Thursday, 06 January 2022 00:00

አቧራውን አራግፎ የተነሳው ኢትዮጵያዊነት

Written by  ነፃነት አምሳሉ አፈወርቅ
Rate this item
(2 votes)


                 በታላቁ መጽሐፍ ላይ ጠቢቡ ሰሎሞን “ለሁሉም ግዜ አለው” የሚለው ንግግሩ የህይወታችን ደረቅ እውነታ ነው፡፡ እብለትም ዝንፈትም የለውም፡፡ ከጽንሰት እስከ ውልደት፣ ከእድገት እስከ ሞት ያለው እጣ ክፍላችን የተቀነበበው በጊዜ ሰሌዳ ላይ በተጻፈልን ህያው ፊደላት ነው፡፡
ሀገርም እንደ ሀገር ለመወለድም፣ ለመሞትም፣ ለማደገም፣ ለመሰበርም፣ ለመጽደቅም፣ ለመድረቅም፣ ለመነሳትም፣ ለመውደቅም የራስዋን ምህዋር ጠብቃ በራስዋ ዛቢያ ላይ ትሽክረከራለች፡፡ ከዑደቱ ሊያነጥባት የሚችል ኃይል አይኖርም፡፡ ሃቁ አንደ ኮሶ ቢመራትም  ትጠጣዋለች፤ እንደ ገለባ ቢያነፍሳትም ትወጣዋለች፤ እንደ መብረቅ ቢያጮሃትም ትታገሰዋለች፤ ቢያጎብጣትም ትሸከመዋለች፤ ቢገፋትም ትችለዋለች፡፡ በዚህ ግብግብ መሀል በልቧ ማህደር ውስጥ ሆኖ የሚያበረታታትና የሚያጽናናት ተስፋ ይሉት ታላቅ ኃይል ነው፡፡ ተስፋ ካለ ሁሉም አለ ነው ነገሩ፡፡
የመጣንበትን የታሪክ ሃዲድ ዞር ብለን ብንመለከት እንዴት ድልድዩን እንደተሻገርነው መገረማችን አይቀሬ ነው። ድልድዩ ብዙ ቦታ ተሰባብሮ እግራችንን አላስቆም ሲለን፣ መጋጠሚያው ወላልቆ አላሻግር ሲለን፣ መደገፍያው አንድ ሐሙስ እንደቀረው ሞት ጠሪ ሲያወዛውዘን ተመልክተነው እንዴት ብዙ ሚሊዮኖች ሆነን ሳለ ድልድዩ ሳይሰበር ለዛሬ ደረስን የሚለው ጥያቄ በይደር ቆይቶ ለዛሬ ደርሰናል፡፡
የባለቤታቸው ሞት ለንጣይነት የዳረጋቸው እቴጌ ጣይቱ ሀዘን፣ ባደቀቀው ጎናቸው የቤተ መንግስቱን የስልጣን ሽኩቻውን መቋቋም ተስኗቸው እንደ ቴአትር ተመልካች ሲታዘቡ ቆይተው መጨረሻ ላይ ራሳቸውን ያገኙት እንጦጦ ማርያም ባለ ስፍራ የቁም እስረኛ ሆነው ነበር፡፡ ነገር ዓለሙ ሁሉ ጭልም ያላባቸው እቴጌ፣ “ነበር ለካ እንዲህ ቅርብ ነው” ማለታቸው፣ ከኛ ሕይወት ጋር ይመሳሰላል፡፡
የኛስ ነገር ይሔው አይደል? ዘመነ ሕወሓት አልፎ ታሪክ ተቀይሮ ስናይ፣ “ለካ ነበር እንደዚህ ቅርብ ነው” ብንል ማን ይፈርድብናል? ዘመነ ሕወሓት ይዞት የመጣውና የሄደው እንደ ሰማይ ከዋክብት የበዛ ስንክሳር፣ ገና በብዙ ጸሐፍት ብዙ እንደሚባልለት ማወቅ ከባድ አይሆንም፡፡
ከዛሬው ጽሑፍ ጋር ወደተገናኘው ነጥብ ስገባ የዘመነ ሕወሓትን ፍጹማዊ ጸረ-ኢትዮጵያዊነትን ለማውሳት ወደድኩ፡፡ ይህ ቡድን ይዞ ከተነሳቸው አጀንዳዎች ዋነኛው የሚከፈለውን ሁሉ መስዋዕትነትን ከፍሎ መንግስት ሆኖ እየበዘበዘ መኖርና ካልደላው ግን ኢትዮጵያ የምትባልን ሀገር አፈራርሶ የአመድ ክምር ማድረግ ነበር፡፡ ለዚህ ደግሞ የእሳት መዶሻ አድርጎት የተጠቀመው ህዳር 29 ቀን 1987 ያጸደቀውን ህገመንግስት ነው። ህገመንግስቱ የብዝሃነትን ጽንሰ ሀሳብ እንያገነገነ የጋራ ሀገር እንደሌለን ለማስመሰል ሰፊ ርቀት መሄዱ አሌ አይባልም፡፡ የአንድነት እሴታችን የሆነችውን ሀገር፣ የእነእከሌ እንጂ የኛ አይደለችም በማለት፣ ሌላ የይዘት ቅርጽ በመፍጠር ሁሉም ወደ መንደሩ አጥር እንዲያተኩር በማድረጉ፣ ኢትዮጵያ ብሎ መናገር የጨፍላቂነት ፍላጎት ነው በሚል ያልተፃፈ ፍረጃ ብዙዎችን በማሸማቀቅ፣ መድረኮች ሁሉ በክልላዊነት እሳቤ ብቻ እንዲታጠሩ እልፍ ምክንያት ፈጥሮ ከህብረታችን ለይቶናል፡፡ በስታሊናዊ እሳቤ ላይ ተንተርሶ የተደረተውና እንኳን የዋሁ ማህበረሰብ ይቅርና እሳት የላሰ ካድሬ የሚባለው አባሉ ጭምር በወጉ ሊተነትነው ያልቻለውን ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች የሚሉ ቃላትና ሐረጎችን በመግቢያው ላይ ሰንቅሮ ሀገራዊነትን አክስሞ፣ በገድምዳሜ ኢትዮጵያዊነትን ለማጥፋት አንድ ብሎ ተነሳ፡፡
በህገመንግስት መግቢያ ላይ በተጻፉ ሃሳቦች ሳይግባቡ ሀገር መገንባት እንዴት ያለ አሳር እንደሆነ እራሳችን ምስክሮች ነን። ብሔር የተባለው ማነው? ብሔረሰቦች የተባሉትስ እነማን ናቸው? ሕዝቦች የተባሉትስ ወዴት ናቸው? ማን ምንን ሲያሟላ ነው ብሔር የሚባለው? ብሔረሰቦች ተብሎ የሚጠራው አካል ምን ቅርጽና ይዘት ስለያዘ ነው? ህዝቦች ተብሎ የሚሰየሙት ምን ቅድመ ሁኔታዎችን የተገበሩ ናቸው? የሚለውን ሙግት ህገመንግስቱ ለራሱ ተርጎሞ ባላስቀመጠበት ሁኔታ፣ ከእጅ ወደ አፍ ኑሮን ለመሸፈን የሚዳክሩት ለፍቶ አዳሪ ካድሬዎቹ እውነቱን መግለጥ አቅቷቸው የሙሉ ቀኑን ስብሰባ አሳጥረውት የሻይ ሰዓት ላይ እያጠናቀቁት አምልጠዋል፡፡
ታዲያ በዚያ ዘመን ውስጥ ኢትዮጵያዊነት ዳግመኛ በምድራችን ይሞካሻል፤ ይወደሳል፤ ይቀነቀናል ብሎ ለማሰብ እጅግ በሳል ወይም መንፈሳዊ ኃይል ኖሮት የመተንበይ ጸጋ ያደለው ሰው ማግኘት ነበረብን፡፡ ይህን ጊዜ መግፋት ተራራን ከመግፋት ይቀል ነበር፤ ይህን ዘመን መሻገር ባህርን ያለተአምር ዘልሎ የማለፍ ያህል ጭንቅ ነበር፤ ይህን ጸረ-ኢትዮጵያ አስተሳሰብ መሻር የፀሐይን የመውጫ አቅጣጫ የመቀየር ያህል አይሞከሬ ነበር፡፡
ጊዜ ደጉ! ጊዜ ዳኛ! ጊዜ ፈራጅ! ጊዜ ከዋኝ! ጊዜ ሰጪ! ጊዜ ነሺ! እርሱ ምን አለበት! ሰዐቱን ጠብቆ ከዙፋኑ ሲነሳ የሕወሓትን ኑዛዜ የሚቀበል ካህን አምጥቶ የንስሐ ዘመን ቢሰጣትም፣ ያደቆነ ሰይጣን ሳያቀስ አይቀርምና በሞትዋ ዋዜማ ላይ ሆናም አማራና ኦሮሞን እሳትና ጭድ አድርጌያለሁ ሁለቱ ሲነዱ እኔ ጋቢዬን ደርቤ እየሞቅሁኝ በእልቂታቸው እዝናናለሁ ስትል መጋቢት 24 ቀን 2010 “ኢትዮጵያ በልጆቿ ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኑር!” የሚለው መብረቅ ወርዶባት የልቅሶ ነጠላዋን እንኳን በወጉ ሳትደርብ ያለእድርተኛ እያለቀሰች መቀሌ ላይ ከተመች፡፡
በዚህ እለት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ንግግር ውስጥ ኢትዮጵያዊነት ተቀነቀነ! ተወደሰ! ተሞካሸ! ተዘመረ! ከፍ ከፍ ተደረገ! ይህ እውነት የናፈቃቸው ዜጎች እንባ እያነቡ፣ ትንሳኤ ዘኢትዮጵያን በእጅጉ ናፈቁ፡፡
ከዚያ ወዲህ የነበሩት ሶስት ዓመታት ግን እንደታሰበው አለመቀጠሉን ልብ ይሏል! ወዲህ ኢትዮጵያዊነት ወንዝ ዳር እንዳለች ተክል ሲያብብ አይተው አብረው የፈኩ ዜጎች አደባባዩን ሲሞሉ፣ ወዲያ ደግም ካለፈው እሳቤ ሳይላቀቁ በመንደርተኝነት ሲንፏቀቁ በኖሩ ወገኖች መሀል ግጭት በመፈጠሩ በርካቶች ህይወታቸውን ተነጠቁ፤ በግፍ ተገደሉ፤ ተፈናቀሉ፤ ተሰደዱ፡፡
በአናቱም የሕወሓት ጥጋብ ልብዋ ላይ የፈላበት ጊዜ ነበርና በሰሜን እዝ ባለው የመከላከያ ሰራዊታችን ላይ የጅምላ ፍጅት መፈጸምዋ ሲሰማ በአራቱም አቅጣጫ ያለው የኢትዮጵያ ህዝብ እሳት ጎርሶ በአንድነት ተነሳ፡፡ አንዳንዴ ከክፉ ነገር ውስጥ በጎ፤ ከመከራ ውስጥ ደስታ፤ ከፈተና ውስጥ ስኬት፤ ከማጣት ውስጥ ማግኘት፤ ከመሰደድ ውስጥ መክበር፤ ከመገፋት ውስጥ ማትረፍ እንዲሚገኝ ሁሉ የሕወሓት ጥቃት ለኢትዮጵያዊነት መነቃቃትና ማበብ ጉልህ አስተዋጽኦ አድርጎ እናገኘዋለን፡፡   
ከዚህ ወዲህ ባለው ጊዜ ለጆሮአችን እሩቅ የነበረው ኢትዮጵያዊነት በንግግር እየተገለጠ፣ በጽሑፍ እየተከተበ፣ በዜማ እየተወደሰ፣ በጥበብ እየተሞካሸ ይገኛል፡፡ የመሪዎች የንግግራቸው ጅማሬና የመዝጊያ ሐረግ ኢትዮጵያዊነት ሆኗል፡፡ ሕዝቡ እጅግ በሚገርም የኑሮ ውድነት መላወሻ አጥቶ በኢዮባዊ ትእግስት መጽናኛ ብርታት የሆነው ኢትዮጵያዊነት እያበበ፣ አንድነት እየተቀነቀነና ህብረት እየተወደሰ ማየቱ ነው። እንደ አይጥና ድመት ለመጠፋፋት ብለው ነገር በደለላ እያፈላለጉ ሲካሰሱ የምናውቃቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች በረጋ መንፈስ ሆነው እየተደማመጡ ሀገርን ለማዳን የሚያደርጉትን ትጋት ስናይ አንዳች በጎ ጊዜ እየመጣ እንደሆነ መገመት አያቅተንም፡፡
እጅግ በሚገርም ሁኔታ ኢትጵያዊነትን የሚያወድሱ የዜማ ሸክላዎች አቧራቸው እየተራገፈ የወኔ መቀስቀሻ፣ የቃልኪዳን ማደሻ የአብሮነት ማሰርያ ድርብ ጅማት ሆነው ተገኝተዋል፡፡ በርካቶቹንም በዕንባ ሆነን ሰምተናቸዋል፡፡ የግጥም ውበታቸውን፣ የዜማ ፍሰታቸውን፣ የቅንብር ውህደታቸውንና የምስል ጥራታቸውን አይተን ተደምመንባቸዋል፡፡ ጥበብ በፍርሃት የሸፈነችውን ጸጋዋን ገላልጣ ኢትዮጵያዊነትን ከነሙሉ ክብሯ እንካችሁ እያለችን ነው፡፡ እኛም ጥበብ ለዘላለም ትኑር ብለን መርቀናታል፡፡
በህወሓት አጥማቂነት በአብዮታዊ ዲሞክራሲ የውኃ ገንዳ ውስጥ ያለስመ ክርስትና ካድሬነትን የተጠመቁት የመንግስት ሚዲያዎች ዛሬ በኢትዮጵያዊነት መንፈስ ሌላ ተሃድሶ  አድርገው አሸናፊነትን፣ ድል አድራጊነትን፣ ጀብደኝነትን፣ አንድነትን፣ ህብረትን፣ አጋርነትን፣ መተሳሰብን፣ አብሮነትን፣ መረዳዳትን፣ ፍቅርን፣ ወንድማማችነትንና መተጋገዝን ሲያስተጋቡ አይተን “ጊዜ ደጉ” ከማለት ውጭ ምን ለማለት እንችላለን፡፡ ከዚህም የተነሳ ቃለመጠይቆች፣ መወድሶች፣ ፉከራዎች፣ ቀረርቶዎችና ሽለላዎች በኢትዮጵያዊነት ተከሽነው እንደቡፌ ምግብ ሲቀርቡልን ስናይ ተስፋ በልባችን ሞልቷል፡፡
ከሀገር ውስጥ እስከ ውጭ ያሉ ዜጎቻችን የአስተሳሰብና የፍላጎት ልዩነታቸውን ወደ ጎን ትተው አንገት ለአንገት ተቃቅፈው በታላላቅ ሰላማዊ ሰልፎች ላይ #ኢትዮጵያን አትንኩ፤ ጣልቃ ገብነታችሁን አቁሙ፤ ሉዓላዊ ክብራችንን አትዳፈሩ፤ ሀገር አጥፊን አትደግፉ፤ ሽብርተኛን አታጽናኑ; እያሉ ድምጻቸውን ሲያሰሙ ስንመለከት ምን ተአምር ተፈጥሮ ነው ህዝቡ አንድ የሆነው ብንል፣ መልሱ የኢትዮጵያዊነት መንፈስ ማንሰራራቱን ያሳየናል፡፡
ስሁት እሳቤዎችን መሞገቱም ተገቢ ነው፡፡ ኢትዮጵያዊነት ማቀንቀንና የዓላማው ደጋፊ መሆን በየትኛውም ስሌት ከጨፍላቂነት ጋር ሊገናኝ አይችልም፡፡ በዚህ ዘመን ማንም ማንንም ጨፍልቆ የመኖር እድል የለውም፡፡ በመጨፍለቅ ከሚገኝ ትርፍ ይልቅ በብዝሃነት የሚገኝ ኪሳራ እልፍ ጊዜ ይበልጣል፡፡ መቼም ቢሆን ጨፍላቂነት አዋጭ ንግድ ሆኖ አያውቅም፡፡  አሁን ባለው የኢትዮጵያ ዘር ተኮር ፖለቲካ ውስጥ አንዱ አንዱን ለመጨፍለቅ የሚያደርገው ጥረት የውድቀት ዋዜማ መሆኑን መካድ አይቻልም፡፡
ኢትዮጵያዊነትን ማንበር ማለት በማንነታችን እውቅና አግኝተን የጋራ ሀገር መገንባት ማለት ነው፡፡ ኢትዮጵያዊነት አሸናፊነት ድል አድራጊትና ጀግንነት ነው። ኢትዮጵያዊነት የተዳፈነ ረመጥ ነው። ለጊዜው የተደበቀ ቢመስልም ውስጥ ለውስጥ እየጋለ እየፋመና እየተቀጣጠለ፣ የተከመረበትን አመድ አራግፎ የሚነሳ ነበልባል ነው፡፡ ኢትዮጵያዊነት ህብራዊ ማንነታችን እንደ እንቁ የሚያበራበት የወል ስማችን ነው፡፡ ኢትዮጵያዊነት ሞተ ሲሉት የሚነሳ፣ ጠፋ ሲሉት የሚከሰት፣ ከሰመ ሲሉት የሚገለጥ፣ መከነ ሲሉት የሚባዛ፣ በነነ ሲሉት አካል ነስቶ የሚገለጥ የአድዋ መንፈስ ነው፡፡   በዚህ ልክ ካየነው የመከላከያ ሰራዊታችን የኢትጵያዊነት ልከኛ ደርዝ ሆኖ እናገኘዋለን። ሰራዊታችን የእከሌ ምድብተኛ ጦር ሳይሆን የሁላችን ወካይ ምልክት ነው። ሰራዊታችን ትንፋሽ በሚያሳጣ ነዲድ በረሃ እግሩ እየተላጠ፣ አፈር ለብሶ፣ አፈር መስሎ፣ ከአፈር እየታገለ የሚውለው ሰውነት በሚቆርጥ ብርድ እየተንቀጠቀ፣ ዝናቡን ታግሶ፣ ተራራ ወጥቶ፣ ቁልቁለት ወርዶ፣ ሸለቆ ተሻግሮ፣ የእድሜውን አፍላ ወራት ምሽግ ውስጥ ተኮራምቶ የሚተኛው ስለኢትጵያዊነት እንጂ ስለብሔር ውክልና አይደለም፡፡
አሁናዊ ትዝብታችንን ስንቃኘውም የኢትዮጵያዊነታችን ነጸብራቅ ከኛም አልፎ ተርፎ የአፍሪካ ሀገራት፣ ታላላቅና ታዋቂ ሰዎችንም ጭምር ለትግል የጋበዘ መንፈሳዊ አጀንዳ ሆኗል፡፡ ለዚህ ምስክር እንዲሆን No More (ይበቃል) የሚለው እንቅስቃሴ ምን ያህል ተጽእኖ እንደፈጠረ ማሰቡ ብቻ በቂ ነው፡፡ ይህን የጋለ ህዝባዊ ስሜት ወደተጨባጭ የተግባር ምእራፍ ለማሻገር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ለ1ሚሊዮን ዲያስፓራዎች ባደረጉት ጥሪ መሰረት ወደ ሀገራቸው ለመመለስ እየተመሙ ያሉት ወገኖቻችን ስናይ ኢትዮጵያዊነት አቧራውን አራግፎ በራሱ ማንነት ሊገለጥ እየዳኸ መሆኑን እንገነዛባለን። ደርዙን ስንመትር ኢትዮጵያዊነት የስነልቦና ትስስር ብቻ ሳይሆን የባህል የእምነት የአስተሳሰብ የልማድ የትውፊት የአብሮነት መስተጋብር፣ የእሴት ተወራራሽነት የመልክዓምድር ተጋርዮሽ፣ የንግግር ውሰቶች ያለፈውን እንከን ከነነቁ መጪው ጊዜ ከነወርቁ ለመቀበል የተዘጋጀ ማህበረሰባዊ እሴት ነው፡፡
እርግጥ ነው እዚህ ላይ ሊነሳ የሚችል ሙግት መኖሩን መካድ አይቻልም፡፡ ይህ ኢትዮጵያዊነት በሁሉም ክልሎች ዘንድ አቻ ስሜት አለው ወይ? በፖለቲካ ፓርቲዎች መሀል የሚታይ የሴራ ጥልፍልፎሽስ ለኢትዮጵያዊነት እኩል አመለካከት አለው ወይ? ይህ ስሜት ዘላቂነት አለው ወይስ ለጊዜው ችግር መፍቻ እንደ እሳት ማጥፍያ የተዘጋጀ አጀንዳ ነው? ማህበረሰቡስ ኢትዮጵያዊነትን እየተረጎመ ያለው በራሱ ወገብ ልክ ብቻ ነው ወይስ ለጋራ ጥቅማችን በሚበጅ ልክ ነው? የሚሉ ውኃ የሚያነሱ ጥያቄዎች እንደሚኖሩ ይታመናል። እነዚህን ጥያቄዎችም አቅልሎ ማለፉ አለባብሰው ቢያርሱ በአረም ይመለሱ እንደሚባለው ሀገርኛ ብሂል ውለን አድረን ውኃ ወደመውቀጥ እንዳይመልሰን የማንቂያ መልእክት አድርገን በመውሰድ እንደ አስተዋይ ህዝብ ሲሻን በክብ ጠረጴዛ ዙርያ አሊያም በሀገር ሽማግሌዎች እግር ስር ተቀመጠን መምከሩ ለጋራ ሀገራችን ሁነኛ መፍትሔ ይሆናል፡፡
ዛሬ በህጻናት አንደበት፣ በወጣቶች ትኩስ ስሜት፣ በጎልማሶች ጥልቅ አስተዋይነት፣ በአረጋዊያን መንገድ መሪነት፣ በሃይማኖት መሪዎች ጥበብ ገላጭነት፣ በሰራዊታችን የህይወት ቤዛነት አቧራውን አራግፎ እየተነሳ ያለው ኢትዮጵያዊነት ነገ እንደ አልዓዛር መቃብሩን ፈንቅሎ እንደሚነሳ ጥርጥር የለውም። ለአፍሪካም ኩራትና ክብር እንደሚሆን ለመገመት የግድ ነቢይ መሆን አይጠበቅብንም። ኢትዮጵያ በፈጣሪ ጸጋ በልጆቿ ውድ ዋጋ ከነክብራ ተሞሽራ ለዘላለም ትኖራለች፡፡

Read 8204 times