Sunday, 09 January 2022 00:00

የኢትዮጵያዊነት ቀለማትና በዓለ ምህረቱ

Written by  ከሲሲፈስ (ወንድይራድ)
Rate this item
(0 votes)

 “በሰማዩ ላይ ቢታይ ቀለም
የርሷ ነው እንጂ ሌላ አይደለም”
እንኳን ለ2014ኛው የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል አደረሳችሁ!
እነሆ የሰው ልጆች ምህረት ስጋ ለብሶ ከተወለደ እንደ ኢትዮጵያውያን አቆጣጠር 2014 ዓመታት አለፉ። ከዚያ ጊዜ ጀምሮ የአመታቱ ንብረትነትና ስም ከፍዳ ወደ ምህረት ተዛውሯል፡፡
እንደ መፅሀፉ ገለፃ፤ የኢየሱስ ልደት የፈጣሪና የሰው ልጆች እርቅም ልደት ነው። በቀደሙት ዘመናት ፈጣሪ ከሰው ልጆች ጋር እርቅ የሚያደርግባቸው መንገዶች ሁሉ በእንስሳት መስዋዕት ላይ የተመሰረቱና ጊዜያዊ ነበሩ። የኢየሱስ ልደት ግን ፈጣሪ ራሱን ከሰው ልጆች ለማስታረቅ የወረደበት የዘለዓለማዊ እርቅ ጅማሬ ነው፤ የምህረት ስጦታ!
እንደዚሁ መፅሐፍ ገለፃ፤ ምህረቱና ኢትዮጵያዊነት የሚገናኙበት ቀዳሚ ገፆችም አሉ፤ ታሪኩም በሰንደቅ አላማችን ቀለማት በኩል የሚያያዝ ነው፡፡ የሰንደቅ አላማችን ሦስት ቀለማት የሩቅ ዕይታ የቀስተ-ደመና ቅጂዎች ናቸው። የሰባት ቀለማቱን የሳይንስ “ግኝት” ካነሳን “የእኛ ነገር” ወዴት እንደሚያመራ እናውቀዋለን። ሦስትም ሆነ ሰባት በክርስትናና በኒዮሜሮሎጂ የፍቅር የአምላክ ማንነት የእረፍትና የመመረጥ የትርጉም ውክልናን ቢጋሩም (ኒዮሜሮሎጂ ስምንና ቁጥርን መሰረት ያደረገ የአስሮቶሎጂ ውልድ የትንቢት “ጥበብ”) እኛ ግን በቁጥሮቹ ስያሜ ተቧድነን ከመናቆር አንመለስም፤ ስለዚህ የሳይንስን ለሳይንስ ትተን ወደ ሰንደቅ አላማችን ሀይማኖታዊ ትርክት እንመለስ (“መነሻችን mythical ነው” ያልከኝ ወዳጄ የሀሳብ ነፃነትህን አከብራለሁ)፡፡
ከኖህ ዘመን የጥፋት ውሃ ዕልቂት በኋላ ፈጣሪ በፀፀት አንድ የምህረት ቃል ኪዳንን ለሰው ልጆች ሰጠ፤ ልብ አድርጉ! የምንገኘውና የተጓዝነው ወደ ብሉይ ኪዳን ገፆች ቢሆንም፣ ቃል ኪዳኑን የሰጠው ለሰው ልጆች ሁሉ እንጂ ለቀደመው ኪዳን ባለ መብቶች (ለአንድ ህዝብ) አይደለም። ይህ ማለት የማዳኑ ኪዳን እንደሙሴ ህግ ለአንድ ህዝብ ብቻ የተሰጠ ሳይሆን የሰው ልጆች ሁሉ ስጦታ ነው። ይህም ለስጋ ለባሹ ሰው ሁሉ ምህረትና እርቅ ለመስጠት ስጋ ለብሶ የወረደው አምላክ ጥላና ምሳሌ መሆኑ ነው።
“ከዚህ በኋላ የሰው ልጅን በውሃ አላጠፋም” ሲል ቀስተ-ደመናን የቃል ኪኑ ምልክት በማድረግ በሰማይ ላይ አኖረ። ኢትዮጵያውያን አባቶችም ይህንን የቃል-ኪዳኑን ምልክት ቀለማት የሀገራቸው ምልክትና ሰንደቅ አላም አድርገው ሲያፀድቁት፣ የአይሁድ አባት የሆነው የያዕቆብ አያት አብርሃም እንኳን ገና አልተወለደም፡፡ ስለዚህ ኪዳኑ ከዘርና ሀይማኖት በላይ ሁሉን ጋባዥ ነበር፡፡ ቃል ኪዳኑ በተሰጠበትና አባቶቻችን አርማቸው ባደረጉበት መካከል ያለው የዘመን ርቀት እርግጡ ባይታወቅም፣ የቃል ኪዳኑን ምልክት “ምልክታችንና መለያችን ይሁን” ሲሉ፣ ቀለማቱን ብቻ መርጠው ወካይ እሴቱን ምህረቱን ገፍተው እንደማይሆን ግን ዕሙን ነው። ሰንደቅ አላማችን ከምህረት ቃል-ኪዳን ቀለማት እንደተቀዳ ሁሉ የህዝቦቿ እሴት መሰረትም ምህረት መሆኑን ለማመን በርካታ የዕርቅ ስርዓት ባህሎቻችን ብቻ ሳይሆኑ ዥንጉርጉር የብዙሀን አንድነታችንም አብነት ነው፡፡
አንድ ከፍ ያለ ልክ ከርሱ የሚያንሰውን ልጅ ሲመታ ቢገኝ የሚታረምበት ባህል “ባንተ እንዲሆን የማትፈልገውን በሌላው ደስ ይልሀል?” የሚል ሌላውን እንደራስ የመመልከትን መርህ የሚያቀብል አጠይቆት ነው፤ የይቅርታ ባይነት ስልጠና ነው። በጥንታውያን ግሪኮችና በእስልምና ሀይማኖት መሪዎች ስለኢትዮጵያ የሰጡት ምስክርነቶች በጎነት የሚመነጨውም ከአባቶቻችን የበጎ ዕሴት አክባሪነት ነው፡፡
ስጦታችን ምህረት ነው
“ህፃን ተወልዶልናልና ወንድ ልጅም ሰጥቶናል”
የኢየሱስ የልደት በዓል ከሁሉም በአላት ይልቅ በስጦታ የሚደምቀው አምላክ ለሰው ልጆች የሰጠው የምህረት ስጦታ በመሆኑ የእምነት መነሻነት ምክንያት ነው። እኛ ኢትዮጵያውያን ይህንን ስጦታ ከሌሎች የሰው ልጆች ሁሉ ጋር አብሮ የሰጠን ቢሆንም፣ ቀዳሚው የምህረት ቃል ኪዳነ ቀለማቱ ግን ከሰማይ የተቀበልነው መለያ ቀለማችን ነው፡፡
የአምላክ ስጋ ለብሶ የመወለድ ተልዕኮ፣ ምህረት ለሰው ልጆች መስጠት ነበር። ፍርደኛውን የሰው ልጅ ከሀጢያት ባርነት ከሞትና ከዘለዓለም ፍርድ ማዳን ነበር። ስለዚህም ስሙ አዳኝ (ኢየሱስ) ተባለ። ኢትዮጵያውያን የልጆቻቸውን ስም እንደ አንዳንድ ህዝቦች ኢየሱስ (Jesus) ብለው ለመሰየም አይደፍሩም፤ ምህረት የሚለውን የማንነት መገለጫውን ግን ለወንድም ሆነ ለሴት ልጆቻቸው ያወጣሉ፡፡ እንደ ቀድሞዎቹ አባቶቻችን የፈጣሪን ምህረትና ተራዳኢነት ወደ ቤታቸው ሲጋብዙ፣ የሰማይ ስጦታቸውን ሲቀበሉ፤ ምህረትን ሲያፀድቁ….
የሚዘረጉት የኢትዮጵያ እጆች
ስጦታ ባይከፈልበትም ስጦታን ለመቀበል ግን እጆችን መዘርጋት ግድ ነው። የአምላክ የምህረት ስጦታ ወደ ምድር የወረደው የዛሬ ሁለት ሺህ አስራ አራት ዓመት ገደማ ቢሆንም፣ ቀደምት አባቶቻችን እንደወሰዱት የምህረት ቃል-ኪዳን በፈቃደኝነትና በገዛ ምርጫችን የምንቀበለው ለየትውልዱና ለየግለሰቡ የቀረበ ስጦታ ነው፤ ስለሆነም ምንም እንኳን ስጦታው የተዘረጋልንና የቀረበልን ቢሆንም ስጦታውን መቀበል የተቀባዩ ድርሻ ነው፤ ምንም እንኳ የተስፋ ቃል ኪዳን ያላት ሀገር ህዝቦች ብንሆንም የመቀበል ቅድመ ሁኔታ ይመለከተናል፤ ምንም እንኳን በጥንታዊ የታሪክ የሚቶሎጂና ቅዱሳት መፅሐፍት ውስጥ የሀገራችን ስም ከበጎ ዕሴቶች ጋር ተቆራኝቶ የተነሳ ቢሆንም ዘለዓለማዊውን እርቅ ለመቀበል መዘርጋት ግዳጃችን ነው፡፡
የትንቢት ባለተስፋዋ ኢትዮጵያ ማለት ኢትዮጵያዊያንና እሴቶቻቸው ማለት ናቸው፤ አሊያ ግዑዝ መልክአ ምድር የሚዘረጋው እጆች የሉትም፤ ኢትዮጵያ ወደ ፈጣሪዋ የምትዘረጋውን እጆቿን የሚዘረጉላት የተስፋ ቃሏንና ስጦታዋን የሚቀበሉላት ዜጎች ናቸው። ታዲያ የዜጎቿ እጆች ከወዴት ናቸው? ወደ ሰማይ አምላክ ለምህረት ተዘርግተዋል? ወይስ ወደ ወንድሞቻቸውና ባልንጀሮቻቸው ለፍርድ ተቀሳስረዋል?
ለመቀበል መዘርጋት የስጦታ ተቀባይ ቅድመ ሁኔታ እንደሆነው ሁሉ ለምህረት ስጦታም ቅድመ ሁኔታ አለ፤
“ይቅር እንድትባሉ ይቅር በሉ!” የሚል መርህ!
በምድራዊው አለም ኢትዮጵያውያን የሆንን ሁሉ በሰማይ መንግስት (መንግስተ-ሰማያት) የሰማይ ዜጎች የመሆን ፈቃዳችን በአባቶቻችን ምርጫ ብቻ የሚፀድቅ አይሆንም፡ ይልቁኑ በትንቢት ፍፃሜና በምህረት ዓመት የምንኖር የዛሬዎቹ ኢትዮጵያውያን በሚኖረን የይቅር ባይነት እሴት ጭምር እንጂ፡፡ ወቅታዊው የሀገራችን ሁኔታና እውነታም ከመቼውም ጊዜ ይልቅ ምህረትና ይቅር ባይነት በሚያስፈልገን የታሪክ አንጓ ላይ መገኘታችንን ይነግሩናል፡፡ ከአምላክ ምህረት ስንቀበል እርስ በእርሳችን ይቅር የተባባልንበት “ደረሰኝ” በእጆቻችን ላይ መገኘት ይኖርበታል አሊያም “ይቅር እንድትባሉ…”ን ዘንግተናል፡፡
ኢትዮጵያዊነትና ይቅር ባይነት
ከፍተኛ የበቀልና የዕርቅ ባህሎች ባለቤት በሆነ ህዝብ መካከል እየኖርን ወደ ሙሉ እጅ ገደማ የተለያዩ ሀይማኖቶች ተከታይ የሆነ ህዝብ የሚኖርበት ሀገር ዜጎች ሆነን ሳለ፤ በርካታ የእርስ በእርስ ጦርነቶች ታሪክ ባለቤቶች ሆነን ሳለ…. ምህረትንና ስነ-ምግባርን (ግብረ ገብን) የሀይማኖት ርዕሰ ጉዳይ ብቻ አድርጎ መቁጠር የመፍትሔ መካን ስነ ዕውቀቶች ኑዛዜ ይመስላል፡፡
አሁን በጦርነት አሊያም በጦርነት “ሀንጎቨር” ውስጥ ሆነን ሳለ ይቅርታ የማያነሳ “ሚዲያ” መቼ ሊያነሳ ነው? ፖለቲካው “ሀገራዊ መግባባት” እያለ የሚጠራው የሀገራዊ ስምምነት ድግሳችንስ ያለ ይቅር ባይነት እንዴት ይሳካልናል? ህጎቻችንስ ያለተግባራዊ የግብረ-ገብ ፈቃደኝነት እንዴት ስጋ ሊለብሱ ይችላሉ? “ወደ መሠረታችን እንመለስ” የሚለው የስነ እውቀት ግንዛቤያችንስ ማዕከሉ መለኮት ወደነበረው የዕውቀት መሠረታችን እንመለስ ማለቱ ካልሆነ ምን ማለቱ ሊሆን ይችላል? (በልዩ ልዩ ሀይማኖቶች ውስጥ ያለ የስነ-ዕውቀት መሰረት)
“የኔ ዜማ” (እንደሁላችን የዜጎች ድምፅ “የኛ ዜማ”) ምህረት ሊሆን የሚሻን ወቅት አሁን ነው፤ ሰንደቅ-አላማችን የምህረት ቃል-ኪዳን አርማ ነው፤ የተስፋ ቃላችን እጆችን ወደ ፈጣሪ የማንሳት የአምላክ መፍትሄ ነው፤ ታሪካችን የግጭትና የእርቅ፤ በአመዛኙ የመቻቻል ነው… እናም አሁን…
“ህፃን ተወልዶልናልና ወንድ ልጅም ተሰጥቶናልና” ስጦታችንን እንቀበል! በኢትዮጵያዊ መሰረታችን በምህረት ቃል-ኪዳን ውስጥ ሆነን፤ እጆቻችንን እርስ በእርስ ከመቀሳሰር ሰብስበን እንደተስፋ ቃላችን ወደ ምህረት አምላክ እንዘርጋ! “…በደላችንን ይቅር በለን! እኛም የበደሉንን ይቅር እንደምንል”!



Read 1032 times