Sunday, 02 January 2022 00:00

ምክትል ፕሬዚደንት አለን እንዴ?

Written by  አበራ ሣህሌ
Rate this item
(1 Vote)

 ባለፈው ሰሞን ፕሬዚደንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ምዕራብ አፍሪካዊቷን ሀገር ኮትዲቯርን ጎብኝተው ነበር። ከአቻቸው አላሳን ዋታራ ጋር ለጋዜጠኞች ንግግር ያደረጉት ሳህለወርቅ፤ የሀገሪቱን መሪ “ወንድሜ” እያሉ ነበር የሚጠሩት። በዓለም አቀፍ ድርጅቶች በመሥራት በርካታ ዓመታት በማሳለፋቸው ሊተዋወቁ እንደሚችሉ ከሁኔታው መገመት ይቻላል። ሌላው ደግሞ ሁለቱም የፈረንሣይ ባህል ተጋሪ ስለሆኑ የሊሴ ገብረማሪያም ጓደኛን የማግኘት ያህል ስለሚሰማም ይመስላል። ሳህለወርቅ ለጋዜጠኞች ባደረጉት ንግግር፣ በሀገሪቱ እንዲሁም በቀጠናው የተፈጠረውን ችግር ለማስረዳትና “መሬት ላይ ስላለው እውነታ ግንዛቤ ለማስጨበጥ” እንደመጡ አስረድተዋል።
ለዚህ ፅሁፍ መነሻ የሆነው ግን ዩሮኒውስ ስለእሳቸው ሲዘግብ “የኢትዮጵያ ምክትል ፕሬዚደንት” እያለ የመጥራቱ ጉዳይ ነው። ነገሮችን ለማስተካከል በ1987 ዓ.ም በፀደቀው ሕገ መንግሥት መሠረት በኢትዮጵያ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እንጂ ምክትል ፕሬዚደንት የሚባል ነገር የለም።
ግምታችን ሊሆን የሚችለው በኖቤል ሽልማትም ሆነ ከዛ በኋላ ባጋጠሙ ሀገራዊ ክስተቶች የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ስም በተደጋጋሚ ስለሚጠራ በአንዳንዶች ዘንድ እንደፕሬዚደንት በመቆጠራቸውና ሌላው ከፍተኛ ሥፍራ ያለው የሀገሩ ተወካይ የሳቸው ተከታይ እንደሚሆን በመገመት ይመስላል።
እንደ ኢትዮጵያ ሁሉ የምክር ቤት አስተዳደር ሥርዓትን የሚከተሉ እንደ እስራኤል፥ ጀርመንና ሕንድን የመሣሠሉ ሀገሮች ፕሬዚደንቶች ብዙም አይታወቁም። የዋና አስፈፃሚነት ሥልጣን ለጠቅላይ ሚኒስትሮቹ ስለሚሰጥ ኔታኛሁ፥ ሜርከል፥ ሞዲ ስንል ባጀን እንጂ ሁሉም ፕሬዚደንት አላቸው።
ለመሆኑ ግን እንዴት ነው ከፕሬዚደንት ወደ ጠቅላይ ሚኒስትርነቱ የተሸጋገርነው?
የተቀቡ ሰዎች አያስፈልጉንም፥ የኛው ብጤ ይምራን ብለን ንጉሣዊ አስተዳደርን ከቀየርን ጊዜ ጀምሮ አንዴ የደርግ ሊቀመንበር፤ ቀጥሎ ጓድ ሊቀመንበር፤ በ1979 ዓ.ም ሕገመንግሥት ሲወጣ ደግሞ ሀገራችንን “ሪፐብሊክ”፤  መሪውን ደግሞ ፕሬዚደንት መንግሥቱ ኃይለማርያም ብለናል።
የደርግ ሥርዓት አብቅቶ በአብዮታዊ ዲሞክራሲ ሲተካ መለስ ዜናዊ ፕሬዚደንት ነበሩ - ያውም ለአራት ዓመት! ጠቅላይ ሚኒስትሩ? … ታምራት ላይኔ!
ሎጋው ሽቦዬ  - የጫረው እሳት ሲፈጀው ታዬ
አቶ መለስ የብሔር ፖለቲካን በጣም ስላራገቡት ወላፈኑ ሊለበልባቸው ሆነ። “የአክሱም ታሪክ ለጉራጌው ምኑ ነው” እያሉ ሲፎልሉበት በነበረው የዘር ፖለቲካ ምክንያት በሀገሪቱ ቀጥተኛ የፕሬዚደንት ምርጫ ቢካሄድ ወይ ከትውልድ ሰፈራቸው፤ ግፋ ቢል እንኳ ከአንድ ክልል በዘለለ የትም እንደማይመረጡ የገባቸው ገና በማለዳው ነው። ስለዚህ ዘዴ መፈለግ ነበረባቸው። በመላ ሀገሩ እየዞሩ የማያውቃቸውን ሕዝብ ከመወትወት በአንድ መንደር ብቻ ተመርጦ ሀገር መምራት የሚያስችል፤ በሳቸው ልክ የተሰፋ አሰራር የሕዝብ ተወካዮች ሥርዓት እንደሆነ ግልፅ ሆነላቸው። የ1987ቱን ሕገመንግሥት ፅፈው/አስፅፈው ወደ ጠቅላይ ሚኒስትርነቱ ተሸጋገሩ። በዛ ህግ መሠረት የሕወሓት/ኢህአዴግ ሊቀመንበር እስከሆኑና ድርጅቱ በውድም በግድም አብዛኛውን የምክር ቤት ወንበር እስከያዘ ድረስ ጠቅላይ ሚኒስትር ማን ይሁን በሚለው ላይ የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚያገባውም ነገር የለም። የምክር ቤት ወንበር አያያዝን ደግሞ ተክነውበታል - 96 አይበቃኝም ብለው መቶ ከመቶ በመድፈን ብቃታቸውን አሳይተዋል።
ብልሃቱ ለመለስ ሰርቷል። ያለምንም ተቀናቃኝ ከሃያ አመት በላይ በሃገሪቱ  ነግሰዋል። ሲያልፉም “ሌጋሲ” የሚያስቀጥል መሪ ትተው ሄደዋል።
እዚህ ላይ የምክር ቤት አስተዳደር ቅንነት በጎደለው መንፈስ አንድን ግለሰብ ሥልጣን ላይ ለማስቀመጥ ሥርዓቱ መበጀቱን ለማሳየት እንጂ ለኢትዮጵያ የሚጠቅም ነገር የለውም ለማለት አይደለም። ቅንነት ጠቅላዩ የሚታወቁበት ልብስ እልነበረም። ስብሰባ የተጠሩት ምሁርም “…በርሶ ቁጥጥር ሥር ስላለን ቅንነቱ እንዳይለይዎ ብቻ ነው ተስፋ ላደርግ የምችለው” ሲሉ ያለምክንያት አልነበረም።
በመቶ የሚቆጠሩ ብሔረሰቦች ያሉባት ናይጄሪያ በፕሬዚደንት ትተዳደራለች። በአንፃሩ ደግሞ በርካታ ሕዝብ፥ ሀይማኖትና ብሔር ተደበላልቆ የሚኖርባት ሕንድ ነፃ ከወጣችበት ጊዜ ጀምሮ በተወካዮች አስተዳደር ትመራለች። ሀገሮች እንደ ህዝቦቻቸው ስብጥር፥ ሥነልቦና፥ አሰፋፈርና እንደ ታሪካቸው ሁኔታ ሲፈልጉ ከላይ በጠቀስናቸው፤ ካሻቸውም ወታደራዊ ፈላጭ ቆራጭ አለያም በንጉሣዊ አገዛዝ መመራት ይችላሉ።  እስካሁን በሀገሪቱ በታየው ግን የአስተዳደር ዘይቤው በመሪዎች መልካም ችሮታ የሚወሰን ጉዳይ ሆኗል።
Read 691 times