Saturday, 08 January 2022 00:00

"ለትውልድ የሚተላለፍ ዘመን ተሻጋሪ ፓርቲ እንገነባለን"

Written by 
Rate this item
(0 votes)

የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ በአጭር ጊዜ ከፍፃሜ የሚደርስ የመቶ ሜትር ሩጫ ሳይሆን ትዕግስትን የሚፈታተን የማራቶን ሩጫን ይመስላል፡፡ በየትኛውም ሀገር ያለመስዋዕትነትና ያለ ትግል ዴሞክራሲ ተወልዶ አያውቅም፡፡ በሀገራችን ኢትዮጵያም በተደጋጋሚ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን ለማምጣት እልህ አስጨራሽ ትግሎች ተደርገዋል፡፡ ዴሞክራሲን ዕውን ለማድረግ የተለያዩ ዕድሎች የነበሩ ቢሆንም በተለያዩ ምክኒያቶች ከሽፈው በአምባገነን ሥርዓት ውስጥ ዘመናትን አሳልፈናል፡፡ በየዘመናቱ በፖለቲካ ስርዓቱ ውስጥ ተፅዕኖ ሊያሳድሩ የሚችሉ ግለሰቦች፤ በተለያዩ ጊዜያት የተፈጠሩ ቡድኖችና የተደራጁ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ሀገራዊ፣ አካባቢያዊና ዓለም አቀፋዊ ኩነቶችን በሚገባ ባልተረዳ ፖለቲካዊ አተያይ እንዲሁም አንድም በመንግሥት ጫና አልያም በውስጣቸው በነበረ ድክመት የመንግሥት ሥልጣን የያዘውን አካል ለመገዳደር  ባለመቻላቸው በአምባገነን ሥርዓት ውስጥ ለመኖራችን የበኩላቸውን አሉታዊ አስተዋፅዖ አበርክተዋል። አማራጭ በሌለ ጊዜ ሁሉ ስርዓቶች ተኪ እንደሌላቸውና ያለ እነሱ ሀገር የማትቆም እስኪመስላቸው ድረስ እንዳሻቸው ይሆናሉ፡፡ ስለዚህም የፖለቲካ ባህላችንን ለሀገራችን ህዝብ የዲሞክራሲ ጥማትና ፍላጎት ተገቢ መልስ የሚሰጥ ሆኖ ማደራጀት እጅጉን አስፈላጊ ነው፡፡
ተፎካካሪ ፓርቲዎች መንግስት የሚሰራውን ከመተቸት በተጨማሪ በሰፊው አማራጭ ያሉትን ሀሳብ ማቅረብ ሳይችሉ የቆዩበት ብዙ ምክንያቶች ቢኖሩም የራሳቸው የፓርቲዎቹ የአቅም ማነስና በዚህም ምክንያት አማራጭ ሀሳብ ለማመንጨት የሚችሉ በቂ ሰዎችን አለመያዝ አንዱና ዋነኛው መሆኑ ከኋላ ታሪካችን በቀላሉ ልንረዳው የምንችለው ሀቅ ነው፡፡ አንድ ፓርቲ መንግሥት ሲሆን ሊያደርጋቸው የሚችላቸውን ወሳኝ ሥራዎች ለመስራት አስቀድሞ ራሱን በመንግሥት ጫማ ውስጥ በማስቀመጥና በመንግሥታዊ ቁመና እና ቅርፅ ራሱን ማደራጀት መቻሉ ትልቅ ሚናን ሊጫወትለት እንደሚችል ከሌሎች ሀገር ልምዶች ማየት ይቻላል፡፡
የመድብለ ፓርቲ ሥርዓት መገንባትን እንደ ትልቅና ወሳኝ ቁምነገር ለሚወስድና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን ያለ ተፎካካሪ ፓርቲዎችና አማራጭ ሀሳቦች ማሰብ እንደማይቻል ለሚገነዘብ እንደ ኢዜማ ላለ ፓርቲ፣ የመንግሥት ሥልጣንን ቢይዝ ያሉትን አማራጭ ሀሳቦች ለሕዝብ የሚያሳይበት አደረጃጀትና መዋቅር መፍጠር መቻል በቀጣይ ምርጫ ከሀቀኛ ተፎካካሪ እንዲቆጠር ከማድረግም ባለፈ የሠለጠነ ዴሞክራሲያዊ ፖለቲካን ለሀገራችን የማስተዋወቅና ለማጎልበት ከፍተኛ በጎ አስተዋፅዖ ይኖረዋል፡፡
በተለያዩ ሀገራት ያሉ ተፎካካሪ ፓርቲዎች እነሱ የመንግሥት ሥልጣን ቢይዙ ምን ሊሠሩ እንደሚችሉና መንግሥት ባዋቀራቸው የአስፈፃሚዎች (በዋናነት ሚኒስትሮች) ምትክ ማንን ያደርጉ እንደነበር የሚያሳዩባቸው መንገዶች ያሉ ሲሆን ከእነዚህ መንገዶች አንዱ ትይዩ/ጥላ ካቢኔ (shadow cabinet) ማቋቋም ነው፡፡ መደበኛ የትይዩ ካቢኔ የተመሰረተው በእንግሊዝ ሀገር በ1960ዎቹ እ.ኤ.አ ሲሆን የተለያዩ ሀገራትም ጥቅም ላይ አውለውታል፡፡
እንዲህ ያለ ካቢኔ የሚመሰረተው፣ እውቅናውን የሚቸረውና ዋና ዋና ስራዎቹን የሚለይለት ማነው የሚለው እንደየሀገራቱ ተጨባጭ የሕግ ድጋፍ የሚወሰን ቢሆንም፣ ብዙዎች የሚስማሙበት ግን የሀገርን ዲሞክራሲያዊ ስርዓት ለማዘመን ትልቅ ሚና እንዳለው ነው፡፡ ከሀገራችን ወቅታዊና ሕጋዊ ሁኔታ አንጻርም የተፎካካሪ ፓርቲነት መዋቅር፣ ልምድ፣ ሰነዶችና መሰል የካበቱ አሠራሮች ባለመኖራቸው ፓርቲዎች ቁመናቸውን በዚህ ልክ ከፍ ማድረግ የሚችሉበት ዕድል ባለመኖሩ ትይዩ/ጥላ ካቢኔ ሳይሞከር ቆይቷል፡፡ በዚህም ምክንያት ተፎካካሪ ፓርቲዎች በአመዛኙ ምርጫ ሲቃረብ ካልሆነ በቀር ገንቢ ሚናቸውን ማሳየት ሳይችሉ፤ አማራጭ ሀሳቦቻቸውን ለሕዝብ በቋሚነት ሳያደርሱ እንዲሁም ራሳቸውን በእውቀትና በመንግስትነት ልምድ ሳያሳድጉ በመጨረሻው የምርጫ ዓመት ብቻ አቧራቸውን አራግፈው ከመንቀሳቀስ በቀር ቀጣይነት ያለው ሥራ ሳይሠሩ ቆይተዋል። በዚህም ምክኒያት ሀሳብን መሰረት አድርጎ የመፎካከር ፖለቲካ በሀገራችን ስር ሳይሰድ ጭንጫ ላይ እንደበቀለ ተክል የመጣው ንፋስ ሁሉ ሲወስደው ቆይቷል፡፡ ፓርቲዎች ራሳቸውን በጠንካራ መሰረት ላይ ለማኖርና በማንኛውም ወቅት ከአንድ ተፎካካሪ ፓርቲ የሚጠበቀውን አማራጭ ሀሳብ የማፍለቅ ሥራ ለመሥራት አማራጭ መዋቅራዊ መንገዶችን ማሰስና መተግበር ይጠበቅባቸዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ከተመሰረተበት ጊዜ አንስቶ የሀገራችንን የዲሞክራሲ ባህል ለማጎልበት የተለያዩ ስራዎችን ሲሰራ የቆየ ሲሆን፤ በምርጫ 2013ም በነበረው ጉልህ ተሳትፎ የሀገሪቱን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እንዲሁም ማኅበራዊ ችግሮችን ለመቅረፍ ይረዳሉ ያላቸውን የተለያዩ የፖሊሲ አማራጮችን ለህዝብ አቅርቦ ተወዳድሯል፡፡ በተጨማሪም ኢዜማ ከሕገ ደንቡ የሚቀዱ የዲሞክራሲ ስርዓትን ለማሻሻል የሚረዱ ፕሮግራሞችን ቀርፆ ሲንቀሳቀስ መቆየቱ ይታወቃል፡፡
በኢዜማ ሕገ ደንብ የመሪው መዋቅር የትይዩ ካቢኔ እንደሚያዋቅር ይደነግጋል፡፡ የሕገ ደንቡ አንቀጽ 7.1.9 ፓርቲው ስልጣን ላይ ካልወጣ መሪው፣ ዋና ወይም ዋና ያልሆነ የፓርላማ ተቃዋሚ ፓርቲ መሪ እንደሚሆን ይደነግጋል፡፡ በተጨማሪም ከስልጣኑ ጋር ተያይዞ የትይዩ ካቢኔ አባላቱንና ሌሎችንም የትይዩ ሚኒስትሮችና የተለያዩ የፓርቲውን የፓርላማ ኃላፊዎች እንደሚሰይም በአንቀጹ ተደንግጓል፡፡ በዚህም መሰረት የኢዜማ መሪ ብርሀኑ ነጋ (ፕሮፌሰር) በሕገ ደንቡ መሰረት፤ የመንግስትን ሥራዎች የሚከታተሉ የትይዩ ካቢኔ አባላት አዋቅረውና መድበው ወደ ሥራ ገብተዋል፡፡
የትይዩ ካቢኔ አባላቱ ከሚከውኗቸው ዋና ዋና ሥራዎች መካከል ረቂቅ ሕጎችን መተቸት፣ በፓርላማ ሀሳብ የሚያቀርቡት አባላትን መደገፍና ማሠልጠን፣ የእያንዳንዱን የሚንስትር መሥሪያ ቤቶች ሥራ መከታተል፣ የተፎካካሪ ፓርቲውን የልዩነት ነጥቦች በየወቅቱ ማስገንዘብ፣ መንግሥትን የሚገዳደር የፖሊሲ ንድፍ ማዘጋጀት፣ በእያንዳንዱ ዘርፍ የተሰየሙት የካቢኔ ሚኒስትሮች ቡድኖቻቸውን በማዋቀርና ኃላፊነታቸውን በማከፋፈል ፓርቲውን ተፎካካሪ ማድረግ ዋነኛ የሥራ ድርሻቸው ይሆናሉ፡፡
ትይዩ ካቢኔ የሚለው እሳቤ ከተዘረዘሩ ተግባሮቹ ባሻገር ከጀርባው ሌሎች ወሳኝ ውጤቶችን ይይዛል፡፡  በስልጣን ላይ ያሉት ሕግ አውጪዎች ተፎካካሪዬ ምን አለ የሚለውን እንዲያውቁ የሚያደርግ ሲሆን፤ ለመራጩ ደግሞ ለወቅታዊ ተግዳሮቶች ከአንድ በላይ መፍትሔ አለ የሚለውን ማሳየቱ ነው፡፡ ሌላኛው ውጤት ሀሳብ አልባ የሆነ ፉክክርን መቀየሩ ሲሆን ተፎካካሪ የሚባሉ ፓርቲዎችን ወደ አንድ በመሰብሰብ አላማቸውን ለማቀናጀት ዕድል ይሰጣል፡፡
የኢዜማ ትይዩ/ጥላ ካቢኔ በምንም መልኩ የተጠባባቂ መንግስትነትና የባለአደራነት ስብስብ እንዳልሆነ ሊሰመርበት ይገባል፡፡ አዎንታዊ ሚናውንም በመለየት የዴሞክራሲ መሣሪያ፣ የሰላምና የልማት መገልገያ አድርጎ ለውጥ አምጪ ማድረግ ይጠበቃል። የሚያሠራና በሕግ አውጪ ወይም በሕግ አስፈጻሚ ውስጥ ቀጥተኛ ሚና ተጫዋች ለማድረግም የሁሉንም ባለድርሻዎች ቅንነትና ዝግጁነት ይሻል፡፡
ረዥም ጉዞ በአንድ እርምጃ ይጀመራል እንዲሉ፣ ዛሬ አሀዱ ተብሎ የሚጀመር እንዲህ ያለው እንቅስቃሴ፣ ግብሩ የሚሰምረው በአዎንታዊነትና ለዴሞክራሲ በሚኖር ቀናዒነት ነው ብለን እናምናለን፡፡ የሀገራችንን የዲሞክራሲ ሂደት በፅኑ መሰረት ላይ ለመገንባት ሊተገበሩ የሚችሉ በጎ ልምምዶችን አጠናክረን በመቀጠል ለትውልድ የሚተላለፍ ከአንድ ምርጫ የዘለለ ፓርቲ እንገነባለን፡፡       

Read 891 times