Sunday, 09 January 2022 00:00

በአማራና አፋር ክልሎች የተፈጸሙ ግድያዎችና የሰብአዊ መብት ጥሰቶች

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

የኢትዮጵያ ሠብአዊ መብቶች ጉባኤ (ኢሠመጉ)፤ ከዓመት በፊት በማይካድራ ስለተፈጸመው ጭፍጨፋና ከሰኔ 2013 ጀምሮ የህወኃት ታጣቂ ሃይሎች በአማራና አፋር ክልል በወረራ ይዘዋቸው በነበሩ አካባቢዎች የተፈፀሙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን  የተመለከቱ ሪፖርቶች ይፋ አድርጓል፡፡
ከዓመት በፊት  በማይካድራ ሣምሪ የተሰኘው የህወኃት መንግስታዊ መዋቅር ያደራጃቸው ገዳይ ቡድኖች፣ ትግርኛ ቋንቋ መናገር የማይችሉትን እየለዩ በፈፀሙት ጭፍጨፋ ከ1100 በላይ ንፁሃንን መጨፍጨፋቸውን ኢሠመጉ ለወራት ያህል ያካሄደው የምርመራ ውጤት ያመለከተ ሲሆን የህወኃት ታጣቂዎች ወረራ በፈፀሙባቸው የአማራና የአፋር አካባቢዎች ደግሞ ከ913 በላይ ንፁሃን በተናጥልና በጅምላ መገደላቸውን ጠቁሟል፡፡
በህወኃት ሃይሎች የተፈፀሙት እነዚህ ጭፍጨፋዎች በዋናነት ዘርን ለይቶ ማጥቃትን መሰረት ያደረጉ፣ ጭካኔ የተሞላባቸውና በሰብአዊነት ላይ የተፈፀሙ ከባድ ወንጀሎች መሆናቸውንም ሪፖርቱ አመልክቷል፡፡
በማይካድራ ጥቃቱ ከመፈፀሙ አንድ ሳምንት አስቀድሞ በከተማዋና በዙሪያዋ የሚገኙ የአማራ ተወላጆችን “መታወቂያ ልንሰጣችሁ ነው” በማለት እንዲመዘገቡ በማድረግ በየቦታው እየተንቀሳቀሱ የማጣራት ስራ መሰራቱን፣ በዚህ ወቅትም ትግርኛ የማይናገሩ ሁሉ ተለይተው መመዝገባቸውን ሪፖርቱ ያትታል፡፡
በሁኔታው ስጋት የገባቸው ሰዎች ከአካባቢው ለመሸሽ ቢሞክሩም፣ በትግራይ ልዩ ሃይልና ሚሊሻ መንገዶች በመዘጋታቸው አስቀድመው ማምለጥ እንዳልቻሉም ተመልክቷል፡፡
ጥቃቱን እንዲፈፅሙ የተመለመሉ የትግራይ ተወላጆችም በወቅቱ መሳሪያ እንዲታጠቁና የመሳሪያ አጠቃቀም ስልጠና እንዲወስዱ ይደረግ እንደነበር፣ ይህም ረዘም ላለ ጊዜ መከወኑን ያተተው ሪፖርቱ፤ ስልጠናው ነሐሴ 2012 ዓ.ም እና ጥቅምት 2013 ዓ.ም እንደተሰጠ አመልክቷል፡፡ ይህም አስቀድሞ የታቀደ ጉዳይ መሆኑን ይጠቁማል ተብሏል፡፡
በዚህ መልኩ ዝግጅት ከተደረገ በኋላ ጥቃቱ በተፈፀመበት ጥቅምት 30 ቀን 2013 ዓ.ም  የትግራይ ልዩ ሃይልና “ሳምሪ” የተሰኘው ቡድን፣ ማንም ሰው ከቤት እንዳይወጣ ትዕዛዝ መስጠታቸው በምርመራው ተረጋግጧል፡፡ በእለቱም ወጣቶቹ (ሳምሪ) በተለያዩ የከተማዋ አካባቢዎች ሲጨፍሩ እንደነበርና በአንዳንድ አካባቢዎች ከቀኑ 5 ሰዓት ጀምሮ በአብዛኛው የአማራ ተወላጆች በሚኖሩበት ልዩ ስሙ “ግምብ ሠፈር” በሚባለው አካባቢ ደግሞ ከቀኑ 9 ሰዓት እስከ ምሽቱ 2 ሰዓት የትግራይ ተወላጆች መሆን አለመሆናቸውን ለመለየት የሰዎችን መታወቂያ በማየት እንዲሁም በትግርኛ በማነጋገር መቻል አለመቻላቸውን በማረጋገጥ ጥቃቱን ማድረስ እንደጀመሩ የምርመራ ግኝቱ ያመለክታል፡፡
በወቅቱ ጥቃቱን የፈፀሙት በገጀራ፣በጩቤ፣በመጥረቢያና ገመድ የመሳሰሉ መሳሪያዎችን በመጠቀም መሆኑንና ዒላማ ያደረገውም በአብዛኛው ወጣት ወንዶችን መሆኑን፣ ሴቶች በአብዛኛው አስገድዶ መደፈር እንደተፈፀመባቸው፣ የሟቾችን አስክሬንም በትራክተር  በመጫን ከከተማዋ ውጪ ባሉ ገደላማ ቦታዎች እየወሰዱ በጅምላ  ይደፏቸው እንደነበር ተጠቁሟል፡፡
“ሳምሪ” የተሰኘው የወጣቶች ቡድን ጥቃቱን ሲፈፅም የትግራይ ልዩ ሃይልና ሚሊሻ ሽፋን መስጠቱን እንዲሁም በአካባቢው የሚኖሩ የትግራይ ባለሃብቶች ለዚሁ ጭፍጨፋ የሚውል የጦር መሳሪያና ሌሎች ቁሳቁሶችን ያከፋፍሉ እንደነበር ሪፖርቱ አትቷል፡፡
ከማይካድራው በተጨማሪ ይህ መሰሉ ጥቃት በሁመራና ዳንሻ አካባቢም መፈፀሙን የጠቆመው ሪፖርቱ፤ በዚህም ጥቃት በአጠቃላይ ከ1100 በላይ ሲገደሉ፣ ህጻናትም የድርጊቱ ሰለባ መሆናቸውን አመልክቷል። በተጨማሪም ከ122 በላይ ሰዎች የተለያየ መጠን ያለው የአካል ጉዳት  የደረሰባቸው ሲሆን ከ20 በላይ ሴቶች በቡድን አስገድዶ መደፈር ተፈፅሞባቸዋል ይላል - ሪፖርቱ፡፡
በአጠቃላይ በማይካድራና አካባቢው የተፈፀመው ጥቃት በሰብአዊነት ላይ የሚፈፀም ወንጀል፣የጦር ወንጀልና የዘር ማጥፋት  ክሶችን ሊያደራጅ የሚችል እጅግ ጭካኔ የተሞላበት ድርጊት መሆኑን ኢሠመጉ በሪፖርቱ አመላክቷል፡፡
የተፈፀመውን ጥቃት ተከትሎ መንግስት የህብረተሰቡን ስነ ልቦና የሚጠግንና የሰብአዊ መብቶችን የሚያረጋግጡ ዘላቂና ጊዜያዊ መፍትሔዎችን ሊያስቀምጥ እንደሚገባ በምክረ ሃሳቡ ያስቀመጠው የኢሰመጉ ሪፖርት፤ ድርጊቱ መጠነ ሰፊ እንደመሆኑ ድጋሚ በገለልተኛ አካል ጥልቅ ምርምር እንዲደረግ እንዲሁም የአካባቢው የፀጥታ መዋቅር ከየትኛውም አይነት ፖለቲካዊ ውግንና ነፃ በሆኑ ለህዝብ በወገኑ አካላት እንዲመራ፣ አጥፊዎችም በግልፅ ለፍርድ እንዲቀርቡ ጠይቋል፡፡
የአማራ እና የአፋር ክልሎች ሰቆቃ
ኢሰመጉ ሌላው ትኩረት አድርጎ ምርመራ እያከናወነ ያለው የህወኃት ወራሪ ሃይል ባለፉት አምስት ወራት ገደማ በአማራና አፋር ክልሎች ባደረሳቸው ጥቃቶች የተፈጸሙ ኢ-ሰብአዊ ድርጊቶችና ውድመቶችን የተመለከተ ነው፡፡ ይህ የምርመራ ተግባር በሂደት ላይ ያለ ቢሆንም፣ የቅድመ ምርመራ ሪፖርቱን ግን ከሰሞኑ ይፋ አድርጓል፡፡
የኢሰመጉ የምርመራ ባለሙያዎች ከታህሳስ 8 እስከ 15 ቀን 2014 ባለው ጊዜ ውስጥ በአፋር ክልል (ጭፍራ፣ሚሌ፣ ቀበሌ 50፣ ጎማያ፣ሰመራ እና በርታ)፤ በደቡብ ወሎ (ደሴ፣ሃይቅ፣ ኮምቦልቻ እና ቦሩ ሜዳ) በሰሜን ሸዋ (ሸዋ ሮቢት፣ አጣዬ፣ ካራ ቆሬ፣ ማጀቴ፣ እና መኮይ) በአማራ ክልል የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን (ከሚሴ ጨፋ ሮቢት እና ሰምበቴ)፣በደቡብ ጎንደር እና ሰሜን ጎንደር በመዘዋወር የምርመራ ስራ ማከናወናቸው ተመልክቷል፡፡
ኢሠመጉ ምርመራ ባከናወነባቸው  በእነዚህ አካባቢዎች እስካሁን በተገኙ መረጃዎች፣ ከ913 በላይ ንጹሃን መገደላቸውን፣ ከ513 በላይ መቁሰላቸውን እንዲሁም ከ65 በላይ ሴቶች በቡድን አስገድዶ መደፈር እንደተፈጸመባቸው አመልክቷል፡፡
በዚህ ጥቃት ከ656 ሺህ በላይ ዜጎች ከቀያቸው መፈናቀላቸውን፤ ከ130 በላይ የሚሆኑ የመንግስትና የግል የህክምና ተቋማት መውደማቸውን፤ከ204 በላይ የትምህርት ተቋማት ሙሉ በሙሉ መውደማቸውን ሪፖርቱ ጠቁሟል፡፡ በአማራ ክልል በትምህርት ተቋማት ላይ የደረሰው ውድመት ከ11 ቢሊዮን ብር በላይ ሲገመት፣ በአፋር ክልል ደግሞ ከ1.1 ቢሊዮን ብር  በላይ ተገምቷል፡፡
በጥቃቱ በአጠቃላይ በመንግስት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ቢሮዎች ላይ ከዘጠኝ ቢሊዮን ብር በላይ የተገመተ ውድመት መድረሱንም ሪፖርቱ ጠቁሟል፡፡ በሰዎች ህይወት ንብረትና በአጠቃላይ የደረሱ ውድመቶች አሃዝ በቀጣይ በሚደረጉ የምርመራው ሂደቶች ሊጨምሩ እንደሚችሉም ኢሠመጉ በቅድመ ሪፖርቱ አስቀምጧል፡፡
በዚህ ጥቃት የተፈናቀሉ በአፋጣኝ ወደ ቀያቸው ተመልሰው እንዲቋቋሙ ሁሉም ርብርብ እንዲያደርግ፣ጥቃት አድራሾች በህግ ተጠያቂ እንዲደረጉ እንዲሁም በአካባቢዎቹ የሚደረጉ ድጋፎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ኢሠመጉ ጥሪ አቅርቧል፡፡

Read 7580 times