Monday, 10 January 2022 15:32

ዳግም የተወለደው ሠራዊታችን!

Written by  ነፃነት አምሳሉ አፈወርቅ
Rate this item
(0 votes)

እንደ አብዛኛው ዓለም ሁሉ፣ ሀገራችንም ሰላምዋንና ደህንነቷን በመከላከያ ሰራዊት፣ በፖሊስና በአየር ኃይል የተደራጀ ስራ እያስጠበቀች ለዛሬው ቀን ደርሳለች፡፡ ይህም ሲባል ህዝባችን የከፈለው ውድ ዋጋ እንደ ማዕዘን ራስ ወሳኝ ሚና ያለው መሆኑን ለአፍታም መዘንጋት አይቻልም፡፡
መከላከያ ሰራዊታችን ትናንትና - ቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴ ከእንግሊዝ መንግስት ጋር ከነበራቸው ቅርበት በመነሳት የተደራጀው የሀገሪቱ የሰራዊት ክንፍ፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተደራጀ ሄዶ፣ በደርግ ዘመን በብዛትም በጥራትም ማደጉ ይታወቃል፡፡ ከ1983 በኋላ በነበረው የመንግስት ለውጥ ኢህአዴግ አዲስ አበባ በገባ ማግስት ለዘመናት ሲገነባ የነበረውን ሰራዊት፣ ከኢትዮጵያዊነት መጠርያ ስሙ ነጥሎት፣ “የደርግ ሰራዊት” ብሎ በአዲስ ቅፅል በመጥራቱ፣ የጥላቻ ስም ተሰጥቶት፣ በከፈለው ዋጋ እንዲሸማቀቅ ተፈርዶበት ነበር፡፡
በዘመነ ሕወሓት የነበረው ሰራዊት በመሳርያ ብዛትና አይነት በተሻለ እውቀትና በተለያዩ ሀገራት በተወጣው ግዳጅ የገዘፈ ስም የገነባ ቢሆንም ቅሉ፣ ወገንተኝነቱ ለሀገር ሳይሆን ለድርጅት፣ ለብሔራዊ ባንዲራ ሳይሆን ለድርጅት ባንዲራ፣ ለሉዓላዊነት ሳይሆን ለገዢ ስርዓት ሎሌነት የተንበረከከ፣ ሲጠሩት “አቤት” ሲልኩት “ወዴት” ባይ የነበረ ሰራዊት ነበር ብሎ መወሰዱ የተጋነነ ግምገማ አይሆንም፡፡
ሰራዊታችን በዘመነ ሕወሓት በህዝብ ዘንድ ካጣው አመኔታ የተነሳ በጎ ምልከታ ይዞ ለማሞገስ ለማሞካሸትና የዓላማው ተጋሪ ሆኖ ከአጠገቡ ለመሰለፍ እንደ ህዝብ ብዙ ጊዜ እንደወሰደብንና ከመጣንበት ቅርርብ አንጻር ካየነው፣ ህዝባችን ለመከላከያ ሰራዊት እንስፍስፍ አንጀት ነበረው ብሎ መናገር አይቻልም፡፡ ለዚህ ክፉ ደዌ ሴራ ጠንሳሽ የነበረችው ደግሞ ሕወሓት ናት፡፡ ሕወሓት ሰራዊቱን የጭራቆች ስብስብ የደም ጠጪዎች ማህበር አስመስላ በዜጎች አእምሮ ላይ በመሳልዋ፣ ሰራዊቱና ህዝቡ ሆድና ጀርባ ሆነው ከርመዋል፡፡ ሽማግሌ ሆኖ የሚያስታርቅ አካል በመጥፋቱም የሕወሓት ስርዓተ ቀብር እስኪፈጸም ድረስ መከላከያ ሰራዊት የባእድ ሀገር ሰራዊት እስኪመስለን ድረስ እንድንጠላውና እንድንርቀው ያልተደረገብን ስነልቦናዊ ጫና አልነበረም፡፡ ለዚህ እርሾ ምክንያት ሊሆኑ የሚችሉ ሚዛን ደፊ አምክንዮዎችን ማስቀመጥ ይቻላል፡፡
ሕወሓት ሰራዊቱን ጡጦ አጥብታ እንዳሳደገችው ማደጎ በመቁጠር፣ እኔ ካልኩህ ውጭ ዝንፍ እንዳትል በማለት አቅመ ደካማ ሆኖ እንዲገኝ አድርጋዋለች፡፡ የሰራዊቱ አባላትም የህዝብና የህገመንግስት ጠበቃ ከመሆን ይልቅ የአንድ ቡድን ጉዳይ አስፈጻሚ እንዲሆኑ በመገደዳቸው የለበሱት ዩኒፎርምና ያጠለቁት መለዮ ለፎቶ መነሻ ብቻ ሆኗቸው አይተናል፡፡ “እንኳን ከዚህ ወርቅ ህዝብ ተፈጠርኩ” በሚል እብሪት ራስን የሰማይ ላይ ዳኛ፣ ሌላውን የበታች አድርጎ የመሳል ክፉ አስተሳሰብ እንደ እባብ ተስቦ የገባው በመከላከያ ሰራዊት ውስጥ እንደነበር የአደባባይ ምስጢር ነው። በዚህም የሕወሓት ልጆች “ደረጃ አንድ ወታደሮች” ሲሆኑ፣ ሌላው ግን እንደ ሠርግ አጃቢ የስርዓቱ አድማቂ ሆኖ እየተቆጠረ፣ “የቤት ልጅና የእንጀራ ልጅ” የሚል ክፍፍል ተፈጥሮ፣ ለቤት ልጆች በነሃስ ማንኪያ ምግብ ሲቀርብላቸው ለምስኪኑ ሀገር ወዳድ ሰራዊት ግን የጥጋብ ተረት እየተነገረው፣ እንቅልፉን እንዲተኛ መደረጉን ማን ይዘነጋዋል፡፡ በኢትዮ ኤርትራ ጦርነትም ወቅት “የትግራይ ልጅ ለ17 ዓመት ተዋግቷል እና ማረፍ አለበት” ብላ ለፈንጂ ማምከኛና ለጥይት አረር ማብረጃ ይሆኑ ዘንድ የሌላ ብሔር ምልምል ወታደሮችን ከፊት አሰልፋ ያስጨረሰችበት ጥቁር ታሪክ፣ ከፈረሱ አፍ እንደሚባለው፣ እያመመንም ቢሆን በወቅቱ ከነበሩ ተዋጊዎች አፍ ሰምተነዋል፡፡
በሌላ መልኩ “የመከላከያ ቀን” በሚል የስላቅ በዓል በማዘጋጀት፣ ደርሶ አዛኝ ለመሆን ስትጥር ታዝበናል፡፡ ሕወሓት ሰራዊቱን ስታሽሞነሙን የነበረችው ጥያቄ የሚያነሱ ዜጎችን ለመግደልና ለማስፈራራት እንጂ ለህዝብ እንዲወግን ፈልጋ አይደለም። ህዝባዊ ስሜት ያየለበት የሰራዊት አባል በየትኛውም መድረክ ላይ ፍትሃዊነትን እኩልነትንና ግልጽነትን ያማከለ ጥያቄ ቢያነሳ፣ እጣ ፈንታው ምን ይሆናል ብሎ ከማሰብ ይልቅ የቀብሩ ቦታ ይታወቅ ይሆን ወይ ብሎ ማሰቡ ይቀል ነበር፡፡ ይህንን የማነቆ ስርዓት ከእሳት በተሰራ ሰንሰለት ለማጥበቅ አንድ ለአምስት የሚባል የፖለቲካ አጀንዳ ማስፈጸሚያ የግምገማ መድረክ በመዘርጋት፣ “ይህን አስበሃል፤ አዝማሚያህ ይህን ይመስላል” በሚል ፍረጃ፣ አንገት የማስደፋትና የማሸማቀቅ ስራ ሲሰራበት መቆየቱ የሩቅ ዘመን ታሪክ ሳይሆን የትናንትና ትዝታ ነበር፡፡
ይህም ሳያንስ “የአብዮታዊ ዲሞክራሲ ምሽጉ ሰራዊቱ ነው” በሚል የት መጣ የሌለው  ድምዳሜ፣ ሰራዊቱ የሕወሓት ርእዮት አስፈጻሚ እንዲሆን ተፈረደበት። ይህ ደግሞ ሰራዊቱ ለማለለት ቃልኪዳን ከመታመን ይልቅ የኢህአዴግ ጽ/ቤት ኃላፊዎችን ውሳኔ ወደመፈጸም እንዲሸጋገር ገፊ ምክንያት ሆነው። ሕወሓት ሰራዊቱ ከህዝብ ጋር ከተስማማ ነገ አፈሙዙን ወደ እኔ ያዞራል በሚል የስካር ትንቢት በመታወሯም፣ በህዝብና በሰራዊቱ መሃል በደም የተመሰረተ ጥላቻ አንብራ፣ አይጥና ድመት አድርጋን ኖረችበት፡፡
ለግዳጅና ለተልእኮ ሲሆን ግንባሩን ለጥይት ሰጥቶ የሚሰለፈው ሰራዊት፣ ተፈጥሮአዊ ማንነቱን ጥሎ ቆሌ ሲርቀው ተቋሙም ያለቅጥ ለኢ-ዲሞክራሲያዊ ልምምድ ተዳርጎ፣ ትልቅ ህንጻ ታቅፎ እንዲቀር አስገድዶታል። ሹመት ሲመጣም “የተለየ ዘር ናቸው” የተባሉት “ምርጦቹ” የቡፌ ስልጣን ቀርቦላቸው እጃቸው የቻለውንና ዓይናቸው ደስ ያለውን እያነሱ፣ ያለምንም ትምህርት ዝግጅትና ልምድ ማዕረጋቸውን ትከሻቸው ላይ ሲደረድሩ፣ ቀሪዉ ተስፈኛ ወታደር ግን ከሹመታቸው ድግስ ገብቶ እንዲበላና በቴሌቪዥን ቀርቦ የድጋፍ አስተያየት እንዲሰጥ ብቻ ነበር የሚፈቀድለት፡፡
ሰራዊቱም ለሀገሩ ባንዲራ መስዋዕት ለመክፈል ፈቃደኛ ሆኖ ሳለ ስርዓቱ በፈጠረው ክፉ ምስል በህዝቡ ዘንድ የተጠላና የተገለለ እንዲሆን ተፈርዶበት፣ በገዛ ሀገሩ ባይተዋር ሆኖ አይተነዋል፡፡ በዚህም የሰራዊት አባል ሆኖ ለመመዝገብ ፈቃደኛ የሆነ ወጣት መጥፋቱን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፣ በአንድ መድረክ ላይ መናገራቸውን እማኝ መቁጠር እንችላለን፡፡
በሌላ መልኩ ሰራዊቱ በብሔር ተዋጽኦ ኢ-ፍትሃዊነትና አይን ያወጣ አድልዎ ሲፈጸምበት፣ አለፍ ሲልም የግለሰቦች ፈላጭ ቆራጭነት የገነገነበት፣ የሕወሓት አዛዥና ናዛዥነት ዓይን ያወጣበት፣ የአንድ ብሔር የበላይነት ህጋዊ በሆነበት በነዚያ ክፉ ጊዜያት፣ ውስጥ ውስጡን የሚብላላ ቀን ጠባቂ ፈንጂ እንደነበር ውሎ አድሮ ለአደባባይ በቅቶ አይተነዋል፡፡ ከረጅም በአጭሩ የሰራዊቱ ጥያቄ ከህዝብ ጥያቄ ጋር አብሮ እንደ ኤርታሌ እሳተገሞራ ገንፍሎ፣ መጋቢት 24 ቀን 2010 ዳግም  ተወልዷል፡፡ መልካም ልደት!
መከላከያ ሰራዊታችን ዛሬ - አሁናዊ ሁኔታውን በቅጡ ካጤንነው፣ የመከላከያ ሰራዊት ዳግመኛ ልደት ነው ብንል እንደሚያስማማን እገምታለሁ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ወደ ስልጣን በመጡ ማግስት የመጀመርያውን የሪፎርም ስራ ለምን በመከላከያ ላይ አደረጉ ብለን ብንጠይቅ፣ የተቋሙን ዘርፈ ብዙ ችግሮች በወጉ ስለተገነዘቡትና ተቋሙ “የቀዩ መጽሐፍ” ሰለባ ሆኖ፣ አብዮታዊ ዲሞክራሲን እንደ ጸሎት መጽሐፍ እየደገመና እያስደገመ  ሀገርን መታደግ እንደማይችል ስለተረዱት ነው ማለት ይቻላል፡፡  አዎ ጠ/ሚኒስትሩ፤ መዋቅራዊ፣ አስተዳደራዊና አስተሳሰባዊ ሪፎርም በማድረግ ተቋሙ በኢትዮጵያዊነትና በህዝባዊነት አለት ላይ እንዲመሰረትና ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ከፖለቲካ ፓርቲ ተላላኪነት፣ ከአንድ ብሔር የበላይነት፣ ከአንድ ለአምስት ጉንጭ አልፋ ግምገማና መያዣ መጨበጫ ከሌለው የሶሻል-ካፒታሊዝም ድቅል ማንነት ካለው የአብዮታዊ ዲሞክራሲ የአዳራሽ ውይይት ተላቅቆ ወደ ሙሉ ቁመና እንዲሸጋገር ወኔ የሚጠይቅ ውሳኔ በመወሰን ትውልድ የሚያመሰግነውን ድንቅ ስራ ሰርተዋል፡፡
በልደቱም ማግስት ታፍኖበት የነበረውን የአፈና ቅርፊት ሰባብሮ የወጣው መከላከያ ከሁሉ አስቀድሞ የፍቅር ማእድ ላይ አብሮ የተቀመጠው ከወገኑ ጋር ነበር፡፡ በዚህም ልዩነትን በአንድነት፣ ጥላቻን በፍቅር፣ መለያየትን በመዋደድ፣ መራራቅን በመተሳሰብ አክስሞ ለአንድ ሀገር ህልውና የድርሻውን ዋጋ ለመክፈል ከፊት ለፊት ለመቆም ችሏል፡፡
ይህ ለውጥ በተቋሙ ውስጥ ሁሉም በሙያው በእውቀቱና በልምዱ ልክ ሀገሩን ለማገለግል መብትም ግዴታም ችሎታም እንዳለው በተግባር አሳይቶናል፡፡ ስልጠና ለማግኘት የዘር ሐረግ መቁጠር ሳይሆን፣ ሆኖ መገኘት ብቻ በቂ እንዲሆን የመመዘኛ መስፈርት ሆኖለታል፡፡ ሰራዊት ማለት ስለጥይትና መድፍ ብቻ የሚያውቅ ከሚል ያረጀ አስተሳሰብ በመውጣት በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ራሱን ያበቃ፣ የነቃ፣ ንቃተ ህሊናው በንባብና በውይይት የዳበረ፣ ግርድፍ መረጃዎችን በሳይንሳዊ ጥበብና መስፈርት ለክቶ መተንተን የሚችል በማህበራዊ ሕይወቱም እንደ ዱር ቀበሮ ከህዝቡ ተነጥሎ በመኖር ሳይሆን የህዝቡን ችግር በመካፈል በአካባቢ ጥበቃ፣ በንጽህና፣ በግንባታ፣ በችግኝ ተከላ፣ በአጨዳ እየተሳተፈ የህዝብ ልጅነቱን በተግባር ያረጋገጠ ስብስብ ሆኗል፡፡ በእግረ መንገድ ለመጠቆምም ነቃ ነቃ ያሉትን በመኮርኮምና ወደ ሹመት ሊመጡ የሚችሉትን ሀገር ወዳድ ወታደሮች ቀደም ብሎ በመቅጠፍ የሚታወቀው የሕወሓት ስርዓት፣ ያለጡረታ ቀናቸው እንዲገለሉ ያደረገቻቸው የሰራዊቱ አባላት፣ ዛሬ ወዳደጉበት ቤት በክብር ተጠርተው ትልቅ ኃላፊነትን ተሸክመው፣ ሰርቶ በማሰራት መርቶ በማሳካት አቅም እንዳላቸው ለዓለም ህዝብ አሳይተዋል፡፡
ድሮ ተለምኖ ለውትድርና እንዲመዘገብ አማላጅ የሚላክበት ወጣቱ፣ ዛሬ ለውትድርና ሙያ ክብርና ዋጋ በመስጠት ለምዝገባ ወረፋ ላይ ሲጋፋ ማየት የለውጡ አካል ሲሆን ወጣቱ መንግስት የተለየ ጥቅም እንደሚሰጠው አስቦ ሳይሆን በመከላከያ ሰራዊት ላይ ሙሉ እምነቱን ስለሳደረ መሆኑን እንገነዘባለን፡፡
ዛሬ ዛሬ የመከላከያ ሰራዊቱ ጠባቂና ተከራካሪ የሆነው አንድ ፓርቲ ሳይሆን የኢትዮጵያ ህዝብ በሙሉ ነው፡፡ ስለሰራዊቱ እለታዊ እንስቃሴ ተጋድሎና ስኬት ዓይኑን ገልጦ ከማየት ጆሮውን ከፍቶ ከማድመጥ የሚቦዝን አንድም ሰው ፈጽሞ አይገኝም፡፡
በርግጥ ሰራዊቱ የደሀ ሀገር ሰራዊት በመሆኑ ከሚከፍለው ውድ ዋጋ አንጻር ውድ ክፍያ ባይከፈለውም፣ ለሀገሩና ለባንዲራው ሲል የኑሮ ጉድለቱን ችላ እያለ ዛሬም ከነትጥቁ ታማኝነቱን አላጎደለም፡፡ በገዛ ወገኑ በተኛበት የጥይት እሩምታ ሲወርድበት፤ በአስከሬኑ ላይ ሲዘፈንበት፤ ለበድን አካሉ ብሔር ተሰይሞለት ሲፌዝበት አይተናል፡፡ ለሀገሩ ሲል ውበቱን በበረሃ ያረግፋል፤ ወጣትነቱን በምሽግ ያሳልፋል፤ ህይወቱን በግዳጅ ላይ ይሰዋል፤ አፈር መስሎ ተራራ ይገፋል፡፡ ለዚህ ሁሉ ዋጋው ጎንበስ ብለን እጅ ነስተናል፡፡  
ባለቤቱ የናቀውን አሞሌ ባለእዳ አይቀበለውም እንደሚባለው ሁሉ፣ እኛ ዝቅ ያደረግነውን ሰራዊት ማንም ሊያከብርልን ስለማይችል የእንቅልፍ ሰአት ተቀያይረንም ቢሆን ሰራዊታችንን ከመጠበቅ፡ ከመከላከልና ደጀንም ከመሆን የሚያግደን አንዳች ኃይል አይኖርም፡፡
ዛሬ በሰራዊታችን ፍቅር ወድቀናል፤ የሚከፍልልንን ውድ መስዋዕትነት በልኩ አውቀነዋል፤ የእያንዳንዱ የሰራዊት እንቅስቃሴ ያገባናል፤ ይገዳል፤ ይጨንቀናል፤ ምን አገባን የምንለው ጉዳይ የለንም፤ ሰራዊቱ ሲታመም እንታመማለን፤ ሲደክም እንደክማለን፤ ሲቆስል እንቆስላለን፤  የተጋድሎውን አንጸባራቂ ድልም በክብር እንዘክራለን፤ ሰራዊታችን ሞታችንን ተሻምቶ ሊሞትልን ወረፋ የያዘ ታማኝ አገልጋያችን መሆኑን ስለምናውቅ ክፉ ዓይን እንዲያይብን አንሻም፡፡
መከላከያ ሰራዊቱ ነገ - የሚያጠግብ እንጀራ ከምጣዱ ያስታውቃል ነውና መከላከያ ሰራዊታችን በአካልም በስነልቦናም በትጥቅም በንቃተ ኅሊናም ተደራጅቶ የአፍሪካ ሰማይ ላይ የሚያበራ ኮከብ እንደሚሆን ከወዲሁ እርግጠኞች መሆን እንችላለን፡፡ ሻሎም!

Read 1541 times