Monday, 03 January 2022 10:18

የተቀናጀ የቴራፒ ህክምና መስጫ ማእከል

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(1 Vote)

 ዓላማችን በተቀናጀ የቴራፒ ህክምና ህሙማኖችን ወደ ቀደመ ጤናቸው መመለስ ነው
                             
       በተለያዩ ተፈጥሮአዊና ሰው ሰራሽ ችግሮች ሳቢያ የሚከሰቱ የአካል ጉዳቶችን በተቀናጀ የቴራፒ አገልግሎት በማከም ህሙማንን ወደ ቀደመ ጤናቸው የሚመልስ ህክምና በአገራችን መስጠት መጀመሩን ሰማንና ወደ ማዕከሉ አቀናን፡፡ በአገራችን እምብዛም ያልተለመዱትን የንግግርና የባህርይ ቴራፒ ህክምናዎችን ጨምሮ የበርካታ ህመሞች ቴራፒዎችንና የአርቴፊሻል የሰውነት አካል ማምረቻ ማዕከልን አጣምሮ የያዘው ድሮጋ ልዩ የቴራፒ ክሊኒኮች በአሁኑ ወቅት በተለያዩ ሁኔተዎች የአካል ጉዳት የደረሰባቸውንና በልዩ ልዩ ህመሞች ሳቢያ የመንቀሳቀስ ችግር ያጋጠማቸውን ወገኖች በብቁ ባለሙያዎችና በዘመናዊ መሳሪያዎች በመታገዝ ወደቀደመ ጤናው የመመለስ ስራን በስፋት ለመስራት ተዘጋጅቷል። የማዕከሉ ዳይሬክተርና ሲኒየር ቴራፒስትና የህጻናት ቴራፒ ስፔሻሊስት የሆኑትን አቶ ነቢዩ ተስፋዬን ጋዜጠኛ መታሰቢያ ካሣዬ አነጋግራቸዋለች።
በማዕከሉ የሚሰጡ ህክምናዎች ምን ምንድን ናቸው?
በድሮጋ ልዩ የቴራፒ ክሊኒኮች የሚሰጡ የቴራፒ ህክምናዎች ከህፃናት እስከ አረጋውያን የሚሰጥ ጠቅላላ የፊዚዮቴራፒ ህክምና፣ የአካል ጉዳት የነርቭ መገጣጠሚያና የአጥንት ጉዳቶችን ማከም፣ ከቀዶ ጥገና በኋላ የሚያጋጥሙ የጤና ችግሮችን ማከም፣ ጠቅላላ የሰውነት እንቅስቃሴ ችግሮችን ማከም፣ የንግግርና የባህርይ ቴራፒ ህክምናዎችን መስጠትና፣ አርተፊሻል የሰውነት አካል የማምረት ስራዎችን እንሰራለን። በድሮጋ ልዩ የፊዚዮቴራፒ ክሊኒኮች ውስጥ የሚሰጠው ህክምና የተቀናጀና በተለያዩ ባለሙያዎች በጋራ የሚሰጥ ህክምና ነው። በተጨማሪም ልዩ የህጸናት የፊዚዮቴራፒ ህክምና አገልግሎትን እንሰጣለን።
የፊዚዮ ቴራፒ ህክምና የሰውነት እንቅስቃሴ ችግር ወይም ጉዳት ያለባቸውን ታካሚዎችን የእንቅስቃሴ ችግራቸውን መቅረፍ ወይም ማረም ማስተካከል፣ ከጉዳት በፊት  ወደነበሩበት ጤንነት ደረጃ መመለስ ማለት ነው። ይህ ለፊዚዮቴራፒ ህክምና የተሰጠው ድርሻ ቢሆንም በተናጠል የሚሰጠው ህክምና የሚፈለገውን ውጤት አያመጣም፤ ቅንጅት ያስልጋል። ለዚህም ነው በጠቅላላ አካላዊ ጤንነት ላይ የሚሰሩ ባለሙያዎችን አጣምረን ይዘን የህክምና አገልግሎቱን በመስጠት ላይ የምንገኘው። ህክምናዎቹ ከመደበኛው የፊዚዮቴራፒ ህክምና ጋር  በጥምረት የሚሰጡ በመሆናቸው ውጤታማነታቸው አስተማማኝ ነው።
ስፒች ቴራፒና ቢኤቪየራል ቴራፒ የምንላቸው ምን አይነት ህክምናዎችን ነው?
ስፒች ቴራፒ ወይም የንግግር ማጎልበቻ ህክምናና ቢኤቪየራል ቴራፒ ወይንም የባህርይ ማስተካከያ ህክምና የሚባሉት የቴራፒ ህክምናዎች በአገራችን እምብዛም የተለመዱ አይደሉም። ይህንን ቴራፒ በማዕከላችን እንድንጀምር ያስገደደንም ህክምናው የሚያስፈልጋቸው ህሙማን በርካታ ቢሆኑም ህክምናው ግን በአገራችን አለመኖሩ ነው። አብዛኛውን ጊዜ ታካሚዎቻችን በተለይ ህጻናት ታካዎቻችን የሚኖራቸው የአካል ጉዳት ወይም እንቅስቃሴ ማድረግ አለመቻል ችግር አይደለም። የንግግርና የባህርይ ችግር ሁሉ ሊኖራቸው ይችላል። ስፒች ቴራፒ የምንለው ንግግርን ወይም ቋንቋን ብቻ አይደለም ማዕከል የሚያደርገው ንግግር አንዱ የባርይ መገለጫ ነው። ንግግር በቋንቋ ብቻ አይገለጽም።
የተግባቦትም  አንዱ መገለጫው ነው። ተግባቦት ደግሞ ማዕከላዊ መስተጋብርን ማዕከል ያደርጋል። ይህ ደግሞ የአንድን ግለሰብ የስነ-ልቦና መዋቅርና የአእምሮ ጤንነትን የሚያማክል ነገር ነው። ስለዚህ በስፒች ቴራፒ የሰውየው የንግግር ወይም የቋንቋ አወጣጥ  ችሎታ ብቻ  ሳይሆን የሚታከመው የአእምሮ ጤናው ነው። ቢኤቪየራል ቴራፒ ወይንም የባህርያ ቴራፒ የምንለው ደግሞ የሰውን ልጅ ባህርይ በመግራት ትርጉም ባለው ደረጃ ባህርይውን በማህበረሰቡ ተቀባይነት ካለው ተለምዶአዊ አኗኗር ጋር እንዲስማማ የማድረግ ህክምና ነው። ታካሚዎቻችን በማዕከላችን አካላቸው ብቻ ሳይሆን ስነልቦናቸው፣ ቋንቋቸውና ባህሪያቸውንም ይታከማል።
የስነ-ምግብ ባለሙያ የፊዚዮቴራፒ ህክምና ማዕከል ውስጥ ድርሻው ምንድን ነው?
ቅድም ለመግለጽ እንደሞከርኩት የፊዞዮቴራፒ ህክምና ድርሻ ጉዳት ከደረሰ በኋላ ማከም ሲሆን የሰውነት የእንቅስቃሴ ችግር ያለባቸውን ታካሚዎችን ችግር ለመቅረፍ የሚያስችል ህክምና እንሰጣለን። ህክምናውን በምንሰጥበት ወቅትም ለጉዳቱ ወይንም ለችግሩ መነሻ የሆኑ ምክንያቶችን ከመሰረታቸው ለማስወገድ እንሰራለን። ለምሳሌ ከመጠን ያለፈ የሰውነት ክብደት ያላቸው ሰዎች ከውፍረታው ጋር ተያይዞ የሚከሰት በርካታ የጤና ችግች ያጋጥማቸዋል። የወገብ፣ የመገጣጠሚ፣ የነርቭና ሌሎች እንደ ስኳር ደምግፊት ያሉ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችም ሊያጋጥሟቸው ይችላል። እነዚህ ደግሞ ለእንቅስቃሴ ችግርና ለአካል ጉዳት ማጋለጣቸው አይቀሬ ነው።
አንድ ሰው ከመጠን በላይ ወፍራም  ከሆነ እንደ አካል ጉዳተኛ  ነው  የሚታሰበው በዘመናዊ የበሽታ መስፈርትም ከልክ በላይ ውፍረት የአካል ጉዳት እንደሆነ ይቆጠራል። ምክንያቱም ከመጠን ያለፈ ውፍረት ያላቸው ሰዎች ሌሎች ጤናማ የሰውነት ክብደት ያላቸው ሰዎች የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ ማድረግ አይችሉም። ስለዚህም እንዲህ አይነት ታካሚዎችን የእንቅስቃሴ ችግሮቻቸውን ከማከም ጎን ለጎን  በስነ-ምግብ ባለሙያ ክብደታቸውን ለመቀነስ  የሚችሉበት መንገድ ላይ እንሰራለን። ይህ ካልሆነና የችግሩ መንስኤ ከመሰረቱ ካልተወገደ የዚህን ሰው ህይወት ትርጉም ባለው ደረጃ በዘላቂነት ማስተካከል አይቻልም። ህክምናው በበርካታ ባለሙያዎች ጥምረት የሚሰጥ እንደመሆኑ ክፍያው ከፍተኛ ሊሆን ይችላል የሚል ግምት አለን?
በፍጹም እኛ ህክምናውን በአንድ ጣራ ስር በቅንጅት እንዲሰጥ ለማድረግ የፈለግነው ፈጣንና አስተማማኝ ውጤት ለማግኘት ነው። እንዲህ አይነት አገልግሎትን በግንባር ቀደምትነት ስንጀምር ሌሎችንም ለማበረታታትና በዘርፉ አስተማማኝ ህክምና መስጠት የሚቻልበትን መንገድ ለማሳየት ነው።
የምናስከፍለው ክፍያ በፊዚዮቴራፒ አገልግሎት ዘርፍ ተሰማርተው ከሚገኙ ክሊኒኮች ጋር ሲወዳደር ምንም ጭማሪ የሌለውና አነስተኛ ነው። ዓለማችን ታካሚዎቻችን በጥምረት በሚያገኙበት ህክምና ወደ ቀደመ ጤናቸው እንዲመለሱ ማድረግ ማስቻል ነው።
አርቴፊሻል የሰውነት አካል ማምረቻ ማዕከላችሁ ምርቶቹን የሚያቀርበው ለማን ነው።
አርቴፊሻል የሰውነት አካል ማምረቻ ማዕከሉ በዘርፉ የሚታየውን ክፍተት ለመሙላት ታስቦ የተጀመረ ነው። በማዕከላችን የተቆለመመ እግር ያላቸውን ህጻናት የማከም ስራ በስፋት ይሰጣል። እነዚህ ህጻናት ከህክምናው በኋላ የሚያደርጉት ለየት ያለ  ጫማ አለ። ይህ ጫማ የሚመረተው በመንግስት ደረጃ ሲሆን አቅርቦቱ በጣም አነስተኛ ነው። ስለዚህ ፍላጎቱና አቅርቦቱ ሊመጣጠን አልቻለም። ሰውሰራሽ የሰውነት አካላትም ፍላጎታቸው ሰፊ ነው። በትራፊክ አደጋና በተለያዩ በሽታዎች ሳቢያ ሰውነታቸው የተጎዳና የእንቅስቃሴ ችግር ያለባቸው ሰዎች በአርቴፊሻል የሰውነት አካል መታገዝ ያስፈልጋሉ። አቅርቦቱ ግን አነስተኛ ነው። ለዚህም ነው ብቁ ባለሙያዎችንና አስተማማኝ የጥሬ እቃ አቅርቦትን ይዘን ወደ ምርት የገባነው። ምርታችንን ከራሳችን አልፎ ለሌሎች  ህሙማን  እያደረስን እንገኛለን።
በወቅቱ ከህልውና ዘመቻው ጋር በተያያዘ በርካቶች ለተለያየ የአካል ጉዳት የተዳረጉበት ወቅት ነው። እነዚህ ጉዳት የደረሰባቸውን ሰዎች ለመርዳት ምን እየሰራችሁ ነው።
እንዳልሽው አገራችን በገጠማት የህልውና ዘመቻ በርካታ ወገኖቻችን ሲቪሉም ወታደሩም ጉዳት ደርሶባቸዋል።
ለዚህ የሚሰጠው ህክምና ደግሞ በቀጥታ እኛን የሚመለከት ነው። የጦር ጉዳተኞች በአብዛኛው ህክምና የሚያገኙት በጦርሃይች ሆስፒታል ቢሆንም እኛም ማህበራዊ ሃላፊነታችን የምንወጣበትና ለወገኖቻችን የህክምና እርዳታ የምንሰጥበትን እቅድ አውጥተን እየተንቀሳቀስን ነው።
ምን ያህል ቅርንጫፎች አላችሁ? በቀጣይ ምን ለማድረግ አቅዳችኋል?
 አሁን አገልግሎት እየሰጠን ያለነው  አራት ኪሎና ቦሌ በሚገኙ ቅርንጫፍ ክሊኒኮቻችን ነው። በቅርቡ ደግሞ ሲኤም ሲ ቤተልና፣ ጎፋ ገብርኤል አካባቢ 3 ቅርንጫፎችን ከፍተን አገልግሎታችንን እናሰፋለን። በቀጣይ ክሊኒኮቻችንን  በስፔሻሊቲ ደረጃ እያሰፋን የፊዚዮቴራፒ ህክምናን  በሆስፒታል ደረጃ ለማዋቀር ዕቅድ አለን- ከዚህ በተጨማሪም የፊዚዮ ቴራፒ ህክምና ትምህርት የሚሰጥበት የልህቀት ማዕከል ወይም ኮሌጅ የማቋቋም እቅድ አለን።

Read 2231 times