Sunday, 09 January 2022 00:00

የንጉሱ ቁንዳላ - ከአዲስ አበባ እስከ ጎንደር

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(0 votes)

በ13 ዓመታት የንግስና ዘመናቸው በዘመነ መሳፍንት ቅርጫ ሆና የተበጣጠሰችውን አገራቸውን አንድ ለማድረግና ጠንካራ ማዕከላዊ መንግስትን ለመመስረት ከላይ እታች ሲኳትኑ ኖረዋል። በኢትዮጵያ ዘመናዊ የመንግስት ስርዓት እንዲስፋፋ፣ አርሶአደሩም ከምርቱ ተጠቃሚ እንዲሆን ወታደሩም፣ ቀዳሹም በደሞዝና በስርዓት እንዲመራ ፈር የቀየሱ ናቸው- ዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ (መይሳው ካሳ)።
ሀገራቸውን አንድ ለማድረግ ብቻቸውን ሲንከራተቱ በነበረበት ጊዜ በጀነራል ናፒር የተመራና እስከ አፍንጫው የታጠቀው የእንግሊዝ ጦር ንጉሱን ለመግጠም መቅደላ የደረሰው በ1860 ነበር። ይህን ጊዜ “እጅህን ስጥ” ሲባሉ፣ ሽጉጣቸውን ጠጥተው እንግሊዝን ለኪሳራ የዳረጉትና በመስዋዕትነታቸው የሀገር ክብር ያሳዩት ዳግማዊ አጤ ቴዎድሮስ፤ ታሪካቸውን በወርቅ ቀለም በድምቀት አጽፈው እስከ ዛሬም ከ150 ዓመታት በላይ በሀገራቸውና በህዝባቸው ልብ ውስጥ ነግሰው ኖረዋል፤ ወደፊትም ይኖራሉ።
አጼ ቴዎድሮስ ሚያዚያ 6 ቀን 1860 ራሳቸውን በክብር በሰውበት ጊዜም፡-
መቅደላ አፋፉ ላይ ጩኸት በረከተ
የሴቱን አናውቅም
ወንድ አንድ ሰው ሞተ
ማረክን እንዳይሉ ሰው የለ በእጃቸው
ገደልን እንዳይሉ ሞተው አገኟቸው
 ምን አሉ እንግሊዞች ሲገቡ አገራቸው
 ለወሬ አይመቹም ተንኮለኛ ናቸው
… ስትል ምንትዋብ የተባለች በንጉሱ ቤተሰቦቿን ያጣች ሴት ነበረች ስንኝ የቋጠረችላቸው።
በጀነራል ናፒር ይመራ የነበረው የእንግሊዝ ጦር በ200 በቅሎና በ18 ዝሆን የቻለውን ያህል ዘርፎ ከወሰዳቸው ቅርሶቻችን በተጨማሪ ከአስክሬናቸው ላይ ፀጉራቸውን ቆርጦ መውሰዱም ይታወቃል።
በወቅቱ ቁንዳላቸውን ቆርጦ የወሰደው የእንግሊዝ ወታደር መቶ አለቃና ሰዓሊ ፍራንክ ጀምስ እንደሆነ የሚያወሱት የታሪክ መዛግብት፤ መቶ አለቃው አስክሬናቸው ቃሬዛ ላይ እንዳለ ንድፍ በሚስልበት ጊዜ ቁንዳላቸውን ቆርጦ እንደወሰደው ይጠቁማሉ። የዚህ ገናና ንጉስ፣ ቁንዳላ ለአንድ መቶ አመታት በፍራንክ ጀምስ ቤተሰብ እጅ ከቆየ በኋላ እ.ኤ.አ በ1959 ዓ.ም ይህ ቤተሰብ የንጉሰ ነገስቱን ቁንዳላ እንግሊዝ ለንደን ከተማ ለሚገኘው ብሔራዊ የጦር ሙዚየም (ናሽናል አርሚ ሙዚየም) አስረከበ።
ይህ የክብር፣ የአንድነትና የሉአላዊነት ምልክትና  የአፄው የሰውነት አንድ ክፍል የሆነው ቁንዳላ፤ በለንደኑ ብሔራዊ የጦር ሙዚየም ለ60 ድፍን ዓመታት በክብር ተቀምጦ ቆየ። የኢትዮጵያ መንግስት ከእንግሊዝ መንግስት ጋር ባደረገው ውይይት፣ ምክክርና ጠንካራ የዲፕሎማሲ ስራ የእንግሊዝ መንግስት የንጉሰ ነገስቱ ቁንዲላ ወደ ሀገሩ፣ ወደ ክብሩ እንዲመለስ መፍቀዱን አበሰረ። እነሆ መጋቢት 11 ቀን 2011 ዓ.ም ቁርጥ ቀንም ሆነ።
የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር በነበሩት ሂሩት ካሳው (ዶ/ር) የሚመራው ልዑክ ቡድን ወደ እንግሊዝ አቀና። ሚኒስትሯን ጨምሮ በአገራቸው የሰንደቅ ቀለም ያሸበረቀ የሀበሻ ቀሚሳቸውን ያደረጉ ውብ ወይዛዝርትና  ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት በለንደኑ ብሄራዊ የጦር ሙዚየም ታድመው የንጉሳቸውን ቁንዳላ በክብር በባህልና ቱሪዝም ሚኒስትሯ በኩል ተረክበው፣ መጋቢት 11 ቀን 2011 ዓ.ም ወደ እናት ሀገራቸው ተመለሱ።
ይህ ከሆነ ከሁለት ዓመት ተኩል በኋላ የንጉሱ ሌላ የክብር መገለጫ ቀን ደረሰ። ታህስ 24 ቀን 2014 ዓ.ም። ከለንደን መጥቶ ብሄራዊ ሙዚየም በክብር የተቀመጠው የዳግማዊ አጼ ቴዎድሮስ ቁንዳላ ሌላ አንድ ጉዞ ይቀረው ነበረ፤ የክብር፣ እንደገና የመወለድና የመንገስ ጉዞ። ጉዞው ወደ ትውልድ አካባቢያቸው ወደ ንግስናቸው አምባ፣ ወደ ጎንደር ከተማ ነበር። የጎንደር ከተማ አስተዳደር የንጉሱን ቁንዳላ ወደ ጎንደር  ሙዚየም አስገብቼ ለእይታ ክፍት ላደርግ ነው ብሎ ብዙም አለፈፈም። ነገር ግን የንጉሱ ታሪክና ግርማ ሞገስ ለአገር ያስቀመጡት የአንድነት ማጠንጠኛ የነፍስ ዋጋ፣ አሁንም ከ154 ዓመታት በኋላ አፍ አውጥቶ ይናገራል።
ታዋቂ ሰዎች፣ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት፣ የጎንደር ከተማ ከንቲባ ተወካይ፣ የባህልና ቱሪዝም መምሪያ ሃላፊዎች፣ ከያኒን የሚዲያ አካላት ባለፈው እሁድ ታህሳስ 24 ማልደው ብሄራዊ ሙዚየም ተገኝተዋል።
“የቴዎድሮስ ራዕይ” በተሰኘው ተውኔት ዳግም አጼ ቴዎድሮስን ያየናቸው እስከሚመስለን ድረስ አቅላችንን የሚያስተን ተዋናይ ሱራፌል ተካ፤ ከነሹሩባውና ከነጃኖው፣ የተዋበችን ገፀ ባህሪ ተላብሳ ትተውን የነበረችውና በቅርቡ ከአሜሪካ ቆይታዋ የተመለሰችው ተዋናይት ብሌን ማሞ ደግሞ በጎንደር ሹሩባና ቀሚስ ተውባ ከግራና ከቀኝ የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን ም/ዋና ዳይሬክተር አበባው አያሌው (ረ/ፕ) ደግሞ በአረንጓዴ ቢጫ ቀይ ባንዲራ የተሸፈነውን የንጉሱን ቁንዳላ የያዘ ሳጥን ይዘው  በመሀል ሆነው፣ ከብሔራዊ ሙዚየም ብቅ ሲሉ ከሙዚየሙ ቅጥር ግቢ ውጭ በተጠንቀቅ የቆመው የፌደራል ማርቺንግ ባንድ በኢትዮጵያዊ ጣዕመ ዜማ ሲያጅበው፣ የአምስት ኪሎን አስፋልት ግራና ቀኝ ግጥም አድርጎ የሞላው የአዲስ አበባ ነዋሪ እልልታና ፉጨት በአንድ ለይ ተደምሮ የቁንዳላቸው ሽኝት ሳይሆን ንጉሰ ነገስቱ ዳግም የነገሱ ይመስል ነበር።
የጎንደር ከተማ አስተዳደር ቀደም ብዬእንዳልኩት ቁንዳላውን ወስዶ በጎንደር ሙዚየም ለእይታ ክፍት ለማድረግ ማቀዱን ብዙ ባይለፍፍም፣ ከብሔራዊ ሙዚየም እስከ አራት ኪሎ የአርበኞች ሀውልት በትንሹ ከ300 ሺህ ሰው በላይ ለአሸኛኘት መውጣቱ ተነግሯል።
ከብሔራዊ ሙዚየም በአባት አርበኞች ተይዞ እስከ አራት ኪሎ በእግር ጉዞ ከተደረገ በኋላ በአደባባዩ ላይ አቶ አገኘሁ ተሻገር- የፌደሬሽን ም/ቤት አፈጉባኤ፣ የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል፣ የአዲስ አበባ ከተማ ም/ከንቲባ አቶ ጃንጥራር አባይ፣ የጎንደር ከተማ ከንቲባ ተወካይና ሌሎቹም የቁንዳላውን ወደ ጎንደር መሸኘት አስመልክተው ንግግር ካደረጉ በኋላ ልክ 4፡45 ላይ ቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ድረስ በህዝብ ታጅቦ ተሸኝቶ ከሰዓት በኋላ ጎንደር ገብቷል።
የጎንደር ከተማ ህዝብ ከከተማው ከ16 ኪ.ሜ በላይ ርቀት ካለው ከጎንደር አፄ ቴዎድሮስ አየር ማረፊያ እስከ መሃል ፒያሳ ቴዎድሮስ አደባባይ ድረስ ከረፋዱ 4፡00 ጀምሮ የቁንዳላውን መምጣት ሲጠባበቅ ውሎ፣ በእልልታ በሆታና በደስታ ተቀብሎ፣ የአፄ ቴዎድሮስ አደባባይ የጥምቀት በዓል አስመስሎት ነበር። አቀባበሉን አስመልክቶ በጎንደር ከተማ ቴዎድሮስ አደባይ እስከ ምሽቱ አንድ ሰዓት የዘለቀ ኪነጥበባዊ የታሪክ ነገራ፣ ፉከራ፣ ሽለላና በርካታ ታሪካዊ ክንውኖች ተካሂደው ከንጉሱ ቁንዳላ ጋር ከለንደን ብሄራዊ የጦር ሙዚየም የመጡት የንጉሱ ጋሻና ጦር፣ ጎራዴና የፀሎት መጽሐፍቶቻቸው በክብር ወደ ጎንደር ሙዚየም የገቡ ሲሆን በቅርቡም ለእይታ ክፍት ይሆናሉ ተብሏል።
በዕለቱ ከአዲስ አበባ ብሔራዊ ሙዚየም እስከ ጎንደር ቴዎድሮስ አደባባይ በተካሄደው የአሸኛኘትና የአቀባበል ስነስርት ላይ፡-
ጎንደር ጎንደር የቴዎድሮስ ሀገር
አምጡ ቆርጣችሁ ከሹሩባው ላይ
ኪዳን እንሰር እንዳንለያይ…
የተሰኘው የተወዳጁ ድምጻዊ ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) ዜማ ከቁንዳላው እኩል ነግሶ ውሏል። መልካም በዓል ይሁንላችሁ!!
  

Read 581 times