Print this page
Tuesday, 11 January 2022 00:00

የሃይማኖት ፍልስፍና

Written by  ብሩህ ዓለምነህ
Rate this item
(2 votes)

(ክፍል-3 Cosmological Argument)

የሃይማኖት ፈላስፎች ‹‹የእግዚአብሔርን ህልውና ከእምነት ባሻገር በአመክንዮም ማስረዳት ይቻላል›› በማለት ከሚያቀርቧቸው ጥንታዊ መከራከሪያዎች ውስጥ የሚከተሉት ይገኙበታል፣
Ontological Argument
Cosmological Argument
Argument from Design
በአብዛኛው እነዚህን ፍልስፍናዊ መከራከሪያዎች ለዓለም ያስተዋወቁት የመካከለኛው ዘመን ካቶሊካውያን መነኮሳት ናቸው፡፡
ከእነዚህ መከራከሪያዎች ውስጥ ‹‹Ontological Argument›› የሚባለው ወደ ውስጣችን ወዳለው ሐሳብ ወይም ህገ ልቦና በማየት የእግዚአብሔርን መኖር ለማረጋገጥ የሚሞክር ሐሳብ ሲሆን፣ ቀሪዎቹ ሁለቱ ደግሞ ውጫዊውን ዓለም በመመልከት የእግዚአብሔርን ህልውና ለማስረዳት የሚቀርቡ መከራከሪያዎች ናቸው፡፡ በክፍል-2 ፅሁፌ ስለ ‹‹Ontological Argument›› የተመለከትን ሲሆን፣ ዛሬ ደግሞ ስለ Cosmological Argument አንዳንድ ሐሳቦችን እንመለከታለን፡፡
ይህ መከራከሪያ ‹‹Cosmos›› ከሚለው ቃል የተወሰደ ሲሆን፣ ትርጉሙም ‹‹ህዋ›› ወይም ዩኒቨርስ ማለት ነው፡፡ መከራከሪያውም የዩኒቨርሱን ክስተቶች በማየትና ክስተቶቹ እርስበርስ ያያያዛቸውን የመንስኤ–ውጤት ሰንሰለት በመመልከት የእግዚአብሔርን ህልውና ለማስረዳት የሚጥር ነው፡፡
‹‹Cosmological Argument›› የሚባለውን መከራከሪያ ለመጀመሪያ ጊዜ ያስተዋወቀን አሪስቶትል ቢሆንም፣ ሐሳቡን በደንብ አስፋፍቶ ያሳየን ግን ጣሊያናዊው መነኩሴና ፈላስፋ ቶማሰ አኳይነስ (Thomas Aquinas (1225–1274)) ነው፡፡ አኳይነስ፣ ካቶሊክ ቤተክርስትያን እጅግ የምትኮራበትና ‹‹የኔ ሃይማኖታዊ አስተምህሮ ወደ ፍልስፍና ሲቀየር የአኳይነስን ይመስላል›› እስከ ማለት የደረሰችለት ታላቅ ሃይማኖታዊ ፈላስፋ ነው፡፡
አኳይነስ ‹‹Summa Theologica››
(Summary of Theology) በሚለው ሥራው ውስጥ እግዚአብሔር ስለ መኖሩ በአምስት መንገዶች (Five Ways) ማወቅ እንደምንችል ፅፏል፡፡
የመጀመሪያው መንገድ ‹‹Argument from Motion›› በማለት የሰየመው ነው። አኳይነስ ‹‹Motion›› ሲል እንቅስቃሴ ለማለት ሳይሆን አሪስቶትል በሚረዳው መልኩ ‹‹ለውጥ›› ለማለት ነው፡፡ አኳይነስ ‹‹ለውጥ›› ሲል የቦታ እንቅስቃሴን፣ የጊዜን ተቀያያሪነትን፣ የዕድገት ሂደትንና የሁኔታዎች ተለዋዋጭነትን ሁሉ ያካትታል፡፡ በዓለም ላይ ያሉ ነገሮችን ስንመለከታቸው ሁሉም ከአንድ ክስተት ወደ ሌላ ክስተት ይቀያየራሉ፤ ይንቀሳቀሳሉ፡፡ ህይወት ያላቸው ነገሮች ይወለዳሉ-ያድጋሉ-ይሞታሉ፤ እንጨት ይነዳል፤ ከዚያም እንደ ሁኔታው ከሰል ወይም አመድ ይሆናል፡፡
እዚህ ላይ የሚነሳው ጥያቄ እንጨት እንዴት እሳት ሊሆን ቻለ? የሚለው ነው፡፡ አኳይነስ የዚህን ጥያቄ ማብራሪያ ከአሪስቶትል ይዋስና እንዲህ ይላል፣ ‹‹እንጨት እሳት ሊሆን የሚችለው በውስጡ እሳት የመሆን አቅም (Potentiality) ስላለው ነው፤ ለዚህም ነው እንጨት እሳት ሲነካው የሚነደው፣ ከዚያም አመድ የሚሆነው››፣ በስተመጨረሻም ወደ አተምነት የሚቀየረው፡፡ እነዚህን ለውጦችና እንቅስቃሴዎች እያያያዝን ወደ ኋላ ስንሄድ፣ እነዚህን እንቅስቃሴዎችን ያስጀመረ የመጀመሪያ አንቀሳቃሽ (first mover) ላይ እንደርሳለን፡፡ ይሄም አንቀሳቃሽ የሌለው የመጀመሪያው አንቀሳቃሽ እግዚአብሔር ነው፡፡
ሁለተኛው የአኳይነስ መከራከሪያ ‹‹Argument from Efficient Causality›› የሚባል ሲሆን፣ እሱም የመንስኤ-ውጤት ሰንሰለትን መሰረት ያደረገ ነው፡፡ ባጠቃላይ፣ የዚህ መከራከሪያ አመክንዮአዊ አወቃቀሩ እንዲህ የሚል ነው፤
በዓለም ላይ ያሉ ነገሮች በሙሉ በመንስኤ የተከሰቱ (caused) ናቸው፤ መንስኤ የምንላቸው ነገሮች ራሳቸው በሌላ ቀደም ባሉ መንስኤዎች የመጡ ናቸው፡፡
እነዚህ ክስተቶች ራሳቸውን በራሳቸው ሊያስገኙ አይችሉም፤
ሁሉም ነገር በመንስኤ–ውጤት የተሳሰረ ቢሆንም፣ ይሄ ነገር ግን ወደኋላ መነሻ የሌለው  የትየለሌ ሊሆን አይችልም፤
ይሄም ማለት የመንስኤ–ውጤት ወደኋላ ሄዶ አንድ መነሻ ላይ ይደርሳል፤ ይሄም መነሻ ‹‹በሌላ መንስኤ ያልተከሰተ የመጀመሪያው ከሳች›› (uncaused first cause) ነው፡፡ ይህ ‹‹ያልተከሰተ የመጀመሪያው ከሳች›› የመንስኤ–ውጤት ሰንሰለትን ያስጀመረ እንጂ እሱ ራሱ በዚህ ሰንሰለት ውስጥ የተከሰተ አይደለም፡፡
ይሄ ‹‹ያልተከሰተ የመጀመሪያው ከሳች›› እግዚአብሔር ነው፡፡
ስለዚህ፣ እግዚአብሔር አለ፡፡
ሦስተኛው መከራከሪያ ‹‹Argument from Possibility and Necessity›› ይባላል፡፡ በዓለም ላይ ያሉ ነገሮች በመሆንና ባለመሆን፣ በመኖርና ባለመኖር ችሎታ ውስጥ የሚገኙ ናቸው፡፡ ለምሳሌ ሰው፣ ህልው ከመሆኑ በፊት ያልኖረበት ዘመን ነበረ፡፡ ሌሎችም ነገሮች እንዲሁ ያልኖሩበት ዘመን ነበር፡፡ ይሄም ማለት ወደኋላ የሆነ ዘመን ላይ ምንም ነገር የሌለበት ዘመን ነበረ ማለት ነው፡፡ ይሄም ሐሳብ፣ ታዲያ እነዚህ ነገሮች ካለመኖር ወደ መኖር እንዴት ሊሸጋገሩ ቻሉ? እነዚህ ነገሮች የሆነ ጊዜ ላይ ካልነበሩ፣ የት፣ እንዴትና በማን መኖሩ ጀመሩ? የሚሉ ጥያቄዎች ያስነሳል፡፡
ይሄም ሐሳብ ወደኋላ የሆነ ጊዜ ላይ አሁን ያሉትን ነገሮች ካለመኖር ወደ መኖር ያመጣቸው አስገዳጅ የሆነ ህልውና ያለው አንድ ነገር እንዳለ ያመላክተናል፡፡ ይሄም ህላዌ ልክ እንደ ሰውና እንስሳ የመሆንና ያለመሆን አቅም (Possibility) ውስጥ የሚገኝ ሳይሆን፣ የግድ ህልው የሆነና ህልው አለመሆን የማይችል ህላዌ (Necessary Being) ነው፤ እሱም እግዚአብሔር ነው፡፡
አራተኛውን መከራከሪያ ‹‹Argument from the Gradation of Things›› ነው። የነገሮችን መገለጫ ባህርያት (qualities) በተለያየ ደረጃ እናስቀምጣቸዋለን፡፡ ለምሳሌ፣ ጥሩነትን በደረጃ ስናስቀምጣቸው ጥሩ፣ በጣም ጥሩ፣ እጅግ በጣም ጥሩ፣ ፍፁም ጥሩ በማለት ፍፅምና ላይ ስንደርስ እናቆመዋለን፡፡ ቅድስና፣ ፍቅር፣ ዕውቀትና ውበትም እንዲሁ ናቸው፡፡
‹‹እገሌ ከእገሌ የተሻለ ቅዱስ ነው›› የምንለው የቅድስናው መጠን ፍፁም ቅዱስ ለሆነው ነገር እየቀረበ ሲሄድ ነው፡፡ ይሄ በነገሮች መካከል ያለ የደረጃ መበላለጥ የሚነግረን ነገር ፍጹም የሆነ ኳሊቲ አለ ማለት ነው፤ ፍፁም ቅድስና፣ ፍፁም ዕውቀት፣ ፍፁም መልካምነት፣ ፍፁም ውበት፣ ፍፁም ፍቅር፣ ፍፁም ቻይነት…። እነዚህን ኳሊቲዎች በፍፁምነት ደረጃ ሰብስቦ የያዘ ህላዌ አለ፤ እሱም እግዚአብሔር ነው፡፡
አምስተኛውንና የመጨረሻው መከራከሪያ ‹‹Argument from the Governance of the World›› ይባላል፡፡ ይሄ መከራከሪያ ‹‹Argument from Design›› ወይም ‹‹Teleological Argument›› የሚባለው ሐሳብ ግልባጭ ነው፡፡ ዩኒቨርሱ ሥርዓት አልባ አይደለም፤ ይልቅስ ዓለም ላይ የምናያቸው ነገሮች ሁሉ በዕቅድና በሥርዓት ሲመሩ እናያለን፡፡ ዩኒቨርሱ ይሄንን ዕቅድና ሥርዓት በራሱ ለራሱ ሊያስገኝ አይችልም፤ የሆነ አዋቂ ህላዌ ካልሰጠው በስተቀር፡፡ ይሄም አዋቂ እና የዓለም ሥርዓት አስገኝ ህላዌ (Intelligent Being) እግዚአብሔር ይባላል፡፡
የቶማስ አኳይነስ አምስቱ መከራከሪያዎች እነዚህ ናቸው፡፡ በሚቀጥለው ክፍል እነዚህ መከራከሪያዎች ላይ የቀረቡትን ትችቶች እንመለከታለን፡፡

Read 4225 times