ዘርዓያዕቆብ ላሉ በርካታ የሃይማኖት ፈላስፎች፣ ሃይማኖታዊ ህይወት የሚጀምረው በእምነት ሳይሆን በማወቅ ነው - እግዚአብሔር ስለመኖሩ በማወቅ፡፡
በጥቅሉ፣ የእግዚአብሔር የህልውና ጉዳይ በጣም መሰረታዊ የሆነበት ዋናው ምክንያት ጥያቄው የዕለትተለት ህይወታችን ላይ፣ ስለ ዓለም ባለን አመለካከት ላይ፣ በሥነ ምግባር እሳቤያችንና ስለ ህይወት ባለን አመለካከት ላይ ትልቅ ተጽዕኖ ስላለው ነው፡፡ በመሆኑም፣ ‹‹እግዚአብሔር አለ? ወይስ የለም?›› የሚለው ጥያቄ  ከሁሉም በፊት በቅድሚያ መመለስ አለበት፡፡ አሁን እሱን ነው የምናየው፡፡
በአጠቃላይ፣ የእግዚአብሔርን ህልውና ለማስረገጥ በፍልስፍና ውስጥ የሚነሱትን ሐሳቦች ‹‹a priori›› እና ‹‹a posteriori›› በመባል በሁለት ቡድን ይከፈላሉ፡፡ እስቲ ሁለቱንም ሐሳቦች በየተራ እንመልከታቸው።
‹‹a priori›› የሚባለው የክርክር ዓይነት፣ የእግዚአብሔርን መኖር ወደ ውጫዊው ዓለም በማየት ሳይሆን፣ ወደ ውስጣችን ወዳለው ሐሳብ ወይም ህገ ልቦና በማየት የእግዚአብሔርን መኖር ለማረጋገጥ የሚሞክር ሐሳብ ነው፡፡ በፍልስፍና ውስጥ ይሄ ሐሳብ ‹‹Ontological Argument›› በመባል ይጠራል፡፡ የዚህ ሐሳብ አመንጪም የ11ኛው ክ/ዘ ጣሊያናዊ መነኩሴና ፈላስፋ የነበረውን ቅዱስ አንስለም (St. Anslem 1033-1109) ነው፡፡ ቅዱስ አንስለም ይሄንን ሐሳቡን የገለፀበት መፅሐፍም ‹‹Proslogion›› (1078) ይባላል፡፡
Ontological Argument and
Negative Theology
‹‹Ontological Argument›› መነሻው የእግዚአብሔር ሐሳብ (The Idea of God) ነው፡፡ አካሄዱም ከእግዚአብሔርነት ሐሳብ በመነሳት የእግዚአብሔርን ህልውና ማስረዳት ነው፡፡ ይሄንን ለማድረግ ደግሞ ቅዱስ አንስለም የሚጀምረው እግዚአብሔርን በመተርጎም ነው፤ እንዲህ በማለት፡- ‹‹እግዚአብሔር ማለት ከእሱ የሚበልጥ ሊታሰብ የማይችል ነው፤ (God is that than which nothing greater can be conceived)››፡፡ በሌላ አገላለፅ፣ እግዚአብሔር ማለት ልናስብ የምንችለው ነገር ሳይሆን፣ ልናስብ ከምንችለው ነገር የሚበልጥ፣ ወይም ደግሞ ባጭሩ ልናስበው የማንችለው ነገር ነው፡፡ የፈለገ ብናስብ ከእግዚአብሔር የሚበልጥ ነገር ልናስብ አንችልም፤ ምንም የሚበልጠው ነገር የሌለው ያ ሐሳብ እግዚአብሔር ነው፡፡
‹‹ከእሱ የሚበልጥ ሊታሰብ የማይችል›› የሚለው አገላለፅ የተወሳሰበ ብቻ ሳይሆን አሉታዊነትም አለው፡፡ ከእዚያ ይልቅ ቅዱስ አንስለም ቀጥተኛ በሆነ አገላለፅ ‹‹በአዕምሯችን ልናስብ የምንችለው ትልቁ ህላዌ እግዚአብሔር ነው (God is the Greatest conceivable Being) ማለት ይችል ነበር፡፡ ሆኖም ግን ‹‹በአዕምሯችን ልናስብ የምንችለው…›› የሚለው አዎንታዊ አገላለፅ፣ እግዚአብሔርን በእኛ የማሰብ አቅም ይገድብብናል፤ ያሳንስብናል። እግዚአብሔርን ከዚህ ሰዋዊ ገደብ የሚያወጣልን አሉታዊ አገላለፅ ነው፡፡ ለዚህም ነው ቅዱስ አንስለም ከአዎንታዊው አገላለፅ ይልቅ አሉታዊውን አገላለፅ የመረጠው፡፡ እንደዚህ ዓይነቱ አገላለፅ Negative Theology ሲባል፣ እሱም Ontological Argument የሚገለፅበት መንገድ (method) ነው፡፡
ከእሱ በላይ ላስብ የማልችለው ነገር ምንድን ነው?
‹‹Ontologicl Argument›› ረቀቅ ያለ የአእምሮ ጂምናስቲክ ነው፡፡ ቅዱስ አንስለም ሐሳቡን ለማስረዳት ሌላ አገላለፅም አለው፡፡ ለምሳሌ፣ ከእሱ በላይ ልናስብ የማንችለው ነገር ዛፍ ነው ብለን እናስብ፡፡ የዛፍን ኳሊቲዎች ስንዘረዝር ግን ውስንነቶች እናገኛለን፤ አንዱ ውስንነቱ ደግሞ የማይንቀሳቀስ መሆኑ ነው፡፡ ስለዚህ፣ ዛፍ፣ ከእሱ በላይ ልናስብ የማንችለው ነገር አይደለም ማለት ነው፡፡ ከዛፍ ሐሳብ አለፍ ብዬ አንበሳ፣ ሰው፣ መላዕክት … እያልኩ ባስብ እንኳ ሁሉም ውስንነት አለባቸው፤ ስለዚህ፣ ከእነሱ በላይ ልናስብ የማንችላቸው ነገሮች አይደሉም ማለት ነው፡፡ ስለዚህ፣ እግዚአብሔር ማን ነው? ሁሉም ፍጹም የሆኑ ነገሮች ያሉት፣ ሳስብ ብውል ከሱ በላይ የሚበልጥ ነገር ላስብ የማልችለው ነገር ነው እግዚአብሔር፤ ከእሱ በላይ ልናስብ የማንችለው ነገር እግዚአብሔር ነው፡፡
ቅዱስ አንስለም እዚህ ቦታ ላይ ሲደርስ በመዝሙረ ዳዊት ምዕራፍ 14 ላይ የተፃፈ አንድ ጥቅስ ትዝ ይለዋል፤ ‹‹ሰነፍ በልቡ እግዚአብሔር የለም›› የሚለው፡፡ እናም ይሄ ‹‹ሰነፍ›› ሰው ለምን እንደዚህ እንዳለ ሁለት መላምቶችን በማቅረብ ይመረምረዋል፡፡
አንደኛው፣ ሰነፉ ይሄንን የሚለው ትርጉሙ ስላልገባው ሊሆን ይችላል። ሁለተኛው መላምት ግን ጠንከር ያለ ነው። ‹‹አንድ ነገር በአእምሮ አለ›› ማለት እና ‹‹ያ ነገር ከአእምሮ ውጭ በአካል አለ›› ማለት የተለያዩ ነገሮች ናቸው፡፡ እናም ሰነፉ ሰው በልቡ ‹‹እግዚአብሔር የለም›› ያለበት ምክንያት ‹‹እግዚአብሔር በሰው አእምሮ ውስጥ እንጂ ከአእምሮ ውጭ የለም›› በሚል እሳቤ ሊሆን ይችላል፡፡
ቅዱስ አንስለም ሁለተኛውን መላምት ለማብራራት ‹‹እስቲ ‹‹እግዚአብሔር በሰው አእምሮ ውስጥ እንጂ ከአእምሮ ውጭ የለም›› የሚለውን አነጋገር ትክክል ነው ብለን እንነሳ›› ይላል፡፡ ከላይ እግዚአብሔርን ‹‹ከእሱ የሚበልጥ ሊታሰብ የማይችል›› በማለት ገልፀነዋል፡፡ ሆኖም ግን፣ ምንም እንኳ ሰነፉ ሰው እግዚአብሔር በአእምሮ ብቻ የሚኖር አድርጎ ቢያስበውም፣ እኛ ግን በሁለቱም የሚኖር (በአእምሯችንም በውጭም የሚኖር) ነገር ማሰብ እንችላለን። በአእምሮ ብቻ ከሚኖር ነገር ይልቅ ደግሞ በአእምሮም በአካልም የሚኖር ነገር ይበልጣል፡፡ ለዚህም ነው የሰነፉ ሰው ሐሳብ ትክክል የማይሆነው።እንግዲህ በቅዱስ አንስለም ድምዳሜ መሰረት፤ ‹‹እግዚአብሔር ከሱ በላይ ልናስብ የማንችለው ህላዌ ከሆነ፣ ይህ ህላዌ  በአእምሮ ብቻ ሳይሆን በአካልም የግድ መኖር አለበት። ምክንያቱም፣ እግዚአብሔር በአእምሮ ብቻ የሚኖር ከሆነ ከሱ በላይ ማሰብ ልንችል ነው፤ በአዕምሮም በአካልም ያለ ነገር ልናስብ ነው፡፡ በመሆኑም፣ ‹‹እግዚአብሔር ማለት ከእሱ የሚበልጥ ሊታሰብ የማይችል ህላዌ›› ከሆነ የግድ በአእምሮም ሆነ በአካል መኖር አለበት፡፡ ቅዱስ አንስለም በዚህ ሐሳቡ ላይ ትችት የመጣበት በራሱ ዘመን በሌላ ገዳም ከሚኖር Gaunilo ከሚባል ሌላ መነኩሴ ነው። ‹‹ሰነፉን ወክዬ ልከራከር (On Behalf of the Fool)›› ብሎ በሰየመው ፅሁፉ Gaunilo ባቀረበው ትችት፤ ‹‹በቅዱስ አንስለም ሐሳብ ሄደን የእግዚአብሔርን ህልውና ማረጋገጥ አንችልም፤ ለምሳሌ፣ እኔ በእውን የሌለ ሆኖም ግን በአእምሮዬ ‹‹በሁለመናው ፍፁም የሆነና ከእሱ የበለጠ ማሰብ የማልችለው›› አንድ እጅግ ውብ የሆነ ደሴት ላስብ እችላለሁ፤ ይሄም ማለት ከእግዚአብሔር የሚበልጥ ነገር ማሰብ ባለመቻላችን ምክንያት ብቻ፣ እግዚአብሔር በእውን አለ ወደሚል መደምደሚያ አያመጣንም፤›› ይላል Gaunilo፡፡ሆኖም ግን፣ ቅዱስ አንስለም ይሄንን የጋኒሎ ትችት አልተቀበለውም፤ ‹‹ደሴት ውስንነት ያለበት ህላዌ በመሆኑ ‹‹ከሱ በላይ ሊታሰብ የማይችል›› ተደርጎ ሊታሰብ አይችልም›› በማለት ነበር ትችቱን ሳይቀበለው የቀረው፡፡ በክፍል-3 ‹‹a posteriori›› ስለሚባሉ መከራከሪያዎች እንመለከታለን፡፡   

Read 2308 times