Print this page
Monday, 03 January 2022 10:24

የ‹‹ወደኋላ›› ረጅም ልቦለድ የአተራረክ ስልቶች ትንተና

Written by  ከአንለይ ጥላሁን ምትኩ
Rate this item
(0 votes)


              (ክፍል ሁለት)

ርዕስ = ወደኋላ
ዘውግ = ረጅም ልቦለድ    
ደራሲ= ሊዲያ ተስፋዬ
ማተሚያ = ሜጋ ማተሚያ ኃ.የተ.የግ.ማህበር
የገጽ ብዛጽ= 174
ዋጋ=120 ብር ( USD 10)
በልቦለድ ውስጥ ኪናዊ ፋይዳ ያላቸው የቅርፅም ሆነ የይዘት ማስተንተኛዎች፣ መመዘኛዎች ሁሉ ስርዓታዊነትን የሚጎናጸፉት በእውቀት ላይ የተመሰረተ አጠቃቀም ሲኖር ነው፡፡ ስለሆነም የትረካ ስልቶችን ፋይዳ መረዳት ያስፈልጋል፡፡ እዚህ ላይ ‹‹ድርሰቱ ተገቢውን ቅርጽና ይዘት አግኝቶ አንድ ውቅር እሚሆነው አላባውያኑ በተገቢው መጠንና ቅደም ተከተል ተዋህደውና ተሳስረው ሲኖሩ ነው፡፡ ይህን መተሳሰር ከሚያስገኙት መሀል ደግሞ ምልልስ፣ ገለፃ፣ ምልሰትና ንግር ዋናዎቹ የአተራረክ ዘዴዎች ናቸው፡፡›› (ዘሪሁን አስፋው፣ ገፅ 204-205 ይመልከቱ)
በ‹‹ወደኋላ›› ረጅም ልቦለድ ውስጥ በርካታ የአተራረክ ስልቶች አገልግሎት ላይ ውለዋል፡፡ ጎልተው የሚታዩት  ገለፃ፣ ምልልስ፣ ዘገባ እና አስተያይት ናቸው፡፡ በእርግጥ ውስን ቦታዎች በምልሰት የተነገሩ (የተተረኩ) ሁነቶች አሉ፡፡
በአተራረክ ሂደት ንግግር ከሚገለፅባቸው ስልቶች ወይም መንገዶች መካከል ከሆኑት ውስጥ ምልልስ፣ ምልሰት እና ንግር ተጠቃሽ ናቸው፡፡ እያንዳንዳቸውን በምሳሌ ተመርኩዘን ቀጥሎ እንመለከታለን፡፡
ሀ.ምልልስ
ምልልስ በየትኛውም የህይወት አጋጣሚ ሰዎች ስለተለያዩ ጉዳዩች ሀሳብ የሚለዋወጡበት ስልት ነው፡፡ በልቦለድም ውስጥ ተግባራዊ እንደሚደረግ ‹‹ዘሪሁን አስፋው›› ይገልፃል፡፡
‹‹በእውኑ ዓለም በሁለት ሰዎች መካከል የሚደረግ የሃሳብ ወይም የንግግር መለዋወጥ
አለ፡፡ ሁለት ሰዎች ባላቸው ግንኙነት መሰረት በየአጋጣሚው በሆነ ጉዳይ ላይ ሲነጋገሩና ሀሳብ
ለሀሳብ ሲለዋወጡ እንሰማለን፡፡ እንዲህ ያለው የሀሳብ መለዋወጥ በልቦለድ ገጸባህሪያትም
መካከል ይደረጋል፡፡ ይህም የሀሳብ መለዋወጥ ምልልስ በመባል ይታወቃል።›› (ገፅ 205) ስለሆነም የገፀባህሪያቱን ምልልስ እየመዘዝን እርስ በርስ ያላቸውን ግንኙነት፣ የቋንቋ አጠቃቀም፣ ስሜት፣ አመለካከት፣ የፈለቁበትን ባህል፣ የግል መርህ … መሰል ተናጠላዊ እና ቡድናዊ መገለጫዎች ለመረዳት ያስችላል፡፡ በመጽሐፉ ውስጥ ትልቁን ቦታ የሚይዘው ምልልስ የትረካ
ዘዴ ነው፡፡ ለምሳሌ፡-
‹‹እድሌን እሞክራለሁ››
‹‹ምርጫው የአንቺ ነው››
‹‹ሶፊ! ምን አደርጋለሁ? ሠላሳ ዓመትስ አልፎኛል፡፡ ዝም ብዬ እንደዚህ ኖራለሁ?››
‹‹እና ሰላሳ… አርባ … አምሳ እያለ ይሂድ፡፡ ከእድሜ ጋር መጣላትን ምን አመጣው?››
‹‹አንድ ዓመት ያደረገ ነው አልኩሽ አይደል? ያዘንኩ በምን መስሎሽ? ሌላ ችግር መጥቶ ነው።››
ምን ዓይነት ፈተና ነው? ‹‹የምን ችግር?››
‹‹ስትመለሺ እነግርሻለሁ፡፡ መያዣ ነው››
‹‹መያዣ  ነገር አብዝተሻል… ይሁን!››
(ገጽ 139-140 ይመልከቱ)
ከላይ በተጠቀሰው ምልልስ ውስጥ  ያልተስተካከለ የቋንቋ አጠቃቀሙ የሰብሪና ቢሆንም በመፅሐፉ ውስጥ ወጥነት ባለው ሁኔታ አልሰፈረም፡፡ በገጸባህሪዋ ትውውቅ ወቅት አማርኛን አቀላጥፋ የምትችል ተደርጎ መገለጹ የተዓማኒነት ጥያቄ የሚያስነሳ ይመስለኛል፡፡ ያው የሰዋስው ግድፈቱን መገለጫዋ ነው ማለቱ ሽንገላ ይመስላልና ነው፡፡
ሌላኛው ምልልስ ደግሞ የሚከተለው  ነው፡፡
‹‹እኔን የማይመስል ነገር አትንገረኝ! አላደርገውም! ሲጀመር ሰርቼ ያላገኘሁት ገንዘብ የእኔ እንደማይመስለኝ  ታውቃለህ፡፡ ሲቀጥል የጀመርኩትን ጽሁፍ እዚህ ሆኘ መጨረስ እፈልጋለሁ፡፡››
‹‹የምትፈልጊው ነገር ካልጎደለብሽ አርፈሽ መኖር ነው፡፡›› እኔ አውቅልሻለሁ ብሎ ነገር …
ትርፍና ጉድለትን እንዴት ነው የሚያሰላው?
‹‹መልሽልኝ እንጂ…›› ብሎ ጮኸ በድንገት። ምንም ጥያቄ እኮ አልጠየቀኝም፡፡ ውስጡ ስላልተረጋጋ ከእኔ ለመስማት የፈለገው ነገር እንዳለ ገብቶኛል፡፡
‹‹ምን ልመልስልህ?››  (ገጽ 60፣ ይመልከቱ)
በዚህ ምልልስ መሀከል ላይ የገባው የማን እንደሆነ ለመለየት አስቸጋሪ ሆኖ አግኝቸዋለሁ።
ይህም ምልልሱ ግልፅነት እንዲጎድለው አድርጓል፡፡ ሊተላለፍ የተፈለገው መልዕክት ከየትኛው ወገን እንደተሰነዘረ ማወቅ አይቻልም። በተጨማሪም ስሜትና ሀሳብ ያጎድላል፡፡
በዚህ ነጥብ ላይ አንድ ምሳሌ አንስተን እናጠናቅ፡፡ እንሆ፡-
‹‹እቴዋ…›› ድምጹ ቀጥ ብሎ ወደ ጆሮዬ ሲገባ መጽሐፉን ፊቴ ላይ ደፋሁ፡፡ እንዳያየኝ፡፡
‹‹አንድ ቀን ይችን ቃል ታስታውሻት ይሆናል፡፡ ቆዳው የነጣ ፣ ኪሱ ያበጠ ሁላ ሰው እንዳይመስልሽ…››
‹‹ምን እያደረግሁ እንደነበር የምታውቀው ነገር አለ?››
‹‹ያው… ገምቼ ነዋ!››
‹‹ግምትህ ልክ አይደለም!››
‹‹እሺ እመቤቴ!›› (ገጽ 109፣ ይመልከቱ)
ምልልሱ የማህበራዊ ውጥንቅጥ ወይም ዝቅጠት ማሳያ ሲሆን ሶፊያ ስደተኛውን አይመንን ፈልጋ ካገኘችው በኋላ አስፓልት ዳር ሲያወሩም ሆነ ሶፍት ተሯሩጦ በሚሸጥበት ሰዓት ያጋጠሟት ንጀሳዎች ሁሉ የሚጠቁሙት መሰረተ ቢስ ፍረጃን ነው፡፡ በተለይም ወንዶች ለፆታዊ ግንኙነት ያላቸውን ምልከታ ለማጉላት ጥቅም ላይ ውሏል፡፡ ስለሆነም ወንዶች ለወሲብ፣ ለምግብ እና ለኳስ ያላቸውን ልዩ ቦታ የሚተችም ጭምር ነው፡፡ ሀገር ምጥ ላይ ባለችበት ወቅት እንዲህ ያለው ድርጊት አዚም፣ ድንዛዜ መሆኑን ጭምር ለመጠቆም ሚና ተሰጥቶታል፡፡
ለ.ምልሰት
ባለፈ ድርጊት፣ ስሜት፣ ገጠመኝ እና ሁነት ወዘተ. ላይ የሚመሰረት ከንግግር መደብ የሆነ
የአተራረክ ስልት ነው፡፡ ስለሆነም ኪናዊ ፋይዳ ያለው ነው፡፡
በዚህ ልቦለድ ውስጥ በርከት ያሉ በምልሰት የቀረቡ ታሪኮች አሉ፡፡ ለምሳሌ፡-
እናቴ ክፉ ናት አልኩሽ አይደለም? ከአያቴ ድሬዳዋ እየኖርኩ እሷ ጠርታኝ ነው ሳውዲ የሄድኩት፡፡ መጀመሪያ ጥፋቱ ምን መስሎሽ? ወልዳናለች አይደለም? ከአባቴ ችግር ስላላት እኛንም አስጠልቷት ጥላን ጠፋች፡፡ እነርሱ መግባባት አልቻሉም አይደለም… በመሃል እኛን ጎዱን፡፡ ልጆች ነን አይደለም? ቤትሽን አፍርሰሽ፣ ልጆችሽን ጥለሽ ትኖሪያለሽ? አባት እና እናት ሲለያዩ ማለት መፍረስ ማለት ነው፡፡ ሌላ አትዪም ገብቶሻል?
እናታችን ትናፍቀናለች፣ አባቴ ስራ ነው ቀን፣ ማታ፡፡ የምንበላው አያይም፡፡ ሚስቱ ታሰቃየናለች፡፡ አድጌ ከእናቴ ሄድኩት፡፡ ግን ምን ታደርጊያለሽ? አብረን አልኖርንም፡፡ ፍቅር ካላደገ መግባባት አትችይም ገብቶሻል? አባቴ ታስታውሳለች መስሎኛል እኔ ስታይ ጭንቅላቷ ልክ አይሰራም፡፡ እኔ ደግሞ ያሳለፍኩትን መከራ አስታውሰዋለሁ፡፡ ስትቆጣ ምናምን አላሳደግሽኝም ጥለሽኛል አሁንስ ለምን? እላታለሁ፡፡ (ገጽ 121፣ ይመልከቱ) በልቦለዱ ውስጥ ሰብሪናን በይበልጥ የምናውቃት በምልሰት በሚቀርቡልና ንግግሮች አማካኝነት ነው፡፡ በተለይም ደግሞ በእናቷ የደረሱባትን ፈተናዎችም ሆነ መገፋት የምንካፈላት ያለፈ ታሪኳን መለስ ብላ ስታስቃኘን ነው፡፡
ይህ ስልት ታሪኩን ሙሉ ለማድረግና ሊተላለፍ ለተፈለገው የልቦለዱ ጭብጥ ሁነኛ ሆኖ አግኝቸዋለሁ፡፡
ሌላው ያለፈውን ዘመን ሴትነት ማሳያ እና የአሁኑ ማንጸሪያ ሆኖ የቀረበ ምልሰት እናንሳና እንደምድመው፡፡
‹‹…ነፍሱን ይማረውና ባለቤቴ እያለ ቡና ሳቀርብ ከአንቀላ ጋር ነው፡፡››
‹‹አነቀላ ነው ያሉኝ?››
‹‹አዎ ልጄ! በቅቤ የታሸ ቆሎ ማለት ነው፡፡ ወይ እሱን ወይ ደግሞ ጭኮ ካልሰጠሁት እንደ ሕጻን ልጅ ያኮርፋል፡፡ እንግዲህ በእኛ ባህል በቅቤ የራሰ ቆሎ፣ ጭኮም የሚሰጠው ለአራስ ወይ ደግሞ ለሙሽራ ነው፡፡ እሱ ልጄ ሁሌም ሙሽራ ነበር፡፡ እንኳን አደረግሁለት! እንኳንም ደስ እንዳለው ኖረ! በዕድሜ ብንቀራረብም ዕድሜውን ሁሉ ስላስደሰትሁት፣ በህመሙ ጊዜም ደከመኝ፣ ሰለቸኝ ሳልል ስላስታመምኩት እንደ አባቴ መርቆኝ ነው ያረፈው፡፡
‹‹ ደስ ይላል እማማ! ደስ የሚል ትዝታ ነው ያልዎት›› ‹‹ፈጣሪ ደግ ነው!››  (ገጽ 84፣ ይመልከቱ) ሶፊያ ራሷን ፣ በእማማ እርጎዬ ትዳር ውሰጥ የተመለከተችው ይመስለኛል፡፡ የመተሳሰብን ዋጋ ከፍ ለማድረግ የገባም ነው፡፡ እንደ ሴት የትዳር በረከት የተፈጥሮን ስልት መጫወት ነውና ፤ማንጸሪያ ነው፡፡
  ሐ. አስተያየት
በልቦለዱ ውስጥ በብዛት ከሚገኙ የትረካ ስልቶች ውስጥ አስተያየት ተጠቃሽ ነው። በእኔ እምነት አብዛኞቹ አስተያየቶች አስፈላጊ አይደሉም፡፡ ምክንያቱም ችክታን ከመፍጠራቸውም በላይ ለታሪኩ አንዳች ጥበባዊ ፋይዳ የሌላቸው በመሆኑ ነው። ማለትም ታሪኩን ያደበዝዛሉ፣ ትረካውን ያንዛዛሉ፡፡ ከዚያም በላይ ደግሞ ተራኪዋ ዋና ገጸባህሪ ከመሆኗ ጋር ተያይዞ ሂደቱን ለአንባቢ  አሰልቺ ያደርገዋል፤ ጀመራት ደግሞ ያስብላል፡፡
በምሳሌ እንመልከተው፡፡
‹‹ትግሉን ገትቶ አራስ ህጻን እንደሚሸተት አይነት ከአንገቴ ስር ጠረኔን ሲወስድ እሱ ጋር ብቻ እንድሆን አደረገኝ፡፡ ለምን እንደሆነ እንጃ? እንዲህ ሲሆን የእውነት ፍቅር የተጠማ፣ የተሸነፈ ያህል ስለሚሰማኝ የሚፈልገውን መሆን፣ ራሴን መስጠት ያሰኘኛል፡፡ እኔም አንገቱ ስር ገባሁ… ከእህል ፣ ውሃ በላይ የሚበላ ፣ ነፍስን የሚጠግን ጠረን ያለው አንገት ስር ነው፡፡›› (ገጽ 69፣ ይመልከቱ) ይህ አይነቱ አስተያየት በአብዛኛው ምልልስ ስር የሚሰጥ በመሆኑ የልቦለዱን ውበት አደብዝዞታል፡፡ ምክንያቱም መሆን የነበረበት ድርጊትን፣ ስሜትን ፣ ሁኔታን መግለፅ እንጂ ስለ ሁሉም ነገር ማብራሪያ መስጠት አልነበረም። በንግግር ሁሉ መሃል እየገባች (ተራኪዋ) የምትሰጠው አስተያየት ልቦለዱን ወደ ዘገባነት ይጎትተዋል፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጸሃፊውን በኢሜይል አድራሻው፡- This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል፡፡


Read 1239 times