Saturday, 08 January 2022 00:00

የአማራ ክልል በህወኃት ወራሪ ሃይል የወደሙ ንብረቶችን የሚያጠና ኮሚቴ አቋቋመ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

በተጎጂዎች ስም እርዳታ የሚሰበስቡ ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ አሳስቧል
  
  በአማራ ክልል በህወኃት ወራሪ ሃይል በንብረቶች ላይ የደረሰውን ዝርፊያና ውድመት የሚያጠና ኮሚቴ የተቋቋመ ሲሆን በተጨማሪም የወደመውን የሚተካና የመልሶ ማቋቋም ስራዎችን በበላይነት የሚሰራ ኮሚቴም ተቋቁሟል፡፡
የህወኃት ወራሪ ሃይል በአማራ ክልል በቆየባቸው ጊዜያት ንብረት ከማውደምና ከመዝረፍ ባለፈም በተጠና መልኩ ሰነዶችንና የተለያዩ ማስረጃዎችን የማጥፋት ተግባር መፈፀሙም ተጠቁሟል፡፡
የክልሉ መንግስት በምክትል ርዕሰ መስተዳደር ማዕረግ፣ የአማራ ክልል ማህበራዊ ጉዳዮች ክላስተር አስተባባሪ አቶ ስዩም መኮንን ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፤ የህወኃት ሃይል በአማራ ክልል የፈፀማቸውን ውድመቶች በሙሉ በአንድ የመረጃ ቋት ስር ለማሰባሰብ እንዲረዳ የሚያጠና ግብረ ሃይል መቋቋሙን ነው ያመለከቱት፡፡
በክልሉ ከሚገኙ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት መካከል የደሴ፣ ወልዲያና መቅደላ ዩኒቨርስቲዎች ከፍተኛ ውድመት እንደደረሰባቸው የጠቆመው የክልሉ መንግስት፤ በአጠቃላይ ወራሪ ቡድኑ ከሰኔ 2013 ጀምሮ በክልሉ ደቡብና ሰሜን ጎንደር፣በሰሜንና ደቡብ ወሎ፣በሰሜን ሸዋ፣ በኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን፣ በደሴና ኮምቦልቻ ከተሞች በቢሊዮን የሚገመት ንብረት መዝረፉንና ማውደሙን አስታውቋል፡፡
በአሁኑ ወቅት በክልሉ በጥቃቱ የተፈናቀሉ ዜጎችን መልሶ የማቋቋምና የመደገፍ ተግባር የሚያከናውን ግብረ ሃይል መቋቋሙ የተገለፀ ሲሆን ከዚህ ግብረ ሃይል ውጪ በተጎጂዎች ስም ግለሰቦች ማንኛውንም ገንዘብ ከማሰባሰብ እንዲቆጠቡ የክልሉ መንግስት አሳስቧል፡፡


  

Read 7330 times