Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 22 September 2012 11:17

ኢትዮጵያዊው ተመራማሪ በጃፓን ዩኒቨርስቲ

Written by 
Rate this item
(2 votes)

በደብረማርቆስ የተወለደው አበባው ደሴ፤ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ከደብረማርቆስ 2ኛ ደረጃ ት/ቤት እንዳጠናቀቀ ሃራማያ ዩኒቨርስቲ በመግባት የእጽዋት ሳይንስ አጥንቷል፡፡ የዩኒቨርስቲ ትምህርቱን ካጠናቀቀ በኋላ በደብረ ኤልያስ ወረዳ ግብርና ቢሮ ለአራት ወራት የሰራ ሲሆን ከዚያም፣ በኢትዮጵያ የእርሻ ምርምር ተቋም (ፓዌ) ውስጥ በተመራማሪነት ተቀጠረ፡፡ በፓዌ ለሦስት ዓመት ተኩል ያህል በሩዝ ላይ ምርምር አድርጓል፡፡ በመጨረሻም የጃፓን ዓለምአቀፍ ትብብር ኤጀንሲ (JICA) በሚሠጠው ነፃ የትምህርት ዕድል (ስኮርላርሺፕ) ተወዳድሮ በማሸነፍ ወደ ጃፓን አቀና፡፡ አሁን በቶክዮ ግብርና ዩኒቨርስቲ ትምህርቱን እየተከታተለ ይገኛል፡፡ በጃፓን የምትገኘው የአዲስ አድማስ ፀሃፊ ሂሮዬ ሺማቡኩሮ፣ ወጣቱን ኢትዮጵያዊ ተመራማሪ አበባው ደሴን እዚያው ጃፓን አግኝታው በትምህርቱና በምርምሩ፣ እንዲሁም በህይወቱ ዙሪያ አነጋግራዋለች፡፡ (ትርጉም ኢ.ካ)

በጃፓን የመማር ዕድሉን እንዴት አገኘህ?

በኢትዮጵያ የእርሻ ምርምር ተቋም ሳለሁ በሩዝ ላይ ምርምር አካሂድ ነበር፤ በአገሪቱ ብሄራዊ የሩዝ ፕሮጀክት ቀረፃ ላይም ተሳትፌያለሁ፡፡

በኢትዮጵያ አብዛኛው ህዝብ የሚመገበው ጤፍ ነው፤ በቅርቡ ግን ሩዝ ተወዳጅና የጤፍ አማራጭ ከሆኑ ምግቦች አንዱ እየሆነ መጥቷል፡፡ የምግብ እጥረትን ለመፍታት እንደመፍትሄ እየተቆጠረ ነው፡፡ የኢትዮጵያ መሬት ከፍተኛ መጠን ያለው የሩዝ ምርት የመስጠት አቅም አለው፡፡ ህዝቡ ግን ሩዝ ለማምረት የሚያስችል በቂ ክህሎት የለውም፡፡ የጃፓን ዓለም አቀፍ ትብብር ኤጀንሲ (JICA) የሩዝ እርሻ ምርታማነትን በማሳደግ ረገድ ድጋፍ በመስጠት ይንቀሳቀሳል፡፡ ይሄን ለማድረግ አንዱ መንገድ ደግሞ ኢትዮጵያውያን በሩዝ ላይ ምርምር እንዲያደርጉ ዕድል መስጠት ነው፡፡ እኔም በተሰጠው የስኮላርሺፕ ዕድል ተወዳድሬ አሸነፍኩ፡፡ አሁን በቶክዮ የግብርና ዩኒቨርስቲ ለመጀመሪያ ድግሪዬ እያጠናሁ ነው፡፡

ስለ ሩዝ ለማጥናት ለምን ጃፓንን መረጥክ?

ሩዝ የጃፓናውያን ባህላዊ ምግብ ነው፡፡ ሩዝ ለጃፓናውያን እንደ እንጀራ ማለት ነው፡፡ በዚህም የተነሳ ሩዝ የማምረት ከፍተኛ አቅምና ብቃት አላቸው፡፡ ከዚህ ጋር በተገናኘ በጃፓን የምማራቸውና የማጠናቸው በርካታ ጉዳዮች አሉ፡፡

ጃፓናውያንን እንዴት አገኘሃቸው?

በጣም ትጉህና ታማኝ ህዝቦች ናቸው፡፡ ጃፓናውያን እንደ ኢትዮጵያውያን ሁሉ አዛውንቶችን (ታላላቆችን) ያከብራሉ፡፡ በባቡር ወይም በአውቶብስ ውስጥ ለሽማግሌዎችና ለአሮጊቶች እንዲሁም ለነፍሰጡሮች ቅድምያ በመስጠት መቀመጫ ይለቃሉ፡፡

እንደ ኢትዮጵያውያን ግን ሰፊ ማህበራዊ ግንኙነት የላቸውም፡፡ ብዙ ትኩረት የሚሰጡት ለሥራቸው ነው፡ እኔ ለምሳሌ እዚህ አገር ስኖር የጐረቤቴን ማንነት አላውቅም፡፡ በኢትዮጵያ አዲስ ሰፈር ሲገባ ጐረቤቶቹ መጥተው ራሳቸውን ያስተዋውቃሉ፡፡ በአውቶብስ ወይም በባቡር ውስጥም ቢሆን ሰዎች እርስ በርስ ያወራሉ፡፡ እዚህ አገር ግን በአውቶብስም ሆነ በታክሲ ውስጥ የሚነጋገር የለም፡፡ ተሳፋሪዎች በፀጥታ ነው የሚጓዙት፡፡ በጉዞ ወቅት ጋዜጣ ወይም መፅሃፍ የሚያነቡ አሉ፡፡ በሞባይል የፅሁፍ መልዕክት (text message) የሚልኩ ተሳፋሪዎችም ይኖራሉ፡፡አንዳንዶቹ እንደውም እንቅልፋቸውን እየለጠጡ ነው የሚጓዙት፡፡ በኢትዮጵያ እኮ ፈፅሞ የማይተዋወቁ ሰዎች እንኳን እርስ በርስ ይነጋገራሉ፡፡

እኔ ያደግሁት በተለየ ባህል ውስጥ ነው፡፡ እናም የጃፓናውያን ዝምታ ብዙም አይመቸኝም፡፡ በኢትዮጵያ ብታዝኚ ወይም ብትደበሪ ከጓደኞችሽ ጋር ታወሪና ቀለል ይልሻል፡፡ በህይወቴ ለመጀመሪያ ጊዜ ብቸኝነት የተሰማኝ ጃፓን ከመጣሁ በኋላ ነው፡፡ ግን ይሁን … ብቻዬን አይደለሁም፤ ብዙ ጃፓኖችም እንደኔ ብቸኝነት የሚሰማቸው ይመስለኛል፡፡ በየዓመቱ 30ሺ ጃፓናውያን ለምን ራሳቸውን እንደሚያጠፉ የገባኝ አሁን ነው፡፡ ብቸኝነቱ እኮ ነው! በሌላ በኩል ሲዝናኑ ወይም ፓርቲ ሲወጡ ብዙ ቢራ ይጠጣሉ፤ ብዙም ያወራሉ፤ ከልክ በላይ ነፃ ይሆናሉ፡፡ እስካሁን ሊገባኝ ያልቻለው ይሄ ነገራቸው ነው፡፡

ጃፓኖቹ ትጉህ ሠራተኞችና ታማኞች እንደሆኑ ነግረኸኛል፡፡ ኢትዮጵያውያንስ?

በጥቅሉ ሲታይ ኢትዮጵያውያን ለሥራ ቁርጠኝነት የላቸውም፡፡ ምናልባት በደሞዛቸው ስለማይረኩ ይሆናል፡ በቢሮ ቁሳቁስ አለመሟላት ወይም ደግሞ የመስክ ቅኝት የሚያደርጉበት በቂ ተሽከርካሪዎች ባለማግኘትም ይሆናል … ግን የሥራ ቁርጠኝነት አይታይባቸውም፡፡

ለምሳሌ የጃፓን ፕሮፌሰሮች እስከ ምሽቱ አንድ ሰዓትና ሁለት ሰዓት ድረስ ሥራቸው ላይ ያመሻሉ፡፡ ለጃፓናውያን የቢዝነስ ሰዎች ደግሞ እስከ እኩለ ሌሊት ድረስ ሥራ ላይ መቆየት የተለመደ ነገር መሆኑን ሰምቻለሁ፡፡ ምናልባት ከማህበራዊ ህይወት ይልቅ ቢሮ ውስጥ መቀመጥን ስለሚመርጡ ይሆናል፡፡ ምክንያታቸውን በእርግጠኝነት ማወቅ አልችልም፡፡ ታማኝነትን በተመለከተ … ለምሳሌ የኪስ ቦርሳ ብትጥይ ወይም ቢጠፋብሽ የመገኘት ዕድሉ ከፍተኛ ነው፡፡ አንዴ ቦርሳዬ ጠፍቶብኝ የማላውቀው ሰው አግኝቶ ለሚመለከተው ክፍል ሪፖርት ማድረጉን አስታውሳለሁ፡፡

በኢትዮጵያ ድህነቱና ችግሩም ወደ ውሸትና ስርቆት ይገፋፋሻል፡፡ ሰዎች መብላት አለባቸው፤ ሥራ ግን የለም፤ ስለዚህ ማጭበርበርና መስረቅ ይኖራል፡፡

እስቲ የጃፓን ዩኒቨርሲቲዎችን ከኢትዮጵያ ጋር እያወዳደርክ ልዩነታቸውን ንገረኝ …

የሚያስተምሩት በእንግሊዝኛ ስለሆነ የመማሩን ሂደት አቅሎልኛል፡፡ የትምህርት አሰጣጣቸው ንድፈ ሃሳብ ላይ ብቻ ያተኮረ አይደለም፤ እንደውም የሚበዛው ተግባራዊ (Practical) ትምህርት ነው፡፡ ስለዚህ በጣም ደስ ይላል፤ በትኩረት ነው የምትማሪው፡፡

እኔ ክፍል ውስጥ 22 ተማሪዎች አሉ - 17 ጃፓናውያንና 5 የውጭ ዜጐች፡፡ የሚያስገርመው ነገር ጃፓናውያን የኢትዮጵያውያንን ያህል ለትምህርታቸው ትኩረት አይሰጡም፡፡

መምህሩ ቆሞ እያስተማረ ሁሉ ሊተኙ (ሊያንቀላፉ) ይችላሉ፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ አስተማሪ ሲያስተምር ብታንቀላፊ መምህሩ ተበሳጭቶ ሊቀጣሽ ይችላል፡፡ እዚህ ግን ተማሪው የሞባይል ጥሪ ለመመለስ ትምህርት አቋርጦ ከክፍል ይወጣል፡፡ እንደሚመስለኝ ጃፓናውያን እንደ ኢትዮጵያ ተማሪዎች ከማለፊያ ውጤት በላይ የማምጣት ጫና የለባቸውም፡፡

ለኢትዮጵያውያን ትምህርት የህይወት ዕጣ ፈንታቸውን የሚወስን ጉዳይ ነው፡፡ ለጃፓን ተማሪዎች ግን ሁኔታው የተለየ ነው፡፡ መሰረታዊ ፍላጐቶቻቸው ስለተሟላላቸው የሚያስጨንቃቸው ነገር የለም፡፡ የዩኒቨርስቲ ትምህርታቸውን ለማጠናቀቅ ማለፊያ ውጤት (Passing grades) ማምጣት ብቻ ይበቃቸዋል፡፡

አንተስ … እንደ ጃፓን ተማሪዎች ክፍል ውስጥ አንቀላፍተህ ታውቃለህ?

ኧረ በፍፁም! እኔ ሁሉንም የትምህርት ዓይነት በትጋት ነው የምከታተለው፡፡

በእረፍት ቀናት ጊዜህን በምን ታሳልፋለህ?

እዚህ አገር ከማውቃቸው ኢትዮጵያውያን ወይም የውጭ ዜጐች አሊያም ጃፓናውያን ጋር ወጥቼ እዝናናለሁ በእግር መዟዟርም በጣም ያስደስታል፡፡

እናም አንዳንዴ ዝም ብዬ በእግሬ እጓዛለሁ - ብቻዬን፡፡ ቤት ከሆንኩኝ የኢትዮጵያ ሬድዮና ቴሌቪዥን ፕሮግራሞችን በኢንተርኔት እከታተላለሁ፡፡ ወይም ደግሞ ቻት አደርጋለሁ፡፡ በኢትዮጵያ ካሉ ጓደኞቼና ቤተሰቦቼ ጋር በፌስ ቡክ እፃፃፋለሁ፡፡ ቤት ውስጥ ለብቻ መቀመጥ ግን ጥሩ አይደለም፤ የአገር ቤት ናፍቆት ይቀሰቅስብሻል፡፡

በጃፓን ስትኖር የገጠመህ ችግር አለ?

አንዱ ችግር ጃፓኖች እንግሊዝኛ አለመናገራቸው ነው፡፡ ከጠቅላላው የጃፓን ህዝብ 3 በመቶ ያህሉ ጃፓናዊ ብቻ እንግሊዝኛ በደንብ እንደሚናገር አንብቤአለሁ፡ አንዴ የሆንኩትን ልንገርሽ፡፡

ስኳር ለመግዛት ወደ ሱፐርማርኬት እሄድና ስኳር የሚመስል ነገር አገኛለሁ፡፡ ስኳር መሆኑን ስለተጠራጠርኩኝ በስፍራው ያገኘሁትን ሰው ሁሉ ጠየቅሁኝ፤ የሚመልስልኝ ግን አላገኘሁም፡፡ ስለዚህ ዝም ብዬ ገዛሁትና ወደ ቤቴ ተመለስኩኝ፡፡ ግን ስኳር አልነበረም፤ ጨው ነው፡፡ ሌላው ችግር … አንዳንድ ጃፓናውያን፤ በተለይ አዛውንቶቹ ለውጭ ዜጐች እንግዳ መሆናቸው ነው፡፡

አውቶብስ ውስጥ ከጐኔ ለመቀመጥ አየት ያደርጉኝና ወዲያው ሌላ ቦታ ፍለጋ ማማተር ይጀምራሉ፡፡ የዘርና የቀለም አድልዎ ማድረጋቸው አይደለም … በቃ ከውጭ ዜጐች ጋር ብዙ አልተለማመዱም፡፡

ለምን የተባለ እንደሆነ … በጃፓን ብዙ የውጭ ዜጐች ስለሌሉ ነው፡፡ ስለ ኢትዮጵያ የሚያውቁት በዕድሜ የገፉ ጃፓናውያን ብቻ ናቸው፡፡ ኢትዮጵያን የሚያውቋት በጀግናው አትሌት አበበ ቢቂላ አማካኝነት ነው፡፡ በዚህም የተነሳ እኔንም “እንደ አበበ ቢቂላ ጐበዝ ሯጭ ነህ?” ብለው ይጠይቁኛል፡፡

ባለፈው ዓመት የመሬት መንቀጥቀጥ (ሱናሚ) አደጋ ሲከሰት እዚሁ ነበርክ አይደል?

አዎ … በጣም አስፈሪ ነበር፡፡ የመሬት መንቀጥቀጥ አይቼ አላውቅም፡፡ ጃፓን በገባሁ በሳምንቴ ግን ትንሽ የመሬት መንቀጥቀጥ ተከስቶ ነበር፡፡ ከወር በኋላ ማርች 11 ደግሞ ያ አሰቃቂው ሱናሚ መጣ፡፡ እኔ በዩኒቨርስቲው 3ኛ ፎቅ ላይ ነበርኩ፡፡ ሁሉም ነገር እየተንቀጠቀጠና ከያለበት ስፍራ እየወደቀ ነበር፡፡ እኛ ጠረጴዛ ሥር ተሸሸግን፡፡ አንዳንዶቹ ሲያለቅሱ፤ እኔ እየፀለይኩ ነበር፡፡

ከጥቂት ጊዜ በኋላ ከህንፃው በሩጫ ወጥተን ወደ እግር ኳስ ስቴዲየሙ ሄድን፡፡ መንቀጥቀጡ ግን አልቆመም፡፡ እኔ ከዚያ በኋላ በህይወት እንደማልኖር አስቤ ነበር፡፡

ያን ዕለት ማታም እንቅልፍ እምቢ አለኝ፡፡ ቤተሰቦቼ ወደ አገር ቤት እንድመለስ ወትውተውኝ ነበር፡፡ ግን ወደ ኢትዮጵያ አልተመለስኩም፡፡ ጃፓኖቹ እየኖሩ አይደለም እንዴ … ቀኔ ከደረሰ የትም ብሆን አልተርፍም … ብዬ አሰብኩ፡፡ ሆኖም ቤተሰቦቼ እንዲረጋጉ በየቀኑ እደውልላቸው ነበር … እነሱ ከኔ በላይ ነበር የተጨነቁት፡፡

ህልምህ ምንድነው?

የምሰራው ምርምር “Cold Tolerance Rice Variety Selection” በሚል ሲሆን ለኢትዮጵያ እጅግ ተስማሚ የሆነውን የሩዝ ዓይነት ነው እያጠናሁ ያለሁት፡፡ ይሄን ግብ ማሳካት የቅርብ ጊዜ ህልሜ ነው፡፡

በኢትዮጵያ ከፍታማ አካባቢዎች ብዙ ሩዝ የማምረት ከፍተኛ አቅም አለ፡፡

ሆኖም የከፍታማ አካባቢዎችን ቀዝቃዛ አየር ሊቋቋም የሚችል የሩዝ ዓይነት አልተገኘም፡፡

ስለዚህ ትክክለኛውን የሩዝ ዓይነት ለመምረጥ እየሞከርኩኝ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ሩዝ ካመረትን የምግብ እጥረትን ለመቅረፍ ያግዘናል፡፡ ከሁሉም በላይ ሩዝ የምግብ ዋስትና የሚሰጥ እህል ነው ተብሎ ይታመናል፡፡

 

 

 

Read 4529 times Last modified on Saturday, 22 September 2012 11:28