Print this page
Sunday, 09 January 2022 00:00

አገራት የሱዳንን ጦር በአዲስ ጠ/ሚኒስትር ሹመት ጉዳይ አስጠንቅቀዋል

Written by 
Rate this item
(0 votes)

የሱዳኑ ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሃምዶክ ባለፈው እሁድ በፈቃዳቸው ስልጣናቸውን መልቀቃቸውን ተከትሎ፣ በብቸኝነት ስልጣኑን ተቆጣጥሮ የሚገኘው የአገሪቱ የጦር ሃይል፣ ሲቪሉንና ሁሉንም ባለድርሻ አካላት ባላሳተፈ መልኩ የራሱን አዲስ ጠቅላይ ሚኒስትር እንዳይሾም አሜሪካ፣ ኖርዌይ፣ እንግሊዝና የአውሮፓ ህብረት ማክሰኞ ዕለት ጥሪ ያቀረቡ ሲሆን፣ ይህን የሚያደርግ ከሆነ አገሪቱ ወደ ከፋ ቀውስና ብጥብጥ ልትገባ እንደምትችል ማስጠንቀቃቸውን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
የጦር ሃይሉ በተናጠል የራሱን አዲስ ጠቅላይ ሚኒስትር የሚሾምና ካቢኔ የሚያዋቅር ከሆነ የተቋማቱን ተቀባይነት ጥያቄ ውስጥ ከማስገባት ባሻገር አገሪቱን ወደ ከፋ ግጭትና ብጥብጥ ሊያስገባት እንደሚችል ነው በጋራ ባወጡት መግለጫ ያስጠነቀቁት፡፡
ሱዳን ትሪቢዩን በበኩሉ፤ የጦር ሃይሉ የቀድሞውን የአገሪቷ የገንዘብ ሚኒስትር ኢብራሂም አል በደዊን ወይም የቀድሞውን ተጠባባቂ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኦመር ዳሃብን በጠቅላይ ሚኒስትርነት ለመሾም ማሰቡ እየተነገረ ነው ሲል የዘገበ ሲሆን፣ በተለይ አል በደዊ ለሹመቱ እንደታጩ እንደተነገራቸውና እሳቸውም ህዝቡና ፖለቲከኞች ከደገፏቸው ሹመቱን እንደሚቀበሉ መግለጻቸውን እንደጠቆሙ አስነብቧል፡፡
ለሶስት አመታት የአገሪቱ የሽግግር መንግስት ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ያገለገሉት ሃምዶክ፣ ከሳምንታት በፊት በጦር ሃይሉ አዛዥ ጄኔራል አል ቡርሃን መሪነት በተካሄደ መፈንቅለ መንግስት ከስልጣናቸው ተነስተው በቁም እስር ላይ መቆየታቸውንና ወደ ስልጣን እንዲመለሱ መደረጉን ያስታወሰው ዘገባው፣ ባለፈው እሁድ ግን በአገሪቱ ፖለቲካ ላይ ተፅእኖ ለመፍጠርና የገቡትን ቃል መጠበቅ ባለመቻላቸው በፈቃዳቸው ስልጣን ለመልቀቅ መገደዳቸውን በቴሌቪዥን ማስታወቃቸውን አመልክቷል፡፡
የሃምዶክ ከስልጣን መልቀቅ #የጦር ሃይሉ የያዘውን ስልጣን ለሲቪሉ ይመልስ; የሚለውን ለወራት የዘለቀ ህዝባዊ ተቃውሞ ማባባሱንና የአገሪቱ ቀጣይ ዕጣ ፋንታ አሳሳቢ ሁኔታ ላይ መውደቁ መነገሩንም ዘገባው አመልክቷል፡፡
የሱዳን ተቃዋሚዎች #የጦር ሃይሉ ስልጣኑን ለሲቪል አስተዳደር ሙሉ በሙሉ ያስረክብ; የሚለውን ለወራት የዘለቀ ጥያቄ አንግበው አደባባይ የወጡ ሲሆን፣ በጄኔራል አልቡርሃን ቀጭን ትዕዛዝ የሚመሩ ወታደሮች ግን ላለፉት ቀናት በርካታ ተቃዋሚዎችን መግደላቸው ነው የተነገረው፡፡

Read 1305 times
Administrator

Latest from Administrator