Print this page
Monday, 03 January 2022 10:26

የሁሴን ከድርን “ንፋስን በወጥመድ” በጨረፍታ

Written by  መልካሙ ተክሌ ኃይለጊዮርጊስ
Rate this item
(4 votes)

ለብዙ ጊዜ ለፍቶባቸው የጻፋቸው የአዕምሮው ጭማቂ የሆኑ 200 ግጥሞቹ ጠፍተውበታል፡፡ ቢሆንም ግጥም መጻፍ አላቆመም፡፡ ተንቀሳቃሽ ስልኩ ላይ የጻፈው ሌላው ግጥሙ ከነ ስልኩ ጠፍቶበታል። አሁንም ግጥም መጻፍ ሳይተው እንደገና ጽፎታል፡፡ እነዚህንና ሌሎች የግጥም ሥራዎቹን አካትቶ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ  #ንፋስን በወጥመድ; የሚል አዲስ የግጥም መጽሐፍ ለንባብ አብቅቷል- ጋዜጠኛ፣ ደራሲና ገጣሚ ሁሴን ከድር፡፡
ስለ ሁሴን ከድር መጀመርያ ያወቅኩት በኢትዮጵያ ሬዲዮ ቅዳሜ መዝናኛ ነው፡፡ ከዚያ ወዲህ ደግሞ በተለያዩ መጽሔቶችና ጋዜጦች ላይ ሲጽፍም አውቀዋለሁ - በጽሑፎቹ፡፡ ሁሴን የሬዲዮም፣ የቴሌቪዥንም፣ የኅትመትም ጋዜጠኛና አርታኢ ነው፡፡
ሁሴን ከራሱ የጋዜጠኝነት ሥራዎች ባልተናነሰ የሌሎች የኪነጥበባት ባለሙያዎችን ሥራዎች አርትዖት በመሥራትና በማበረታታት ይታወቃል፡፡ ማበረታቻው ደግሞ ከያንያኑ ሥራዎቻቸውን እንዲያሳትሙ የገንዘብ ድጋፍ ከማሰባበሰብ እስከ ገበያ ማፈላለግ ይደርሳል፡፡ ለዚህም ይመስላል በግጥም መጽሐፉ የሽፋን ገጽ አስተያየት ላይ ደራሲና የፍልስፍና መምህሩ መሃመድ አሊ፤ “ሁሴን ከድር ብዕርና ፊደልን ከመዝራት ይልቅ በሌሎች የተዘሩ ሰብሎችን ማረምና መኮትኮትን የየዕለት ጉዳዩ ያደረገ ሰው ነው፡፡ የተዘራን ሰብል ኮትኩቶና አርሞ ለፍሬ ማብቃቱ ለራሷ ለሚኖርላት ሥነ ጽሑፍ ታማኝ አገልጋይነቱን ይገልጣል፡፡” ያለው፡፡
መምህር መሃመድ አሊ ስለ ገጣሚነቱ በሰጠው አስተያየትም፤ “ግጥም ሲጽፍ እንደ ቀልድ ነው ድንገት አንዳች ሁነት በታዘበ ጊዜ፣ አለያም ከራር ስሜት ሲገባው በደመቀ ጸሐይ እንደሚዘንበው (ጅብ ወለደች ዝናብ) ፊደሎቹን በመልክና ውበት አጣምሮ ያንጻል” ብሏል፡፡
#ንፋስን በወጥመድ; ግጥሞቹ በአብዛኛው ከ1980ዎቹ እስከ አሁን በተጠቀሰው መልኩ እንደቀልድ የተገጠሙ ናቸው፡፡ ለመጽሐፉ የመጀመርያው ግጥም ያደረገው “መንገድ” በ1986 ጃንሜዳን ሲያቋርጥ የገጠመው ነው፡፡
በቀጭኗ ሲቻል መሔድ፣
በጠባቧ በራስ መንገድ፡፡
መዞር መጠምዘዝ ሌላ ፍለጋ፣
የሰው መንገድ አጋም ቀጋ፡፡  (ገጽ1)
እያለ ይቀጥላል፡፡ ለጊዜው ያን ሰፊ ሜዳ ስለማቋረጥ ቢሰነኝም፣ በዚህ ግጥሙ በራስ አማራጭ ስለመሔድ፣ የራስ ስለማዛለቁ በራስ ውስጥ ሌሎች ስለመኖራቸውና ያንን አጣጥሞ ካልተኬደ ጀማው ጎትቶ እንደሚያወጣ፣ አንቅሮ እንደሚተፋ የታዘበበትን ነው የነገረን፡፡
በቀጣዩ ገጽ ደግሞ ወደ ግል ሕይወቱ መለስ በማለት “ልብ”ን ያመጣል፡፡
ልብ
ሰው መሐል ገበያ ከአስማሚ ተስማሚ፣
ከገበያ ውድድር ከግብይት ጎራ፣
ልቤን ለጨረታ ለሽያጭ አቅርቤ፣
ተጫርቼ መጣሁ ሌላ ልብ ሸምቼ በእጥፍ የጠራ፡፡ (ገጽ 2)
ይህን ግጥም በ1990 ሁሴን ራሱ ለተማረከባት ሴት የገጠመው ነው፡፡ ኋላ ይህች ሴት የትዳር አጋሩ ሆናለች፡፡ የግጥሙ መልዕክት ግን ለሁላችንም ነው፡፡
በአንድ ነገር ተስፋ ስንቆርጥ ወይም ስሜታችን ሲቀዛቀዝ “ውይ” ማለታችን የተለመደ ነው፡፡ ሁሴን ግን “ውይ” የኛ ዜማ አይደለም ይለናል፡፡
ውይ
ረቂቅ አወራረድ ተስረቅራቂ ትንፋሽ ምጥቀቱ የበቃ፣
ለሰው ባማክረው የአዘፋፈን ስልቱን የልቤን ሙዚቃ፣
ውይ… ውይ ውይ ውይ…ውይይይይ ማለቱ፣
የሰይጣን ነው አሉኝ የዜማ ቅኝቱ፡፡
ስለዚህ ገጣሚው ተስፋ ማድረግ እንጂ ተስፋ መቁረጥ የኛ የሰዎች መገለጫ መሆን የለበትም፣ ተስፋ አድራጊ እንሁን እያለ የሚመክር ይመስላል፡፡
በሌላ “ጎዶሎ” በተሰኘ ግጥም ማነው አካል ጉዳተኛ ሲል ይጠይቅና ራሱ ምላሹን እንካችሁ ይለናል፡፡
የሕሊና ሽርፈት የልብ ጉስቁልና፣
የብስለት መደኅየት ፈዛዛ ልቦና
ሲነሳው ነው ከላይ እንዲሁ ሲፈጥረው፣
የዚህ ሰው አካሉ ጎደለ ምንለው፡፡
ሁሴን በ”ንፋስን በወጥመድ” ከወቅቱ የሀገራችን ኢትዮጵያ ሁኔታ ጋር የሚነጻጸር፣ እነ ሶርያ እና እነ ኢራቅ የተቃኙበት ግጥምም አለው፡፡
 በሀገራቱ የደረሰውን ነግ በኔ በሚል ስሜት ተሳልቋል፡፡ እንደ ገጣሚም ከፍተኛ የሆነ ምሬቱን ገልጾበታል፡፡ “ለሰላም” ይሰኛል ርእሱ፡፡
ለሰላም
ጦርነት ከፍታችሁ ውቅሩን ተርክኩ፣
ይፈራርስ ቤታቸው ድልድሉን አውኩ፡፡
አታረጋጉዋቸው፣ አይደላደሉ፣
ዝም ከተባሉ ሰላም ይገዛሉ፡፡
እያለ የሚቀጥል እና ምዕራባውያን ሀገራት በሌሎች ሀገራት ላይ በሚፈጽሙት ደባ ላይ ያጠነጠነ ግጥም ነው፡፡
ሁሴን “አልቅስ” የተሰኘ ግጥሙን የጻፈው ምሽት ላይ ታክሲ ውስጥ ሲያለቅስ ላየው ወጣት ነው፡፡ በወጣቱ መነሻነት ይጻፍ እንጂ መልዕክቱ ለሁላችንም ነው፡፡ በዚህ ግጥም ጥልቅ ስሜቱን የገለጸው ገጣሚው አለመሸነፍን ሰብኳል፡፡
አልቅስ
አልቅስ የኔ ጋሻ፣
በራስህ ትከሻ፡፡
በራስህ ጫንቃ ላይ፣
የማንንም ሳታይ፡፡
ግጥሙ ዐራት ገጽ ስለሆነ ሙሉውን እዚህ ዳሰሳ ላይ ማምጣት አይቻልም፡፡ ነገር ግን በግጥሙ መጨረሻ ስንኞች እና ቤት መድፊያው አልቅስ እንዳላለ ሁሉ
ዳግመኛ አትሸነፍ፣ እርም ይሁን ማንባትህ፣
በራስህ ቃል ጽና፣
ዳግመኛ አትንበርከክ ተነስ እንደገና፡፡
ይለናል፡፡
“ልጆቹ እስኪነቁ” የሚለው ግጥሙ ደግሞ ባለፈ ታሪክ ከመመጻደቅ የራሳችንን አስተዋጽዖና ታሪክ መሥራት እንዳለብን ያሳየናል፡፡
ሁሴን ከድር በሌላ ስፍራ አርአያዬ የሚለውን ባለቅኔ ሎሬት ጸጋዬ ገብረመድህንን ኅልፈት ሲሰማ ዋርካው ወደቀ የሚል ግጥሙን አበርክቶልናል፡፡ (ገጽ 59-60)
ሁሴን ማለት ጥርሱን እያመመው እንኳ ግጥም የሚገጥም ነው፡፡ (ገጽ 74) ስለ ሰብእናውና ሥራዎቹ ብዙ ማለት ይቻላል፡፡ ነገር ግን የጋዜጣው ቦታ ውሱን ነው፡፡ የግጥም መድበሉ በገበያ ላይ ስለዋለ እናንተም  አንብባችሁ ሃሳባችሁን እንድታካፍሉ ግብዣዬ ነው፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጸሃፊውን በኢሜይል አድራሻው፡- This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል፡፡



Read 1102 times