Sunday, 09 January 2022 00:00

6.4 ሚ. ኢትዮጵያውያን በድርቅ ምክንያት ለምግብ እጥረት ተዳርገዋል ተባለ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

በአዲሱ የ2022 የፈረንጆች ዓመት 6.4 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን በድርቅ ምክንያት ለምግብ እርዳታ ጠባቂነት መዳረጋቸውን የዓለም ምግብ ፕሮግራም አስታውቋል፡፡
ባለፈው ክረምት ማግኘት የሚገባቸውን ዝናብ ባለማግኘታቸው ለድርቅ ተጋልጠዋል የተባሉት የሃገሪቱ አካባቢዎች የሶማሌ ክልል  ምስራቅና ደቡብ ኦሮሚያ መሆናቸውም በሪፖርቱ ተጠቁሟል፡፡
በእነዚህ አካባቢዎች በ2014 ወይም በፈረንጆች 2022 ለምግብ እጥረት ተጋልጠዋል የተባሉት 6.4 ሚሊዮን ዜጎች ሲሆኑ 3 ሚሊዮኑ በሶማሌ ክልል፣ 2.4 ሚሊዮኑ በምስራቅ ኦሮሚያ  እንዲሁም 1 ሚሊዮኑ በደቡብ ኦሮሚያ አካባቢ  እንደሚገኙ ነው ሪፖርቱ ያመለከተው፡፡
በአሁኑ ወቅት መንግስትና የሠብአዊ ድጋፍ  አድራጊ ድርጅቶች ለድርቅ ተጎጂ ዜጎች የምግብ እርዳታ እያቀረቡ ቢሆንም፣ አቅርቦቱ በቂና አስተማማኝ አለመሆኑን  ሪፖርቱ ጠቁሟል፡፡  በሶማሌ ክልል ሰብል አምራች በሆነው የፋፈን እና ሲቲ ዞን ይጠበቅ ከነበረው የበቆሎና የማሽላ ምርት 70 በመቶው በድርቁ ምክንያት መውደሙን ያመለከተው ሪፖርቱ፤ 30 በመቶ የቀይ ሽንኩርትና የቲማቲም ምርትም በድርቁ ምክንያት ማግኘት አልተቻለም ብሏል፡፡
በምስራቅና ደቡብ ኦሮሚያ ይጠበቅ ከነበረው ምርት በተመሳሳይ 70 በመቶ ያህሉን ማግኘት እንዳልተቻለ በሪፖርቱ የተመለከተ ሲሆን በድርቁ ተጠቂ በሆኑ የሶማሊያና የኦሮሚያ አካባቢዎች ከ267 ሺህ በላይ የቁም  እንስሳት ህይወታቸውን ማቆያ በማጣታቸው መሞታቸውም ተመልክቷል፡፡
በዚህ ድርቅ ምክንያት የትምህርትና ጤና ተቋማት ተገቢውን አገልግሎት መስጠት እንደተሳናቸው ያወሳው ሪፖርቱ፤ በሶማሌ ክልል 99 ሺህ፣ በሁለቱ የኦሮሚያ አካባቢዎች ደግሞ 56 ሺህ በድምሩ 155 ሺህ ያህል ተማሪዎች ትምህርት ቤቶች በመዘጋታቸው ከትምህርት ገበታ ውጪ መሆናቸውን አመልክቷል፡፡
በድርቅ በተጠቁ የሶማሌ ክልል 93 ወረዳዎችና ስድስት ዞኖች ውስጥ የሚገኙ ከ813 ሺህ በላይ ህፃናት ለአልሚ ምግብ እጥረት መጋለጣቸውንም ሪፖርቱ ጠቁሟል።

Read 7592 times