Monday, 03 January 2022 10:16

"ከቀጠፋችሁ አይቀር ተመካከሩ..."

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(1 Vote)

  እንኳን ለብርሀነ ልደቱ ዋዜማ ቀናት አደረሳችሁ!
አንዴት ሰነበታችሁሳ!
ምስኪን ሀበሻ፡- አንድዬ...
አንድዬ፡- ምስኪኑ ሀበሻ እንዴት ነህ?
ምስኪን ሀበሻ፡- ደህና ነኝ አንድዬ፣ ደህና ነኝ፡፡ አንተ እያለህልኝ ምን እሆናለሁ ብለህ ነው፡፡
አንድዬ፡- ጎሽ፣  ዛሬስ ጠባይህን አሻሽለህ ነው የመጣኸው፡፡ እኔ ሳላውቀው እዛ እናንተ ያላችሁበት የተገኘ ነገር አለ እንዴ!
ምስኪን ሀበሻ፡- አንድዬ...ያው በፊት የምታቀኝ ነኝ እኮ! ምኔ ተለወጠብህ?
አንድዬ፡- ትንሽማ ለወጥ ብለሃል። ቢያንስ ዛሬ ከሰላምታ በፊት አቤቱታ ባለመስቀደምህ ወይ ረስተኸው ነው፡፡ ወይ ደግሞ በጣም ደስ ያለህ ነገር አለ፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡- ሌላም ጊዜ እኮ በጣም ሲጨንቀኝ ነው እንደዛ የሚያጣድፈኝ፣ አንድዬ፡፡ ደግሞ ምድር ላይ ዘንድሮ ምን ደስ ያሚል ነገር አለና!
አንድዬ፡- ይኸው ልትጀምረኝ ነው፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡- አንድዬ፣ እንደሱ አይደለም፡፡ አንተ ልታናግረኝ ፈቃደኛ ከመሆንህ በላይ ምን የሚያስደስት ነገር ሊኖር ይችላል ልልህ ፈልጌ ነው፡፡
አንድዬ፡- ደግሞ ስማ፣ አንተ እያለህልኝ ምን እሆናለሁ ስትል ራሱ መሻሻል አይደለም እንዴ!
ምስኪን ሀበሻ፡- አንድዬ...ድሮስ ሁላችንስ አንተ እያለኸን ምን እንሆናለን! እንደውም አንድዬ፣ ዘንድሮ ምድር የከሃዲ መጠራቀሚያ ሆና አንተ ብቻ ነህ እኮ የቀረኸን!
አንድዬ፡- ተው እንጂ ምሰኪን ሀበሻ! አንደው ምስክር ጥራ ካላልከኝ ስንት ወር ሙሉ ጥለኸን፣ ችላ ብለኸን፣ ረስተኸን እያላችሁ ስትጨቀጭቁኝ አልነበረም እንዴ የከረማችሁት! በላ ከፈለግህ ዋሸህ በለኝ፡፡ እኔ አልቀየምህም፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡- አንድዬ! እንደሱ አትበል። ምንስ ብዳፈር አንተን ነው ዋሸኸኝ የምለው! አእምሮዬን ብስት እንኳን እንዲህ አይነት ንግግር አይወጣኝም፡፡
አንድዬ፡- አእምሮ መሳት አልክ! በል... በበዓል ሰሞን አላስቀይማችሁም፡፡ ሌላ ጊዜ ስትመጣ አስታውሰኝ፡፡ እሺ፣ ዛሬ አመጣጥህ እንኳን አደረሰህ ልትለኝ ነው፣ አይደል!
ምስኪን ሀበሻ፡-አንድዬ!
አንድዬ፡- ምስኪን ሀበሻ፣ እኔ ዘንድ ስትመጣ መቼ መቼ እንደምትደነግጥ ልንገርህ... ሁልጊዜም እውነቱን ስናገር ነው የምትደነግጠው፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡- አንዴ፣ አንድዬ! ደግሞ አንተ ምን ትሆናለህ ብላን እንኳን አደረሰህ የምንለው! እንዲህ በመናገሬ እንኳን እንዴት እንደሚሰቀጠጠኝ... አንድዬ!
አንድዬ፡- ለነገሩ እናንተ እንኳን ስለእኔ የሚሆነውንና የማይሆነውን ለማወቅ ስለራሳችሁስ ምን እንሚሠራ  ታውቁና...ወይስ እንደዛ በማለቴ ተሳስቻለሁ?
ምስኪን ሀበሻ፡- በጭራሽ አንድዬ...በጭራሽ፡፡ ልክ ነህ፡፡ ግብ ደግሞ አንተን  ማን ይነካሃል፣ ምንስ ይደርሰብሀል ብለን እንጨነቅ!
አንድዬ፡- ስማ... ይህ የእናንተን መንግሥት ካልገለበጥን ብለው ዙሪያችሁን መከራቸውን የሚያዩ አሉ አይደል! እየው ምስኪን ሀበሻ፣ ...የእኔንም መንግሥት ለመገልበጥ የሚፈልገው ስንት እንደሆነ አታውቁም፡፡ ጦር መላክ ስላልቻሉ ነው እንጂ ለእኔም አይመለሱልኝም ነበር፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡- እንዴት ብለው አንድዬ! የአንተን መንግሥት ለመገልበጥ የሚያስቡትማ ያው የዲያብሎስ አገልጋዮች እንጂ ሌላ ማን ይሆናል፡፡
አንድዬ፡- እነሱ በስንት ጣእማቸው! ስማኝ ምስኪኑ ሀበሻ...እነሱ እኮ በግልጽ ነው የሚሄዱት፡፡ እኔም ስለማውቅባቸው ችግር የለውም፡፡ እኔ የምለው... በእኔ ስም እየማሉ እየተገዘቱ፣ ቤተ እምነቱ ሄደው እንዲህ አድርግልን፣ እንደዛ ፍጠሩልን እያሉ እየለመኑ፣ ዘወር ይሉና ደግሞ እንዴት የእኔን ስልጣን ለመውሰድ እንደሚችሉ የሚዶልቱት ማለቴ ነው፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡-አንድዬ!  የፈለገው ቢዶልቱ አይሳካላቸውማ! አንተ ዙፋን ላይ ለመቀመጥ...
አንድዬ፡- ስማኝ ምስኪን ሀበሻ፣ እንደእናንተ ሥጋና ደም ያለው ሰው በላቦራቶሪ ለመፍጠር እየሞከሩ እንደሆነ ታውቃለህ!
ምስኪን ሀበሻ፡- እንዴት ተደርጎ፣ አንድዬ! እንዴት ተደርጎ!
አንድዬ፡- እንዴት ተደርጎ እንደሆነማ እናንተ ንገሩኝ እንጂ!
ምስኪን ሀበሻ፡- እኛማ ምኑን አውቀነው አንድዬ! 
አንድዬ፡- ስማ ምስኪኑ ሀበሻ፣ እኔ ግርም የሚለኝ ነገር ምን እንደሆነ ልንገርህ፡፡ በአንድ በኩል የህዝብ ቁጥር በዝቷል እያላችሁ ድሀው፣ ድሀው ሀገር እየሄዳችሁ ሴቱን ኪኒን ታስቅማላችሁ፡፡ በሌላ በኩል ደግም ጭራሽ እንደራሳችሁ ስጋና ደም ያለው ሰው ሠራሽ ሰው እንፈጥራለን እያላችሁ ይኸው ጠዋት ማታ ትባዝናላችሁ፡፡ ጉድ እኮ ነው! እነዚህ ነገሮች እንዴት እንደሚጣጣሙ የምታውቀው ነገር ካለ እስቲ እንዲገባኝ አድርገህ አስረዳኝ፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡- እኔ ምኑን አውቄው አንድዬ!
አንድዬ፡- ሌላ ደግሞ ሁልጊዜ የሚገርመኝን ነገር ልንገርህ፡፡ ምነው ሀብታም ሀብታሙ የራሱን ሳይነካ ድሀው፣ ድሀው ሀገር እየዞረ ለሴቱ ሁሉ ኪኒን ሲያድል እንዴት ነው ነገሩ አይባልም? ለአንዳችሁ መብዛት፣ መባዛት ሲፈቀድ ለሌላኛችሁ ክልክል ነው እንዴ? እኔ ይህኛው ህዘብ በዛብኝ ይህኛው አነሰብኝ አልኩ?
ምስኪን ሀበሻ፡- አን....
አንድዬ፡- ቆየኝ፣ ቆየኛ! ደግሞ ኪኒኑ በአውሮፕላኑም በምኑም እየተጫነ የሚመጣው፣ መዋለዱ በቃችሁ የሚባለውም በብዛት እናንተ ጥቁሮቹ ሀገር ብቻ መሆኑ የማይከነክናችሁ ለምንድነው!
ምስኪን ሀበሻ፡- አንድዬ፣ ቢከነክነንስ ምን እናመጣለን?
አንድዬ፡- መጀመሪያ ነገር የጉንፋን መድሀኒት እንኳን ማግኘት አቅቷቸው ሰው ካልፈጠርን የሚሉት ያው እኔን የሚሆነውን እናያለን ብለው አይደል! አየህ የእኔን ስልጣን የሚፈልጉ ብዙ ናቸው ስልህ ዝም ብዬ አይደለም፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡- አንድዬ፣ እኛ ምስኪኖቹ እኮ በየጓዳው ምን እንደሚሠራ አናውቅም። ግራ ግብት ነው ያለን!
አንድዬ፡- ደግሞ ከዚህ በፊት የነገርኩህ ነበር፡፡ እሱ አናግሮኝ፣ እሱ ልኮኝ፣ እሱ እንዲህ ብሎኝ የሚለው ሰው ቁጥር እኮ ከማይለው ሰው እኩል ለእኩል ሊሆን ምንም አልቀረው፡፡ ምስኪኑ ሀበሻ፣ ደግሞ እንደ እኛ ማጋነን ጀመርክ ወይ በል አሉ፡፡
ምስኪን ሀበሻ፡- ኸረ አንድዬ፣ ምን ቆርጦኝ ነው እንደእሱ ያለ ነገር የሚወጣኝ!
አንድዬ፡- ሁላችሁም በትንሹም፣ በትልቁም እንቁራሪት በሬ እያሳከላችሁ እኔስ ለምን ይቀርብኝ! ደግሞ ስታስበው እነዚህ አናገረን፣ መልእክት ይዛችሁ ሂዱ አለን፣ ማስጠንቀቂያ ነግሮ ላከን ከሚለው ሁሉ ጋር የምለፋለፈው ይህን ያህል ጊዜ ተርፎታል ያላቸው ማነው?
ምስኪን ሀበሻ፡- ምኑን አውቄው አንድዬ!
አንድዬ፡- ደግሞ ቆይ በተመቻችሁ ጊዜ እስቲ ጠይቁልኝ፣ ሁሉም ደግሞ እኔን አናገረን የሚሉት በምሽት ነው፡፡ ቆይ እኔ የሌሊት ዘዋሪ ነኝ እንዴ?
ምስኪን ሀበሻ፡- አንድዬ፣ እባክሀ እንደሱ አትበል!
አንድዬ፡- አንዱ ይነሳና ትናንት ማታ በራዕይ አሳይቶኝ ይላል፣ ሌላው ደግሞ እኩለ ሌት በህልሜ
መጥቶ አናገረኝ ይላል፡፡ ልክ እኮ እነኚህ ምንድነው የምትሏቸው...አዎ፣ ሎቢይስት እንደምትሏቸው እኔ ከእነሱ ጋር ሎቢይስቶች ሊሆኑኝ ኮንትራት የተፈራረምን ነው የሚያስመስሉት!
ምስኪን ሀበሻ፡- አንድዬ፣ አን....
አንድዬ፡- እንደሱ አትበለኝ ልትለኝ ነው፣ አይደል! ቆይ ልጨርስ...እዚህ ማዶ ያለው “በምስራቅ በኩል ሀይለኛ ማዕበል ስለሚመጣ ተጠንቀቁ በላቸው ብሎኛል፣” ይላል፡፡ በዛኛው በኩል ያለው ደግሞ “በምስራቅ በኩል ፀሀይ ፏ ብላ ስለምትወጣ ደስ ይበላችሁ ብለህ አብስር ብሎኛል፣” ይላል፡፡ ምስኪኑ ሀበሻ፣ ስማኝ...
ምስኪን ሀበሻ፡- እሺ አንድዬ፣
አንድዬ፡- እንደው ድንገት ከተመቸህ...እንዲህ በልልኝ፤፡ እንደልባችሁ ከቀጠፋችሁ አይቀር ሰዉም እንዳይደናገር ቢያንስ ተመካከሩና አድርጉት ብሏል በልልኝ፡፡ ተማክረው ምን ያሉት ምን፣ ምን አይልም ትሉ የለ!
ምስኪን ሀበሻ፡- ኸረ አንድዬ፣ እሱ ለአንተ የሚመች ተረት አይደለም!
አንድዬ፡- በል በሰላም ግባ!
ምስኪን ሀበሻ፡- አሜን አንድዬ፣ አሜን!
ደህና ሰንብቱልኝማ!


Read 775 times