Print this page
Monday, 03 January 2022 17:32

ሲዲ አዟሪው ሚሊየነር

Written by 
Rate this item
(2 votes)

የክሪስ ሌቲ የህይወት ጉዞ ታሪክ  በአስደሳች የልብ ወለድ መድብል ውስጥ የምናገኘውን ዓይነት ታሪክ ይመስላል። የአጎቱን መኪና አጥቦ፣ ለማክዶናድ በርገር መግዣ በተሰጠው ዘጠኝ ዶላር የሙዚቃ ካሴትና ሲዲ በኒዮርክ አውራ ጎዳናዎች እየዞረ መሸጥ የጀመረው ኬቲ ትልቅ ህልም ነበረው- የራሱን የቢዝነስ ኩባንያ በመክፈት የተለያዩ አርቲስቶችን ስራዎች ማሳተምና ማከፋፈል።
ዛሬ የትናንት ህልሙን እውን አድርጎ እንደተመኘው የራሱን የሙዚቃ አሳታሚና አከፋፋይ ኩባንያ አቋቁሞ፣ የተለያዩ የአሜሪካ እውቅ አርቲስቶችን ስራዎች እያሳተመ ከፋፍላል። ሙዚቃ ከማተምና ከማከፋፈል ስራው በተጨማሪም ከስራው ጋር ተያያዥ የሆኑ ሁለት የቢዝነስ ኩባንያዎችን ከፍቶ አርቲስቶችን ያስተዳድራል። የአርቲስቶችን የስነ-ጥበብ ክህሎት የማዳበሪያና የማስታወቂያ ስራዎችን ያከናውናል።
ክሪስ ሌቲ ኩባንያዎቹን ሲያቋቁም በእጁ ላይ የነበረውን ካፒታል፣ ታላቅና የተሳካለት ሰው የመሆን ምኞትና  ህልም ብቻ ነበር።ዓይነት ቢዝነስ እንደሚጀምር ጥርት ያለ ሀሳብና ሀሳቡን ወደ ተግባር ለመተርጎም የሚያስችል ቁርጠኝነትም ነበረው- ኬቲ። የራሱን ኩባንያ ለማቋቋም ሲነሳ በእጁ ላይ የነበረው ጥሬ ገንዘብ እዚህ ግባ የሚባል አልነበረም- ከሚተኛበት ፍራሽ ስር ቆጥቦ ያስቀመጣት ገንዘብ አንድ ሺ ዶላር እንኳ አትሞላም።
ክሪስ ሌቲ ገና በለጋ እድሜው ህልምና ምኞቱ ሁሉ ትልልቅ ነገሮች ነበሩ። ሲዲና ካሴቶችን እያዞረ ይሸጥ በነበረበት ጊዜ ከሚያያቸው የተለያዩ ቢሮዎች መካከል እርሱ የሚፈልገውን የወደፊት ቢሮ ከእነቢሮ ማጌጫዎቹ ጭምር በምናቡ ይስል ነበር። የራሴን ቢዝነስ ስጀምር ካየኋቸው ቢሮዎች ሁሉ የበለጠና የተዋበ ቢሮ ይኖረኛል ይልም ነበር።
ክሪስ ሌቲ ገና በለጋ ዕድሜው አስገራሚ የማስተዳደር ችሎታ እንደነበረው እናቱ ዛሬም ድረስ በአድናቆት ታስታውሰዋለች። የቤተሰቡ የበኩር ልጅ በመሆኑ ታናናሽ ወንድሞቹ ያለአንዳች ችግር ትምህርት ቤት ሄደው እንዲመለሱና ቤታቸውም ውስጥ እናታቸው ባወጣችላቸው የጨዋታና የጥናት ፕሮግራም መሰረት ማድረግ ያለባቸውን ነገር ያለ ረብሻና ሁከት  ማከናወናቸውን የማረጋገጥ ሃላፊነት የወደቀው በእርሱ ላይ ነበር። ይህንን ሃላፊነቱንም በብልህነትና በፍቅር ሲፈጽመው ማየትና ለልጆች ጤናማ እድገት አይመችም በሚባለው የኒውዮርክ  ብሮንክስ ሰፈር  እየኖረ፣ የውጪውን አስቸጋሪ ሁኔታ ተቋቁሞ የተረጋጋና ከእድሜው  በላይ በሳል የሆነ ባህርይ ባለቤት መሆኑ ለእናቱ የጽድቅ ያህል የሚቆጠር ነበር።
የብሮንክስ መንደር ሰፈር ለወጣቱ ክሪስ ሌቲ ያቀረበችለት ገፀበረከት መልካም  አልነበረም- በጦር መሳሪያ የታገዘ የሰፈር ወጠምሻዎች የእርስበርስ ግጭት፣ አደንዛዥ እጽንና የራፕ ሙዚቃን ነበር። የተቀሩትን ሁሉ ችላ በማለት በወቅቱ  የወጣቱን ትውልድ ቀልብ መግዛት የቻለውን የራፕና የሂፕሆፕ ሙዚቃን መረጠ።
ክሪስ ሌቲ ሙዚቃ ሲመርጥ አርቲስት ለመሆን ወይም የራሱን የሙዚቃ ስራ ለማቅረብ አልነበረም። በሙዚቃው ዓለም የታወቁ አርቲስቶች እያዘጋጁ በሚያቀርቡት የሙዚቃ ቢዝነስ ውስጥ የራሱን ድርሻ ለማግኘት እንጂ። ህልሙንም ለማሳካት ማድረግ የሚችለውን ሁሉ ከማድረግ ወደ ኋላ አላለም።
ካሴቶችንና ሲዲዎችን በጎዳና በሚሸጥበት ወቅት ካዳበረው ልምድ በመነሳት ቀስ በቀስ “ቫዮሌተር” የሚል ስያሜ የሰጠውን የሙዚቃ አሳታሚና አከፋፋይ ቢዝነሱን በ1990 ዓ.ም ለማቋቋም በቃ። ከአንድ ዓመት በኋላም የ”ቫዮሌተር” እህት ኩባንያ የሆኑትን የአርቲስቶች አስተዳደር የክህሎት ማዳበሪያ፣ የማስታወቂና የሽያጭ ኩባንያዎችን ማቋቋም ቻለ።
ልዩ የአስተዳደር ችሎታውም እውቅ የራፕና የሂፓፕ ሙዚቃ አርቲስቶችን ቀልብ መማረክ ቻለ።
ክሪስ ሌቲ የሙዚቃውን የቢዝነስ ዓለም አሰራር ጠንቅቆ በማወቁና በትጋት መስራት በመቻሉ ትናንትን በኒውዮርክ አውራ መንገዶች የሙዚቃ ስራዎቻቸውን እያዞረ ሲሸጥላቸው የነበሩትን እውቅ የራፕና የሂፓፕ አርቲስቶች፣ የእነ ማሲ ግሬይና የእነ ኤል ኤል ኩል ጄን የሙዚቃ አልበሞች በራሱ ኩባንያ ለማሳተምና ለማከፋፈል በቃ።
ዛሬ የሙዚቃ ስራዎቻቸውን በማሳተምና በማከፋፈል ብቻ ሳይሆን የተለያዩ የስነጥበብና የሙዚቃ እንቅስቃሴዎቻቸውን  የሚያስተዳድርላቸው፣ የኮንሰርትና የማስታወቂያ ኮንትራቶችን የሚዋዋልላቸውና የሚመራላቸው እንዲሁም  የማስታወቂ ስራዎቻቸውን የሚያከናውንላቸው እውቅና ጀማሪ አርቲስቶች ቁጥር ቀላል አይደለም።
የትላንቱ “ችስታ” ካሴትና ሲዲ አዟሪ ክሪስ ሌቲ፤ ስራውን በማሳደግ ዛሬ የ3 ትላልቅ የቢዝነስ ኩባንያዎች ባለቤትና ገና በ24 ዓመቱ የተሳካለት ሚሊዮነር መሆን የቻለ ወጣት ነው።
በሀገራችንም ካሴትና ሲዲ አዙሮ በመሸጥ ንግድ ከተሰማሩት በርካታ ወጣቶች መካከል እንደ ክሪስ ሌቲ የራሳቸውን ትላልቅ ኩባንያ በማቋቋም ስኬታማ የሚሆኑ ወጣቶችን የማናይበት አንዳችም  ምክንያት የለም። ስኬት ዘርና ቀለም፣ቋንቋና ሃይማኖት፣ ሀገርና ድንበር  የላትም።
የላቀ ብቃት
ለላቀ ውጤት ቀርጠኛ ሁሉ። በተሰማራችሁበት የስራ ዘርፍ የላቀ ብቃት ለማሳየት ዛሬውኑ ቆርጣችሁ ተነሱ። የስራ መስኩ ምንም ይሁን ምን በዘርፉ ከተሰማሩት ምርጦች (አስር በመቶዎቹ) ተርታ ለመሰለፍ አልሙ። ይሄ ውሳኔ የህይወታችሁ ወሳኝ ምዕራፍ እንደሆነ አስታውሱ። በመረጡት ማናቸውም የስራ መስክ ባሳዩት የላቀ ብቃት ያልታወቁ ብዙ ስኬታማ ሰዎች የሉም።
አስታውሱ -ማንም ከናንተ የተሻለ ብልህ ወይም ብሩህ አይደለም። ዛሬ  ከምርጥ አስር በመቶዎቹ ተርታ ተሰልፈው የምታይዋቸው ሁሉ ሲጀምሩ ከተራዎቹ ዘጠና በመቶዎቹ ጎራ እንደነበሩ ልታውቁ ይገባል።
አሁን የላቀ ብቃት ላይ የደረሱ ስኬታማ ሰዎች በአንድ ወቅት እዚህ ግቡ የማይባሉ ተራ ሰዎች ነበሩ። አሁን በያዙት የሥራ ዘርፍ ግንባር ቀደሞቹ በአንድ ወቅት ከእነአካቴው በሌላ ሙያ ውስጥ የነበሩ ናቸው። እናም ሌላው ማድረግ የቻለውን እናንተም ማድረግ አይሳናችሁም።
ታላቁ የስኬት ህግ “ሕይወትህ የተሻለ የሚሆነው አንተ ራስህን የተሻለ ማድረግ ስትችል ብቻ ነው” ይላል። እናም በስራችሁ የላቀ ብቃት ለማሳየት ቁርጠኝነት ማሳየታችሁ የታላቅ ስኬት ቁልፍ ነው። የከበረ የራስ ግምት፣  የራስ አክብሮትና በራስ መመካት መሰረቱ እንደሆነም እወቁ።
በምትሰሩት ስራ የምር ልቃችሁ ስትገኙ ስለራሳችሁ የሚኖራችሁ ስሜት የተለየ ይሆናል። በተሰማራችሁበት የስራ ዘርፍ የስኬት ማማ ላይ መውጣታሁን ስትገነዘቡ፣ ለራሳችሁ ስብእና ላይ ብቻ ሳይሆን ከሌሎች ጋር በሚኖራችሁ ግንኙነት ላይም በጎ ተጽዕኖ ማሳረፋችሁ የተፈተነ ሀቅ ነው።
የሙያ ህይወታሁን በቅጡ ብታዳብሩትና በሚያስደንቅ ተዓምር መከወን ብትችሉ ለህይወታችሁ ታላቅ አወንታዊ ለውጥ የሚያጎናጽፋችሁ ቁልፍ ክህሎት ምን ይመስላችኋል?
በአንድ ጀምበር በሁሉም ነገር የተካናችሁ መሆን አትችሉም። ነገር ግን ህይወታችሁን በእጅጉ ሊቀይረው የሚችለውንና ሙሉ ልባችሁን ሰጥታችሁ የምታዳብሩትን አንድ ወሳኝ ክህሎት ማወቅ ትችላላችሁ። እስቲ ይሄን ተግባር እንደ ግብ ቅረጹት። በጽሁፍም አስፍሩት። ቀነ ገደብም አስቀምጡለት። ከዚያም እቅድ ንደፉ። በመጨረሻም በእያንዳንዱ ቀን በዚያ ዘርፍ የተሻለ ውጤት ለመቀዳጀት ተግታችሁ መስራት ጀምሩ። የላቀ ውጤት ለመቀዳጀት የምታሳዩት ቁርጠኝነት በህይወታችሁ ላይ በሚያመጣው ተአምራዊ ለውጥ ትደመማላችሁ። በዚህ ተግታችሁ ከቀጠላችሁም ወደ ሚሊየነርነት የሚያደርሰውን ጉዞ ጀምራችኋል ማለት ነው።
 (የታላላቅ ህልሞች” ከተሰኘው የኢዮብ ካሣና ሰለሞን ከበደ መፅሐፍ የተወሰደ፤ 2003)

Read 1651 times
Administrator

Latest from Administrator